ከሳምንት በኋላ በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ቻምፒየን ሺፕ(ቻን) ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በፊት ዝግጅት መጀመሩ ይታወቃል። የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኢትዮጵያ በውድድሩ ለሶስተኛ ጊዜ ስትሳተፍ የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ሃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን ለሃያ ስምንት ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ወደ ዝግጅት ገብተዋል። ይሁን እንጂ ቡድኑ ዝግጅቱን ሲጀምር ወሳኙ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል መገኘት እንዳልቻለ ታውቋል። ከትናንት በስቲያ ሶከር ኢትዮጵያ ባስነበበው ዘገባ መሰረት የቡድኑ ቁልፍ የፊት መስመር ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉ ተጠቁሟል።
ጌታነህ ከበደ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንዲመለስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አመራሮች ከፍተኛ የማግባባት ስራ ሲሰራ እንደነበረ ዘገባው የጠቆመ ሲሆን ተጫዋቹ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው አስቦበት መሆኑን አሳውቋል።ከ2001 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አጥቂ በመሆን ያገለገለው ጌታነህ በሀገሩ መለያ 33 ግቦችን በማስቆጠር ትልቅ ታሪክ መስራቱ ይታወቃል። ጌታነህ አሰልጣኝ ውበቱ የዋልያዎቹ መሪ ሆነውም ቡድኑን በአምበልነት ማገልገል የቻለ ሲሆን ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በአሰልጣኙና ተጫዋቹ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ይታወሳል።
በሁለቱ ግለሰቦች መካከል አለመግባባት የተፈጠረው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ማላዊና ግብጽን በገጠሙባቸው ጨዋታዎች ጌታነህ በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በነበረበት ሰዓት አሰልጣኝ ውበቱ ተጫዋቹን ከቡድኑ በመቀነሳቸው ነበር። ለዚህም አሰልጣኙ “ደጋግሜ ስልክ ስደውልለት አለማንሳቱ የዲሲፕሊን ችግር በመሆኑ ከቡድኑ ውጭ አድርጌዋለሁ” የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ጌታነህ በበኩሉ “የዲሲፕሊን ችግር የለብኝም ስልኩን ለምን እንዳላነሳሁ ግን አሰልጣኝ ውበቱ በደንብ ያውቃል” ሲል በወቅቱ አስተባብሎ ነበር።
አሰልጣኝ ውበቱ ከጌታነህ ጋር አለመግባባቱ በተፈጠረበት ወቅት ከተጫዋቹ ጋር ሌላ ችግር እንደሌለባቸውና ብቃቱ ጥሩ እስከሆነ ድረስ ዳግም ለብሔራዊ ቡድኑ ሊጠሩት እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር። በዚህም መሰረት ከስምንት ወር በኋላ ለተጫዋቹ ጥሪ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ጌታነህ ብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ አህጉራዊ ውድድር ሊያደርግ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በዚህ ወቅት ያልተጠበቀ ውሳኔ ወስኗል። ይህም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተጫዋቹ ራሱን በዚህ ሰዓት ከብሔራዊ ቡድኑ ያገለለው ባለፈው ቁርሾ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩ አልቀረም።
አሰልጣኝ ውበቱ ትናንት የቡድኑን የቻን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት መድረክ በጌታነህ ከበደ ጉዳይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ተጫዋቾች ወደ ብሔራዊ ቡድን እንዲገቡ ጥሪ በቀረበላቸው ቀን መሰረት ጌታነህ ቀኑን አክብሮ ባለመገኘቱና ዘግይቶ በመምጣቱ እንደተቀነሰ አብራርተዋል፡፡
‹‹የጥሪ ቀን ባለማክበሩና በመዘግየቱ ጌታነህ ከበደን ለምን ዘገየህ ስለው ጥሪውን ስላልሰማሁ ነው አለ፣ እንዴት አይሰማም? እሱን ብቀበል በጊዜ አልመጡም ብዬ ያሰናበትኳቸውን እንዴት እመራለሁ፣ ስለዚህ ከቡድኑ አሰናብቼዋለሁ›› ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ ጌታነህ ‹‹ራሴን ከቡድኑ አግልያለሁ›› ማለቱንም ከሚዲያ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ተጫዋቾች ባለፈው ታኅሣሥ 18/2015 ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ያስታወሱት አሰልጣኙ፣ ጌታነህ ከበደ ብቻ ሳይሆን በተጠቀሰው ቀን ያልተገኙ ሌሎች ተጫዋቾች ከቡድኑ መቀነሳቸው ገልፀዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ታፈሰ ሰለሞንና አማኑዔል ገብረሚካኤል የሚገኙ ሲሆን ጌታነህ ከተጠቀሰው አንድ ቀን ዘግይቶ ቢገኝም ሪፖርት እንዳላደረገ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት ተጫዋች ከቡድናቸው ጋር ለማስቀጠል እንደሚቸገሩ ጠቁመው ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ክብር ሊኖራቸው እንደሚገባና ህግም መከበር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
‹‹ እንዴት በሊጉ 29 ግብ ያስቆጠረው አቡበከር ናስር እያለ ጌታነህ ከበደ በቋሚነት ይጫወታል የሚል በርካታ ወቀሳ እየደረሰብኝ ሳጫውተውም ነበር፣ በዕርግጥ አቅምም ስለነበረው ነው፣ በተያያዘም እንዴት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጥሩ ባልነበረ መልኩ የተለያየውን እና ጉዳት ላይ የነበረውን ተጫዋች ይመርጣል ተብዬ ብዙ ስታማ በነበረበት ወቅት ጫናዎችን ተቋቁሜ ተጫዋቹን ስመርጥ እና ሳጫውት ነበር። በመጨረሻም ጌታነህ ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉን ሰማሁ ውሳኔው የራሱ ነው። ምናልባት ስሜታዊ ሆኖ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ውሳኔውን አከብራለሁ›› በማለትም አሰልጣኝ ውበቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015