
ዜና ሐተታ
የኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ መሆን ብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ስጋት ደቅኖ፣ ዜጎቿንም ለቁጭት ዳርጎ ቆይቷል።
ባለፉት ዓመታት ጉዳዩን ማንሳት እንደጥፋተኛ ሲያስቆጥር ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የባሕር በር ሀገራዊ አጀንዳ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታም፤ ኢትዮጵያ ከሕግ ውጭ ባሕር አልባ የሆነችበት መንገድ እንደሚያስቆጫቸው ገልጸዋል።
ይህ ኢ-ፍትሐዊነት አፋጣኝ ፍትሕ እንዲያገኝ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የዘመኑ የሀገር ባለአደራ የሆኑ ወጣቶችስ በጉዳዩ ላይ ምን ይላሉ ስንል አስተያየታቸውን ጠይቀናል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሰፊ የባሕር በር የነበራት ሀገር ነበረች። በጊዜ ሂደት በተፈጸሙ ፍርደ-ገምድል ውሳኔዎች የባሕር በር አልባ ሀገር እንድትሆን ተደርጓል።
እንደሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ለውጦችም እየተመዘገቡ ነው። እነዚህ ጥረቶችና ለውጦች የባሕር በር ኖሮን ቢሆን ወጣቶች ማግኘት የሚገባቸውን ሁለንተናዊ ጥቅም እንዲያረጋግጡ ትልቅ አቅም ይፈጠር ነበር ይላል።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆኗ ብሔራዊ ደኅንነቷ እንዳይረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቷም በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ እንቅፋት ሆኖባታል የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ሌላውን ሁሉ ትተን በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምናወጣውን ወጪ ብንወስድ እንኳን በርካታ ማኅበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት ብሎም ሥራ ዕድል መፍጠር ያስችል እንደነበር ይገልጻል።
ለበርካታ ዓመታት የባሕር በርን ማንሳት ትክክል ያልሆነ አለፍ ሲልም እንደወንጀል ሲቆጠር እንደነበር አስታውሶ፤ የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቁና ልማትን የሚያፋጥኑ አጀንዳዎች ሁሉ መነሳት አለባቸው ይላል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት አለባት የሚለው አጀንዳ በመንግሥት መነሳቱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሶ፤ ጥያቄው ዓለም አቀፍ ሕግንና ዲፕሎማሲን ተከትሎ መልስ እንዲያገኝም መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ወጣቶች የዘመናቸው ዐሻራ መሆኑን ተገንዝበው በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክቶ፤ የየዘርፉ ምሑራንም ጥያቄው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት የሚያገኝበትን መንገድ ማመላከት ይኖርባቸዋል ሲል ይጠቁማል።
መላው ኢትዮጵያውያንም በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ሊያደርጉ እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙሕዲን ናስር በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ ላለፉት ከ30 በላይ ዓመታት ባሕር በር አልባ ሆና መቆየቷ ልታገኝ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አለፍ ሲልም ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንድትሰጥ እንዳደረጋት ይጠቁማል።
ላለፉት ዓመታት ጉዳዩ ተሸፋፍኖ መቆየቱን አስታውሶ፤ የባሕር በር አስፈላጊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ መምጣቱ አስደስቶናል። ለውጤታማነቱም በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደወጣት አደረጃጀት የሚጠበቅብንን አስተዋፅዖ ለማበርከት ዝግጁ ነን ይላል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ብትሆን ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ወጣቶች ናቸው የሚለው ጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠር እና ድንበር ዘለል ግንኙነቶች መጠናከር በሂደቱ ሊገኙ ከሚችሉ ጥቅሞች መካከል ናቸው። የባሕር በር ለማግኘት የተለመደውን ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፤ ለዚህም ሁላችንም በእውቀታችን፣ በጉልበታችንና ባለን አቅም ሁሉ ዐሻራችንን ልናሳርፍ ያስፈልጋል ይላል።
ትኩረቱን ወጣቶች ላይ አድርጎ የሚሠራ ‹ኒው ላይፍ ቲን ቻሌንጂ› የተባለ ድርጅትን በሥራ አስኪያጅነት እየመራች የምትገኘው ሄለን ጥላሁን እንደምትለው ደግሞ፤ የባህር በር መኖር የወጣቶችን ተጠቃሚነት ያሳድጋል።
እንደሀገር ያለን የወጣት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሳ፤ ወጣቶችን ያላሳተፈና ድምፃቸው ያልተሰማበት ነገር ውጤታማ ሊሆን አይችልም። የባሕር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥም ወጣቶችን ማዳመጥ፣ ሃሳባቸውን መተግበርና በሂደቱ ላይ ተገቢው ሚና እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያለችው።
የባሕር በር ቢኖረን የሥራ እድል ፈጠራን ለማስፋትና ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ለማከናወን ስለሚያስችለን ወጣቶችም በባለቤትነት ሊሠሩበት እንደሚገባ አመላክታለች።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም