ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከብዙ ቀናት መሰወር በኋላ ዛሬ ሲነጋጋ ፤ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል በሰፋራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ሲጮህ ፤ በይልቃል አዲሴ ድንገተኛ መሰወር ክፉኛ ተጨንቀው የነበሩ የሰፈራችን ነዋሪዎች በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን በመተው ይልቃል አዲሴ ወደሚጮህበት ዋርካ ስር ተሰበሰቡ ።
አንድም ሰው እንዳይቀር ተብሎ የታወጀ ይመስል የሰፈራችን ነዋሪዎች ከህጻን እስከ አዛውንት ዋርካው ስር ተገኝተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ እየደጋገመ ይድረስ ለእግዜሩ እንደቃሪያ ከተሰነግኩት ልጅህ እያለ ይጮኻል። ነገር ግን የዛሬውን የይልቃል ንግግር ማንም በቀላሉ መገንዘብ አልቻለም።
በሰፈራችን ትዕግስቱ አፍንጫው ስር ነው የሚባለው አብሿሙ ከፌ ጉደታ የይልቃልን የንግግር ሚስጢር ማግኘት ስላልቻለ ከይልቃል በላይ ጩኾ ወፈፌው ይልቃል አዲሴን ከንግግሩ አስቆመው።
«የምትለን ነገር ምኑም እየገባን አይደለም። ይህ ሁሉ ሕዝብ የተሰባሰበው የአንተን መሬት ጠብ የማይሉ ትእንቢት የመሰሉ ንግግሮችን ለማዳመጥ ነው። ስለዚህ የምትነግረንን ነገር በስርዓት ንገረን !»ሲል ይልቃልን ገሰጸው።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴም አንድ እጁን ወደ ሰማይ በማንሳት «በእጄ ላይ በምትመለከቷት ኤንቨሎፕ ውስጥ አንድ ከእናታችን የተላከች ደብዳቤ ትገኛለች። ዛሬ ከጠፋሁበት በድንገት እዚህ የተገኘሁት ከእናታችን የተላከችውን ደብዳቤ ለእናንተ እንዳነብላችሁ በእናታችን ታዝዤ ነው» ሲል ለተሰብሳቢው ገለጸ።
ይህን ደብዳቤ እንድትጽፍ ያስገደዳት ዋናው ምክንያት አሁን አሁን የምታገባቸው ባሎቿ ራሳቸው ወንጀል ሰርተው ራሳቸው ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ አስከሳሽ፣ ምስክሩም እና ዳኛ እየሆኑ ስላስቸገሯት እንደሆነ ነግራኛለች ።
«ለማንኛውም ደብዳቤው እንዲህ ይላል» አለና ደብዳቤውን ማንበብ ቀጠለ…. ይድረስ ለእግዜሩ እንደቃሪያ ከተሰነግኩት ልጅህ እግዜሩ አንተ አዳምን እና ሄዋንን ፈጠርክ። ብዙ ተባዙም አልክ። እኔም የአንተን ምክር ሰምቼ እና ፍቃድህ ሆኖ ባል አግብቼ ተባዛሁ። ልጆቼም የአንተኑ ምክር ሰምተው እና ፍቃድህ ሆኖ እንደባህር አሸዋ ተባዙ።
ባሎቼ ቶሎ ቶሎ እየሞቱ ብቸገርም እንደፍቃድህ ሆኖ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ አንድ ባል ሲሞትብኝ ሌላ ባል እያገባሁ እየኖርኩ ነው። ልጆቼን የወልድኳቸው ግን ከመጀመሪያው ባሌ ብቻ ስለነበር ክብሩ ይስፋ ዘር የልጆቼን ዘር ከሌላ ዘር ጋር አልቀየጥኩም። ባሎቼ ይቀያየሩ እንጂ እርስቴን ልጆቼ እና ለልጅ ልጆቼ አውርሼ ተቀምጫለሁ። በዚህም ፈጣሪን አብዝቼ አመሰግነዋለሁ።
የእግር እሳት ሆኖ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ የሚያንገበግበኝ ነገር የባሎቼ በየጊዜው መሞት እና እኔም ያለመታከት አንዱ ባል ሲሞት ሌላ ባል ማግባቴ አይደለም። ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማገባቸው የባሎቼ ፀባይ እንጂ።
ከዛሬ 50 እና 60 ዓመታት በፊት ያገባኋቸው ባሎቼ ይብዛም ይነስም ቀና፣ ሩህሩህ፣ ልጆቼን የሚንከባከቡ እኔን አብዝተው የሚወዱ እና ለእኔ መኖር አብዝተው የሚሰሩ ነበሩ። «ጉድ እና ጅራት ከወደ ኋላ ነው» እንዲሉ አሁን አሁን ግን የማገባቸው ባሎች ልጆቼን በሚፈልጉት መንገድ አቧድነው የሚያባሉ፣ የእኔን ጭጉት (ገንዘብ ማስቀመጫ) የሚበረብሩ እና የሚዘርፉ፣ እኔን አግብተው ሲያበቁ በቤታችን የሚፈጠር ችግር ለመፍታት እኔን ማመከር ሲገባቸው ከእናካቴው ከምድረ ገጽ ብንጠፋ ለሚመኙ ጎረቤቶቻችን ማማከርን እንደስልጣኔ የሚቆጥሩ፣ የእኔን የሚስታቸውን የቆየ ጥበብ ተጠቅመው የቤታቸውን ችግር በራሳቸው ከመፍታት ይልቅ «ሳይቸግር ጨው ብድር» እንዲሉ ያልቸገራቸውን ከጎረቤት መፍትሄ ለማግኘት ሲሉ እኔን ለጎረቤት በባርነት አሳልፈው የሚሸጡ ፣ የእኔን እና የልጆቻቸውን ሀብት በስውር የሚዘርፉ፣ ከልጆቻቸው ጉቦ የሚበሉ ናቸው።
የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኢፔሪያሊስቶችን በከፍተኛ ተጋድሎ ከሰፈራችን እና ከእርስታችን ቀጥቅጠው ያስወጡት ልጆቼ ዛሬም ላይ አይለፍላችሁ ተብለው የተረገሙ ይመስላል። ልጆቼ የአውሮፓ ኢፔሪያሊስቶችን ከእርስታቸው ያስወጡ እንጂ ሰርተው ከማደግ ይልቅ በአቋራጭ ዘርፈው መክበርን በሚሹ የእድር እና የእርስት መሪዎች፣ ደላሎች እና ባለሀብቶች ክፉኛ እየተፈተኑ ኑሯቸውም ተመሰቃቅሎ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆኖባቸዋል።
አሁን ላይ ሰፈራችን እና እርስታችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ እድገቶች እንዳይጎበኙት እና ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችል እንደ ጎን ውጋት ቀዝፎ የያዙት እና አንድም እርምጃ ወደፊት መሄድ እንዳይችል ጋሬጣ ሆኖ ከፊቱ የተቀመጠው የማይነቃነቅ ደንቃራ ስርቆት ወይም ሌብነት ሆኖ ሳለ አንድም የሰፋራችን ሰው ይህንን የእድገት ደንቃራ በስሙ ለመጥራት የደፈረ አልተገኘም። ይልቁንም «ሙስና » እያሉ ያሽሞነሙኑታል እንጂ።
ስርቆት ስለምን ይሽሞነሞናል ? ሌብነት ሌብነት ነው! ስለምን የእድር መሪ ስልጣኑን ተጠቅሞ ሲሰርቅ ሙስና የሚል የዳቦ ስም ይሰጠዋል ? ይህ ስህተት ነው። ሌባ … ሌባ ነው ! ግለሰብ ሲሰርቅ ሌባ ፤ ባለስልጣን ሲሰርቅ ሙስና የሚባል ስም ሊሰጠው አይገባም!
የህግ የበላይነት በአንድ ሀገር የሚረጋገጠው ባለስልጣናት እና ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሲሆኑ ነው። ስለሆነም ባለስልጣን ሲሰርቅ ሙስና ብሎ ማሽሞንሞን ተራ ዜጎች ሲሰርቁ ሌባ ማለት የህግ የበላይነትንም የዘነጋ አካሄድ ስለሆነ ሁሉንም ሌባ አልያም ሁሉንም ሙሰኛ ብሎ መጥራት ያስፈልጋል። እንደኔ ግን ሌባን … ሌባ ! ብሎ መጥራቱ ብቻ አዋጭ ይመስለኛል።
ሌባን ማሽሞንሞን ስል የአንድ በአንድ ትንሽየ የገጠር መንደር የሚኖር ሌባ ታሪክ ትዝ አለኝ። በአንድ በትንሽዬ የገጠር መንደር የሚኖር እጅጉን የሚፈራ አለ ደሴ የሚባል ሌባ ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን አቶ አለ ደሴ የጎረቤቱን በሬ ይሰርቃል። በሬው የተሰረቀው ሰውየም በሬዬ ስለጠፋ የሰፈራችን ሰው ተሰብስቦ ይጠየቅልኝ ሲል በሰፈራቸው የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሽማግሌዎች ይጠይቃል፡፡
ሽማግሌዎችም የቀረበላቸውን አቤቱታ መሰረት አድርገው የሰፈራቸውን ሰዎች በሙሉ ሰበሰቡ። ሽማግሌዎቹም በዚች ሰፈር በባህል «እውስ ማውጣት» የተባለ በሚታወቀው ሌባውን የማፈላለግ ዘዴ ተጠቅመው የአቤቱታ አቅራቢውን በሬ የሰረቀውን ሌባ ማፈላለግ ይጀምራሉ። «በእውስ ማውጣት » ዘዴም በሬውን የሰረቀው ሰው አቶ አለ ደሴ የተባለው አስፈሪው ሌባ መሆኑንም ይደርሱበታል።
ነገር ግን ሌባውን ስለሚፈሩት በሬውን የሰረቀው ሰው አለ ደሴ ነው ለማለት ፈሩ። ምክንያቱም አንደኛ አቶ አለ ደሴ የእነሱንም በሬ ይሰርቃቸዋል። ሁለተኛ አቶ አለ ደሴ ከግብረ አበሮቹ ጋር ተባብሮ ሽማግሌዎቸንም ሊገድላቸው ይችላል። በመሆኑም አቶ አለ ደሴን የፈሩት «እውስ የሚያወጡ» ሽማግሌዎች በሬውን የሰረቀው ሌባው ከዚህ ሰፈር አይደለም ብለው አረፉት ።
በዚህ የተበሳጨው ፍትህ ፈላጊው በሬው የተሰረቀበት ገበሬ ምን ቢል ጥሩ ነው … እናንተ ሌባው ከሰፈር የለም እያላችሁ ብትናገሩም ሌባው ግን ከዚህ ሰፈር «አለ» ሲል በአሽሙር ሌባው አቶ አለ ደሴ መሆኑን ተናገረ። ሌባ የጠፋው ሰው በአሽሙር የመናገሩ ዋና ምክንያት አቶ አለ ደሴ ከበሬው መጥፋት ለሚብስ ችግር እንዳይዳርገው በመስጋት ነበር ።
የሰውየው ቅኔ የገባቸው ሰዎችም ሌባውን እያወቁት ትክክለኛውን ፍርድ መፍረድ ባለመቻላቸው እያዘኑ «ሌባውማ «አለ» ። ግን ሌባውን እንዴት አድርገን ማወቅ እንችላለን ? » አሉ ይባላል።
በእኛ እድር እና ሰፈርም እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ሌባው አለ። የሰፈራችን ሰዎችም ሌባው ማን እንደሆነ ያውቁታል። ግን ማን ደፍሮ የሌባውን ስም ይናገር። ምክንያቱም የሰፈራችን ሰዎች የሌባውን ስም ቢናገሩ ሌባው ለከፋ ችግር ይዳርገናል ብለው ይሰጋሉ።
የሚገርመው የእኛ ሰፈር ሌቦች ደግሞ ሌብነታቸውን ለመደበቅ ሲሉ የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ አይነት እንዲሉ ራሳቸው ከሰፈራችን የሆነ ነገር ሰርቀው ራሳቸው መሰረቁን ይጠቁሙናል። ራሳቸው ከሳሽ ይሆናሉ። ተከሳሽ፣ ምስክር ፣ ዳኛም ራሳቸው ይሆናሉ። ይህ በሆነበት ሰፈር እንዴት ሌብነት ሊጠፋ ይችላል ?
የእኛ ሰፈር እና የእድር ኃላፊ ግብዝነት የሚስተዋልበት በመሆኑ የሰፈራችንን ሰዎች ከማራቆት በዘለለ የሰፈራችን ህልውና የሆኑትን ካስማ እና ማገር የሚሰባብር እና ለዘመናት ስንገነባው የቆየነውን እድራችንንም የሚያፈርስ ነው።
በእኛ ሰፈር ያሉ ሌቦች መዝረፋቸው ብቻ አይደለም ሰፈራችንን እየጎዳ ያለው። ይልቁንም ስለመስረቃቸው በመረጃ እና በማስረጃ ሲደረስባቸው ስርቆታቸውን ለመሸፋፈን ወይም ለማደባበስ ጎሳን እና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን መጠቀማቸው እንጂ። ይህ አካሄድ በብሔር ብሔረሰቦች እና በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ቅራኔ ከመፍጠር ባለፈ እስከደም መፋሰስ እንዳደረሰ በተደጋጋሚ አይተናል። በቅናት በምቀኝነት፣ ከላይም ከታችም ብሎ መቧደን እንደማይጠቅም አይተናል። እንጥላለን ያሉ ሲወድቁ፣ የጠሉትን ሲወርሱ አስተውለናል። ክፋት የእጅን ይከፍላል እንዲሉ ሌላው ከዚህ መማር አለበት።
ይህንን አባባል በአንድ የትንሽየ የገጠር ከተማ የተፈጠረ እውነተኛ ታሪክን እንደምሳሌ ተጠቅሜ ላሳያችሁ፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ በትንሽዬ የገጠር ከተማ ውስጥ የሚኖሩ አንድ መነኩሴ እና አንድ ጠላ በመሸጥ ልጆቿን የምታስተምር እናት ነበሩ።
በትንሿ የገጠር ከተማ የሚኖሩት መነኩሴ እና ጠላ ሻጯ እናት በጣም ይቀራረባሉ። ክፉና ደጉንም በጉርብትና ለዘመናት አብረው ማሳለፍ የቻሉ ነበሩ። መነኩሴው ጠላ ሻጯን እናት አብዝተው ይወዷታል። ሶስት ልጆችን ያለ አባት ጠላ ሸጣ እያሳደገች ብለውም ያዝኑላታል። በዚህም ፈጣሪ ኑሮዋን ያስተካክላት ዘንድ አብዝተው ይጸልዩላታል፡፡
ይሁን እንጂ ጠላ ሻጯ እናት አጋጣሚ ሆኖ ለመሸጥ የጠመቁት ጠላ ባልተሸጠ ጊዜ ይሄ የፀሐይ ቆብ ያደረገ መነኩሴ ምናምን ስለሚያደርግብኝ እያሉ መነኩሴውን ይወነጅሉ ነበር።
አንድ ቀን ጠላ ሻጯ እናትም እኚህን መነኩሴ ካልገደልኩ ጠላዬ መሸጥ አይችልም ብለው ይደመድማሉ። ከዕለታት በአንዱ ቀን ጠላ ሻጯ እናት ለመነኩሴው ሽሮ ወጥ በላይ በላዩ የተቸለሰበት እንጀራ በትሪ እና በደቂቃዎች መግደል የሚችል መርዝ የተጨመረበት በማንቆርቆሪያ የሞላ ጠላ ያመጡላቸዋል። መነኩሴውም የዘወትር ጸሎታቸውን ሳይጨርሱ ኖረው ጸሎታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ጠላውን እና እንጀራውን ከድነው አስቀመጡ ።
ይህ በእንዲህ እያለ በጠዋቱ ፈረቃ ሲማሩ የዋሉ የጠላ ሻጯ ሶስት ልጆች ከትምህርት ቤት ይመለሳሉ። ሶስቱም ልጆች መነኩሴውንም እንደአባታቸው ይመለከቱ ስለነበር ከትምህርት ቤት መልስ ሁሌም ወደቤታቸው የሚሄዱት መነኩሴውን ካገኙ በኋላ ነበር። እንደተለመደው በዚህ ቀንም የጠላ ሻጯ ልጆች መነኩሴውን ሰላም አረፈዱ አባባ እያሉ ወደ መነኩሴውን ለመሳም ወደ መነኩሴው ቤት አመሩ።
መነኩሴውም የሶስቱንም ልጆች ከሳሙ በኋላ ከጭቃ ከተሰራቸው መደብ መቀመጫ ላይ እንዲቀመጡ አዘዟቸው። ልጆችም የመነኩሴው ነገር ስለማይሆንላቸው በመነኩሴው ቤት ገብተው ይቀመጣሉ። መነኩሴውም ልጆቹን እናታችሁ ካመጣችው ጠላ እና ምግብ ካልቀማሳችሁ ብለው አጥብቀው ይለምኗቸዋል። ልጆቹም መነኩሴውን ያከብሯቸው ኑሮ እናታቸው ካመጣችው ጠላ እና ምግብ ተካፍለው በሉ፤ ጠጡ።
ልጆቹ ግን አንድ እርምጃም እንኳን ሳይንቀሳቀሱ በያሉበት ተዘረሩ። በሁኔታው የተደናገጡት መነኩሴም ጭንቅላታቸውን ይዘው ኡ…ኡ… ብለው ጮሁ። የመነኩሴውን ጩኸት የሰሙ የትንሿ የገጠር ከተማ ነዋሪዎችም «አባ ምን አጋጠመዎት» እያሉ ወደ መነኩሴው ቤት አቀኑ። መነኩሴው ቤት በደረሱ ወቅትም የጠላ ሻጯ ልጆች መሬት ላይ ተዘርረው አገኙ።
የሰፈር ሰዎችም የወደቁትን የጠላ ሻጯን ልጆች አፋፍሰው ወደ ሐኪም ቤት ወሰዷቸው። ነገር ግን መትረፍ የቻለው አንደኛው ልጅ ብቻ ነበር። ሁለቱ ሞቱ።
ልብ በሉ! በሰዎች ላይ ያልሆነ ነገር ተቧድኖ ፤ ከኋላቸው ለመውጋት መስራት ትርፉ ራስን መጉዳት ነው። መጨረሻውም የጠሉትን መውረስ መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ።
የእናንተው ውድ እናት የተስፋዋ ምድር ብሎ ደብዳቤ ማንበቡን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎች ወፈፌው ይልቃል አዲሴን በጭብጫባ ሸኙት።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም