የሰኔ ግርግር

የግንቦት ወር የዘመነ ደርግ እና የዘመነ ኢህአዴግ ክስተቶች ይበዙበት ነበር:: እነሆ የሰኔ ወር ደግሞ በዘመነ ብልፅግና የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተከታታይ ዓመታት በተከሰቱ ክስተቶች የሚታወስ ሆነ:: አንደኛው ከሰባት ዓመታት በፊት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተጣለው ቦምብና ግርግሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከስድስት ዓመታት በፊት (በሰኔ 16ቱ ክስተት በዓመቱ ማለት ነው) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ ደግሞ የከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያ ነው::

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከስድስት ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተውን የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በአዲስ አበባ የጦር መኮንኖችን ግድያ ክስተት እናስታውሳለን::

ከእዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የእዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ::

ከስድስት ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ደራሲ አውግቸው ተረፈ አረፈ:: አውግቸው ተረፈ በሚለው ስሙ ቢታወቅም ይህ ግን የብዕር ስሙ እንደሆነ ይነገራል:: ወላጆቹ ያወጡለት ስም ኅሩይ ሚናስ ነው:: ከመጽሐፍ ሻጭነት ተነስቶ ደራሲ የሆነው አውግቸው ተረፈ ከ20 በላይ መጻሕፍትን በድርሰትና በትርጉም በመጻፍ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይታወሳል::

ከ810 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 12 ቀን 1207 ዓ.ም ቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ አረፈ:: ንጉሥ ላሊበላ የተወለደበትም (ታኅሣሥ 29) ሆነ። ያረፈበት ቀን ሃይማኖታዊ ንግሥ ያለበት ስለሆነ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ይከበራል:: ንጉሥ ላሊበላ ከሰውየው በላይ ሥራዎቹ ስለሚታወሱ በላሊበላ ቅርስ እነሆ ለሚሊኒየም ዓመታት ይታወሳል::

ከ97 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 12 ቀን 1920 ዓ.ም ሐኪምና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ተወለዱ:: ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ከእዚህ በፊት በዝርዝር አስታውሰናቸዋል::

ከ10 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ አረፈ:: ዳሪዮስ ሞዲ በሬዲዮ ጋዜጠኛነት ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የዜና አንባቢ ነው:: በነጐድጓዳማ ድምጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ሰኔ 13 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከኢትዮጵያ ለቀው ሲወጡ፤ እንዲሁም ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ባነበባቸው ዜናዎች በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል::

ከ44 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 14 ቀን 1973 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሽ ጋር በተዋጉበት ቦታ (በኋላ ‹ዮሐንስ› ተብሎ በተሰየመው) ተራራ አናት ላይ ‹‹ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሾች ጋር የተዋጉበት ስፍራ›› ብሎ የደርግ መንግሥት መታሰቢያ አቆመላቸው::

ከ27 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 14 ቀን 1990 ዓ.ም ዶክተር እሸቱ ጮሌ አረፈ:: እሸቱ ጮሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማህበር መሥራችና ፕሬዚዳንት የነበረ ሲሆን፤ ከኢኮኖሚክስ ምሁርነቱ ባሻገር የፍትሕና ዴሞክራሲ ተሟጋች ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስሙ አዳራሽ (እሸቱ ጮሌ አዳራሽ) ሰይሞለታል::

ከ71 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ሰኔ 15 ቀን 1946 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ሜክሲኮ በሄዱበት ወቅት የሜክሲኮ መንግሥት በሀገሪቱ ዋና ከተማ ላይ በኢትዮጵያ ስም የሚጠራ አደባባይ ሰየመ:: ኢትዮጵያም አዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ የሚባል ሰፈር እንዳላት ይታወሳል::

ከ117 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን ሰኔ 16 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሞተን ሰው በአግባቡ መቅበር እንደሚገባ የሚገልጽ አዋጅ አወጁ:: አዋጁም የሚከተለው ነበር::

‹‹ሰው ሲሞት መቅበር ከጥንት የመጣ ልማድ ነበር አሁን ግን በየቦታው የሚታየው የሰው አጽም ብቻ ሆነ:: የጥንቱ ልማድ መቅረቱስ ለምንድን ነው? አሁንም በየገዳማቱና በየአድባራቱ በሌላውም ስፍራ ሳይቀበር የተገኘ የሰው አጽም፣ የክርስቲያንም ሆነ የሌላ፣ በየግዛትህ በየአጥቢያ ቦታ እያስፈለግክ በሥርዓት ቅበር:: ከእንግዲህ ወዲህ ግን በየግዛቱና በየአጥቢያው የሰው አጽም ሳይቀብር የተገኘ ሰው ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል::››

በእዚሁ በዝርዝር ወደምናየው የእዚህ ሳምንት ታሪክ እንለፍ::

የመስቀል አደባባዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ የቦምብ ፍንዳታ በተከሰተ በዓመቱ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ ተገደሉ:: እነዚህን ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች በጥቂቱ እናስታውስ::

ዶክተር አምባቸው መኮንን

ዶክተር አምባቸው መኮንን ሲሳይ ደቡብ ጎንደር ጋይንት ተወልደው አደጉ:: በልጅነታቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶችን አብልጠው ይወዱ እንደነበርና ምኞታቸውም መምህር መሆን እንደነበር በወቅቱ የተገለጸው ታሪካቸው ያሳያል::

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከእዚያም ትግሉን ከተቀላቀሉ ከ5 ዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በርቀት አጠናቀዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ነው። የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በሚገኘው ኬ ዲ አይ የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በቅድመ ምረቃም ሆነ በድህረ ምረቃ ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ምጣኔ ሀብትን ነው።

ከኮሪያ ተመልሰው ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ከእንግሊዙ ኬንት ዩኒቨርሲቲ ነው ያገኙት።

ዶክተር አምባቸው ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ በተለያየ እርከን አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል በአማራ ክልል የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነቶች ይገኙባቸዋል።

በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል። ከእዚያ በኋላም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ሠርተዋል።

ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፤ ከኅዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ እና ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል::

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከአስር አለቃ መኮንን ይመር እና ከወይዘሮ ሕይወት ይህደጎ በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገዳ ጽምብላ ወረዳ እንዳባጉና ከተማ 1954 ዓ.ም ተወለዱ::

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በእንዳባጉና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል እንዲሁም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽሬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: ነገር ግን በመማር ላይ እያሉ የደርግን ሥርዓት ለመታገል በሕወሓት የሚመራው የትጥቅ ትግል እየተካሄደ ስለነበር ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በ1969 ዓ.ም የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ:: በጉንደት ስልጠና ማዕከል ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው እስከ ታኅሣሥ 1971 ዓ.ም ድረስ በሕወሓት 91ኛ እና 73ኛ ሻምበሎች በተዋጊነት እና በጓድ መሪነት አገልግለዋል::

ከእዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ ያለው የጄኔራል ሰዓረ መኮንን ታሪክ የወታደርነትና የጦር መሪነት ታሪክ ነው::

በነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በ1988 ዓ.ም በሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ ጀምረው በ2010 ዓ.ም የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ደርሰዋል:: በነበራቸው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳልያን ጨምሮ በርካታ ኒሻኖችን ከኢፌዴሪ መንግሥት ማግኘታቸው የሚታወስ ነው::

ጄኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የመማርና ራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት በ‹ማኔጅመንት› የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ‹ትራንስ ፎርሜሽን› እና ‹ሊደርሽፕ› ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪኒዊች ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: ጀኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የማንበብ ልምድ የሚታወቁና ለሌሎችም አርዓያ የነበሩ መሆናቸው በወቅቱ የተነገረው ታሪካቸው ያሳያል::

ባለትዳር እና የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጆች አባት የነበሩት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፤ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከተደረገው ግድያ በኋላ ‹‹በጠባቂያቸው ነው›› በተባለ የጥይት ተኩስ ተገድለዋል::

በእዚሁ ዕለትና በእዚያው ሰዓት ከጄኔራል ሰዓረ መኮንን ቤት የነበሩትና ከመከላከያ በጡረታ የተሰናበቱት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ተገድለዋል::

በተመሳሳይ በእዚሁ ዕለት፤ የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ እዘዝ ዋሴ በእዚያው በባሕር ዳር ተገድለዋል::

አቶ ምግባሩ ከበደ

ከእዚሁ ጋር ተያያዥ የሆነውና ያረፉበት ቀን የሚለየው የአቶ ምግባሩ ከበደ ነው:: አቶ ምግባሩ ከበደ ያረፉት ከሁለት ቀን በኋላ ነው::

አቶ ምግባሩ ከበደ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በ1966 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፤ ሥራ የጀመሩት የወረዳና ዞን ዐቃቤ ሕግ በመሆን ነበር።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ የደብረ ማርቆስ ከንቲባ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፣ የአዴፓ የገጠር ፖለቲካና አደረጃጀት አማካሪ፣ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኃላፊ በመሆን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።

አቶ ምግባሩ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተፈጸመው ጥቃት በጥይት ተመተው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ነው ሕይወታቸው ያለፈው::

ከእነዚህ ቀናት በኋላ በእዚያው ሳምንት፤ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ግድያ መርተዋል የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በድርጊቱ ተጠርጥረው በጸጥታ ኃይሎች እየተፈለጉ ባለበት ‹‹ለማምለጥ ሞክረዋል›› በሚል በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውም የእዚሁ ታሪክ አካል ነው::

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በነበረው ግርግር የተገደሉ

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You