ኢትዮጵያ የበርካታ መስህቦች ባለቤት ነች። ውብ ተፈጥሮን፣ ባህሎችን፣ ዘመናትን ያስቆጠሩ ታሪክና ቅርሳ ቅርሶችን ይዛለች። “ምድረ ቀደምት” የሚለውን ስያሜ ያሰጣት የሰው ዘር መገኛና የልዩ ልዩ አርኪዮሎጂካል ሀብቶች ባለቤትም ጭምር ናት።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የባህል ቅርስ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቻቸውን ካስመዘገቡ ሀገራት መካከልም አንዷና ቀዳሚዋ እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ። በዩኔስኮ በአራት የማይዳሰሱ እና በዘጠኝ የሚዳሰሱ (በአጠቃላይ 13) ቅርሶች እውቅና አግኝታለች። እነዚህ ዓለም አቀፍ ቅርሶችም አገሪቱን በዩኔስኮ ከአፍሪካ ከፍተኛውን የመስህብ ሀብት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ አስመድበዋታል።
ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የሰው ልጅ ያፈራቸውንና የየዘመናቱን የህንፃ ጥበብ እውቀት የሚያሳዩ ሀብቶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ አያሌ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል ለሚመዘገበው ቅርስ መጠበቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ የመላውን ዓለም ትኩረት እንዲያገኝ ይረዳል። ቅርሱን በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን ለመሳብና የገቢ ምንጭ ለማድረግ እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ የራሱ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። ቅርሱ ምናልባት ጉዳት የሚደርስበት ቢሆንና ጥገናና እንክብካቤ ቢያሻው የባለሙያና የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘትም እድሉ ሰፊ መሆኑን ነው እነዚሁ ምሁራን የሚናገሩት።
ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ ካስመዘገበቻቸው 13 ሀብቶች በተጨማሪ አምስት የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና ሌሎች የቅርሳ ቅርስ ሀብቶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ ሰፍረው በቋሚነት በዓለም ቅርስነት እስኪመዘገቡ ድረስ እየተጠበቁ ይገኛሉ። እነዚህም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ (እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 የተመዘገበ)፣ የድሬ ሼህ ሁሴን ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራ፤ የሶፎመር ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርስ፣ የመልካ ቁንጥሬና ባጪልት አርኪዮሎጂካል ስፍራ እንዲሁም ዛሬ በስፋት የምንዳስሰው የጌዲዮ መልክዓ ምድርና ባህላዊ ስርአት ይገኙበታል።
የዝግጅት ክፍላችን ከሰሞኑ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ ጫፍ የደረሰውን ፣ መልከዓ ምድርና ቅርስ ይህን መልከዓ ምድር ለመጠበቅ እንዳስቻለ የሚታመንበት የጌዴኦ ባህላዊ ስርአት ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ከመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ወደ ጌዴኦ ዞን አንዳንድ ቦታዎች አቅንቶ ነበር። በዚህም ስፍራዎቹን ከመመልከቱም በላይ የምዝገባ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ የትኞቹ ሀብቶች በዓለም ቅርስነት እንደሚመዘገቡ መረጃዎችን አግኝቷል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊዎችን እና የዞኑን አስተዳዳሪዎችን አነጋግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ባለስልጣኑ የጌዴኦ መልከዓ ምድርንና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ የዞኑ ቅርስ ሃብቶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ፣ ለማስተዋወቅና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ። የሶስት ሺሀ ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች ባለቤት መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች መካከልም 9 የሚዳሰሱ እንዲሁም አራት የማይዳሰሱ በአጠቃላይ አስራ ሶስት ቅርሶቿን በዓለም አቀፍ ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗንም ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ቅርሶች ዛሬ ላይ ህያው ምስክር ከመሆንም ባሻገር በቱሪስት መስህብነት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ኢኮኖሚውን እየደጎሙና አገርንም ለመላው ዓለም እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ያስረዳሉ። የጌዴኦ መልከዓ ምድርና ባህላዊ ስርአት ደግሞ በዩኔስኮ ሲመዘገብ ተጨማሪ የቱሪዝም አቅምና የህብረተሰቡ የኩራት ምንጭ እንደሚሆን ነው የሚገልፁት።
በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በጊዜያዊነት ተመዘገብው የቆዩት የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድርን ባህላዊ ስርእቱ እንዲሁም ሌሎች ሀብቶችን በቋሚነት ለማስመዝገብ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፤ በመገናኛ ብዙሃን የተጎበኘው ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገበት የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ ስርአት፣ መልከዓ ምድርና ቅርስ ተጠቃሽ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህ ሀብት ባለፈው ዓመት ይመዘገባል ተብሎ ሲጠበቅ እንደነበረ አስታውሰው፣ በሩሲያና በዩክሬን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ቅርሱ እንዲመዘገብ ይሁንታ የሚሰጠው ኮሚቴ ውሳኔውን የሚያስተላልፍበትን ጊዜ ለሌላ ጊዜ ማሸጋገሩንም ተናግረዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንዳሉት፤ የጌዴኦ ባህላዊ ቅርስ በርካታ ገፅታዎች አሉት። በተለይ የግብርናና ደን ልማትና ጥበቃ ስርአቱ ፣ የሜጋሊቲክ ሀውልቶች፣ የሮክ ጥበብ ቦታዎች እና በባህላዊ ስርአቱ የተጠበቁ ደኖች ልዩ ያደርጉታል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የጌዴኦ ማህበረሰብ ከሚኖርበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር የተጣጣመ የግብርናና ባህል ስርአት ያለውና በረቀቀ የጥምር ግብርናና /አግሮ ፎረስተሪ/ ደን ልማት ስርዓት የሚመራ ነው፡፡ ይህም መሰል ልምድ ለሌላቸው አካባቢዎች ትልቅ ተሞክሮ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋትና የቅርስ ሀብቶቿ ብዛት አንጻር በአንድ ተቋም (በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን) ብቻ ጥበቃና እንክብካቤው፣ የማስተዋወቁ፣ የምዝገባው ማሰባሰቡ እና ሌሎችም ተግባራት እንደማይሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ሁሉም የሚመለከተው አካል በዋናነትም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የቅርሱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ በዚህ ላይ ተቀናጅተው መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ባለስልጣኑ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች እሴታቸው በተጠበቀ መልኩ ተጠብቀውና ለምተው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማስቻል ነው፡፡ ተቋሙ በቅርሶች ላይ ምዝገባና ቁጥጥር በማካሄድ፣ ቅርሶችን በመፈለግ፣ በማሰባሰብ፣ በመንከባከብ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉ ለማድረግ፣ ቅርሶችን ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ይሰራል፡፡ ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ እንዲደራጁና ለጎብኚዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ ከቅርሶች የሚገኙ ጥቅሞች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እገዛ እንዲያደርግ ለማስቻል በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ግንዛቤ መፍጠርና ቅርሶቻችን በሁሉም ዓለም እንዲተዋወቁ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት መስራትም ሌላው ኃላፈነቱ ነው። የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድርንም ከዚህ አንፃር ለመቃኘትና ቅርሱን ጠብቆና ለዓለም ማህበረሰብ አስተዋውቆ ከዚያ ከሚገኘው ጥቅም አገር ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው።
የጌዴኦ መልከዓ ምድርና ባህላዊ ስርአትን ማስተዋወቅና የመገናኛ ብዙሃን ሚና
የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መመሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ማሩ በዞኑ የሚገኘው ወግድ አምባ የሚባለው አካባቢ በዩኔስኮ በሚዳሰስ ቅርስነት ሊመዘገብ የተቃረበው “የጌዴኦ ጥብቅ ደን” የሚገኝበት ቀበሌ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ከዲላ እስከ ወግድ አምባ ያለው አካባቢም በጥምር ግብርና ስርዓት፣ በመልካ ምድሩና በጥቅጥቅ ጥብቅ ደን የታደለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ጊዜያዊ ምዝገባ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል ይላሉ።
ኃላፊው በጌዴኦ የሜጋሊቲክ አርኪኦሎጂካል ስፍራዎች/ ትክል ድንጋዮች / በብዛት እንደሚገኙም ጠቅሰው፣ ለአብነትም ቱቱ ፈላ ሜጋሊቲክ፤ ጨልባቲቲቲ ሜጋሊቲክ፣ ሴዴ መርካቶ ሜሜጋሊቲክ ፣አዶላ ጋልማ ሮክ ጥበብ እንዲሁም የተጠበቁ ደኖች እና ሌሎችም በርካታ እምቅ ሀብቶች በዞኑ እንደሚገኙ ያብራራሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ሀብት አስተሳስሮ የያዘው መልከአ ምድርም በቅርቡ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት የሆነው ዩኔስኮ ስብሰባ ላይ በቋሚነት እንዲመዘገብ ሊወሰን እንደሚችል ነው የሚናገሩት።
የጌዴኦ ሕዝብ በአካባቢ ጥበቃ ባህሉ ደንና አካባቢን እንደ ልጁ በመንከባከብ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር የሚመሳሰል ባህላዊ እውቀት ባለቤት መሆኑን ይገልጻሉ፤ የጌዴኦ መልከዓ ምድር በርካታ ገጽታ እንዳለው ጠቁመው፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ በአፍሪካ ደረጃ ተጠቃሽ የቱሪዝም ሀብቶች የሆኑ ትክል ድንጋዮችና የድንጋይ ላይ ጽሁፎች ባለቤት መሆኑንም አስረድተዋል። ይህንንም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የወረቀት ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ምዕራፎችን በማለፍ ምዝገባው እየጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ግርማይ “የጌዴኦ ባህላዊ ስርአትና መልክዓ ምድር ቅርስ የምዝገባ ሂደት ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደሚሉት፤ የእርሻና የደን ጥበቃ ሀገር በቀል እውቀት፣ ትክል ድንጋዮች፣ የዋሻ ውስጥ ስዕሎች፣ ጥብቅ ደኖች እንዲሁም የደራሮ፣ የሶንጎ እና መሰል ባህላዊ ስርአቶች መልከዓ ምድሩን ጠብቆ ማቆየት ያስቻሉ ሀብቶች መካተታቸውን ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ የጌዴኦ ባህላዊ ስርአትና መልከዓ ምድር የዓለምን ትኩረት እንዲያገኝ ከማስተዋወቅና ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ከማስቻል አንፃር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን መሆን ይኖርበታል፡፡
የጉብኝቱና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ዓላማ፣ በዋነኛነት በሀገራችን በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ያለውን 296 ነጥብ 2 ስኩየር ኪ.ሜ ላይ ያረፈውን የጌዴኦ የመልከዓ ምድር ቅርስ ለውጭ፣ ለሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲሁም ለመላው ማህበረሰብ በሰፊው በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ አንፃር የመገናኛ ብዙሃን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ይላሉ። በተለይ የመገናኛ ብዙሃኑ ማህበረሰቡ ስለ ቅርስ ሀብቶቹ በቂ ግንዛቤ ኖሮት በመጠበቅ፣ በመንከባከብና ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል ዋንኛ ባለድርሻ አካል መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
“ማህበረሰቡ ቅርሱንም እየጠበቀ ከዘርፉም ተጠቃሚ ለመሆን ስለጌዴኦ መልከዓ ምድር እና ባህላዊ ስርአቱን ምንነትንና አካቶ የያዛቸውን የተለያዩ ክፍሎችን ማወቅ ይኖርበታል” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የመገናኛ ብዙሃን በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ቅርሱን በሚመለከት ለሚሰሩት ዘገባ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ብሎም በዞኑ ውስጥ ያሉትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲያስተዋውቁ እድል ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ የቱሪዝም ጋዜጠኞችና የቅርሱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ የሀገር ዋልታና ማገር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙትን የጌዴኦ መልከዓ ምድርና ባህላዊ ስርአት እንዲጠበቁና ለትውልድ እንዲሻገሩ እጅና ጓንት ሆነው መስራት ይኖርባቸዋል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል። ከነዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራበት ያለውን የጌዴኦ ባህላዊ ስርአትና መልከዓ ምድር ቅርስ ለምዝገባው እንዲታጭ አስተዋጽኦ ያደረጉትን፣ የላቀ እሴትነት ያላቸው መስፈርቶቹን፣ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ፋይዳዎቹን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
እንደ መውጫ
የጌዴኦ መልከዓ ምድር በውስጡ ጥብቅ ደን፣ ጥምር ግብርናና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ትክል ድንጋዮችን ያካተተ ሲሆን፣ በምስራቅ አፍሪካ በእድሜ ረጅም እንደሆኑ የተነገረላቸው ከ6000 በላይ የትክል ድንጋዮች በዞኑ እንደሚገኙም መረጃዎች ያመለክታሉ። ቅርሱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንም የመገናኛ ብዙሃን የመስህብ ሀብቱን ከማስተዋወቅና ለማህበረሰቡ ያለውን ፋይዳ በስፋት ከማስገንዘብ አንፃር ጉልህ ድርሻ አላቸው በሚል ወደ ስፍራው የልኡካን ቡድን ይዞ በስፍራው በመገኘት ምልከታ አድርጓል። መገናኛ ብዙሃንም ይህን ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም