ሲስተር ዘምዘም መሀመድ ይባላሉ። ከ20 ዓመት በላይ በህክምና ሙያ ላይ ሰርተዋል። ዛሬ ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክቶሬት ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው። በእናቶች ጤና ላይ ጥልቅ የሥራ ልምድና እውቀት እንዳላቸው በደንብ ያስታውቃሉ። ብዙ ያጋጠሟቸው ነገሮች እንዳሉም ለጋዜጠኞች ስልጠና በሰጡበት ወቅት ሲያብራሩ ነበር። ሥራው እጅግ ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነም ከእርሳቸው ንግግር በእጅጉ መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም አብዛኛው ገጠመኛቸውን ሲናገሩ እንባ ዓይናቸው እያቀረረና ሲያሻውም እየወረደ ነው።
እናቶች በብዙ መልኩ ልዩ ትኩረት ካልተቸራቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱ እንደሆኑም በደንብ ያሳያል። ከነገሩን መካከልም ለዛሬ አንዷን ባለታሪክ ልናወሳ ወደናል። እንደሚታወቀው እናትነት በብዙ መልኩ የሚተረጎም ቢሆንም ወላድ መሆን ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። እናም እርሳቸው እንደሚሉት፤ እናቶች ምድርን በልጅ በረከት ለመሙላት ሲሉ ራሳቸውን ያጣሉ። ይህ ደግሞ የሚከሰተው በተለያየ ምክንያት ነው። ማለትም ወሊዱ የእናትን ጤና በሚጠብቅ መልኩ ካልሆነ ብዙዎችን እንድናጣ እንሆናለን።
በህክምናው መዘግየት ተብሎ የሚጠራው ጉዳይ ደግሞ ብዙዎችን ለሞት የዳረገ ነው። ይህም ሦስት መሰረታዊ ነገሮች የሚነሱበት ሲሆን፤ የመጀመሪያው መዘግየት ነው። እናቶች ጤና አገልግሎትን በሚመለከት በቂ መረጃ አለማግኘት፣ በእርግዝናና ወሊድ ጊዜ የሚከሰተውን የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ህመሞች ለይቶ ያለማወቅ፣ እናቶች በጤና ተቋም በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ያላቸው አመለካከት አናሳ መሆንና ውሳኔ ሰጪነታቸው በእነርሱ እጅ አለመሆኑ በዋናነት ለችግሩ ሰላባ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ሁለተኛው ጤና ተቋማት ለመድረስ የሚገጥም መዘግየት ሲሆን፤ ጤና ተቋማት የሚገኙበት ርቀት፣ ወደ ጤና ተቋማት ለመድረስ ያለ የትራንስፖርት ሁኔታ፣ ወደ ጤና ተቋማት ያለ የመንገድ ሁኔታ፣ የፀጥታ ሁኔታ የችግሩ መንስኤዎች ናቸው። ሦስተኛው መዘግየት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈለገውን የጤና አገልግሎት ለማግኘት መቸገር ነው። ማለትም የህክምና ግብዓቶች እጥረት፣ የጤና ባለሙያዎች እጥረት እንዲሁም ተገቢውን ክህሎት ያለመኖርና የቅብብሎሽ አገልግሎቱ ላይ የሚኖሩ ችግሮች ናቸው።
እናም ባለታሪካችን የመጀመሪያው የመዘግየት ሁኔታ ያጋጠማት ናት። ክትትል ሳታደርግ ቆይታ ችግር ገጥሟት ወደ ጤና ተቋም ታመራለች። ልጆቿን ከዚህ ቀደምም በቤቷ ነው የወለደችው። አሁንም ያው ሁኔታ እንዲቀጥል ትሻ ነበርና ክትትል አላደረገችም። በመጨረሻ ግን ምጡ ሲከብድ መድረሻዋ ጤና ጣቢያ ሆነ። ጽንሱ ከመጀመሪያ ጀምሮ ችግር ያለበት ስለነበር በህክምናው የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉና ቢያግዟትም በቀላሉ ሊታደጓት አልቻሉም። እርሷን ከእነልጇ ሞት ወሰዳቸው።
የነበረውን ወቅታዊ ሁኔታ ሲስተሯ ሲያብራሩ ስቃይዋ ከባድ ነበር። ወዲያው እንኳን ሊያሳርፋት አልቻለም። ህክምና ሥራ ቢሆንም ህሊናንም ይሸከማልና የጤና ባለሙያዎች እርሷን ለማዳን ርብርብ ያደረጉት እያለቀሱ ጭምር እንደነበር አይረሱትም። ግን ሳይሳካላቸው ቀረ። እርሷንም ልጇንም ሞት ነጠቃቸው። በዚህም ዛሬ ድረስ እንዳይረሷት ሆኑ። በእርግጥ ይላሉ ሲስተር ዘምዘም በእርግጥ ይህ ችግር የብዙዎቹ እናቶች ነው። ምክንያቱም ለጤናቸው ትኩረት እይሰጡም። ማህበረሰቡ፣ ባለቤታቸውና መሰል ችግሮች ጤና ተቋም በመሄድ ክትትል እንዲያደርጉ አያግዛቸውም። የራሳቸው የግንዛቤ ልክም እንዲሁ ለሞታቸው መንስኤ ነው። በዚህም ለእናቶች ሞት ተጠያቂው ከግለሰቡ የሚጀምር ነው። እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ኃላፊነት አለበት። ምክንያቱም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነፍሰጡር እናቶች ወደጤና ተቋም ሄደው ክትትል እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት ይኖርበታል።
ጉዳዩ ማህበራዊ መነቃቃትን መፍጠርንም ይጠይቃል። እንክብካቤና መረጃንም ይፈልጋል። እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቤታቸው የሚወልዱ ኢትዮጵያዊያን በርካታ ናቸው። ይህ ደግሞ ለእናቶች ሞት ቁጥር ማሻቀብ የመጀመሪያውን ድርሻ የሚይዝ እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ነገር ነው።
ጤናማ እናትነት ማለት ሁሉም እናቶች ጤናማ የእርግዝና፤ የወሊድና የድህረ-ወሊድ ጊዜ እንዲኖራቸው አስፈላጊውን የጤና መረጃና እና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ማረጋገጥ ነው የሚሉት ሲስተር ዘምዘም፤ ይህ ታይቶና ትርጉሙን ተረድቶ መስራት ባለመቻሉ እ.ኤ.አ በ2017 በተደረገው ጥናት በዓለም ላይ በዓመት 295 ሺ000 (በቀን 810) እናቶች ይሞታሉ:: ከእነዚህም ውስጥ 94 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የሚሞቱት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገራት ማለት ነው።
ጥናቱ እንደሚለው፤ ከሰሀራ በታችና በደቡብ እስያ የሚገኙ አገራት 86 በመቶ የሚሆነው የእናቶች ሞት ይመዘገብባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአፍላ እድሜ ውስጥ የሚገኙ እናቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው። ታዲያ ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ምን ላይ ትገኛለች ከተባለ ደግሞ እርሳቸው እንዳሉት፤ እ.ኤ.አ በ2017 በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ በህይወት ከሚወለዱ 100ሺ ጨቅላ ህፃናት 401 እናቶች ይሞታሉ። ይህ ማለትም 14,000 የሚጠጉ እናቶች በዓመት ይሞታሉ ማለት ነው።
ለዚህ ደግሞ መሰረታዊ መንስኤዎቹ አምስት ናቸው። በእርግዝና በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት የሚከሰት የደም መፍሰስ፣ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ኢንፌክሽን፣ የተደናቀፈ/ምጥ(Obstructed Labor) እና የደም ማነስ ናቸው።
ይህንን ለመቀነስ እንደ አገር የተያዙ በርካታ እቅዶች መኖራቸውን የሚያነሱት ሲስተር ዘምዘም፤ አንዱ በ2025 የእናቶችን ሞት ወደ 279 ማውረድ እና በ2030 ደግሞ የእናቶችን ሞት ወደ140 መቀነስ ነው። ለዚህም በኢትዮጵያ፡ (MPDSR report) ለእናቶች ሞት ዋና ዋና ምክንያቶች ተብለው የተለዩት ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ይሰጥባቸዋል። በተመሳሳይ የዓለም ጤና ድርጅት (2017) የእናቶች ሞት ባደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ አገራት በሚል ንጽጽር ሲያስቀምጠው በማደግ ላይ ያሉ አገራት በህይወት ከሚወለዱ 100ሺ ህጻናት 462 ሲሞቱ ባደጉ አገራት ግን በህይወት ከሚወለዱ 100ሺ ህጻናት 11ንዱ እናቶች ይሞታሉ። ስለዚህም በማደግ ላይ ያሉ አገራት በርካታ ችግሮች እዳሉባቸው እንመለከታለን።
እንደ አገር የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነት፣ ጥራት እንዲሁም ተደራሽነት ላይ ብዙ ተግዳሮቶች አሉና ችግሩን ለመፍታት የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሥራት ያስፈልጋል። በመሆኑም ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ በመንግስታቱ ድርጅት የፀደቀው ዘለቄታዊ የልማት ግቡ ልዩ ትኩረት አግኝቶ እንዲሰራበት ይደረጋል። ምክንያቱም ይህ ካልሆነ አደጋው የከፋ ነው። ማለትም ለአብነት በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ አማካይ የእናቶች ሞት ከሚወለዱ 100ሺ ህጻናት የእናቶችን ሞት ወደ 70 ለመቀነስ ታቅዷል። ማንኛውም አገር በዓለም አቀፍ ከተቀመጠው ግብ ከሁለት እጥፍ በላይ የእናቶች ሞት መጠን ማስመዝገብ የለበትም ተብሏልም። እናም ኢትዮጵያም ይህንን በማሰብ መንቀሳቀስ ይኖርባታል ይላሉ ሲስተር ዘምዘም።
እንደ አገር በዚህ አይነት ሁኔታ መሰራት ካልተቻለ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ የሚሉት ሲስተሯ፤ በእናቶች ጤና ዙሪያ ያሉ አገልግሎቶች ምን እንደሚመስሉ መረጃዎችን አብነት በማድረግ ያነሳሉ። የቅድመወሊድ አገልግሎት የሚያገኙት እናቶች በመቶኛ 74 ሲሆኑ፤ በባለሙያ የተደገፈ ክትትል ማለትም የአራተኛው የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ላይ የሚደርሱት ደግሞ 43 በመቶ ብቻ ናቸው። በጤና ተቋም የሚወልዱት ደግሞ ከ50 በመቶ በታች ሲሆኑ፤ ይህ የሚያሳየውም ብዙዎቹ ቤት ወይም ከዚያ ውጪ ይወልዳሉ። ይህ ማለት ደግሞ እናቶች አስጊ ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ባልታወቀ ምክንያት ልጃቸውን፣ ራሳቸውን ያጣሉ።
በተመሳሳይ ጤናማ ያልሆነ ልጅ ወልደው ይሰቃያሉ። ይህ ደግሞ ከማህበረሰቡ እስከመገለል የሚደርስ ስቃይን ሊያስተናግዱ ይችላሉ። ሌላው ደግሞ የድህረ ወሊድ አገልግሎት የሚያደርጉት አናሳ መሆናቸው ሲሆን፤ በቁጥር ደረጃ ሲገለጽ 34 በመቶ ብቻ ናቸው። እናም ይህንን ትኩረት አድርጎ መስራት የጤና ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው። በተለይም የመገናኛ ብዙኃኑ እገዛ ከሁሉም የላቀ ነው። ስለዚህም መገናኛ ብዙኃኑ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አጥብቆ ቢሰራበት ሲሉ ይመክራሉ።
ህመምና ሞት በተመለከተ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካላት ዘንድ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲደርስ ማድረግ፣ በየደረጃው ያለው አመራር (ባለድርሻ አካላት) ተነሳሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ፣ የእናቶች ህመምና ሞት መቀነስና የእናቶች ጤና በሁሉም ደረጃ የትኩረት አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ፣ የእናቶች ጤና በተመለከተ በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። እናቶች በእርግዝና ወቅት ከ12 ሳምንት በፊት በጤና ተቋም ክትትል እንዲጀምሩና ቢያንስ ስምንት ጊዜ የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤ መፍጠር ላይም የተለያዩ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ሊያግዙ ይገባል።
ከጤና ተቋም እርቀው የሚገኙ ነፍሰጡር እናቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ የነፍሰጡር ማቆያ ቤትን እንዲጠቀሙ ማሳወቅና ለዚህም የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር ላይ መስራትም ትኩረታቸው ቢሆን መልካም ነው። ሌላው በጤና ተቋማት መካከል ስለሚደረገው የቅብብሎሽ ስርዓት ግንዛቤ መፍጠር፣ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት፣ ከወሊድ በኋላ እናቶች ለ24 ሰዓት በጤና ተቋም እንዲቆዩና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚገፋፉ ሥራዎች ላይ ትኩረት መስጠትም ይኖርባቸዋል።
የጤናማ እናትነትን ወር በማስመልከት አገራዊ ንቅናቄ የሚፈጠርበትን መንገድ መፍጠር፣ እናቶች በእርግዝና፣ በወሊድ እና ከወሊድ በኋላ ችግር ሲያጋጥም ፈጥነዉ ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ የሚያስችላቸውን መረዳት መፍጠርና በጤና ተቋማት መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማነቃቃት (መንገድ፤ ውሀ፤ መብራት ወዘተ……)ም የእነርሱ ድርሻ መሆኑን አምነው መንቀሳቀስ ይገባልም ይላሉ።
በሁሉም ደረጃ ተጠያቂነት ያለበት አሰራር እንዲሰፍን ማድረግ የመገናኛ ብዙኃኑ ዋነኛ ሥራ እንደሆነ ይታወቃል። እናም በዚህ ላይ በስፋት ቢሰሩ ለእናቶች የተሻለ እድል ይፈጥራሉም ባይናቸው። በአጠቃላይ መገናኛ ብዙኃን የእናቶች እና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ስርአት ላይ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነውና ለማህበረሰቡ በመንገር ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
አዎ የእናቶች ጉዳይ የሁሉም ሰው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ያለ እናት አልተፈጠረምና። ስለዚህም ስለተባልን ሳይሆን መሆን ስላለበት ብቻ እናድርገው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ወር ሳይሆን ቀንን መሰረት ማድረግ ይኖርብናል። በእርግጥ በአገር ደረጃ የጤናማ እናትነት ወር በ1998 ዓ.ም ጥር ላይ ተጀምሯል። አሁን ለ17ኛ ጊዜ እናከብረዋለን። ወሩ መታሰቡ ደግሞ እንድንነቃና ዝም ካልን እንድናስታውሳቸው ያደርገናልና እንጠቀምበት ማለት እንወዳለን።
በመጨረሻ አንድ ነገር ላንሳና ሀሳቤን ልቋጭ። ለጤናማ እናትነት ወር ጥር ለምን ተመረጠ የሚለውን ነው። እንደሚታወቀው ጥር ወር ለኢትዮጵያውያን ልዩ የደስታ ቀን ነው። ምርት ይሰበሰብበታል፣ ልጅ ይዳርበታል፣ ዘመድ አዝማዱ ይሰባሰብበታል። ሁሉም አምሮና ተውቦ የሚወጣበትም ወር ነው። እንደውም ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስም ይባልበታል። ስለዚህም በዚህ የደስታ ቀን ከእናት በላይ የሚደሰት አይኖርም። በመሆኑም ይህንን የደስታ ቀኗን የበለጠ የደመቀ ለማድረግ የእናቶች ጤና ጉዳይን መነጋገሪያ እንድናደርገው በማስፈለጉ ነው ጥር የተመረጠው።
ከዚያ ባሻገር ከሰርግ በኋላ ልጅ መምጣቱ አይቀርምና ይህም በደስታ እንዲቀጥል ‹‹ የዛሬ ዓመት የሚሚ ወይም የማሙሽ እናት›› እያልን እንደምንዘፍነው ሁሉ ጤናማ ልጅ፤ ጤናማ እናት እንድትኖረን ከመጀመሪያው ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ እንድታገኝ ግንዛቤ የማስጨበጫ ወር እንዲሆን ያስፈልጋልና ወሩ ተመርጧል። ስለሆነም ሁሉም ይህንን እያሰበ እንዲሰራበት በመጠቆም ሀሳባችንን ጨረስን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015