ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት የሆነው የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉት። ከተፈጥሮ ሀብቶቹ መካከልም፣ የሀዋሳ ሐይቅ፣ ፍልውሃዎች፣ ለተለያዩ የግብርና እና የቱሪዝም ስራዎች ሊውሉ የሚችሉ መልክዓምድሮቹ ይጠቀሳሉ። እነዚህ የክልሉ ሀብቶች ሀገርን የሚያኮሩ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሱ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ፀጋዎች ናቸው።
ክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ያሉበትም ነው። ግዙፉ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የይርጋአለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኙበታል። በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ኢንዱስትሪዎችም ይገኙበታል። ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማሳደግ በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደለት ያለው የሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካም ሌላው የክልሉ የኢንቨስትመነት መዳረሻ ነው፡፡
በመሰረተ ልማት በኩልም ምቹ ሁኔታዎች ያሉበት ነው፤ ከአዲስ አበባ ሀዋሳ ካለው ነበሩ መንገድ በተጨማሪ ከሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ እየተካሄደለት ይገኛል። ከእዚህ መንገድ ግንባታ የሞጆ ዝዋይ መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል። የአውሮፕላን ማረፊያ ባለቤትም ነው።
የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛም ነው። ከፍተኛ የቡናና ሌሎች ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ እነዚህ ሀብቶች ከክልሉ አልፈው ለሀገርም እየተረፉ ይገኛሉ። የክልሉ ሁለንተናዊ ሀብትና አቅም የባለሀብቶችን ትኩረት እንደሚስብ ይጠበቃል። ስለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ሀብትና የዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴዎች የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ዘነበ ለገሰ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የሲዳማ ክልል የኢንቨስትመንት አቅም
የሲዳማ ክልል በርካታ የኢንቨስትመንት አቅሞች አሉት። ክልሉ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች ይመረቱበታል። ብዙ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ቡና፣ ወተት፣ ዶሮ፣ ማር፣ ስጋና ሌሎችም ይመረቱበታል። ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከግብርናው በተጨማሪ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እድል የሚፈጥር ነው። በማዕድን ዘርፍ በክልሉ ከ17 በላይ የማዕድን ዓይነቶች ይገኛሉ።
ክልሉ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንዲሆን ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል በአንፃራዊነት የተሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦት (ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን የሚያገናኙ መንገዶች) አሉት። አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ያለበት ክልልም ነው። ስራ ፈላጊ ወጣት የሰው ኃይል መኖሩ፣ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ የሚዘልቀው መንገድ የክልሉን ዋና ከተማ ሐዋሳን አቋርጦ ማለፉ እና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት ያለው መሆኑ ተመራጭ ከሚያደርጉት መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢንቨስትመንት ተግባራት በሲዳማ ክልል
ክልሉን ከሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ የኢንቨስትመንት ልማት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በክልሉ አራት የኢንዱስትሪ ክላስተር ዞኖችን በማደራጀት የክልሉን ሀብት ለኢንቨስተሮች የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል። የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል። በተሰሩ የንቅናቄ ተግባራት አማካኝነትም በርካታ ባለሀብቶች በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል፡፡
በሲዳማ ክልል 2ሺ301 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል 1ሺ867 የሚሆኑት በስራ ላይ ይገኛሉ። 464 ፕሮጀክቶች ደግሞ ፈቃድ ወስደው ስራ ባለመጀራቸው ፈቃዳቸው ተሰርዟል። በስራ ላይ ያሉት ኢንቨስትመንቶች ከ52ሺ በላይ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ አድርገዋል። ከግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች በተጨማሪ በክልሉ በአገልግሎት ዘርፉ በሆቴልና መዝናኛ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎችም በርካታ ባለሀብቶች ተሰማርተዋል።
ለኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። ከ1986 እስከ 2012 ዓ.ም ለ26 ዓመታት ያልተመዘገበ የኢንቨስትመንት ካፒታል በ2014 ዓ.ም ማስመዝገብ ተችሏል። በ26 ዓመታት የነበረው የኢንቨስትመንት ካፒታል ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን፣ የ2014 ዓ.ም ብቻ ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ሆኗል።
በሀገር ደረጃ ትኩረት በተሰጣቸው ጉዳዮች ረገድ ደግሞ በቅርቡ በበጋ ስንዴ ልማት ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች 550 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ወደ ስራ ተገብቷል።
በ2015 ዓ.ም ለ400 ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ ለ165 ባለሀብቶች ፈቃድ መስጠት ተችሏል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው የበለጠ ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ16ሺ በላይ የሆኑ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።
በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ አምስት ወራት 160 ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች ለመስጠት ታቅዶ 583 ሄክታር መሬት ማቅረብ ተችሏል። የክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል። የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ምን እንደሚመስል እና ጉድለቶቻቸው ምን እንደሆኑ ክትትል ይደረጋል። በዚህ ረገድ በአምስቱ ወራት ለ309 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትል ለማድረግ ታቅዶ ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል።
ክልሉ ትኩረት ከሰጣቸው የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ነው። ሲዳማ ክልል በቡና ሀብት ትልቅ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። በክልሉ 700 የቡና ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የጥራት ውድድር (Cup of Excellence) ላይ ቀርቦ አሸናፊ የሆነው የሲዳማ ቡና ነው። ከዚህ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት አቅጣጫ የተያዘው እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ጉዳይ ነው። በዚህም ቡናን እሴት ጨምሮ የሚያቀርብ የኢጣሊያ ኩባንያ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ስራ ጀምሯል።
ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ሲሳተፉ ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ክልሉ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የባለሀብቶችን የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅም ለመጠቀምና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም ለመገንባትና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ክልሉ በትኩረት እየሰራ ነው።
በክልሉ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለክልሉ ኢንቨስትመንት ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ስለሆኑ የባለሀብቶችን ስራ በአንፃራዊነት ቀላልና ፈጣን ለማድረግ ያስችላሉ። ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማምረቻ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ትልቅ እድልን ይፈጥራል። በግብርናና የግብርና ውጤቶች ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚገቡበት ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ እምቅ የሆነውን የክልሉን የግብርና ዘርፍ አቅም ለመጠቀም ያግዛል። የበንሳ መካከለኛ የኢንዱስትሪ ፓርክም ለክልሉ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ አቅም መሆን የሚችል የማምረቻ ስፍራ ነው።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ
በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ያለው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እየተሻሻለ መጥቷል። ይሁን እንጂ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ያላቸው ተሳትፎ አሁንም ዝቅተኛ ነው። ለአብነት ያህል በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ አምራቾች መካከል የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሦስት ብቻ ናቸው። ስለሆነም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ በቅርቡ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክን የማስተዋወቅ ስራ በተሰራበት ወቅት 106 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተመዝግበዋል።
የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች
ክልሉ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር የሚያደርጋቸው ማበረታቻዎች በአዋጅና በመመሪያ በተደነገጉ የማበረታቻዎች (Incentives) አሰጣጥ መሰረት የሚፈፀሙ ይሆናል። ክልሉ ‹‹የኢንቨስትመንት አዋጅ 1180/2012››ንና ሌሎች ሕጋዊ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ለባለሀብቶች ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን ያደርጋል። ቦታዎችን አዘጋጅቶ ለባለሀብቶች ማቅረብን ጨምሮ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባራትን ያከናውናል። ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች
በሲዳማ ክልል በኢንቨስትመንት አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የወሰዱትን መሬት ለረጅም ጊዜያት አጥሮ ማስቀመጥ ነው። ይህ ደግሞ ባለሀብቶቹ ወደ ስራ ቢገቡ እነሱም ሆኑ ሀገሪቱ የሚያገኙትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲያጡ ያደርጋል። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ባለፉት አምስት ወራት ለ68 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል። 19 ባለሀብቶች የወሰዱት መሬት ደግሞ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ተደርጓል።
የረጅም ጊዜ ብድር ያለማግኘትም ሌላው የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግዳሮት ነው። አልፎ አልፎ የኃይል መቆራረጥ የሚከሰትባቸው ራቅ ያሉ አንዳንድ ወረዳዎች አሉ። የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች የዘርፉ መሰናክል የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች የሉም። ሕጋዊ ሆነው የኢንቨስትመንት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች በፍጥነት ይስተናገዳሉ።
እቅዶች
የሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ዋናዎቹ ቀጣይ እቅዶች የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማጠናከር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለሚያደርጉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት መስጠት ናቸው። በዚህም ዜጎች ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጡ ዘላቂ ተግባራት ይከናወናሉ።
ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል። ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት የሚታሰብ አይደለም። ሰላምን ለማስፈን የተወሰደው እርምጃ ለባለሀብቶች እንዲሁም ለመላው ህብረተሰብ ተስፋ የሰጠ ነው። ከዚህ አንፃር በሲዳማ ክልል ያለውን ሰላም አስጠብቆ በማስቀጠል የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ በትኩረት ይሰራል።
በአጠቃላይ በሲዳማ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ቢመጡ ክልሉ ባለሀብቶቹን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሆነ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ዘነበ ለገሰ ተናግረዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም