የዛሬ አስራ ሁለት አመት ገደማ በአንዱ ቀን ነበር፤ አነስ ካለችው ጎጆ ውስጥ የሰቆቃ ድምፅ መሰማት የጀመረው። ቀኑ ሊነጋጋ አካባቢ ቢሆንም የንጋት ጨለማ ነገር ሆኖ አይን ቢወጉ የማይሰማ ያህል ድቅድቅ ጨለማ ነበር። በትንሿ ጎጆ ውስጥ የተለኮሰችው ሻማ ጨለማውን ገፍፋ በብርሃን ለመሙላት እየተፍጨረጨረች ወዲያና ወዲህ ትወዛወዛለች። አቶ ነገሰ አለሙ የሚይዙት የሚጨብጡትን አጥተው ወጣ ገባ ይላሉ።
ይህች አነስተኛ ጎጆ ከመንደሩ ነጠል ብላ አንድ ጉብታ ስር የተሰራች በመሆኗ እንኳን እንዲህ ጨልሞ በቀኑም የተወሰነ ሰው ወደ ቦታው ከመምጣቱ በስተቀር የሰው ዘር ዝር አይልም ነበር። “እ…እ…እ ወይኔ እናቴ ኡ….ኡ….ኡ ድረሱልኝ” ከዛ ደግሞ ዝም “ እመቤቴ እባክሽ አግዥኝ መሞቴ ነው” በማለት ታቃስታለች። የአቶ ነገሰ ባለቤት በምጥ ተይዛ የምታሰማውን የሰቆቃ ድምፅ ማዳመጥ የቃታቸው ባለቤቷ አልነጋ ብላቸው ደጅ ደጁን ያያሉ።
አቶ ነገሰና ባለቤታቸው ከተጋቡ አንድ አመት ከሁለት ወር አካባቢ ሆኗቸዋል። የበኩር ልጃቸውን ለመቀበልም ለዘጠኝ ወራት በጉጉት ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ዛሬ የባለቤታቸው የምጥ ቀን ደረሰ፤ ከምሽት ጀምሮ እጅግ በጣም በከባድ ስቃይ ውስጥ ያነጋችው ወይዘሮ ስቃይ ለመገላገለ ከዛኛው መንደር አዋላጇን ለማመጣት ነጋ አልነጋ እያሉ ደጅ ደጁን በጉጉት ይመለከታሉ።
አይነጋ የለም ምድርና ሰማይ ተላቀቁ። ያኔ አቶ ነገሰ በሩጫ ወዲያኛው ሰፈር ሄደው አዋላጇን ሴትና ሌሎች ሰዎችን አስከትለው መጡ። በስቃይ ውስጥ ሃያ አራት ሰዓት ሊሞላት የደረሰችው ወይዘሮ በህመምና በስቃይ ተዳክማ የደረሱት አዋላጅ ሴት ልጅ እንድትገላገል ቢያግዟትም እሷን ግን ከሞት ማትረፍ አልቻሉም ነበር። በምጥ ድካም የተከደነው አይኗ ሳይገለጥ እስከ ወዲያኛው አሸለበች።
አቶ ነገሰ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጡ፤ በሀዘን ተቆራምደው አቅላቸውን ሳቱ፤ ነገር ግን ጨቅላዋን ሲመለከቱ ደግሞ ትንሽ ተስፋ ይታያቸው ጀመር። እቺን የሚስታቸውን ምትክ አስቴር ነገሰ ብለው ሰየሟት። ከአስቴር ጋ ግን ከሶስት አመት በላይ ሊኖሩ አልቻሉም። ሚስታቸውን በሞት ያጡት እኚህ ሰው ልጃቸውን ለብቻቸው ለማሳደግ ቢሞክሩም ሀዘን ውስጣቸውን ጎድቶ አላላውስ ብሏቸው ገና የሶስት አመት ህፃን እያለች እሳቸውም በሞት ተለዩ።
እደለቢሷ አስቴር
ስትወለድ ጀምሮ እናቷን አጥታ በደንብ ነፍስ ሳታውቅ ደግሞ ወላጅ አባቷን ያጣችው ህፃን ለነፍሴ ያለ እየወሰደ አመትም ሁለት አመትም እያሳደገ ለሌላው ሲያቀበል ሌላው ደግሞ አሳዳጊነቱንም ያለውን ስራ እያሰራ ሲያስቀምጣት ይቆያል። አስቴር አስር አመት እንደሞላት አንድ ከአዲስ አበባ የመጣች የጎረቤታቸው ልጅን ተከተላ ከተማ ወጣች። ምንም እንኳን አስር አመት ቢሞላትም በምግብ እጥረትና በስራ ጫና የደቀቀ ሰውነቷ ሰባት አመት የሞላት እንኳን እንዳትመሰል አደርጓታል።
ከገጠር ይዛት የመጣችው የጎረቤታቸው ልጅ ሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራ ስለነበረች ልጅቷንም በአነስተኛ ደሞዝ ልጅ ለመጠበቅ አንድ ቤት ታስቀጥራታለች። አስቴር አይታ የማታውቃቸውን ምግብና አልባሳት ስታይ ሁሉንም ለራሷ ለማድረግ የመፈለግ አዝማሚያ ይታይባት ጀመር። በችግር ያደገችው ልጅ ሁሉንም መንካት መስረቅ መደበቅ ባህሪዋ ሆነ። ይህንን ጥፋት ያሉት አሰሪዎቿ ሲያባርሯት ደግሞ ሌላ ቤት ስትገባ አሁንም ሲያባርሯት በሁለት አመት ውስጥ ወደ ስድስት ቤት ከቀያየረች በኋላ ልጃለም ጌታቸው እና ቆንጂት ሙለታ የተባሉት ባልና ሚስት ቤት ትቀጠራለች።
ቀጣሪዎቿም ልጅነቷን ፈጣን መሆኗን ይወዱላታል። የተባለችውን ነገር ምንም ሳታዛንፍ የምትሰራው ህፃን የልጅ ቅመም በመሆን በቀጣሪዎቿ ፊት ሞገስን አገኘች።
እንደተወደደች የገባት አስቴር የቀደመ አመሏ አለቅ ብሏት ከምግብና ከአልባሳት በተጨማሪ ገንዘብ እያሳደደች መስረቅ ጀመረች። ልጅቷ ፈጣን ስራዋ የአስራ ሁለት አመት ልጅ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው መሆኑን የወደዱላት አሰሪዎቿ በየጊዜው ገንዘብ መጥፋቱ ቢያናድዳቸውም እርግጠኛ እስኪሆኑ ድረስ ምንም ማድረግ አለፈለጉም ነበር።
ከእለታት በአንዱ ቀን ሆን ብለው ገንዘብ ልታገኝበት የምትችለው ቦታ አስቀምጠው ይከታተሏት ጀመር። እሷም ሀገር ሰላም ብላ እንደልማዷ ያገኘችውን አንስታ ስትደበቅ በቀጣሪዎቿ ትታያለች። ያኔ በንዴት የጦፉት ባልና ሚስት ይችን በልታ የምታድር የማትመስል ደቃቃ ልጅ ይቀጠቅጧት ገቡ።
የዱላውን ብዛት መቋቋም ያቃታት ታዳጊ
በልጅቷ ድርጊት እጅግ የተናደዱት አቶ ልጃለም ጌታቸው ታዬ እና ወይዘሮ ቆንጂት ሙለታ በቀለ የተባሉት ባልና ሚስት በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታኅሣሥ 17/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 17/2014 ዓ.ም ባለ ጊዜ አስቴር ነገሰን ዘግቶ በማስቀመጥ በተደጋጋሚ በተለያየ ጊዜ በፍልጥ እንጨት፣ በእርግጫ፤ በሞባልይ ቻርጀር ገመድ ጀርባዋን፣ ወገቧን እና እግሯን ደጋግመው በመደብደብ እውነቱን እንድትናገርና የደበቀችውን ገንዘብ እንድታወጣ ያስገድዷታል።
ልጅቷ ደግሞ ወትሮም ለመከራ የተፈጠረች ናትና ከማልቀስ በቀር ምንም አይነት ምላሽ መስጠት ታቆማለች። ንዴት በንዴት ላይ እየተደራረበ ባገኙት ነገር ሁሉ በእልህ የምትቀጠቀጠው ህፃን ዱላውን መቋቋም ተሳናትና እጅ ሰጠች። አስቴር ሀይ ባይ ተመልካች በሌለበት በሰው ቤት ውስጥ ባልተገባ ቅጣት ምክንያት ሕይወቷ አለፈ።
አሰሪዎቿም አስቴርን ከገደሏት በኋላ የሟችን አስከሬን በሳጥን በማድረግ በድብቅ ለመቅበር ሲሰናዱ አንድ የቅርብ ጎረቤታቸው ስለሁኔታው ጥርጣሬ አድሮባት ለፖሊስ ጥቆማ ትሰጣለች።
ፖሊስም በጥቆማው መሰረት ቤት የመበርበሪያ ወረቀት ይዞ ሲመጣ በሟች ላይ በርካታ የቆዳ መጋጋጥ እና የመበለዝ፣ ከአንገትዋ የፊተኛው ክፍል አንስቶ ወደ ቀኝ እና ግራ ትከሻዋ የተሰራጨ የመበለዝ፣ በደረትዋ የላይኛው ፊተኛና ጎን 1/3 ክፍል የመበለዝ፣ በቀኝና በግራ ቂጥዋ ጭን የላይኛው ኋለኛ ክፍል እና በጀርባዋ የታችኛው ክፍል ላይ በርካታ የቆየ የቆዳ መጋጥ፣ በራስ ቅልዋ ፊተኛ መካከለኛ ክፍል የመበለዝ፣ በእጅ እና እግሮቿ ላይ ወደ ውስጥ ደም የመፍሰስ፣ የመሰራጨትና የመበለዝ ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ይመለከታል።
በመቀጠል ፖሊስ ተገቢውን ምርመራ ካደረገ በኋላ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ያቀርባል። ዐቃቤ ህግም ምርመራውን አጠናቆ ክስ ይመሰረታል።
የፍርድ ቤት ክርክር
ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ነው። የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ልጃለም ጌታቸው ታዬ እና 2ኛ ቆንጂት ሙለታ በቀለ የተባሉት ባልና ሚስት ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታኅሣሥ 17/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 17/2014 ዓ.ም ባለ ጊዜ ሟች አስቴር ነገሰን ተከሳሾች በተደጋጋሚ በተለያየ ጊዜ በፍልጥ እንጨት፣ በእርግጫ፤ በሞባልይ ቻርጀር ገመድ ጀርባዋን፣ ወገቧን እና እግሯን ደጋግመው በመደብደብ፤ ከገደሏት በኋላ የሟችን አስከሬን በሳጥን በማድረግ በድብቅ ለመቅበር ሲሰናዱ ተይዘው ምርመራ ሲጣራ በሟች ላይ በርካታ የቆዳ መጋጋጥ እና የመበለዝ፣ ከአንገትዋ የፊተኛው ክፍል አንስቶ ወደ ቀኝ እና ግራ ትከሻዋ የተሰራጨ የመበለዝ፣ በደረትዋ የላይኛው ፊተኛና ጎን 1/3 ክፍል የመበለዝ፣ በቀኝና በግራ ቂጥዋ ጭን የላይኛው ኋለኛ ክፍል እና በጀርባዋ የታችኛው ክፍል ላይ በርካታ የቆየ የቆዳ መጋጥ፣ በራስ ቅልዋ ፊተኛ መካከለኛ ክፍል የመበለዝ፣ በእጅ እና እግሮቿ ላይ ወደ ውስጥ ደም የመፍሰስ፣ የመሰራጨትና የመበለዝ ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉ በማስረጃ በመረጋገጡ ዐቃቤ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ተከሳሾችም በችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸው ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ብለው የተከራከሩ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አስደግፎ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያረጋገጠ በመሆኑ እና ተከሳሾችም ይህን የዐቃቤ ህግ ክስ እና የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲያስተባብሉ በተሰጠ ብይን መሰረት ሁለት የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ሰጥቶ ቅጣት ለመወሰን ለታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ውሳኔ
ግራ ቀኙን ሲያዳምጥ የቆየውና ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 02/2006 መሰረት የወንጀል ደረጃውን ሁለት እርከን 39 ስር በማድረግ መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ሁለቱም ተከሳሾች ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው በእርከን 37 ስር ተከሳሾችን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን እያንዳንዳቸውን በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ እና እንዲሁም ተከሳሾች ለ5 ዓመት ከመብቶቻቸው እንዲሻሩ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015