የሰው ልጅ የመኖሩን ትርጉም የሚገልጥበት ልዩ ጥበብን የታደለ ፍጡር ነው። በዚህ ጥበብ ደስታውን ያገኛል።
ከእነዚህ መሃል ደግሞ የፋሽን አልባሳት ዲዛይንና ቀለማት አንዱ ነው። ለመሆኑ የፋሽን አልባሳትና ቀለማት ትስስር በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ በምን መልኩ ይገለፅ ይሆን?
ፋሽንን ከውበት፣ ውበትን ከዘመን፣ ዘመንን ከጥበብ ስናዋህድ በነዚህ ሁሉ መሃከል ቀለማት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። ፈጣሪ ታላቁን የሰውን ልጅ ከአፈርና ውሃ ካበጀ በኋላ ሰው እንዲሆን ያደረገበት ጥበብ እስትንፋስ ነው። ወደ ፋሽን ጥበብ ስንመጣም የፋሽን ጥበበኛ እጆች ጨርቁን ከዲዛይኑ አጣምረው ከሰሩት በኋላ ፋሽኑን በቀለማት ነብስ ካልዘሩበት፣ ፈጠራቸው ሰውነትን ከመሸፈንና ብርድን ከመከላከል በዘለለ በዘመንና ፋሽን የውበት ማህደር ውስጥ ዋጋ አይኖራቸውም። ይህ ማለት ጣፋጭ ኬክ አዘጋጅተን ክሬሙን ሽሮ ወጥ እንደማድረግ ነው። በፋሽን ዲዛይን ውስጥ ውበትን ለመፍጠር የቀለማትን ሚስጥርና ትክክለኛ ቦታ ለይተን ማወቅ አለብን።
በዘመናዊ ፋሽን ውስጥ ቀዳሚው ነገር እይታን መሳብ ነው። በመጀመሪያ እናያለን፣ ያየነውንም እንወዳለን፣ የወደድነውንም ምርጫችን እናደርገዋለን። ገና በመጀመሪያው እይታ ቀለማት ምርጫችንን እንድንወስን የማድረግ አቅም አላቸው። በእርግጥ ውበት እንደምርጫ ነው። አንዱ የወደደውን ሌላኛው ሊጠላው፣ ያደነቀውንም ሊያንቋሽሸው ይችላል። ውበትና ፋሽን እንደምርጫችን ቢሆንም፣ በምርጫችን ውስጥ አስገዳጅ የሆኑ መመዘኛዎች አሉ። እነዚህም ባህል፣ ወግ ልማድ፣ ሀይማኖትና ያደግንበት ማህበረሰብ ናቸው።
ቀለማት ከስነ ውበትና ከግለሰባዊ ምርጫ ሰፋ ባለ መልኩ በባህልና እምነት እንዲሁም አገራት ውስጥ ልዩ ቦታና ትኩረት ይሰጠዋል። በሳይንሱ የሚታወቁት ቀለማትን አገራት ከራሳቸው ባህላዊና ስነልቦናዊ ሁኔታ በመነሳት የሚሰጡት ትርጓሜ አላቸው። በአብዛኛው ማለት በሚቻል መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀለማት የሚከተለውን ትርጓሜ እንደአግባብነቱ እንዲይዙ ተደርገዋል። በዚህ መሰረትም ጥቂቶቹን ብንመለከት፤
ቀይ ቀለም:- ጥልቅ ስሜት፣ ፍቅር፣ ቁጣ… ብርቱካናማ:- ጉልበት፣ ደስታ፣ ህይወት… ቢጫ:- ደስታ፣ ተስፋ፣ ማታለል… አረንጓዴ:- አዲስ ጅማሮ፣ የተትረፈረፈ፣ ተፈጥሮ… ሰማያዊ:- ረጋ ያለ፣ ኃላፊነት፣ ሀዘን… ሐምራዊ:- ፈጠራ፣ ንጉሳዊ፣ ሀብት… ጥቁር:- ምስጢር፣ ውበት፣ ክፋት… ግራጫ:- ተለዋዋጭ ስሜት፣ ወግ አጥባቂ፣ መደበኛነት… ነጭ:- ጥሩነት፣ ንጽህና፣ በጎነት… ቡናማ:- ተፈጥሮ፣ ጤናማነት፣ ጥገኛነት…የሚሉ ትርጓሜዎችን ይይዛሉ። የተዋጣለት የፋሽን ዲዛይን ለመስራት ስናስብም አስቀድመን፣ ስራችንን የምናቀርብለት ማህበረሰብ በየትኛው የትርጓሜ መደብ ውስጥ እንዳለ ማጤን አለብን።
ፋሽን እንደ ዘመኑና እንደ ሁኔታው ሊቀያየር ይችላል። በፋሽን ውስጥ ያሉት ቀለማት ግን ሁልጊዜ ከሰው ልጆች ስብዕናና ማንነት ጋር ተያያዥነት አላቸው። ድምጽ አልባ መሳሪያ እንደመሆናቸውም ቃላት የማይገልጹትን እልፍ ትርጓሜዎች ይዘው ይገኛሉ። በአገራችን ታሪክ ውስጥም በኃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ቀለማት ሚስጢራዊ ይዘት እንዳላቸው እንመለከታለን። በደስታ ጊዜ የብሩህነት መገለጫ የሆነውን ነጭና በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀውን ጥለት፣ እንዲሁም ጎላ ብለው የሚታዩ የቢጫ፣ ቀይና አረንጓዴ አልባሳት ይዘወተራል።
በሃዘን ጊዜያት ደግሞ ደብዘዝ ብለው የሚታዩ ልብሶችን በተለይ ጥቁር ቀለም እንጠቀማለን። ታዲያ አንድ አባቱ ወይም እናቱ የሞተበት ሰው ከቀብር መልስ እቤቱ ገብቶ ነጭ በነጭ ለብሶ ቢወጣ ማህበረሰቡ የሚረዳው ይህ ሰው በአባቱ ወይም በእናቱ ሞት ደስተኛ መሆኑን ነው። ባህልና ስርዓትን ከመጣሱ በተጨማሪ እንደ ጨካኝና አረመኔ አሊያም እንደ እብድ ሊቆጠር ይችላል። ይሄም ቀለማት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ያሳየናል።
በኃይማኖት ውስጥ ያለው የቀለም እይታና ትርጓሜ ደግሞ ከባህል የጠነከረ ነው። እያንዳንዱ የቀለም ጠብታ ልዩ ሚስጥራትን የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን። የምንጠቀማቸው ቀለማት እራሳቸውን ችለው እንደ ፊደላት የሚነበቡ ናቸውና፣ ቀለማቱን በተገቢው ካላሰባጠርናቸው ፊደላቱ የተዘበራረቀ መጽሃፍ ጽፎ እንደማሳተም ይሆንብናል። በተመሳሳይ በፋሽኖች ውስጥም ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘበ ቀለማትን የምንጠቀም ከሆነ የምናቀርብለት ማህበረሰብ ይህንን የመቀበል ፍላጎት አይኖረውም። ጊዜና ሁኔታዎችን ማገናዘብ በእጅጉ ወሳኝነት አላቸው። በአብዛኛው የምንከተላቸው የፋሽን ፈጠራዎች ውድቀት የሚጀምረው ከእነዚህ አንጻር ነው። የፈጠራዎቹ እድሜም በጣም አጭርና እንደ መብረቅ ብልጭታ ገና ሳይታዩ የሚከስሙ ይሆናሉ።
ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የጥበብ ሰዎች እንዲሁም በርካታ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ስለ ቀለማት አፈጣጠርና ስብጥር በተለያዩ ጊዜያት ጥናትና ምርምር አካሂደዋል። ሁሉም የራሳቸውን መላምት ከመሰንዘር ውጭ ይሄ ነው የሚባል የቀለማትን ስነ ልቦናዊ ቀመር የደረሰበት ግን የለም። በአለማችን በቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ ቀለማት እንዳሉ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን እያንዳንዳቸው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ።
ለዚህም ነው የፋሽን ዲዛይነሮች አልባሳትን ዲዛይን በሚያደርጉበት ወቅት ከውበት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከስነ ልቦና ውቅርና ተፅዕኖ አንፃር የሚቃኙት። በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ ደማቅ ቀለማት ይፈራሉ። ደብዘዝ ያሉ ቀለማት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ለበዓላትና ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች ካልሆነ በቀር ደማቅ ቀለማት ያስፈሩናል። ምቾት አይሰጡንም። አሁን አሁን ግን በከተሞች አካባቢ በተነሳው የፋሽን አቢዮት ቀለማትን ደፍሮ የመጠቀምና በእነርሱ በተቃኙ አልባሳት የመዋብ ልምዱ ቀስ በቀስ እየዳበረ በመምጣቱ የባህል አብዮቱን እየቀሰቀሱት ነው።
ፋሽንና ቀለማት ነጠላ ፍቺ ሰጥተን እንደዚህ ናቸው ለማለት የማያስደፍሩ ጥልቅ የሆነ ይዘትና ሀሳብ ያላቸው አውደ ብዙ ቃላት ናቸው። በዚህ ጹሁፍ ውስጥ በብዛት ከአልባሳት አንጻር ቢገለጹም ቅሉ ተቀዝፈው የማያልቁ ውቅያኖስ፣ ተገልጠው የማያልቁ መጽሐፍት ናቸው። እኛም ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015