የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) ከቀናት በኋላ ይካሄዳል። ውድድሩ በአልጄሪያ ለ7ኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፤ ተሳታፊ የሚሆኑት 18 አገራትም ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ብሄራዊ ቡድኗን በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ ዝግጅቷን አጠናክራ ማከናወኗን ቀጥላለች።
ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በዚህ ውድድር የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመድረኩ ከምድብ ያለፈ ውጤት የለውም። ከስድስት ዓመታት በኋላም ዳግም የመድረኩ ተሳታፊ ሆኗል። በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ በሚካፈሉ ተጫዋቾች መካከል የሚካሄደው ይህ ውድድር ለወጣት ተጫዋቾች በርካታ እድልን ሊያስገኝ እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ ባሻገር አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአውሮፓና ሌሎች አገራት ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ እንደመሆናቸው በዚህ ውድድር ላይ ይዘው የሚቀርቡት ቡድን ከሌላው የተለየ ነው የሚሆነው። ይኸውም እንደ ኢትዮጵያ ያሉና በርካታ የውጪ አገራት ተጫዋቾች የሌሏቸው ቡድኖችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
በመሆኑም በመድረኩ ከዚህ ቀደም ጎልቶ የሚነገር ታሪክ የሌላት ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ለመሆን ወደ አልጄሪያ ታቀናለች። ለዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዚህ ረገድ ኃላፊነት የሰጠው ፌዴሬሽኑ ለዝግጅቱም የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው የሚገኘው። ለቻን ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከአገር ውስጥ ዝግጅቱ ባለፈ ቀጣይ ዝግጅቱን በሞሮኮ የሚያደርግ ይሆናል። ቡድኑ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ከነገ በስቲያ ታህሳስ 26/2015 ዓ.ም ወደ ሞሮኮ በማቅናት እስከ ውድድሩ መዳረሻ ያሉት ስምንት ቀናት ዝግጅት እንደሚያከናውን ፌዴሬሽኑ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት አስታውቋል። በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ የሚደረገውን ውድድር ተከትሎ የቡድን አባላቱ ከአየር ሁኔታው ጋር እንዲላመዱ በሚል ከተመረጡ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሞሮኮ ናት።
ፌዴሬሽኑ የቻን ተሳታፊነቱን ተከትሎ ለተለያዩ ወጪዎች የሚሆነውን 50 ሚሊየን ገንዘብ ከመንግስት እገዛ እንዲደረግለት መጠየቁ የሚታወስ ነው። ይሁንና የተሰጠው ምላሽ ግን 28 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ተጨማሪ ስፖንሰሮችንና የገንዘብ ምንጮችን ከመፈለግ ባለፈ ሌሎች ወጪ ቀናሽ አማራጮችን ሲያማትር ቆይቷል። በዚህም መሰረት ከሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተገባው ስምምነት ቡድኑ የመጓጓዣ ወጪውን ብቻ በመሸፈን ሌሎች የቆይታ እንዲሁም የልምምድ አስፈላጊ ሁኔታዎችን በነጻ መስተናገድ እንዲችል ተፈቅዶለታል። በተጓዳኝም በቻን ከሚሳተፈው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት ሁለተኛውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታም ከቡድኑ ጋር ለማከናወን ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ቡድኑ በአጠቃላይ 41 አባላትን ይዞ በውድድሩ ላይ የሚሳተፍ ሲሆን፤ ከተመረጡት 28 ተጫዋቾች መካከልም ሁለቱ ተቀንሰው 26 ናቸው። ከተጫዋች ባሻገር የስልጠና ቡድን እና የፌዴሬሽኑ ተወካዮች ብቻ የተካተቱበት መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል። የውድድሩ ተሳታፊ ከሆነው ቡድኑ ጎን ለጎንም በሌሎች ስራዎች አገሪቷን የሚወክሉ ባለሙያዎችም አሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የቻን ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በመሆን ተመርጠዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደምም በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተመሳሳይ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም በቴክኒክ ጥናት ቡድን አባልነት የሚያገለግሉ ሲሆን፤ እአአ በ2019 እና 2021 አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተመሳሳይ ተሳትፎ ነበራቸው። ሌላኛው ባለሙያ የፊፋ ዓለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማም በጨዋታ አመራርነት በቻን ውድድር እንደሚካፈሉ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ኢንስትራክተር ባምላክ በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ 12 የቪድዮ ረዳት ዳኞች መካከል አንዱም ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015