መቸም የኢትዮጵያ ሥነግጥም ታሪክ ሲነሳ ሺህ ዘመናትን ወደ ኋላ መሄድ፤ በግዕዝና አማርኛው የተቀኙ በርካታ ልሂቃንን መጥቀስ የግድ ቢሆንም፣ እንደ አንድ የጋዜጣ ገጽ ይዞታ ግን በአንድ ሰው ላይ ማተኮር፣ አተኩሮም በእርሱ አማካኝነት የተቻለውን ያህል ባለውለታዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናልና በዚሁ ስምምነት እንቀጥል።
የዛሬው ተስተዋሻችን ምንም ሳይታሰብ፣ ያለ እድሜና ሰአቱ፣ ያለ ጊዜው … በድንገትና ቅፅበት ከፊታችን ሽው፣ እልም ያለው፣ የዘመናዊ ሥነግጥም ትንታኔ ፈር ቀዳጅ፣ የሥነጽሑፍ መድረኮች ሁሉ ግርማ ሞገስና ባለባት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ይሆናል።
ብርሀኑ ገበየሁ በወዳጅ ዘመዶቹ፣ አድናቂ ተከታዮቹ፤ ተማሪዎቹና ደቀ መዝሙሮቹ፤ በሥነግጥም (በአጠቃላይ በሥነጽሑፍ) ቤተሰቦች፣ ገጣሚያንና አድናቂያኑ . . . ዘንድ ገና ምኑም ያልጠፋ፤ ስራዎቹም ሆኑ ትዝታው በሚያውቁት ዘንድ ሁሉ ህያው ሆኖ፣ ግዘፍ ነስቶ ፊት ለፊታቸው በአካል ያለ፤ ትዝታው ያላረጀ … ብልጭ ብሎ ድርግም ያለ ወጣት ምሁር ነው (”ነበር እንበል መሰለኝ . . .” አለ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ አዎ፣ ነበር)።
ብርሀኑ ገበየሁ ምሁርነቱ ያስታጠቀውን ሁለገብ መሳሪያ በመጠቀም ሥነጽሑፍን በአይነት በአይነት የመበለት ሙሉ አቅምን ያዳበረ፤ አዳብሮም በጥናትና ምርምር ስራዎች (ህትመቶች)ም ሆነ መድረኮች ዐይንከሰበከት እያገላበጠ ማየትና ማሳየት የቻለ፤ ከመንዙማ እስከ አለማዊው፤ ከቤተ ክርስቲያን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዘለቁ የአማርኛ ሥነግጥም ስራዎችን በፈር ቀዳጅነት ያስተነተነ … የሥነጽሑፍ ሊቅ ነበር። ፈጣሪ ትንሽ እድሜውን ሰጥቶት ቢሆን ኖሮ ደግሞ ተአምር ሊሰራ የሚችል መሆኑን አስቀድሞ ራሱ ያስመሰከረ ትንታግና በሙሉ ስሜት የታመቀ ኃይልን የተሞላ ሰው ነበር።
ለብርሀኑ የሥነጽሑፍ ልሂቅነት ማሳያ ይሆን ዘንድ አዲስ አበባን አስመልክቶ ”አዲስ አበባ በአማርኛ ሥነ-ግጥም” በሚሊኒየሙ መሸጋገሪያ ላይ አቅርቦት ከነበረው ጥናት አንድ ገለፃውን እንመልከት፤
የኪነጥበብ መንገድ ብዙ ነው፤ የገጣሚያንም መንፈስና ስሜት እንዲሁ ከአያሌ ስሜቶች ይወለዳል፤ ከብዙ እውነቶች ይመነጫል፤ ብዙ ጊዜም የዘመን መንፈስ፣ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም አንደበት ይሆናል። በዚህ ምክንያት፣ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጥቅሉ፣ በልቦለድና በግጥም በተለይ አዲሰ አበባ የማኅበረ ባህላዊ ቀውስ መገለጫ መቼት ሆና በተደጋጋሚ መሳሏ። ምናልባትም፣ ሥነ ጽሑፋችን እራሱን እንደ አንድ የጥበብ ዘርፍ አጎልምሶ በዘመናዊነት መንገድ መጓዝ በጀመረበት ዘመን የማኅበረሰባችን አስተዳደር፣ ወግና ልማድ የላሸቀበት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር በዚያ ዘመን የነበሩት ደራስያንና ገጣምያን አዲስ አበባን ከውጫዊ ገጽታዋች ይልቅ በሰብዓዊና ማኅበራዊ እውነቷ የመግለጽ ዝንባሌ የበረታባቸው። ስለዚህም የ1950ዎቹና 1960ዎቹ ገጣምያን አዲስ አበባን በማኅበሩ ውስጥ የሚታዩ ቅራኔዎች፣ ድቀቶች፣ ቀውሶችና የሰብዕና መንጠፍ መናኸሪያና መገለጫ ደሴት አድርገው ስለዋታል። የዘመኑን ገጣምያን መንፈስና እውነት ሊወከሉ ከሚችሉ ግጥሞች መካከል ቀጥዬ ጥቂት ስንኞችን የምዘርፍበት የጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹አይ መርካቶ›› አንዱ ነው። (ግጥሙ በጥናቱ ላይ ቀርቦ ተብራርቷል፤ ተተንትኗል።)
“ልቦለድ እንደ ርዕዮተዓለም መገለጫ” በሚል ርእስ ያደረገውም ጥናት፣ የስፍራ ማጣት እንጂ፣ ሳይነሳና ሳይብራራ መታለፍ ያልነበረበት ድንቅ ስራው ነው። በገፀባህርያት ስያሜ ላይ ያካሄደው፣ በአይነቱ ”አዲስ” ሊባል የሚችል ጥናት (የኢት. ቋንቋዎች ጥናት ጆርናልን ይመለከቷል)፤ እንዲሁም፣ ስለ አገር ጉዳይ እየተብከነከነ የሰራቸው በርካታ ጥናቶችም እንደዚሁ።
እዚህ ላይ የእኛን አስተያየት ገታ እናድርግና በቅርብ የሚያውቁት ምሁራን ስለ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ያሉትን እንመልከት።
ስለ ስራው (ከአማርኛ ሥነግጥም መጽሐፉ የጀርባ አስተያየት የተወሰዱ)
ሥነግጥም ታስቦበት በስርዓትና በጥበብ የሚከናወን “አመጽ” ነው። ይህን አመጽ ማጥናት “አዲስ ስርዓት” የመትከልን፣ ግጥሙን መልሶ የመፍጠርን ያህል ፈታኝ ተግባር በመሆኑ ላብን፣ ምናባዊ ብቃትንና ነጻነትን ይጠይቃል። ግጥምን በወጉ ማንበብ ሙዚቃን፣ ስዕልንና ቅርጽን በግጥም ውስጥ አድምጦ፣ ተመልክቶና ዳብሶ ማድነቅ ማለት ነው። በዚህ በጥበቡ ባሕርያት ጸናናነት ምክንያት ይመስለኛል በአገራችን ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም የሥነግጥም ማስተማሪያ መጻሕፍት እንደልብ የማይገኙት። ካሉትም ጥበቡን የሚገሩና የሚያለምዱ፣ አንባቢን መማረክና ማሸነፍ የሚችሉ ጥቂቱ ብቻ ናቸው። ይህ የብርሃኑ መጽሐፍ ከእነዚህ አንዱ የሚሆን ይመስለኛል ᎐ ᎐ ᎐ ብርሃኑን በመጀመሪያ ተማሪው ሆኜ፣ በኋላም በጓደኝነትና በስራ ባልደረባነት አውቀዋለሁ። ይህ እውቀቴም ብርሃኑ በሥነጽሑፍ ላይ የሚያካሂዳቸውን ምርምሮች በቅርበት እንድከታተል አስችሎኛልና የአማርኛ ሥነግጥም የዚህ ልምዱና ምርምሩ ውጤት መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። መጽሐፉ በአማርኛ የሥነግጥም ትምህርት ያለውን ክፍተት ይሞላል ᎐ ᎐ ᎐ የመተንተኛና የመተርጎሚያ ብልሃቶቹ ተጨባጭ በመሆናቸው፣ ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን በእውቀትና በንቃት ለመከወኛነት፣ አንባቢያንም በወጉ አንብበው ለማጣጣሚያነት ሊገለገሉባቸው ይችላሉ። ትንታኔዎቹና ትርጓሜዎቹ በምስል የተሞሉ ናቸው፤ አይናገሩም፤ አይዘረዝሩም፤ አያብራሩም። ይልቁኑ ልክ እንደግጥሞቹ ባለ መንገድ ይስላሉ፤ ይቀርጻሉ፤ ያሳያሉ። ስለዚህ ዘና ማድረግ ኪናዊ እርካታን መስጠት የመጽሐፉ ሌላው ተግባር ይመስለኛል።
ቴዎድሮስ ገብሬ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሥነጽሑፍ መምህር
ክዋኔ የሥነግጥም ህይወት መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎቻችን ወጣቶች የቀደምት ገጣሚዎቻችንን የግጥም ክዋኔ ለማየት አልታደልንም። ይሁንና ብርሃኑ በዚህ መጽሐፍ፣ ግጥሞቹን ከነኪናዊ ምልዐታቸው እንድናውቃቸው ክዋኔ-አከል ተጨባጭና ምናባዊ ትንታኔዎችን ለኛም ሆነ ለታላላቆቻችን በሚደርስ መልኩ አቅርቦልናል። መጽሐፉ ለምሁራዊ ተብሰልስሎት (intellectual exercise)፣ ለትምህርታዊ ፋይዳና ለምናባዊ እርካታ እንደየመጥለቂያችን የምንቀዳበት የአማርኛ ሥነግጥም ባሕር ነው። በተለይም ለኛ ለወጣቶች ከአባቶቻችን የሥነግጥም ጥበብ ሊያጋባን የሚችል የነገር አባት ነው።
ነቢዩ ባዬ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የትያትር ጥበባት መምህር
የአገሬ ሰው ገጣሚ ነው፤ ከንጉሱ እስከ እረኛ። ለዚህም ሃይ ሎጋው፣ ሙሾው፣ ጌረርሳው፣ ቀረርቶው፣ ሂያሴው ᎐ ᎐ ᎐ ህያው ምስክሮች ናቸው። አሁን አሁን ደሞ በሕትመት የሚደርሱን ግጥሞች ብዛት መጨመር እጁጉን አስደሳች ነው። ይሁንና ግጥሞቻችን ለምን፣ በምን፣ ከምንና እንዴት ነው የሚሸመኑት? እንዴትስ ነው፣ ልናደምጣቸውና ልናደንቃቸው እምንችለው? የብርሃኑ መጽሐፍ እነዚህን ለመሳሰሉ ግጥሞችን አንብቦ ከመረዳት ጋር ለሚዛመዱ ገራገር፣ ግን ውስብስብ ጥያቄዎች በምርምር የተገኙ ምላሾችን ይሰጣል። በመሆኑም፣ የአማርኛ ሥነግጥምን ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግጥማዊ ባህሎችና ግጥሞች መረዳት ለሚሹ ሁሉ ጠቃሚ መሳሪያ ይመስለኛል።
አብርሃም ዓለሙ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛና የአፋን ኦሮሞ ሥነጽሑፍ መምህር
አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ህልፈተ-ሕይወቱን በተመለከተ
ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ እዛው የሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ (ያኔ ”ILS” ሕንፃ) ሲያስተምር ውሎ፤ ምሳውን ከጓደኞቹ ጋር በልቶ፣ ከሰአታት በኋላ ህልፈተ ሕይወቱ መሰማቱን የሰማውን ሁሉ ያስደነገጠ ሲሆን፤ በተለይም ሶስተኛ ዲግሪውን (ፒኤች.ዲ) ለመያዝ ሳምንታት ሲቀሩት መሞቱ ብዙዎችን የረበሸ ሆኖ ነበር። ይህ ጸሐፊም በወቅቱ የጋሽ ብርሀኑ ባልደረባ ከነበረው (አሁን ካናዳ ነው) አቶ ገዛኸኝ ጌታቸው ጋር ስለደረሰው አደጋ ሲያወራ፣ አቶ ገዛኸኝ ”ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው” ሲል ነበር አስደንጋጩንና እጅግ አሳዛኙን ክስተት የገለፀው። ተጨማሪ ይሆን ዘንድ፣ ለማሳያ ያህል (ከብዙዎቹ) የሚከተሉትን ብቻ እንመልከት።
”የረዳት ፕሮፌሰሩ ሞት በጣም አሳዛኝ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነበርኩ ጊዜ ሁለት ሴሚስተር አስተምሮኛል። አቶ ብርሃኑ በጣም ተማሪዎችን የሚወዱና የሚያቀርቡ መምህር ሲሆኑ፣ በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ፣ ተምረው ከሚያስተምሩ ጥቂት መምህራን መካከል አንዱ ነበሩ።” (”የሥነ ግጥሙ ብርሃን ጠለቀ” በሚል ርእስ ስር ሔኖክ ያሬድ የተባሉ ለንባብ ያበቁት)
“ፈልገነው ነበር ባለበት ከተማ
ዱዓ አድርገን ነበር በወሎ መንዙማ
አልተገናኘንም ጀሊሉም አልሰማ“
በሚል አንጓ አስተያየታቸውን የጀመሩት አሌክስ አብርሃም በበኩላቸው፤
በሕይወት እያለ በአካል አግኝቸው ለማላውቀው . . . ዩኒቨርሲቲ ገብቼ እፊቱ ተቀምጨ መማር ብጓጓም እኔ ስደርስ ይችን ዓለም በሞት ስለተሰናበተ ታላቅ መምህሬ ላወሳ ወደድኩ! በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ፤ በተለይም፣ በሥነግጥም እንደዚህ ሰው የተመራመረ፣ ያጠናና ያስተማረ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። የማወራችሁ ስለ ረዳት ፕ/ር ብርሃኑ ገበየሁ ነው። . . . በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነጽሑፍ፣ በተለይም በሥነ ግጥም መምህርነትና ተመራማሪነት ይታወቅ ስለነበረው ብርሃኑ ገበየሁ። ብርሃኑ ገበየሁን ያወኩት ገና ስራዎቹ በመጽሐፍ ሳይታተሙ ደሴ፣ የሃይስኩል ተማሪ እያለሁ ነበር። ማወቅ ብቻ አይደለም ያወራ፣ የተነፈሰው፤ የጻፈ፣ ያስተማረውን ሁሉ የማግኘት እድል ነበረኝ። በርቀት አስተማረኝ ብል ምንም ግነት የለውም። [. . .] 2002 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ የብርሃኑ ገበየሁን ድንገተኛ ሞት ሰማሁ። . . . የሆነ ሁኖ ታላቁ የሥነጽሑፍ ሰው፣ ረ/ፕ/ር ብርሃኑ ገበየሁ . . . ለአገራችን ሥነጽሑፍ ትልቅ ቦታ ያለው ‹‹የአማርኛ ሥነግጥም ንድፈ ሐሳብ፣ ማብራሪያ ትንታኔ›› መጽሐፉን አበርክቶልን በ45 ዓመቱ ነበር ይችን ዓለም በድንገት የተሰናበተው! እነሆ ነፍሱ ትሰማንም ከሆነ ሳያውቅ ብዙ ያስተማረኝ ተማሪው ዛሬ ስለተወልን ነገር ሁሉ እድሜውን ሙሉ ስለደከመበትም የአገራችን ሥነጽሑፍ ላመሰግነው ወደድኩ። ነፍስህ በሰላም ትረፍ።
ሲሉ ይገልፁታል።
በወቅቱ ለንባብ ሲቀርቡ የነበሩ ጽሑፎች”የደራሲያን ምስጢራዊ አሟሟት” (ብርሃኑ ሰሙ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ)፣ ”የሥነ ግጥሙ ብርሃን ጠለቀ” (abiy.wordpress.com)፣ ገዛኸኝ ፀ. የተባሉ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወቅቱ ቋሚ አምደኛ በወቅቱ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ያሰፈሩትንም እዚሁ ላይ ማስታወስና ፈልጎ ማየት ጠቃሚ ነው።
ጋሽ ብርሀኑ ከልቡ ምሁር ነው (ኤምኤ. — በሥነጽሑፍ፤ ኤም ኢዲ. በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በትምህርት ዘርፍ)። ያስተማራቸው (ይህንን ጸሐፊ ጨምሮ) እንደሚመሰክሩት ሥነጽሑፍ ውስጡ ነው፤ ስለሥነጽሑፍ ተናግሮ አይጠግብም፤ ስለ ሥነጽሑፍ ጽፎ አይረካም፤ በሥነጽሑፍ ጉዳይ ላይ ሳያስብና ሳያብሰለስል ውሎ አያድርም። ሁሌም በሥነጽሑፍ ጉዳይ ላይ እንደ ቆዘመ ነው። እንደ ተከራከረ፤ እንደ ተጨቃጨቀም . . . ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ አንድ ለእናቱ የሆነው ”የአማርኛ ሥነግጥም” ስራውም የዚሁ ውጤት ነውና ህያው ምስክር ሆኖት ይኖራል።
የምናውቀው ሁሉ እንደምናውቀው፣ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ገና ሮጦ የጠገበ አልነበረም፤ ጽፎ የረካም ሰው አይደለም። ገና ብዙ እንደሚቀረው፤ ገና ብዙ መስራት እንዳለበት አስቦ ሲንቀሳቀስ የነበረ የጥናትና ምርምር ሰው ነበር። አልተፈቀደምና ባጭር ቀረ።
ብርሀኑ ገበየሁ የሚዲያው ግርማ ሞገስ ሁሉ ነበር። እሱ የጥናትና ምርምር ስራዎቹን ባቀረበበት ሁሉ ሚዲያው አለ። እሱ በተናገረበት ሁሉ ሚዲያው አለ። በሙሉ ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ በከፍተኛ ሙቀትና ግለት … ሲሰጣቸው የነበሩ ሙያዊና ምሁራዊ አስተያየቶች ለሚዲያው ከሚሰጡት ድምቀትና ተወዳጅነት ባለፈ ለአድማጭ ተመልካቾች የሚሰጡት ትምህርት ቀላል አልነበረም።
ብርሀኑ ከሥነግጥም ስራዎች ባለፈም የአገራችንን ድምፃውያን ስራዎችም አድናቂና ፈታሽም ነበር።
ከእነዚህ ድምፃውያን መካከልም አንዷ ድምፀ ሸጋዋ ጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባው) ስትሆን፣ ብሬ እያገላበጠ ከፈተሻቸው፣ ይሁንታን ከሰጣቸውና በየመድረኩም ሆነ በጥናትና ምርምር ስራዎቹ ከሚያደንቃቸው መካከል የዚህችው ድምፃዊት ስራዎች ይገኙበታል።
ሎሬቱ “ሥነግጥም ወይም ቅኔ የሥነጽሑፍ የሥነጥበባቱ ሁሉ፤ የፈጠራ ሁሉ የደም ጠብታ ነው።” የሚለውን ባፀና መልኩ ብርሀኑ ገበየሁ ስለ ሥነግጥም ያላለው ያለም። ያልመረመራቸው የእውቅ ገጣሚያን ስራዎች የሉም። ከውጭም ከውስጥም እያጣቀሰ በብዕሩ ስለ ሥነግጥም ያልጫረው ካለ ይህ ጸሐፊ ያላየው ብቻ ነው የሚሆነው። ያልተነተነው፣ ያላብራራው፣ ያላስተነተነው ግጥም አለ ለማለት በሚያስቸግር መልኩ ብርሀኑ ሄዶበታል። ለዚህ አስተያየታችን ደግሞ፣ በዋናነት የበኩር ስራው (ግን ደግሞ የበኩር የማይመስለው) የሆነው፣ ዳጎስ ያለው የአማርኛ ሥነግጥም መጽሐፉ ነው።
በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ አሻራውን አሳርፎ ያለፈው ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ ባለ ትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የነበረ ሲሆን፣ ባጋጠመው ድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ ተማሪዎቹና አድናቂዎቹ፤ እንዲሁም የሥነፅሁፍ ቤተሰቦች በተገኙበት ሐምሌ 13 ቀን 2002 ዓ.ም በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ። ነፍስ ይማር።
ስም ከመቃብር በላይ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015