ሁሉም ነገር ሰላም ሲሆን እጅግ መደሰት አይቀርም። ስለጦርነት ማሰላሰልና ማሰብ ቀርቶ ስለመልካም ስራ ስለዕድገት እያሰቡ ጊዜ ማሳለፍ ትልቅ መታደል ነው። መታደል ብቻ አይደለም ፤ መታደስ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ለእንዲህ ዓይነት ዕድል እየቀረበች ይመስላል። ስለጦርነት፣ ስለሞት እና እልቂት የምናወራበት ጊዜ ሊያበቃ ቅንጣት ቀርቶናል። የሰላም ደጃፍ ላይ ደርሰናል፤ እያንኳኳን ነው።
የሁሉም የሰላም በር ሲከፈት፤ ጦርነት ቀርቶ በምትኩ ሰላማዊ ውይይት መስመር ይይዛል። በትዕግስት እና በጥበብ ውይይት ሲካሄድ እና መግባባት ላይ መድረስ ሲጀመር ኢትዮጵያ እየታደሰች ታብባለች። ልጆቿም በእርሷ መደሰት ብቻ ሳይሆን በሀብቷ እየተጠቀምን ኑሯችንን በተድላ እናጣጥማለን። ዓለም ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ያዞራል። ይህ ቀን በፍፁም የሚቀር አይደለም። አሁን ደግሞ የበለጠ እየቀረበ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ነቅተናል። ጦርነት እንደማይበጅ ትርፉ ጉዳት መሆኑን ተረድተናል።
ጦርነት ዕድገትን የሚያደናቅፍ ወደፊት ለመጓዝ ጥረት ሲደረግ ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን አውቀናል። አጉል እልህ እና ጦር እየነቀነቁ ከእኔ ወዲያ ላሳር ማለት ትርፍ እንደሌለው ተገንዝበናል። አሁን የምንፈልገው ከጦርነት ማረፍ እና እፎይ ብሎ ፊትን ወደ ሥራ ማዞር ብቻ ነው። አሁን ምኞታችን ዕድገት ነው።
ፍላጎታችን ሰላም ብቻ ነው። አሁን በጦርነት ስጋት ተወጥሮ ቀኑን ሙሉ ሥራ ሳይሰሩ መዋል ሳይሆን፤ በትክክል ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት ወይም ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ለራስና ለአገር የሚተርፍ ሥራን መስራት በሚል ቆርጠን ተነስተናል።
እርግጥ ነው፤ ጦርነት ከሚያስከትለው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ባለፈ ማህበራዊ ግንኙነትን ያበላሻል ፤ የአገር ህልውናንም ይፈታተናል። ይህንንም የቅርቡ የትናንት ታሪካችን ተጨባጭ ማሳያ ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ባለመደማመጣችን ተፈጠረውን ግጭት እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው እስከምን ድረስ እንደሄዱ ለኛ ነጋሪ የሚያስፈልገን ጉዳይ አይደለም።
አሁን በየትኛወም መልኩ የሚፈጠር ግጭት፤ በግጭት ውስጥ የሚጠፋ የሰው ሀብትና የሀገር ንብረት የአገርን እና የሕዝብን ኢኮኖሚ ከማድቀቅ እና ሁሉንም መልካም ጉዞ ወደኋላ ከማስቀረት ውጪ ጥቅም አልባ መሆኑን ተገንዝበናል።
እሳት እንጨት ካላገኘ እንደማይነደው እና እንደማይቀጣጠለው ሁሉ ኢትዮጵያውያን የጦርነት ሃሳብን ከውስጣችን ማውጣታችን ለአገር ሰላም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አምነናል። እሳቱም የሚጠፋበትን ዕድል በማመቻቸት ላይ ነን። የሠላምን ትሩፋት ለማጣጣም ጓጉተናል። ሠላም ከሆነ ደግሞ መሰረተ ልማት መገንባት ይቻላል።
ከአዲስ አበባ ጅጅጋ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ አፋር፣ ከአዲስ አበባ ቤኒሻንጉል፣ ከአዲስ አበባ ጋምቤላ፣ ከአዲስ አበባ ደቡብ ኦሞ ከአዲስ አበባ ጎንደርም ሆነ ባህርዳር፣ ከአዲስ አበባ ወለጋም ሆነ ጉጂ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ፈጣን የባቡር መስመር ለመገንባት እድል ይፈጥርልናል። ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል መስመር ልንዘረጋ እርስበእርስ በሰላም በኢኮኖሚ ለመቆራኘት ያስችለናል።
ይህ የባቡር መስመር ግንባታ ምርት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲንቀሳቀስ፤ ሰዎች ከአንድ ክልል ወደ አንድ ክልል ወይም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እንደፈለጉት ተንቀሳቅሰው መኖር እንዲችሉ ያደርጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው። መሰረተ ልማት የሰላም ትሩፋት ነው።
በኢትዮጵያ መኖር ሲታሰብ አዲስ አበባ ብቸኛ አማራጭ የምትሆንበት ዕድል ይጠባል። ሰው የትም ሰርቶ በፍጥነት የትም አካባቢ ገብቶ ማደር እና መኖር ይችላል። ይህ የሰላም ትሩፋት አዲስ አበባን እና መላው የኢትዮጵያን ክልል ከኢኮኖሚ ችግርም የሚያላቅቅ ይሆናል።
ደግሞ መረሳት የሌለበት ማንኛውም ነገር የሚፈልገውን ካላገኘ መፈለጉን አያቋርጥም። በተቃራኒው በኢትዮጵያ መደብዘዝ የሚደሰቱ፤ በመደብዘዟ ዛሬም እየተጠቀሙ ያሉ፤ ነገ የኢትዮጵያ መጥፋት ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው የሚያስቡ ስግብግቦች የዘመናዊ ቅኝ ገዢነት አስተሳሰብ ውስጣቸው የዳበረ የአፍሪካ ጠላቶች በመሙላታቸው እነርሱም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወደ ኋላ አይሉም።
ይህንን የጠላት ፍላጎት ተገንዝበን ጭንቅላታችንን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ለአፍሪካ ሰላም፤ ለጋራ መግባባት ካላሰላሰልን፤ እግራችን እና እጃችን ብቻ ሳይሆኑ መላው ሰውነታችን በሰላም ሥራ ላይ ካልተወጠረ እንኳን አንድነትን ማጠናከር፤ ዕድገትን ማረጋገጥ እና አፍሪካውያንን ማንቃት ቀርቶ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንደምትቀጥል ፤ ስሟም ከዓለም ካርታ ላይ እንደማይጠፋ ማረጋገጥ አዳጋች ነው።
የሰውን ሃሳብ አለመቀበል፤ በተለይ ለራስ አጉል ደረጃ ሰጥቶ መመፃደቅ እና አልሰማም ማለት ሁሉም ነገር የተሳካ እንዳይሆን ያደርጋል። እሳት የላስኩ ፈጣን፣ ጮሌ ወይም በጣም ንቁ ሰው ነኝ ብሎ የሚያምን ሰው በቀላሉ ተታሎ ሊገኝ ይችላል። ሥልጣን ወይም ገንዘብ ፈልጎ ይታለላል። መሳሪያ ይሆናል። ከተራ የቃላት አጠቃቀም ጀምሮ የሚፈፅመው ትልልቅ ስህተት ቅራኔ ፈጥሮ ወደ መበሻሸቅ ያመራል። እንደተለመደው ጦር መማዘዝ ይመጣል። ከጦር መማዘዝ በኋላ የሚመጣው ደግሞ ሞት እና ጉዳት ብቻ ነው። በመጨረሻም የግለሰብ ሞት፤ የቤተሰብ መፍረስ፤ የአገርን የሚያናውጥ አደጋ ይጋረጣል።
ነቅቶ የሌሎችን ሃሳብ አዳምጦ፤ የሌሎችን ቁስል ተረድቶ፤ የሚመጣን ማታለያ አልቀበልም ብሎ፤ ራስን ከስግብግብነት ገድቦ በእውነት ከልብ ሰለሰላም እና ስለአገር ጥቅም ብቻ አስቦ መንቀሳቀስ ከተቻለ ትርፉ ትልቅ ነው። አንዱ ሌላውን ካዳመጠ፤ ለሰላም ቅድሚያ ከተሰጠ፤ ሰላም ከተትረፈረፈ እና ሞልቶ ከፈሰሰ የሚገኘው ጥቅም የትየለሌ ነው። እንኳን ኢትዮጵያን የምታክል አገር በተመቸ የአየር ሁኔታ፣ በተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት የታደለች አገር ቀርታ፤ እንኳን በተፈጥሮ ሀብት ብዙዎችን የምታጓጓው አፍሪካ ቀርታ በረዷቸው እና ሙቀታቸው ሰው የሚገድል የተፈጥሮ ሀብት ያልታደሉ አገሮች እንኳን የዓለም ሃያል ለመሆን በቅተዋል።
እነርሱን ከኢትዮጵያ ከአፍሪካ የሚለያቸው ምክንያት አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ካለፈው መጥፎ ታሪካቸው ተምረው እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን አያባክኑም። ትኩረታቸው የራሳቸውን አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ እና በተለያየ መንገድ ሀብት መሰብሰብ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን አፍሪካውያን ደግሞ ጦርነት ውስጥ በመግባት የያዝነውንና ያለንን መበተን መለያችን ሆኗል። አሁን ግን መፍትሔው ሰላም ነው። ጦርነት ብዙ ጉዳት ማስከተሉ እንደማይቀር ሁሉ ከሰላም የሚገኘው ጥቅም ብዙ ነውና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይሻላል። ይህ ሲታሰብ በእርግጥ ያለፈው ሁሉ አልፏል። ከአሁን በኋላ ግን መላው ኢትዮጵያውያን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015