በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ የተመሰረተው (ለሕትመት የበቃው) ከ98 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ነበር፡፡
አንጋፋው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም በንጉሥ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) መኖሪያ ግቢ ውስጥ ጨው ቤት በሚባለው ባለ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ስራውን ጀመረ፡፡
ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ደግሞ ብርሃንና ሰላም የተባለውን ጋዜጣ ማተም ሲጀምር ስሙንም ከዚሁ ጋዜጣ ወረሰና ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› ተባለ፡፡ ይህም ማተሚያ ቤቱ ጋዜጦችን እንዲያትም (የማተም አገልግሎት እንዲሰጥ) አስቻለው፡፡
‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ በ500 ቅጂዎች ያህል በሳምንት አንድ ጊዜ (ሐሙስ ዕለት) ይታተምና፣ የስርጭቱም ሁኔታ ይካሄድ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
ጋዜጣው ሲመሰረት (ከ1917) ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የጋዜጣው ዳይሬክተር (ዋና አዘጋጅ ለማለት ነው) የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት የተባሉት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ በ1921 ዓ.ም አቶ ማኅተመወርቅ እሸቴ የጋዜጣው ዳይሬክተር ሆኑ፡፡
ጊዜው ለኢትዮጵያ የብርሃንና የደስታ ( ሰላም) እንዲሆን በመመኘት (በማሰብ) ንጉሥ ተፈሪ መኮንን የጋዜጣውን ስያሜ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ብለው እንደሰየሙት ይነገራል!
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም