ይህ ወቅት በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የአብይ ጾም (ሁዳዴ) መሆኑ ይታወቃል። በእኛዋ ኢትዮጵያ የሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮችም እስከ ትንሳኤ ራሳቸውን ከብዙ ነገሮች እንደሚቆጥቡ ይታወቃል። እቀባቸውም ከምግብ ባሻገር የአልኮል መጠጦችንም የሚጨምር ነው።
በአንጻሩ በ17 ክፍለ ዘመን በጀርመን የነበሩ መነኮሳት በዚህ ወቅት ራሳቸውን ከየትኛውም ምግብ ነክ ነገር ራሳቸውን በማራቅ «ዶፔልቦክ» በተባለ ቢራ ይዘልቁ እንደነበር ኦዲቲ ሴንትራል ያስነብባል። ነዋሪነቱን በኦሃዮ ያደረገ አንድ ግለሰብም እስከ ትንሳኤ ያሉትን 46 ቀናት ራሱን ከደረቅ ምግቦች ውጪ በማድረግ በቢራ ብቻ ጾሙን እያሳለፈ ይገኛል።
የአልኮል መጠጦች የአእምሮ ሚዛንን በማሳት ያልተገቡ ድርጊቶች ላይ ማሳተፋቸው እንደማይቀር ግልጽ ነው። በዚሁ ምክንያትም ጾመኞች ከማይተገብሯቸው ነገሮች መካከል አንዱ ቢራን የመሳሰሉ መጠጦች አለመጠቀም ነው። ዴል ሃል የተባለው ይህ ሰው ግን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጥንታዊያኑን መነኮሳት ታሪክ እየደገመ ይገኛል።
ባሳለፍነው ወር ጾሙን የጀመረው ሃል ከምግብ የሚያገኛቸውን ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ከቢራ እያገኘ መሆኑም ነው በዘገባው የተጠቀሰው። ጾሙ በመጀመሪያዎቹ ዕለታት ከባድ ቢመስለውም
ሰንበትበት ሲል ግን ወደ ጥሩ ሁኔታ መመለሱንም ገልጿል።
ሁኔታውን ሲያስታውስም «ሁለተኛውና ሶስተኛው ቀን ጥሩ አልነበሩም፤ ቢራ እጠጣ የነበረውም ሆዴን ቆልፎ እንዲይዝልኝ ነበር። በሚቀጥሉት ቀናት ግን የረሃብ ስሜት ስላልተሰማኝ ጥሩ ምልክት ነበር» ነበር ያለው።
እንደ እርሱ ሁሉ ጾሙን በቢራ ብቻ ያሳልፉ የነበሩት ጥንታዊያኑ መነኮሳት ቢራን «ፈሳሽ ዳቦ» ሲሉ ነበር የሚጠሩት፤ በውስጡ ባለው ከፍተኛ የሆነ የካርቦሃይድሬት ይዘት ማለት ነው። ሃል ግን ቢራው እንዳያሳምመው አልፎ አልፎም ቢሆን፤ ጥቁር ቡና፣ ስኳር የሌለው ሻይ እንዲሁም ውሃ ይቀማምሳል።
እርግጥ ነው የጾም ጥቅሙ መንፈሳዊ ነው፤ ሆኖም ሌሎች ጥቅሞችንም ማስከተሉ አይቀርም። ሃል ያገኘውን ጥቅም ብናነሳ እንኳን ጾሙን በጀመረበት አንድ ወር ብቻ ሞላ ካለው ሰውነቱ 34 ፓውንድ ቀንሷል። እንደእርሱ አባባል ከሆነም የማሽተት አቅሙ ቀድሞ ከነበረው በመጨመሩ እዚህ ተቀምጦ ከእዚያ ያለው ሽታ ያውደዋል።
ይህንን ድርጊቱን የመገናኛ ብዙሃን እየተቀባበሉት ሲሆን፤ እርሱም ሁኔታውን በዩቲዩብ እና በፌስቡክ ማስቀረቱ አልቀረም። ጾሙ ከተፈታ በኃላም ትንሽ በትንሽ እያደረገ ወደ ደረቅ ምግብ እንደሚመለስም አልሸሸገም። እናሳ ይህንን ሲሰሙ እንደጥንታዊያኑ መነኮሳት፤ «እውነትም ፈሳሽ ዳቦ» ሲሉ ቢራን አላንቆለጳጰሱትም?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
ብርሃን ፈይሳ