ስለ ስልጡንነቷ፣ የተለያዩ ዜጎች መኖሪያ ስለመሆኗ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና «ዲፕሎማቲክ» ከተማ መሆኗን እና ሌላም ሌላም እያሉ ያንቆለጳጵሷታል፤ አዲስ አበባን። እርግጥ ነው የሃገሪቷ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ከሌሎች ከተሞች አንጻር ስትስተዋል የተሻለ ነገር አላት።
«አዱ ገነት» በሚል የሚያቆላምጧት ወዳጆቿም በዜማ ተቀኝተውላታል፣ በተመረጡ ቃላት ታሪኳን ከትበዋል፣ ሰዓሊያንም በሸራቸው ነድፈዋታል፣ ስንኝ ተቋጥሮላታል፣ … አሁን ግን የብዙዎች ምርጫ የሆነችው ከተማ ሳታረጅ አልቀረችም። ምክንያቱም ከስሟ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ አኳኃን ላይ ነዋ የምትገኘው።
ብዙ የተባለላትን ይህቺን ከተማ ዞር ዞር ብዬ ልመልከታት ያለ ሰው በእግርም ሆነ በመኪና የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። መቼም የሰው ልጅ ለማዳ ነው፤ የትም ወስዳችሁ ብታስቀምጡት ራሱን ከሁኔታዎች ጋር አዋድዶ መኖርን ተክኖበታል። አዲስ አበቤዎችም ለምደውት እንጂ አኗኗራቸው ከባድ የሚሰኝ ዓይነት ነው።
በተለይ እንዲህ ዓይነቱ ርዕስ ከተነሳ አይቀር የኑሮ ውድነት፣ ለቤት ኪራይ፣ ልጆችን ለማስተማር፣ ለትራንስፖርት፣… ከባድ ሆኗል። ሌላው ቀርቶ አንድ ምግብ ቤት ገብቶ ለመገልገል እንኳን ድሮ ድሮ ሲታይ የሚያስደነግጠውን አረንጓዴ የብር ኖት በብዛት የሚያስመዝዝ ሆኗል። ነዋሪውን ስለ ኑሮው ብትጠይቁት ይህን መሰሉን ምሬት ያሰማችኋል።
አዲስ አበባ የበርካቶች ምኞት ናት፤ በሌላው የሃገሪቷ ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ኑሯቸውን ለማሻሻልና ነጋቸውን ለማቃናት ያልሟታል። ገባሮቿም በርካቶች ናቸው፤ በየዕለቱ ሰው እንደ ደራሽ ይጎርፍባታል። እንዲያም ሆኖ በቃኝ አታውቅም፤ ባይሆን በኑሮ ሁኔታዋ አማርራ ወደ መጡበት ትመልስ ይሆናል እንጂ።
የእኔ ትዝብት ግን ከኑሮው ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ነገርን ነገር አመጣው እንጂ ነገሬ ከጎዳናዎቿ ነው። መቼም በዚህ ያልተማረረ ሰው የለምና ጎዳናዎቿ ስል በሰው አእምሮ ቀድሞ የሚቀረጸው የመንገዶቿ ጥራት አልባነት ጉዳይ ነው።
እውነት ነው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እግረኛ እና
መንገደኛን ከማስተናገድ ባለፈ የተለያዩ ስራዎች አሏቸው። መንገዶቿ የንግድ ማዕከላት ናቸው፣ የዕቃ ማከማቻ ናቸው፣ የቆሻሻ መጣያ እና የፍሳሽ ማስወገጃዎች ናቸው፣ አንዳች ክብረ በዓልና መሰል ክንውን ሲኖርም ድንኳን ተጥሎባቸው እንደ ዳስ ይሆናሉ፣ ጸሃይ ብልጭ ሲልም መጥፎ ጠረንን ለአካባቢው ይለግሳሉ፣ ክረምት ሲመጣ ደግሞ እንደ ወንዞች ሁሉ ጎርፍን በማሳለፍ ሚናቸውን ይወጣሉ።
ታዲያ በእነዚህ ዘርፈ ብዙ ጎዳናዎች ላይ ጸሃይ ማቆልቆል ጀምራ ነፋሻማ አየር መንፈስ ሲጀምር በስራ የተወጠረ አእምሮዎትን ለማሳረፍ፣ አየር ለመቀበል፣ በእርምጃ አሊያም በሩጫ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ በእግረ መንገድ ከወዳጅ ጋር ለመጨዋወት፣ እዚያም እዚህም መንገዱ እየተዘጋጋ ረጅም ሰዓታትን በመኪና ውስጥ መቆየትን በመጥላት፣ ህጻናት ልጆችን ለማንሸራሸር፣ ለከተማው አዲስ የሆነን ሰው ይዘው በጎዳናዎቿ ላይ መንቀሳቀስ፣ አሊያም ለጉዳይ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ለማቅናት የማይታሰብ እየሆነ ነው።
ይህንን ጉዳይ እርስዎም ታዝበውት ይሆናል፤ አዲስ አበባ ላይ በእግር ለመጓዝ በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ ይግድ ይልዎታል። ቀጥ ባለ አንድ መንገድ ረጅም ርቀት መጓዝማ እጅግ ለተወሰኑ ጎዳናዎች ብቻ የተፈቀደ ነው የሚመስለው። ከሰፈርዎ ብንነሳ በርዎን ከመክፈትዎ ደጃፍዎ ተቆፍሮ በአፈርና በድንጋይ ቁልል ተመሰቃቅሎ ያገኙታል(የእድሜ ባለጸጎችን፣ ህጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችን፣… ደግሞ አስቡ)።
ጥቂት ሲራመዱ ደግሞ በአሸዋ፣ በድንጋይ፣ በአፈር እና በሌሎች የግንባታ ቁሳቁስ መንገድዎ ታጥሮ ያገኙታል። በዚህ ብቻ አያበቃም፤ እነዚህን ቁሳቁስ የሚጭኑ እና የሚያወርዱ መኪኖች እንዲሁም የግንባታ ማሽኖች የመኪናውንም መንገድ በከፊል ዘግተውት ይመለከታሉ። የእርስዎ አማራጭም መኪና ገጨኝ አልገጨኝ እያሉ መሃል መንገድ ላይ መጓዝ ነው።
አለፍ እንዳሉ የተለያዩ ዕቃዎችን ለሽያጭ የያዙ ነጋዴዎች ይገጥምዎታል። መንገድዎ ላይ በተነጠፉት ሸራዎች «ይህንን ይግዙን፤ ይህ ዕቃ በርካሽ» እያሉ በጩኸት ጭምር የሚጋብዞት ነጋዴ ስለ እርስዎ ደህንነት ጥቂት እንኳን አያሳስበውም። ጭራሽ ደንብ አስከባሪ ሲመጣበት ገፈታትርዎት ከመሮጥ ወደኃላ አይልም።
በዚህ ሰበብ ስለተጣሰው ህጋዊነት እያሰቡ ሳለም፤ በህጋዊ መንገድ የተከፈቱ ሱቆች ላይ ይደርሳሉ። ግን እዚያም የሚሸጡ እቃዎች እንዲታዩ በከፊል የእግረኛ መንገድዎን ተሻምተውት ነው የሚያገኙት። ደግሞ የጀበና ቡና በመባል የሚጠሩ የመንገድ ዳር መሸጫዎች አሉላችሁ። መንገድዎ ላይ መቀመጫዎችን ደርድረው ልክ እንደመብታቸው በኩራት ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱ።
ይህንን ሁሉ አቆራርጠው ከዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሲደርሱማ የት እንዳሉ ከሚያጠራጥርዎት የህዝብ ጎርፍ ይቀላቀላሉ። የእርስዎ ቢጤ ባለ ጉዳይ እግረኞች ከመብዛታቸው የተነሳም ልክ እንደ ሰልፍ ተጠባብቀውና ተራዎትን እየጠበቁ መጓዝ የግድ ይሆንብዎታል። የሚገርመው ደግሞ በዚህ አጀብ መሃል ሌላውን ማሳለፍ የማይፈልግ፣ ቀስ ብሎ የሚጓዝ፣ ድንገት ቆሞ መንገድዎን የሚዘጋ፣… ማጋጠሙ አይቀሬ ነው።
ጉዞ በአዲስ አበባ የእግረኛ መንገዶች ላይ ከባድ ነው። ወዲህ በመንገዱ ብልሽት፣ ወዲያ በነጋዴዎች እንዲሁም በተጠቃሚው የኤሊ ጉዞ እያዘገሙ ሰዓትዎን ያባክናሉ። በአንጻራዊነት ሻል ያለ ስፍራ ደርሰው መራመድ ሲያሰኝዎ ደግሞ «ሰልፊ» የተባለ ሌላ እንቅፋት ያስተናግዳሉ። ይህኛውን ለየት የሚለው ዘመናዊነትን በተላበሱ ከተሜ ወጣቶች ፎቶ ለመነሳት የሚደረግ ድንገቴ ገጠመኝ ነው።
አካል ጉዳተኞች የተለየ እንክብካቤ የሚሹ የህብረተሰባችን አንድ ክፍል ናቸው፤ ነገር ግን በአዲስ አበባ መንገዶች መሄድ ሌላ ፈተና ነው። የመንገዱን ወጣገባነት ብንተወው እንኳን ለእነርሱ በሚል የተሰሩ መንገዶች የሌላ አደጋ ምንጮች ነው የሚሆኑት። ምክንያቱም መድረሻቸው ወይ ከዛፍ፣ ወይ ያለ ስራ የተቆፈረ ጉድጓድ፣ ወይ ከውሃ መውረጃ ቦይ አሊያም ከአውቶብስ መጠበቂያዎች ነዋ።
ሰሞኑን ዝናብ እየዘነበ መሆኑን ተከትሎም ጉዞው ሌላ ችግር አስከትሏል። በየቦታው ውሃ በሚያቁሩት እና ትንንሽ ኩሬዎችን በሚፈጥሩት መንገዶች ላይ የሚያልፉት ማለት ነው። ምክንያቱም ውሃውን ሲረግጡት ጦሱ ለእግረኞች የሚተርፍ በመሆኑ፤ እግረኛው ወዲያ ትንሽ ውሃ ከአስፓልቱ ሲመለከት በ«ተረጨሁ አልተረጨሁ» ሰቀቀን ነው መንገዱን የሚሄደው።— እነሆ አዲስ አበባችን ዛሬ እንዲህ ናት፤ ነገስ?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
ብርሃን ፈይሳ