የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዘንድ የሚታየው ጥፍጥፍ ወርቅ ብዙ ልፋትን አልፎ የተገኘ ነው። በዋጋቸው ውድና የሰዎች ክብር መገለጫ የሆኑ ከከበሩ የድንጋይ ማዕድናት የሚሰሩ የአንገት፣የእጅ፣ የጣት፣ የጆሮና የተለያዩ ጌጣጌጦችም በቀላሉ ከጉድጓድ ውስጥ የተገኙ አይደሉም፤ ወደ ጌጣጌጥነትም ለመቀየር የሚወስደው ጊዜና ልፋትም ብዙ ነው።
አልሚዎቹ በአንገታቸውና በጀርባቸው ላብ እንደ ውሃ እየተቆንቆረ ነው እነዚህን ማዕድናት የሚያመርቱት። በያዙት ባህላዊ መቆፈሪያ የሚምሱት ጥልቅ ጉድጓድ አፈር ተደርምሶ እንደሚጎዳቸው አያስተውሉም፤ ስራ ስራቸውን ነው የሚመለከቱት። ማዕድኑን እስኪያገኙ ድረስ ቁፋሮአቸውን ይቀጥላሉ፤ ሊደርስባቸው የሚችለው ጉዳትና ድካም ብዙም አይታሰባቸውም።
ይህን ሁሉ የሚያከናውኑት የረጋ ራስን መጠበቂያ ሳያደርጉ ነው። ማዕድኑን ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የሚጠቀሙባት ባትሪ ብርሃን ትፈነጥቃለች ተብላ የማትገመት አነስተኛ ባትሪ ናት፤ እሷን በግንባራቸው ላይ አርገው ነው የሚጠቀሙባት። ከብዙ ልፋት በኋላ የተገኘውን የወርቅ ማዕድን አጥበው ከአፈሩ የሚለዩበትና ደቃቁን ወርቅ ሰብስበው አቅልጠው በጥፍጥፍ መልክ የሚያዘጋጁበት ዘዴም እጅግ ኋላቀር እንደሆነ ይታወቃል።
በዚህ ውስጥ ሁሉ አልፈው ለገበያ አውለው የሚያገኙት ገቢ ኑሮአቸውን የሚያሻሽልላቸው አይደለም። ከተመሳሳይ ኑሮ እያወጣቸው እንዳልሆነም ከሚያለሙበት ዘዴ ጀምሮ ያለው ሂደት ይመሰክራል። ግን ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ሲታይ በማዕድን ዘርፉ እነዚህ አልሚዎች ናቸው በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ሚና እየተወጡ የሚገኙት። የዘርፉ ተስፋ የተጣለባቸውም እነሱው ናቸው።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ከአምስት የኢኮኖሚ የትኩረት አቅጣጫዎች የማዕድን ዘርፉ አንዱ ሆኖ በእቅድ ሲያዝም የባህላዊ ማዕድን አልሚዎች ሚናም ታሳቢ ተደርጎ ነው። ምንም እንኳን በዚህ ወቅት ዘርፉን ለማዘመን በተለይም የወርቅ ማዕድን መቆፈሪያ፣ ወርቁን ከአፈሩ ለይቶ በማጠብና ወርቁንም በአንድ ጨፍልቆ ከብክነት የሚከላከል የማጠቢያ ማሽኖችን በአገር ውስጥ ማቅረብ እየተቻለ ቢሆንም፣ የማዕድን ልማቱ ሙሉ ለሙሉ ከባህላዊ የልማት ዘዴ አልተላቀቀም። በሂደት ግን የአልሚውን ድካም የሚቀንስና ብክነትንም የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለበት ሁኔታ እየተስፋፋ ከመጣ ባህላዊው የማዕድን ልማት በዘመናዊው እየተተካ ይመጣል።
መንግሥት የነደፈውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አቅድ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ከማእድን ዘርፉ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድም የማዕድን ልማቱ የሚከናወንባቸው ክልሎች የላቀ ድርሻ አላቸው። ለኢንዱስትሪና ለግንባታው ዘርፍ እንዲሁም ለጌጣጌጥ የሚውሉ የማዕድን አይነቶችን በጥናት ለይቶና አደራጅቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የማዕድን ልማቱ የተረጋጋ ሰላምና የተሟላ መሠረተ ልማት የሚፈልግ በመሆኑም ይህንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጨማሪ የቤት ሥራቸው ይሆናል።
ከባለድርሻ አካላት መካከል የሚጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎችም ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል የምርምር ሥራ ማከናወን ይኖርባቸዋል። ከዚህም በተጓዳኝ አገራዊ የምጣኔ ሀብትንም ሊያሳድጉ የሚችሉ የምርምር ውጤቶችን ለፖሊሲ አውጭዎች የማመላከት፣ ዘርፉን ለሚመራው አካል በመስጠትና የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። በቅርቡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከክልሉ የማእድን ልማት ቢሮ ጋር የማእድን ሀብት ለየታ ጥናት ለማካሄድ ያደረጉት ስምምነት ለእዚህ በአብነት ሊጠቀስ ይችላል።
እኛም በዚህ ረገድ የጋምቤላ ክልል ማእድን ልማት ቢሮና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ይህን ኃላፊነታቸውን እንዴት እየተወጡ ስለመሆናቸው የእነዚህን አካላት የሚመለከታቸውን ክፍሎች አነጋግረናል። እጅግ ሞቃታማው የጋምቤላ ክልል በረሃውን የሚያስረሳ ታይቶ በማይጠገብ አረንጓዴ የተሞላ ነው። በዚህም የበረሃው ገነት የሚል ስያሜ አግኝቷል። በአሣ ሀብቱም ይጠቀሳል።የአሣ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በማቋቋም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በአንድ ወቅት መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት ነበር። በክልሉ በተገነባው የአልዌሮ ግድብ ሰፊ የመስኖ ልማት ማካሄድም ይቻላል። አሁንም ቢሆን በተወሰነ መልኩም ቢሆን በግድቡ አንድ ኩባንያ የመስኖ ልማት እያካሄደ ይገኛል።
ክልሉ ከነዚህ ሀብቶች በተጨማሪ የማዕድን ሀብት ባለቤትም ስለመሆኑ ይታወቃል። በምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው የወርቅ ማዕድን ልማት በማከናወንም ተጠቃሽ ሆኗል። ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ በልዩ ትኩረት በክልሉ ዲማ ወረዳ ውስጥ እየለማ ያለው የወርቅ ማዕድን አበርክቶው ከፍ እያለ መጥቷል። ልማቱ በስፋት የሚከናወንበት ዲማ ወረዳ ለአብነት ይጠቀስ እንጂ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሀብቱ መኖሩን ከክልሉ ማእድን ሀብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ለተለያየ ግብአት የሚውሉ ማዕድኖች መኖራቸውን በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
በክልሉ እየተከናወነ ስላለው የማዕድን ልማትና ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ሌሎች የማዕድን ሀብቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ስላለው እንቅስቃሴ የጋምቤላ ክልል ማእድን ሀብት ልማት ቢሮ ዋና የሥራ ሂደት አቶ ሙድ ሎንግ እንደገለጹት፤ በክልሉ በርካታ ማእድናት ቢኖሩም፣ ለጊዜው በትኩረት እየተሰራበት ያለው የወርቅ ማዕድንና ለግንባታ ግብአትነት የሚውሉት አሸዋና ድንጋይ ናቸው።
በክልሉ በሚገኙ ባሮ፣ አልዌሮና ኢሉ ወንዞች አካባቢ ከፍተኛ የአሸዋ ክምችት ይገኛል። በባሮ ወንዝ ደግሞ የክምችት መጠኑ ከፍተኛ ነው። እንደ ሴራሚክ ያሉ የግንባታ ማጠናቀቂያ ማእድናት፣ ግራናይትን የመሳሰሉ ማእድናት ከክልሉ ዋና ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ።
እነዚህን ማእድናት ለማልማት አንድ ባለሀብት ባለፈው ዓመት ፍቃድ ወስዶ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ባለሀብቱ ማዕድኑ ስለመኖሩ በጥናት ቢያረጋግጥም እስከ አሁን ግን ስራውን አልጀመረም። ባለሀብቱ ወደ ሥራ ላለመግባቱ በምክንያትነት የሚያነሳው ለሥራው የሚያስፈልገው መሳሪያ ከውጭ የሚመጣ ነው። መሳሪያውን ለማስገባት ገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም ባለሀብቱ ከባንክ ብድር እንደሚጠብቅ መግለጹን ነው አቶ ሙድ ያስረዱት።
የድንጋይ ከሰል መጀንግ ቤሄረሰብ አካባቢ እንደሚገኝና ሌሎችም የማዕድን አይነቶች በክልሉ እንደሚኖሩ ከመገመቱ ውጭ በጥናት ተለይቶና ተደራጅቶ የተቀመጠ መረጃ ቢሮው ለጊዜው እንደሌለውም ገልጸዋል።
ወርቅን ጨምሮ ውስን የሆኑት የክልሉ ማዕድን ሀብቶችም መኖራቸው ታውቆ ወደ ልማቱ የተገባው በተለይም የወርቅ ማዕድኑ እየለማ ያለው በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት በተደረገ ጥናት ተለይቶ እንደሆነ አቶ ሙድ ይጠቅሳሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ አቅም በጥናት የተደገፈ የሀብት ልየታ ለማከናወን በሥነምድር (ጂኦሎጂ) ቋንቋ ፒር ማቴሪያል ወይንም ቴክኖሎጂ እንዲሁም የናሙና ፍተሻ የሚከናወንበት ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ) እና የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል።
ማዕድን ሚኒስቴር በየክልሉ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች/ በዘርፉ ላይ ጥናት መሥራት እንዳለባቸውና ቢሮዎችም ከተቋማቱ/ከዩኒቨርሲቲዎች/ ጋር እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጧል። ይህ አሰራር ክልሎች በራሳቸው አቅም እንዲንቀሳቀሱ እድል ይፈጥራል። አንዳንድ ክልሎችም ወደ ሥራ በመግባት ሀብታቸውን የመለየት ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል።
በጋምቤላ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ግን በክልሉ የሚገኘው ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ የትምህርት ክፍል ባለመክፈቱ ምክንያት በጋራ ለመሥራት አልተቻለም። አቶ ሙድ እነዚህ ችግሮች እንደሚፈቱ ተስፋ አላቸው። የክልሉ ተወላጆች የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ በማስገንዘብና ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት እንደሚያደርጉም እምነታቸው ነው። ከማእድን ሚኒስቴር ጋር ያለው ግንኙነትም ቀደም ካሉት ዓመታት የተሻለ እንደሆነ ነው የገለጹት።
የአካባቢውን የማዕድን ሀብት በጥናት ለይቶ ለሚመለከተው ክፍል በማቅረብና ከክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በጋራ በመሥራት ረገድ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚደንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክኡኩሙ ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ስምንት ነው።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በማዕድን ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማርም ሆነ ተመራማሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለመግባት የወራት እድሜ ነው የቀረው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በማዕድን ዘርፉ የሚጠበቅበትን ተልእኮ የሚወጣው በዘርፉ የትምህርት ክፍል ካደራጀ በኋላ ነው። ዩኒቨርሲቲው በጥናት የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ማዕድንን ጨምሮ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ የተፈጥሮ ሀብት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። በዚህ በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ ሰፊ ሥራዎች ይሰራሉ።
በዩኒቨርሲቲው በኩል የጥናት ሥራው ገና ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በተለያየ መንገድ በተደረጉ ጥናቶች በጋምቤላ ክልል የወርቅ ማዕድን ልማት በዲማ ወረዳ ብቻ ሳይሆን፣ አኝዋክ ዞን፣አቦቦ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ መጃን ዞን በተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም የከበሩ የድንጋይ ማዕድናት ይገኛሉ።
እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገር ነዳጅን ጨምሮ እምቅ የሆነ የምድር በረከት ሀብት እንዳለ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በሚፈለገው ልክ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳልተገኘበት ተናግረዋል። ማእድን ዘርፍ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት ጀምሮ ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የትምህርት ተቋማት ድርሻ ከፍ ያለ መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ኡጁሉ ያምናሉ። እርሳቸውም በግላቸው የሚችሉትን በማድረግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ሁሉም የየድርሻውን ከተወጣ በዘርፉ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ተናግረዋል።የማዕድን ልማቱ ከሚፈልገው ሰላምና የተረጋጋ አካባቢ ከመፍጠር እንዲሁም መሠረተ ልማትን ከማሟላት አኳያም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ እንደሆነ ነው የገለጹት። የአካባቢውን ሰላምን በመጠበቅ ለልማቱ ምቹ እንዲሆን ከማድረግ አንጻርም ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰቡ ጋር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በጋምቤላ ክልል ያለውን የማዕድን ልማትና የግብይት ሂደቱን በማዘመን ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከሁለት ዓመት በፊት በክልሉ ተገኝተው ከሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዘርፉ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ምክክር ባደረጉበት ወቅት ማስገንዘባቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መዘገቡ ይታወሳል። ሚኒስትሩ በወቅቱም ከግብርናው ቀጥሎ ኢኮኖሚውን እየደገፈ ያለው የማዕድኑ ዘርፍ እንደሆነ መግለጻቸው በዘገባው ተመልክቷል። ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎችን ጭምር በማሻሻል ረገድ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበው ነበር። በተለይም የወርቅ ማዕድን ልማትና የግብይት ሂደቱን በማዘመን ሀብቱን ለክልሉ ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል አመራሩ ለዘርፉ መጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ በሁሉም አካባቢዎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛው የወርቅ ማዕድን በብር በመቀየር ለማስቀመጥ በሚንቀሳቀሱ የኢኮኖሚ አሻጥረኞች ምክንያት አብዛኛው የወርቅ ምርት ወደ ባንክ እየገባ አይደለም። ፈቃድ በተሰጣቸው የወርቅ አዘዋዋሪዎች አስፈላጊውን ክትትልና ጥናት በማካሄድ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በጋምቤላ ክልል ያለውን የወርቅ ሀብት የአመራረትና ግብይት ሰንሰለት ለማዘመን ሚኒስቴሩ አስፈለጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በወቅቱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፤ በክልሉ ሰፊ የወርቅ ሀብት ቢኖርም በተፈለገው መጠን ለምቶ ለክልሉ ብሎም ለአገር ጥቅም አለማዋሉን አስታውቀዋል። ሀብቱን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማልማት ለአገር የኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በተለይም የፌደራሉ መንግስት የቴክኖሎጂና የሙያዊ ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ በግብይት ሂደቱም ሆነ በሌሎች የመንግስት መደበኛ ስራዎች እንቅፋት መፈጠሩን አስታውቀው ነበር። በክልሉ በሚገኙ የዞንና ወረዳ ከተሞች ባንኮች ተደራሽ የሚሆኑበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባም መናገራቸውን በዘገባው ተጠቅሷል።
በክልሉ መንግስት የቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውንና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ የባንክ ቅርንጫፎችን ለመክፋት እየተሰራ እንደሆነም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋን ዋቢ አድርጎ በወቅቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ክልሉ በ2013 በጀት አመት ማጠናቀቂያ ከ1 ሺህ 213 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉንም አመልክቷል።
ክልሉ በራሱ አቅም የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ ከክልሉ የሚገኘው የወርቅና የመሳሰለው ሀብት የአገርም ጭምር እንደመሆኑ የፌዴራል መንግስት ለወርቅ ልማቱ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል።
በክልሉ ህገወጥ የወርቅ ዝውውርን ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው። ይህን ተከትሎም ከክልሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ጨምሯል። በልማቱም በኩል ተመሳሳይ ርብርብ ማድረግ ይገባል። የፌዴራል መንግስት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ባለሀብቶች በክልሉ ያለውን ወርቅ በማልማት አምራቾቹም የክልሉ ህዝብም አገርም ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2015