ባለፈው ሰሞን ለአንድ ጉዳይ በአቅራቢያዬ የሚገኝ ወረዳ ሄጄ ነበር። እንደተለመደው የወረዳው ግቢ በትርምስ ተሞልቶ ማን ለምን ጉዳይ አንደመጣ በማይታወቅበት መልኩ የቅዳሜ ገበያ መስሏል። እኔ የሄድኩት ደግሞ ወሳኝ ኩነት የሚባለው ከገበያም በላይ የሚደምቅ ቦታ ነው። በጊዜ የደረስኩ ቢመስለኝም ሰልፉ ግን ተጠማዞ የትና የት ሄዷል። እንደማንኛውም ሰው ተሰለፍኩ። ሰራተኞቹ አሰራራቸው ዲጂታላይዝድ ነው ቢባልም መንቀራፈፋቸው ግን ጥልፍ እንደሚሰራ ሰው ነው። አስተሳሰብ ዲጂታላይዝ ካልሆነ ስርአት ዲጂታላይዝ ቢሆን ጥቅም እንደሌለው ሁነኛ ማሳያ ይሆናሉ።
ከብዙ መቆየት በኋላ ደረሰኝ። መሳሪያ ተደግኖበት የሚሰራ የሚመስል አንድ ስልቹ ሰው ቆጣ ቆጣ እያለ ወደ መዝገብ ቤት መራኝ። መዝገብ ቤት ያለችው ደልዳላ ሴትዮ ከሰውየው በበለጠ በስራውም ብቻ ሳይሆን በህይወቷም የተበሳጨት ትመስላለች። ማነው የላከህ አለችኝ። ወደላከኝ ሰውዬ ጠቆምኳት። እኔ የማንንም ፋይል በመጎተት ክንዴ ተገነጠለ፤ ለምን እነሱ ኮምፒተር ላይ አያዩላችሁም ብላ ተፈናጥራ ተነሳች። ፋይሉን ካለበት ጎትታ አምጥታ አገላብጣ ማየት ጀመረች። እርግጥ የኛም ቤት ፋይል ከመወፈርም በላይ በጣም አርጅቶ ለአይንም ይከብዳል። የሆነ ነገር ጽፋ ወረቀቱን ሰጠችኝ፤ ወደ ሰውየው ተመለስኩ። ወረቀቱን አየና በል ወደ ወረፋህ ተመለስና ተራህን ጠብቀህ ትስተናገዳለህ አለኝ። ተመልሼ ተቀመጥኩ።
ተራዬ ሲደርስ ኮምፒውተር ላይ ወደተቀመጠ ወጣት ልጅ ሄድኩ። ለምን ቀስ ብለው እንደሚሰሩ አሁን ገባኝ። ልጁና ሲስተሙ ብዙም አይተዋወቁም። ስለዚህም ቀስ እያለ ነው የሚሰራው። የሲስተሙን አንዳንድ ክፍል እንደማይረዳው ከአሰራሩ ማየት ችያለሁ። መረጃዎችን እየጠየቀኝ ሞላ። ከዚያ ግን መሞላት ግዴታ ያልሆነበት ክፍል ላይ ደረሰ። መረጃ ሲጠይቀኝ ይህ ክፍል ግዴታ እንዳልሆነ ነገርኩት። ግዴታ ነው አለኝ። ግዴታ እንዳልሆነ ኮምፒውተሩ ላይ እንደሚያሳይ ባመላክተውም ሊሰማኝ ፈቃደኛ አልሆነም። ሞላው።
መረጃው ተጠናቆ ሲወጣ እኔ ከምፈልገው በተቃራኒው ሆነ። ሁሉንም በተራ አናገርኳቸው። አንዳቸውም ስህተታቸውን ለማመን አልፈለጉም። ሲስተሙ ግድ ይለናል አሉ። ሲስተሙ የግድ እንደማይል ባሳያቸውም ሊቀበሉ አልፈቀዱም። ሽንፈት መሰላቸው። በኋላ አናግረው ተብዬ ወደ ቡድን መሪው ጋር ደረስኩ። ወጣት ነው። ጉዳዬን ከሰማኝ በኋላ ትንሽ እንድጠብቅ ነግሮኝ ሄደና ሌላ ጉዳይ ፈጽሞ ሲመጣ አወራን። መመሪያው ይፈቅዳል አለ። ሌሎቹ አይፈቅድም አሉ። እርስ በርስ ክርክር ተጀመረ። ክፍለ ከተማ እና ሌላ ወረዳ ደወሉ። በመጨረሻ መመሪያው እንደሚፈቅድ ተረጋገጠና በድጋሚ ተስተካክሎ ተሰራልኝ።
ከአንድ ቢሮ ጠቅላላ ሰራተኛ መመሪያ በትክክል የሚያውቀው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ አስገረመኝ። ብዙዎቹ መመሪያውን አያውቁትም ወይም የሚያውቁት በአንድ ወቅት የነበረውን ብቻ ነው። ሲለወጥ አልሰሙም ወይም አላስተዋሉም። ይሄ አንደኛው ችግር ነው። መመሪያ ተለዋዋጭ ነው። ያን ግን የሚረዳው ሰው ጥቂት ነው። ብዙው ሰው እንደ መንፈሳዊ ህግ አንዴ ከሰፈረ የሚቀየር አይመስለውም።
ዋነኛው ችግር ግን የመመሪያ እውቀት አለመኖር አይደለም። ስንፍና ነው። እንዳስተዋልኩት ብዙዎቹ አለማወቃቸውን ወይም ስህተታቸውን የሚሸፍኑት መመሪያው አይፈቅድም ወይም ሲስተሙ አይፈቅድም በሚል ሽፋን ነው። የትኛው መመሪያ መቼ የወጣው መመሪያ ቁጥር ስንት ቢባሉ ማስረዳት አይችሉም። እንዲሁ በደፈናው መመሪያው ይሉሃል። ህዝብም መንግስት ያወጣው መመሪያ ከሆነ መቼስ ምን አደርጋለሁ ብሎ እሺ ይላል።
በዚህ የተነሳ መንግስት ባላወጣው መመሪያ ህዝብ ይጉላላል። ብዙው ህዝባችን በተለይ እናቶችን እና አባቶች ዛሬም ቢሆን መንግስትን የሚያምኑ ናቸው። የመንግስት መመሪያ ነው ከተባሉ እሺ ብለው ነው የሚሄዱት። በዚህም የተነሳ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ሳያገኙ ነው የሚሄዱት ማለት ነው። ይህ መንግስት ገቢ፤ ህዝብን አገልግሎት ያሳጣል። ምሬትን ይወልዳል። ምሬት ደግሞ ሲጠራቀም አመጽን ይወልዳል። እንዲህ አይነቱ አመጽን የሚፈጥሩት እንዝላል ሰራተኞች ይሆናሉ ማለት ነው።
ሲስተምም ላይ እንደዚያው። በጣም ያስገረመኝ ራሱ የጻፈው ጽሁፍ ላይ ያለን የፊደል ግድፈት ሲስተሙ ነው ሲለኝ ነው። ሲስተሙ በባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው። ምን ተብሎ እንደሚጻፍ በግልጽ ተቀምጧል። status የሚልን ቃል states ብሎ ሲጽፍ ስህተት እንደሆነ ብነግረው ሲስተም ነው ብሎኝ ድርቅ አለ። በሁለቱ ቃላት መሀከል ያለው የፍቺ ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ይህ ዶክመንት በዓለም ዙሪያ የሚሰራ ዶክመንት ነው። ስለዚህ ይህ ዶክመንት የኢትዮጵያን መንግስት አቅም የሚያሳይ ነው። ታዲያ 120 ሚሊየን ህዝብ የሚመራ መንግስት እንዲህ አይነት ስህተት ተሳሳተ ቢባል ማን ያምናል። መንግስት ተሳስቶ አይደለም፤ ሲስተሙ አስገድዶም አይደለም፤ ሲስተሙ ላይ ያለው ሰው ንዝላልነት ግን ይህን አላስፈላጊ ስህተት ፈጥሯል።
በጥቅሉ ብዙዎች መመሪያ እና ሲስተምን እነሱ ላለባቸው ንዝላልነት፤ የቀናነት ችግር እና የሙስና ዝንባሌ እንደመጠቀሚያ እያደረጉት ነው። ይሄ በእርግጥ የእነሱ ችግር ብቻ ሳይሆን የብዙ ህዝባችን ችግር ነው። እሱ የማያውቀውን እውቀት እንደ እውቀት የማይቆጥር፤ እሱ ያልሰማውን መረጃ እንደ ፈጠራ ወሬ የሚያናንቅ፤ ለአዲስ ነገር ክፍት ያልሆነ ህዝብ ብዙ ነው። ጓዶች እውቀት ማለት እኛ የሰማነው እና የምናውቀው ብቻ አይደለም።
እንዲያውም እኛ የማናውቀው ብዙ ነገር እንዳለ ማወቅ የእውቀት ጅማሮ ነው። ብዙ ሰዎች ዛሬ ላይ ስለ ዓለም፤ ስለ አገር፤ ስለ መንግስት፤ ስለ ኃይማኖት፤ ስለ ሌላውም እነሱ ጋር ያለው እውቀት የመጨረሻው እውቀት እንደሆነ በማመን በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ይህ ስህተት ነው። እውቀት ተለዋዋጭ ነው። ነባራዊው ሁኔታም ተለዋዋጭ ነው። ሲስተምም መመሪያም ህግም ተለዋዋጭ ነው። ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ማወቅ እና መዘጋጀት እንጂ እኔ የማውቀው ብቻ ነው የመጨረሻው እውቀት ከዚያ ወዲህ አዲስ እውቀት አልመጣም ብሎ መታገል ስህተት ነው።
ሲጠቃለል፤ በመንግስት ተቋማት የምትሰሩ ሰዎች እባካችሁ ስንፍናችሁን በመመሪያ፤ በደንብ፤ በህግ፤ በሲስተም አንሸፍነው። ይልቁንም ወቅታዊውን መረጃ በትክክል ማወቃችንን እርግጠኛ እንሁን፤ ለማወቅም እንጣር። እንደ ህዝብ ደግሞ ለአዲስ እውቀት በራችንን እንክፈት፤ ያላወቅነው ነገር ሊኖር እንደሚችል በጥቂቱም ቢሆን እንጠርጥር።
ቸር እንሰንብት!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015