‹‹ከፔሌ በፊት እግር ኳስ ስፖርት ብቻ ነበር፤ እሱ ግን ወደ ጥበብ እና መዝናኛነት ቀየረው›› ይህን ያለው የወቅቱ ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማር ጁኒየር ነው፡፡ በእርግጥም እግር ኳስ አሁን የሚታወቅበት ውብ መልኩን ያገኘው ፔሌ ከተሰኘው ቅመም በኋላ ስለመሆኑ በርካቶችን ያስማማል፡፡ የደቡብ አሜሪካዊቷን አገር መለያ እግር ኳስ እንዲሆን የመሰረት ድንጋይ ያኖረው ዘመን ተሻጋሪ የኳስ አርቲስት ወደማይቀረው ሞት ነጎደ። ከ64 ዓመታት በፊት በእግር ኳሱ ዓለም የፈነጠቀው ጸሃይ በመጨረሻም ከትናንት በስቲያ ምሽት ጠለቀ፡፡
ለስፖርቱ ሩቅ ለሆኑ ሰዎች ጭምር አዲስ ያልሆነው ፔሌ፤ የእግር ኳስ ስፖርት ምልክት፣ የብራዚላዊያን ሀብት፣ የስፖርቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ የዓለም ዋንጫ ጀግና፣ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ተጫዋች ‹‹የእግር ኳስ ንጉስ›› ከሚል ክብር ጋር ኖሯል፡፡ በመጨረሻም ለዓመታት ሲታገለው የቆየው ህመሙ አሸንፎት በ82 ዓመቱ አርፏል፡፡ ያሳመራት እግር ኳስም እነሆ ሃዘን ተቀምጣለች፤ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም ‹‹ለእግር ኳስ አሳዛኙ ቀን ነው፤ የምንጊዜውም ምርጡ ተጫዋች ስለተለየም መላው ዓለም ሀዘን ላይ ነው›› ሲሉ ከባዱን የሀዘን ስሜት ገልጸውታል።
ጥበበኛው ተጫዋች ‹‹ፔሌ›› በመላው ዓለም የሰዎች እና የስፖርት ስፍራዎች መጠሪያ ለመሆን ይብቃ እንጂ ሙሉ ስሙ ኤዲሰን አራንቴስ ዶናሲሚንቶ ይሰኛል፡፡ እአአ ጥቅምት 23/1940 በብራዚል ትሬስ ኮራኮስ ፍጹም ድህነት በነገሰበት መንደር ውስጥ የተወለደው ፔሌ በልጅነቱ ፓይለት የመሆን ህልም የነበረው ቢሆንም በቤታቸው አቅራቢያ አውሮፕላን ተከስክሶ ፓይለቱና ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ መመልከቱን ተከትሎ ህልሙን ለመቀየር ወሰነ፡፡ አባቱ ጆኣኦ ራሞስ ዶ ናሲሚንቶ ፕሮፌሽናል እግር ኳሰ ተጫዋች ነበሩና ወደዚያው አማተረ፡፡ በወቅቱ በብራዚል የቤት ውስጥ እግር ኳስ (ፉትሳል) ተወዳጅ ስፖርት በመሆኑ የሊስትሮ ሳጥኑን ጥሎ የሕይወቱ ጥሪ ወደ ሆነው እግር ኳስ አማትሮ ችሎታውን እንዲያወጣና ተሰጥኦውን እንዲያዳብር አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡ የማንጠባጠብ፣ አታሎ የማለፍ፣ ፍጥነትና የግብ አስቆጣሪነት ብቃቱ የሕዝቡን ትኩረት ሲያስገኝለት ለኮኮብነትም በይበልጥ አነሳስቶታል፡፡
ይህ እንደ እግር ኳስ በዓለም ሕዝብ ሁሉ ተወዳጅ የሆነ የስፖርቱ ፈርጥ በተለይም በብራዚላውያን ዘንድ የተለየ ክብር ቢሰጠው አይገርምም። ስፖርት ብዙም ትኩረት በማይሰጠው ዘመን ተፈጥሮ አገሩን በእግር ኳስ ምትሃቱ ከተሸናፊነትና የበታቸኝነት ስሜት ፈንቅሎ በማውጣት የአሸናፊነት ልቦና አላብሷል። ከእሱ በኋላ ለፈለቁ አያሌ ብራዚላውያን ከዋክብትም ምክንያት ሆኗል።
ፔሌ እግር ኳስን በተጫወተባቸው ዓመታት አስቸጋሪ ናቸው ተብሎ የሚታሰቡትን ክብረወሰኖች ማስመዝገብ ችሏል። እግር ኳስን በፊት መስመር አጥቂነት የተጫወተው ፔሌ በአጠቃላይ ለሀገሩና ለክለቦች 1ሺ363 ጨዋታዎችን አድርጎ 1ሺ281 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ ይህም በጨዋታ በአማካይ ለአንድ ግብ የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአራት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በመሰለፍ ሶስቱን (እአአ በ1958፣ በ1962 እና በ1970) የዓለም ዋንጫዎችን በማንሳት ብቸኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ነው፡፡ ፔሌ ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት እድሜው ባገለገለው በክለቡ ሳንቶስ በ15 እንዲሁም በብራዚል ብሄራዊ ቡድን በ16 ዓመቱ በመሰለፍና የዓለም ዋንጫንም በ17 ዓመቱ በማንሳት ታሪክ ሰርቷል፡፡ ሳንቶስም ለዚህ ውለታው በክለቡ አርማ ላይ የዘውድ ምልክት አስቀምጦለታል። ይህም ፔሌ የእግር ኳስ ንጉስ መሆኑን ለማስታወስ ታስቦ የተደረገ ነው።
ፔሌ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን 97 ጎሎችን ሲያስቆጥር ለክለቡ ሳንቶስ ደግሞ 1ሺ88 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፤ እአአ በ1958ቱ የዓለም ዋንጫ የውድድሩ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች፣ በ1970 የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች፣ በ1973 የደቡብ አሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የክብር ካባ ደርቧል። ከክለቡ ሳንቶስ ጋርም ስድስት የብራዚል ሊግ ዋንጫዎችን፣ ሁለት ኮፓ ሊበርታዶስ ዋንጫን፣ ሁለት የዓለም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡
ፔሌ ለሳንቶስ 18 ዓመታት ከተጫወተ በኋላ እአአ በ1975 የኒውዮርክ ኮስሞስ ቡድንን ተቀላቀለ፡፡ ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት ግን ፔሌ በብራዚላውያን እጅግ ተወዳጅና የአገር አርማ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበረ አገሩ ብራዚል ወደ ሌላ አገር ተሸጦ እንዳይጫወት አግዳዋለች። ይህም በሌሎች ታላላቅ የዓለማችን ክለቦች አፍላ አቅሙን እንዳያሳይና በጥበቡም የሀብት ማማ ላይ እንዳይቀመጥ አድርጎታል። የማታ ማታ ግን ወደ አሜሪካ አቅንቶ በሶስት ዓመታት የኒውዮርክ ቆይታው (በ1977)የሊግ ቻምፒዮን እንዲሆን አስችሏል፡፡ በዚያው ዓመትም በጀንትስ ስታዲየም በተገኘው 75ሺ ደጋፊዎች ፊት ተገኝቶ እግር ኳስን ሊሰናበት የግድ ሆኗል፡፡ ከእግር ኳስ ዓለም ከተገለለ በኋላም ለዓለም እግር ኳስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ቀጥሎ፤ እአአ በ1995 ለእግር ኳስ እድገት ሙያዊ ልምዱን እንዲያካፍል የብራዚል ስፖርት ልዩ ሚንስትር ሆኖ ተሾመ፡፡ በወቅቱም ከስፖርቱ ሙስናን ለማጥፋት በመስራቱ ‹‹የፔሌ ህግ›› የሚል ቅጽ ስም ተሰጥቶታል፡፡ የእግር ኳስ ስኬቱን ተከትሎ አምስት ዘጋቢ ፊልሞች የተሰሩለት ፔሌ፤ ስድስት ፊልሞች ላይ ተሳትፏል። አምስት መጻሐፍትን መድረስ ሲችልም አንዱ ወደ ፊልም ተቀይሯል።
ፔሌ በእግር ኳሱ ዓለም ከዋክብት የቀዳሚነቱን ስፍራ እንደሚይዝ ብዙዎች ቢስማሙም ከአርጀንቲናዊው አርማንዶ ማራዶና ጋር እያወዳደሩት የዘመኑን የንግስና ካባ አጎናጽፎውታል፡፡ ፔሌና ማራዶና ራሳቸው በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ለደጋፊዎቻቸው ‹‹እኔ እበልጥ፤ እኔ እበልጥ›› የሚለውን አጀንዳ እያነሱ የብዙዎቻችን ቀልብ መግዛትም ችለዋል። ከዚህም ጋር አያይዞም ፔሌ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹ሰዎች ስለ ፔሌና ማራዶና ይወያያሉ ለኔ ግን አልፍሬዶ ዲ ስቲፋኖ ጥሩ ተጨዋች ነው፤ በእርግጥ ማራዶና ምሳሌ አይደለም ከእግዚአብሔር ስጦታ የመቀበል ዕድል ነበረው ታላቅ ተጫዋች ነበር ግን ምሳሌ አይደለም››፡፡ ስፖርቱን የሚመራው ፊፋም ሁለቱን ተጫዋቾች በጋራ እአአ በ2000 የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጦች ብሏቸዋል፡፡ ለብዙ ዓመታት ይህን ጡዘት አፋፍመው ከቆዩ በኋላ ባልታሰበና በድንገተኛ የልብ ህመም ተቀናቃኙ ማራዶና እአአ 2022 በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ፔሌም እንዲህ ሲል ሀዘኑን ገለጾ ነበር ‹‹ዓለም አንድ ታላቅ ሰው አጣች፣ አንድ ቀን ሰማይ ቤት እግር ኳስን አብረን እንደምንጫወት ተስፋ አደርጋለሁ››። ፔሌ ከሁለት አመት በፊት ማራዶና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እሱም ብዙ እንደማይቆይ የታወቀው ይመስላል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም