ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ሳምንቱ ያለፈው በትምህርት ነበር እንዳላችሁ እርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርት ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ እንደሆናችሁ አምናለሁ፡፡ ጎበዝ ተማሪ ትምህርቱን በአግባቡ ያጠናል፣ የቤት ስራውን ይሰራል እና የቤተሰብ ምክር ይሰማል፡፡ እናንተም እነዚህን ተግባራት ስለምታከናውኑ ጎበዝ ናችሁ ማለት ነው፡፡
ልጆች የትኛውም ሰው ሲፈጠር የራሱ የሆነ ልዩ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እንዳለው ታውቃላችሁ? እስቲ የናንተ ልዩ ችሎታ ምን እንደሆነና ያንን ችሎታችሁን ለማዳበርና በልምምድ ለማጎልበት ምን ያህል እየሰራችሁ እንደሆነ ለማሰተዋል ሞክሩ፡፡ ትምህርት ቤት ሄዶ የቀለም ትምህርት ከመከታተልና ጥሩ ውጤት ከማምጣት ባሻገር ችሎታችሁን ለይታችሁ ማወቅና ለማዳበር መስራት ይኖርባችኋል፡፡ ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ባለብዙ ተሰጥኦንና በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ የቻለውን የ12 ዓመት ታዳጊ ዳግማዊ ቴዎድሮስን ነው፡፡
ዳግማዊ ቴዎድሮስ በጊብሰን ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ዳግማዊ የብዙ ተሰጥኦዎች ባለቤት እና በትምህርቱም ጎበዝ ተማሪ ነው፡፡ ተሰጥኦዎቹ ምን ምን እንደሆኑ ልንገራችሁ፤ በዋናነት የእግር ኳስ ችሎታ አለው ከዛ በተጨማሪ ግን የልጆች መፅሀፍትን ይፅፋል፡፡
ገና የሶስት ወር ጨቅላ እያለ የዓለም ዋንጫ በየሀገሩ እየዞረ ይጎበኝ ነበርና ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አባቱ ከዋንጫው ጋር ፎቶ አነሳው፡፡ ከዚያ በኋላ በ3 አመቱ በአሰግድ ተስፋዬ እግር ኳስ ፕሮጀክት ውስጥ ተቅፎ እግር ኳስ መሰልጠን ጀመረ፤ ያለው የኳስ ችሎታ ከእድሜ እኩዮቹ በላይ በመሆኑ አሁን ላይ የ12 አመት ታዳጊ ቢሆንም የሚጫወተው ግን ከ15 አመት ልጆች ጋር ነው ፡፡
ከስምንት አመት በኋላ የዓለም ዋንጫ ድጋሚ ሊጎበኝ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እሱ የስምንት አመት ልጅ ሆኖ ከዋንጫው ጋር ፎቶ ተነሳ፤ እናም ፎቶዎቹ መነጋገሪያ ሆኑ፡፡ ይህንን የተመለከ የዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በፈረንጆች 2018 ሩሲያ የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ አራት ጨዋታዎችን እንዲመለከት ተጋበዘ፤ ከአራት አመት በኋላ በድጋሚ ዘንድሮ ኳታር ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ተጋባዥ ተመልካች በመሆን ወደ ኳታር በመጓዝ ለአንድ ወር የቆየውን ዝግጅት ለመመልከት ችሏል፡፡
ኳታር በተጓዘበት ወቅት ጨዋታዎችን ከመመልከት በተጨማሪ ከአባቱ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ የማስተዋወቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ለመመልከት ስታዲየም በሚገቡበት ወቅት የተለያዩ የባህል ልብሶች ለብሰው በመግባት እንዲሁም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለኢትዮጵያ ባህልና ሲላሏት ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ሊጎበኙ ስለሚገባቸው ታሪካዊ ቦታዎች በመንገር ሀገራቸውን ሲያስተዋውቁ ቆይተው ተመልሰዋል፡፡
ልጆች ዳግማዊ ከዓለም የእግር ኳስ ተጫዋቾች የክርስትያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነው፡፡ ወደፊትም ለሊቨርፑል መጫወትና ልክ እንደሱ ጠንክሮ ሰርቶ የዓለም ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ሽልማትን መውሰድ ይፈልጋል፤ ለዛም እንዲረዳው ከትምህርቱ ጋር እንዳይጋጭበት እቅድ አውጥቶ የእግር ኳስ ልምምድ ያደርጋል፡፡ ያሰበው እንዲሳካለት አባቱ ሁሌም ካጠገቡ በመሆን ያግዘዋል፤ እሱም አባቱ የሚሰጠውን ሃሳቦች ወደ ተግባር በመለወጥ ካሰበበት ለመድረስ ዘወትር ይተጋል፡፡ “አባቴ ሁሌም ከጎኔ በመሆን በብዙ ነገር ያግዘኛል ላመሰግነው እፈልጋለሁ” ይላል ዳግማዊ ስለአባቱ ሲናገር፡፡
ዳግማዊ ከስፖርቱ ባሻገር በትምህርቱም ጎበዝ ተማሪ ነው ወደፊት ተምሮ ሜካኒካል ኢንጂነር በመሆን አዳዲስና ምቾት ያላቸው መኪናዎችን መፍጠር ይፈልጋል፡፡ የተለያዩ ከመኪና ጋር የተያያዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያያል ስለመኪና የተፃፉ መፃህፍትን ያነባል፡፡ ልጆችዬ ዳግማዊ ስለመኪና ያለውን እውቀት ቢታዩ በጣም ነው የምትገረሙት፤ ስለእያንዳንዱ የመኪና ክፍል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ልጆች ዳግማዊ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው አስገራሚ ነው፤ ይህንን ያዳበረው ደግሞ የተለያዩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃህፍትን በማንበብ ነው፡፡ የ12 አመት ልጅ ቢሆንም እስካሁን 400 የሚሆኑ መፃህፍትን አንብቧል፤ ከነዚህ መፃህፍት መካከል አብዛኞቹ በእንግሊዝኛ የተፃፉ ተከታታይ ክፍል ያላቸው መፃህፍት ናቸው፡፡ ልጆች የተለያዩ መፃህፍትን በማንበብ የእንግሊዝኛ ቋንቋቸውን ቢያዳብሩ መልካም ነው ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ልጆች ዳግማዊ መፃህፍትን በማንበብ ብቻ አልተገደበም፤ ከሚያነባቸው መፃህፍት በመነሳት በርካታ የልጆች መፃህፍትን እየፃፈ ይገኛል፡፡ ልጆችዬ የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ተስፋ ሳትቆርጡ ደጋግማችሁ በመሞከር ያሰባችሁት ቦታ መድረስ ወይም የፈለጋችሁትን ነገር ማግኘት ይችላሉ፡፡ “ብዙ ጊዜ ተሞክሮ የሚገኝ ድል ጣፋጭ ነው” ይላችኋል ዳግማዊ፡፡
ወላጆች ልጆቻቸው የሚፈልጉትን ነገር ባለመረዳት ትምህርት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ሲጫኗቸውና ልጆችም በወላጆቻቸው ጫና መሆን የማይፈልጉትን ሙያ ተምረው ይመረቃሉ፤ ይህ ደግሞ ውጤታማነታቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሲያሳድር ይስተዋላል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ያላቸውን ችሎታ አውጥተው እንዲጠቀሙበት ማበረታታትና ችሎታቸውን ሊያዳብርላቸው የሚችል ስልጠና እንዲያገኙ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፤ ይህም ልጆች በልጅነታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እድል ይፈጥርላቸዋል ሲል ዳግማዊ ለወላጆች መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ልጆች ከዳግማዊ ብዙ ነገር እንደተማራችሁ እርግጠኛ ነኝ፤ እናንተም ወደፊት ልክ እንደሱ ባለብዙ ተሰጥኦ ሆናችሁ ስኬታማ እንደምትሆኑ አምናለሁ ለዛሬ በዚህ ላብቃ ሳምንት በሌላ ፅሁፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ፡፡
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም