አንድ ለስፖርት ቅርበት የሌለው ሰው ‹‹እስኪ ከድሮ የስፖርት ጋዜጠኞች የአንድ ሰው ስም ጥቀስ›› ቢባል ‹‹ደምሴ ዳምጤ›› ሊል ይችላል፡፡ ደምሴ ዳምጤን የሚያውቅ ሰው ደግሞ ‹‹እስኪ ከደምሴ ዳምጤ ምን ታስታውሳለህ?›› ቢባል ወዲያውኑ ወደ አዕምሮው የሚመጣው ‹‹…ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን…››
‹‹…ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ!…›› የሚለው አይረሴ ድምጹን ነው፡፡
ይህ የደምሴ ዳምጤ ድምጽ የብዙ የሬዲዮ ስፖርት ፕሮግራሞች መግቢያ ነው፡፡ በየመሃሉም መሸጋገሪያ ነው። በሌሎች የታሪክና የትዝታ ፕሮግራሞችም ይጠቀሳል፡፡ ወጣቶች በተለያዩ የጨዋታ መድረኮች ላይ ለማስመሰል ይጠቀሙታል፡፡ በአጠቃላይ ማንም ለስፖርት ቅርብ ያልሆነ ሰው ሁሉ ሳይቀር ይህን የደምሴን ድምጽ ሰምቶ አያውቅም ለማለት አያስደፍርም፡፡
የደምሴ ዳምጤን የስፖርት ጋዜጠኝነት ሕይወት በሌላ ዓምድ የምናየው ይሆናል፡፡ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ግን ይህ አይረሴ ድምጹ ከ35 ዓመታት በፊት የተሰማበትን ክስተት እናስታውሳለን፡፡ ይህ ድምጹ የተሰማው በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ክስተቱን እናስታውስ!
‹‹ … ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … (እንባና ሳቅ እየተናነቀው) አማኑኤል! አማኑኤል ለገብረመድኅን … ገብረመድኅን! ገብረመድኅን በጭንቅላት የመታውን ኳስ የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … ጨዋታው ወደማለቁ ነበር፡፡ አማኑኤል ለገብረመድኅን የሰጠውን ኳስ ሁለት ቁጥሩ የዚምባብዌው በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … አሁን አንድ ለአንድ ካለቀ 30 ደቂቃ ይጨመራል፡ ፡ ሰዓቱ አልቆ ነበር፡፡ … ተመልካቹ ተደስቷል። ዙሪያውን እያጨበጨበ ነው፡፡ ደከም ብለው የነበሩት ተጨዋቾቻችን በመጨረሻ ላይ ባገኙት እድል በመጠቀማቸው አሁን … አሁን … 30 ደቂቃ መጨመሩ አይቀርም … ››
‹‹ … አሁን ዳኛቸው ነው የሚመታው … አሁን ዳኙ ሊመታ ነው … አሁን ይገላግለናል … ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ! ዳኝሻ አገባ! በጣም አስደናቂ ግብ ነው ዳኝሻ! ቀኙን አሳይቶ ግራውን፤ ግራውን አሳይቶ በቀኙ … አሁን ተጨዋቾቻችን ደስታቸውን እየገለጹ ነው! … ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው … ተመልካቹም ‹እንደተመኘኋት አገኘኋት› እያለ ነው … ችቦ በራ! ስታዲዬሙ ተንቀለቀለ …››
ይህ ሳቅና እንባ የተቀላቀለበት የደምሴ ዳምጤ የደስታ ጩኸት የተሰማው ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ) ለመጀመሪያ ጊዜ ስታሸንፍ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና ስምንት አገራት (ኢትዮጵያ፣ ዚምባብዌ፣ ዛንዚባር፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ) በተካፈሉበት 15ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ/CECAFA) ለፍፃሜ የቀረቡት አስተናጋጇ ኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ነበሩ፡፡ የወቅቱ የሁለቱ አገራት መሪዎች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እና ሮበርት ሙጋቤ ነበሩ፡፡
በዚህ ዕለት ጨዋታ (ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም) መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜው የተጠናቀቀው 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ነበር፡፡ በዕለቱ 2 ቁጥር መለያ ለብሶ ለዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የነበረው ተጫዋች በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የአቻነት ግብ ሲያገኝ በዕለቱ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ‹‹ … ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … (እንባና ሳቅ እየተናነቀው) አማኑኤል ለገብረመድኅን … ገብረመድኅን በጭንቅላት ገጭቶ የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … ጨዋታው ወደማለቁ ነበር … አሁን 1 ለ 1 ካለቀ 30 ደቂቃ ይጨመራል … ተመልካቹ ተደስቷል … 30 ደቂቃ መጨመሩ አይቀርም … ›› እያለ በስሜት ይጮህ ነበር፡፡
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜው 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቆ በተሰጡት የመለያ ምቶች ዳኛቸው የመጨረሻዋን ግብ ሲያስቆጥር ጋዜጠኛ ደምሴ ‹‹ … አሁን ዳኛቸው ነው የሚመታው … አሁን ዳኙ ሊመታ ነው … አሁን ይገላግለናል … ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ! ዳኝሻ አገባ! በጣም አስደናቂ ግብ ነው ዳኝሻ! ቀኙን አሳይቶ ግራውን፤ ግራውን አሳይቶ በቀኙ … አሁን ተጨዋቾቻችን ደስታቸውን እየገለጹ ነው! … ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው … ተመልካቹም ‹እንደተመኘኋት አገኘኋት› እያለ ነው … ችቦ በራ! ስታዲዬሙ ተንቀለቀለ …›› ብሎ የተናገረው የደስታ ጩኸት እነሆ ዛሬ ድረስ ከብዙ ሰው አዕምሮ አልተዘነጋም፤ ወደፊትም አይዘነጋም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም