አርመን ትምህርት ቤት ማነው?
የኮቭሮኮፍ አርመኒያ ትምህርት ቤት አፄ ኃይለስላሴ አርመኖች በስደት ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ልጆቻቸውን ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ቦታው ለትምህር ቤት አገልግሎት ብቻ እንዲጠቀሙበት በነፃ የተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል። መገኛው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ወይንም ከናዝሬት ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ ነው።
ታዲያ ይህ ትምህርት ቤት ግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በመሻገር በርካቶች ተምረውበት ለቁምነገር በቅተዋል። እስከ 2014 ዓ.ም ድረስም ትምህር ቤቱ በርካቶች መርጠውት የሚሄዱበትና በትምህርት ሥርዓቱም በእጅጉ የሚመረጥና የሚመሰገን ነበር። ዳሩ ግን በሂደት ቀድሞ የነበረው ሥም እና ዝናው እየተቀዛቀዘ መጣ። ይህም አልበቃ ብሎት ትምህር ቤቱን ይመሩና ያስተዳድሩት የነበሩት አርመናውያን ትኩረት ነፈጉት። በእርግጥ በርካታ ዜጎቻቸው በችግራቸው ጊዜ የተማሩበትና በዚሁ ትምህርት ቤት እውቀት ቀስመው ለትልቅ ቁምነገር የበቁበት የዕውቀት ማዕድ መሆኑ ሳይዘነጋ። ከዚህም ባሻገር የአርመን እና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደላቀ ደረጃ እንዳሻገረው ይታመናል። ይሁንና የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት የሆነውና በብዛትና በበላይነት በአርመን የዘር ሐረግ ባላቸው ሰዎች የሚተዳደረው ይህ ትምህርት ቤት በ2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ማስተማር ሥርዓቱ በይፋ የተፋታ ሲሆን የበርካታ ወላጆችን ልብ የሰበረ ስለመሆኑ ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ።
ትምህርት ቤቱ ለምን ሥራውን አቆመ ?
የኮቭሮ ኮፍ አርመኒያ ትምህርት ቤት በርካታ ዓመታት እየተደራጀና ትውልድ የተቀረፀበት መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና እነዚህን ዘመናት የተሻገረው ትምህር ቤት ለመዘጋት ዋና ምክንያት የሆነው ግብዓት አለሟላችሁም የሚል ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ምዘና ሲደረግና የትምህርት ቤት መስፈርት መሰረት ሲመዘን እጁግ ዝቅተኛ ውጤት ያመጣ በመሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በወላጆች፣ መምህራንና አስተዳደር መካከል ጤናማ ግኝኙነት በመጥፋቱ ጭምር ነው።
የወላጆች ቅሬታ
ይህ ትምህርት ቤት እንዳይዘጋ የተማሪ ወላጆች ‹‹ትምህር ቤቱን ለመዝጋት ያቀረባችሁት ምክንያት ውሃ የማይቋጥር በመሆኑ ያለባችሁ ክፍተትና ጉድለቶችን በዝርዝር ንገሩንና እኛ ወላጆች ለልጆቻችን ስንል ጉድለቱን እናሟላለን ቢሉም የትምህርት ቤቱ ማናጀር ግን ትምህርት ቤቱ በ2014 ዓ.ም እንደማያስቀጥሉት እና ለልጆቻቸው ትምህር ቤት እንዲፈልጉ አስረግጠው እንደነገሯቸው ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ከወላጆች የመጣ ግብዓት ፈጽሞ አንቀበልም ብለው የወላጆችን ጥረት እንዳኮለሹ ይናገራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያንና አርመን ወዳጅነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ትልቅ ታሪክ ያለው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ቤቱ ባለውለታችን ነው በሚል ስሜት ድጋፍ ለማድረግ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ድረስ ቢንቀሳቀሱም በአርመኖቹ ፈቃደኛ አለመሆን ተሰሚነት በማጣታቸው ትምህርት ቤቱን መታደግ አለመቻሉን ይናገራሉ።
መማር ማስተማሩን ለምን ማቋረጥ አስፈለገ?
ወላጆች እንደሚሉት፤ ለአራዳ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ‹‹ጉዳዩ፤ የኮቭሮ ኮፍ አርመኒያ ትምህርት ቤት በ2014 ዓ.ም አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዳይቋረጥ መጠየቅን ይመለከታል›› በሚል በተፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል።
የኮቭሮኮፍ አርመኒያ ትምህር ቤት አፄ ኃይለስላሴ አርመኖች በስደት ወደ አገራችን በመጡበት ወቅት ልጆቻቸውን ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ 1844 ካሬ ሜትር ቦታ ለትምህርት ቤት አገልግሎት ብቻ እንዲጠቀሙበት በነፃ የተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ዛሬ የእነሱን ልጆች አስተምረው ከጨረሱ በኋላ የትምህርቱን ጥራት ሆን ብለው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲወርድ እያደረጉ ለመምጣታቸው የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ስልጠናና ጥራት ሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ በየዓመቱ ለትምህርት ቤቱ የሰጠው ውጤት ማሳያ ነው።
በዚህ ዓመት ደግሞ ትምህርት ቤቱን በማናጀርነት የሚያገለግሉት ወይዘሮ አሊስ ፓርኑኪያ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ስልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ በቀን 19/06/2013 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ መንግስት ያስቀመጠውን እስታንዳርድ ማሟላት እና የመምህራንን ደመወዝ መሸፈን ባለመቻላቸው በ2014 ዓ.ም ትምህርት ቤቱን እንደሚዘጉት በደብዳቤም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ አስታውቀዋል።
በመቀጠልም በዐ4/07/2013 ዓ.ም የትምህርት ቤቱን ወላጆችን ሰብስበው በ2014 ዓ.ም ትምህርት ቤቱን እንደሚዘጉትና ይህንኑም ጉዳይ ለሬጉላቶሪ ቢሮ – አሳውቀን ተቀባይነት ስላገኘን ከአሁኑ ትምህርት ቤት ፈልጉ በማለት የተማሪውን፤ የወላጁን እና የመምህራንን ሥነ-ልቦና በላይም አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ሁኔታን እና ሞራል ላይ ጫና ከማሳደር በተጨማሪ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ሳያስገቡ በተልካሻ ምክንያት ትምህር ቤቱን እንደሚዘጉት ለወላጅም አሳውቀዋል ይላሉ።
ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆናቸው ደግሞ የትምህርት ግብዓቶችን አላሟላችሁም በሚል በ2013 ዓ.ም የመዋለ ህፃናቱን እንዲዘጋ ስለተደረገ በዚህ ዓመትም በቀላሉ ሊሞሉ የሚገባቸውን መርጃ መሳሪያዎችን ባለማሟላት መምህራንንም እንደማይቀጥሉ እየነገሯቸውና በህፃናት ተማሪዎች ላይ ህገወጥ ተግባር እየሰሩ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ የሚችሉትን እያደረጉ እንደነበር ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ የተማሪው ወላጆች ትምህር ቤቱን ለመዝጋት ያቀረባችሁት ምክንያት ውሃ የማይቋጥር በመሆኑ ያለባችሁ ክፍተትና ጉድለቶችን በዝርዝር ንገሩንና እኛ ወላጆች ለልጆቻችን ስንል እናሟላለን ቢሉም የትምህርት ቤቱ ማናጀር ግን ትምህርት ቤቱ በ2014 ዓ.ም እንደማያስቀጥሉትና ለልጆቻቸው ትምህር ቤት እንዲፈልጉ አስረግጠው ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ ወላጅ፤ ተማሪዎችና መምህራን ህብረት ምንም እንኳን የሂሳብ እንቅስቃሴያቸውን መመልከት የሚመለከተው ባይሆንም ትምህርት ቤቱን ከሚዘጉበት ምክንያት አንዱ ገቢ ለመምህራን ደመወዝ መክፈል አይችልም የሚል በመሆኑ ከትምህርት ቤቱ ማናጀር ሙሉ መረጃውን ተቀብለን ገቢና ወጪያቸውን ተሰልቷል። ምንም እንኳን ትምህርት ቤቱ የተቋቋመው ለትርፍ ባይሆንም የመምህራኑንና የአስተዳደር ሠራተኞችን ደመወዝ ሸፍኖ ትርፍ እንዳለውም ከማናጀሯ ጋር መተማመን ላይ ደርሰናል ይላሉ።
ስለዚህ ይላሉ ወላጆች፤ የክፍለ ከተማው ትምህርት ፅህፈት ቤት የምንጠይቀው ነገር ቢኖር ልጆቻቸውን ካስተማሩ በኋላ የኢትዮጵያን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው አፈናቅለው በነፃ ያገኙትን መሬት ለሌላ ንግድ ለማዋል መፈለጋቸውን ተረድተናል። ይህ ደግሞ ‹‹ያጎረሳቸውን እጅ ነካሽ›› መሆናቸውን በግልፅ ያሳዩበት ውሳኔ በ11/07/2013 ዓ.ም በቀጣይ ትምህርት ቤቱን እንደሚዘጉትና በሚቀጥለው ዓመት ምዝገባ እንደማያካሂዱ ለእያንዳንዱ ወላጅ በደብዳቤ በተማሪው እጅ ልከውለታል። ስለዚህ የክፍለ ከተማው ትምህርት ፅህፈት ቤት ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶት ጉዳዩን በህግ አግባብ እንዲያየው እና በ2014 ዓ.ም የመማር ማስተማሩ እንዲቀጥልም የቦርድ አባላቱንና ወላጆች በጋራ አነጋግራችሁ ቀጣይ እርምጃዎችን እንዲወሰድ በትህትና እንጠይቃለን ሲል በግልባጭ ለአዲስ አበባ ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ አሳውቆ ነበር።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እና መመህራንም በበኩላቸው፤ በተደጋጋሚ ጊዜ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ተቋሙን ለመታደግ ጥረት መደረጉን ያስታውሳሉ። ይሁንና ግን ጉንጭ አልፋ ክርክሮችና መመላለሶች በስተቀር ትምህርት ቤቱን ከመዘጋት መምህራንና ተማሪዎቹን ከመበተን አለመታደጉን የሚናገሩት። ከዚህም በተጨማሪ ምክንያቶችን መፍጠርና የአገልግሎት ጭማሪ ክፍያ እየጠየቀ ወላጆችና ተማሪዎችን ማስጨነቁን ያስታውሳሉ።
ከመንግስት ጋር እሰጥ-አገባ
በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ አግባብነት ሬጉላቶሪ ፅህፈት ቤት በ15/08/2011 ዓ.ም ለአርመን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ‹‹ጉዳዩ፦ለ2012 ዓ.ም የአገልግሎት ጭማሪ ክፍያ አለማድረግ ይመለከታል›› በሚል በፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ተቋማት የትምህርት አገልግሎት አሰጣጥ እና ክፍያ ስርዓት መመሪያ ቁጥር 1/2007 በቁጥር አ1-1/989/አ28-40/49 በ20/12/0 ተግባራዊ እንዲሆን አሳውቆናል። በዚህ መሰረት የግል ተቋም የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ ሲፈልግ እውቅና ፈቃድ ለሰጠው አካል እና በሥሩ ለተዋቀረው ወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት (ወመህ) ከመጋቢት 1-15 ባሉት ቀናት የጭማሪውን አስፈላጊት እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ፕሮፖዛል ማቅረብ ይጠበቅበታል።
ሆኖም ግን ትምህርት ቤቱ በመመሪያው አንቀጽ 9 ንዐስ አንቀፅ 9.1 እስከ ንዐስ አንቀጽ 9.7 በቅደም ተከተል መሰረት ተግባራዊ ባለማድረጉ በቀጣይ ዓመት በ2012 የትምህርት ዘመን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ለውጥ እንደማያደርግ- እያሳወቅን ትምህርት ቤቱ በራሱ ፈቃድ የጭማሬ ለውጥ ካደረገ በመመሪያው አንቀጽ 22 በንዑስ አንቀጽ 22.4 መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን እናሳስባለን ሲል በግልባጭ ለአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እና ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ጽህፈት ቤት አሳውቋል።
አራዳ ክፍለ ከተማ
በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ፅህፈት ቤት በ25/07/ 2011 ዓ.ም ጉዳዩ፡- የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ የመመሪያና ደንብ ጥሰትን እንዲስተካከል ማሳሰብ ይሆናል በሚል የፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግል የትምህርት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ስርዓት ደንብና መመሪያ ቁጥር 1/2007 ሐምሌ 30/2007 የጸደቀውን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በቁጥር አ/ገ/878/አ28-40/11ተግባራዊ እንዲሆን ማሳወቁ ይታወሳል።
በዚህ መሰረት ትምህርት ቤቱ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ መመሪያና ደንብ ቁጥር 1/2007 አንቀጽ 9 በመተላለፍ በወላጆች ላይ አላስፈላጊና ወቅቱን ያልጠበቀ እና ምርጫ በማሳጣት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ማድረጉን በተደረገው ድጋፍና ክትትል በመረጋጋጡ ትምህርት ቤት እስከ መጋቢት 16/2011 ዓ.ም ድረስ የጨመረውን ጭማሪ ለወላጆች ተመላሽ በማድረግ በጽሁፍ ለጽህፈት ቤቱ እና በሥሩ ላደራጀው ወላጆች፣ ተማሪና መምህራን ህብረት ሪፖርት ካላሳወቀን በመመሪያ አንቀጽ 22 በንዑስ አንቀፅ 22.4 ተግባራዊ እንደሚሆን እናሳስባለን ይላል።
የትምህርት ቤቱ ምላሽ
የኮቭሮኮፍ አርመኒያ ትምህር ቤት የወላጆች፣ የክፍለ ከተማው ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤዎችና ተማፅኖዎችን ከቁብ የቆጠራቸው አይመስልም። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ አብነት ማንሳት ተገቢ ነው።
በኢትዮጵያ የአርመን ህዝብ ማህበር መሪ ጉባዔ በሚል ሚያዚያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ለአራዳ ክፍለ ከተማ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደብዳቤ የፃፈ ሲሆን ጉዳዩ፦ ‹‹በትምህርት ሥራ አገልግሎታችን ላይ የገጠመንን ችግር ስለማሳወቅ›› በሚል ይጀምራል።
ኬቮርኮ አርመኒያን ትምህርት ቤታችን በአገሪቱ የትምህርት ሥራ ለረዥም ዓመታት ራሱ ባስገነባውና የትምህርት ሥራውን ደረጃም ሆነ ጥራት በጠበቀ የትምህር ቤት ሕንፃ ውስጥ አገልግሎቱን ሲሰጥ እንደነበር ይታወሳል። ይሁንና የደርግ መንግሥት ያለአግባብ የትምህርት ቤታችንን ሕንፃ ወስዶ በጊዜው ለትምህርት ሥራ አገልግሎት ባልተገነባ ደሳሳ ቤቶች ውስጥ ተማሪዎቹን በማዛወር የትምህርት ሥራ እና ጥራቱን በከፍተኛ ደረጃ በሚጎዳ ሁኔታ ኮሚኒቲያችን ያለአግባብ የትምህርት ሥራውን እንዲሠራ ጫና ተፈጥሮበታል።
በዚህም ምክንያት በየጊዜው ትምህርት ቤቱ ተገቢውን የትምህርት ደረጃና ጥራት አያሟላም እየተባለ በተለያየ ጊዜ ከሬጉላቶሪ ቢሮ በሚሰጥ አስተዳደራዊ ውሳኔ መነሻ ትምህርት ቤቱ ሲያከናውነው የነበረውን የመዕዋለ ሕፃናት (KG) አልግሎታችን እንዲዘጋ ግድ ሆኗል። /KG/ እንዲቀጥል ለማድረግ ሲባል ለእድሳትና ጥገና ያወጣነው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲሁ ባክኖ ቀርቷል።
አሁን ደግሞ ያለው የ1ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ተገቢውን ግብዓት አላሟላም ተብሎ ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እንማይቀጥል ማስጠንቀቂያ የደረሰን በመሆኑ ይህንኑ ተከትለን ችግሩ የትምህርት ሥራውን ለመቀጠል የማያስችል እንደሆነ ግምት በመውሰድ ወላጆች ለልጆቻቸው ከወዲሁ ትምህር ቤት ይፈልጉ ዘንድ እና በኋላም ትምህር ቤቱ በሬጉላቶሪው ማሳሰቢያ መሠረት ቢዘጋ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ማሳሰቢያ በመስጠታችን ትምህር ቤቱን ያለአግባብ ለመዝጋት እንደተነሳን በማስመሰል በአንዳንድ ወላጆች በተነሳው ቅሬታ መነሻ ተደጋጋሚ መፃፃፎችና በመጨረሻም የትምህርት ቤቱን ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፈዎች በተገኙበት ስብሰባ ተደርጎ በችግሩ ላይ ግንዛቤ እንዲወሰድ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።
በመሠረቱም ይላል፤ ተማሪዎቹ የሚማሩበት ክፍሎች ደረጃቸውን ያልጠበቁና ጠባብና በቂ መራወጫና መንቀሳቀሻ የሌላቸው መሆኑ፤ ክፍሎቹ ቀድሞው ለትምህርት ሥራና አገልግሎት ተብለው ያልተገነቡ መሆናቸው፣ ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ እንቅስቃሴና ስፖርታዊ ጨዋታ የሚያገለግል ሜዳ የሌለው መሆኑ፣ ሌላው ቀርቶ ተማሪዎቹ ምግብ የሚመገቡበት ክፍል ባለመኖሩ በክፍል እጥረት ምክንያትም መመገቢያ ቤት መፍጠርም ሆነ ማዘጋጀት ባለመቻሉ ለዓመታት በክለቡ ይዞታ ላይ ድንኳን በመትከል አገልግሎት መስጠት ከልጆቹ ደህንነትም ሆነ ከክለቡ የይዞታ መብት ጋር ምቹ ባለመሆኑ፣ ትምህርት ቤቱ ራሱን የቻለ የላብራቶሪ እና የቤተመጽሀፍ ክፍል ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ያልተሠራለትና የሌለው መሆኑ፣ የአርመኒያ ኮሚኒቲ ክለብ ራሱን የቻለ ግቢና ይዞታ ያለው ሲሆን፤ ከትምህርት ቤቱ መግቢያ ጋር ተመሳሳይ በር መጠቀሙ በተለይም የይዞታ መደበላለቅ ማስከተሉና ራሱን ችሎ በሚተዳደረው ክለብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከተለ መሆኑ የትምህር ቤቱ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው።
የእነዚህ ችግሮች መፈጠር በትምህርት ሥራው ላይ ከፍተኛ የሆነ የጥራት ችግር አስከትሏል። እነኝህን ችግሮች መሠረታዊ በሆነ ደረጃ መፍትሔ ካልተሰጠ በስተቀር የትምህርት ጥራቱን ችግር ላይ በመጣል በሕፃናቱ የወደፊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ማድረስ የሚችልና በቀላሉ የማይታይ ክፍተት መሆኑን ወላጆችም ሆነ አስተዳደሩ ግንዛቤ ሊወስዱበት የሚገባ በመሆኑ የተፋጠነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ይጠይቃል።
ስለሆነም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የትምህርት ሥራውንም በጥራት ለማስቀጠል እንዲቻል ቀደም ሲል ያለአግባብ የተወሰደብን ትምህርት ቤታችን ሕንፃ እንዲመለስልን በትህትና እንጠይቃለን። ጉዳዩ ጎን ለጎን ይታያል ከተባለም ትምህርት ቤቱ የራሱ በር ለብቻ እንዲከፈትለትና ከክለቡ ይዞታ ጋር ባልተቀላቀለ ሁኔታ የትምህርት ሥራውን መቀጠል እንድንችል ከሬጉላቶሪው ቢሮ በተፋጠነ መመሪያ እንዲሰጠን ይደረግልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ሲል የጠየቀውና በግልባጭ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን እና ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር ትምህርትና ስልጠና ጽህፈት ቤት በግልባጭ ያሳወቀው።
የትምህርት ቤቱ ወቀሳ
ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማሩን ሥራ ያቆመው ከላይ ባቀረባቸውና በሚላቸው ምክንያቶች ሳይሆን እውነታዎቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ሐምሌ 05 ቀን 2014 ዓ.ም ለአዲስ አበበባ ከተማ አስተዳደር ትምህር ቢሮ በፃፈው ደብዳቤ እንደሚከተሉት ቀርበዋል።
አንደኛ አርመን ትምህር ቤት በካርታ ቁጥር አ/11/32/5192/00/00 በ06/10/2004 ዓ.ም በወጣው ካርታ ስፋቱ 1844 የሆነበትን የአርመን ህዝብ ማህበር ትምህር ቤት በሚል ለአርመን ህዝብ ማህበረሰብ የትምህርት አገልግሎት እንዲያገለግል ከመንግስት በነጻ ለትምህርት የተሰጠ በመሆኑ፤
ሁለተኛ የትምህር ቤቱን ግቢ 1844 ካ.ሜ የነበረውን ለሌላ የንግድ ስራ ለምሳሌ የምግብ ቤት፤ የመጠጥ ቤት፣ ቤተ መፅሃፍት የነበረውን ዘግተው ለሚከራይ አዳራሽ ማድረጋቸው፤ ከዚህ በፊት የትምህርት አገልግሎት መሥጫ ክፍሎች በመዝጋት ከትምህርት ውጭ ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል ሆን ብሎ በተደራጀ መልኩ የተቋሙ ጥራት እንዲወድቅ ማድረጋቸው፣
ሦስተኛ በትምህር ቤቱ በጣም ጠንካራና የትምህርት ባለሙያዎች የሆኑ የወላጅ ተማሪዎች መምህራን ህብረት አመራር አባላትና አጠቃላይ ወላጆች የትምህርት ቤቱን ክፍተት ሞልተው ለማስቀጠል ፈቃደኛ መሆናቸው እየታወቀ እንዲዘጋ መፈለጋቸው፣
በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቋሙ ጥራት በማጓዳል ሆን ብሎ እንዲዘጋ እያደረገ በመሆኑ መንግስት የአርመንን ትምህርት ቤት የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ለወላጆች ጥያቄና መንግስት ለትምህርት የሰጠውን ቦታ ለሌላ እንዳይውል በማሰብ እንዲቆይ ተደርጓል። ይሁንና ባለስልጣን መስሪያቤቱ ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር የትምህርት ጥራቱ ችግር ላይ የወደቀ በመሆኑ
በ20/10/2014 ዓ.ም በቁጥር አ/ቀ./6891/መ.26/14 በተፃፈ ደብዳቤ የተዘጋ መሆኑን እያሳወቅን የከተማው አስተዳደር ለትምህርት አገልግሉት መገልገያ የሰጠውን ቦታ ለሆቴልና ለመጠጥ እንዳይውል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ተረክቦ ዜጎች ትምህርት እንዲያገኙበት እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
የተሰረዘው ፈቃድ
በ20/10/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለኬቮር ኮፍ አርመን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ጉዳዩ፡- እውቅና ፈቃዳችሁ የተሰረዘ መሆኑን ስለማሳወቅ በሚለው ደብዳቤው፤
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በከተማ አስተዳደሩ አዋጅ 74/2014 በተቀመጠው መሠረት የአራዳና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የትምህርትና ስልጠና ተቋማት እውቅና ፈቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት በአራዳ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ሥር የሚገኙ የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ፣ የሁለተኛና መሰናዶ የትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ከአገሪቱና ከከተማ አስተዳደሩ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍላጎትና አግባብነት ካላቸው ሥርዓተ ትምህርት፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር መገናዘባቸውን ያረጋግጣል።
እንዲሁም የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት የተቀመጠውን የትምህርት ስታንዳርድ፣ የትምህርት አገልግሎት አሰጣጥ መስፈርት ማሟላታቸውን፣ ጥራቱና ደረጃውን ጠብቀው መፈፀማቸውን ያረጋግጣል። በመሆኑም በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 በቤት ቁጥር 726 የሚገኘው ለኬቮር ኮፍ አርመን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ለ2013 የትምህርት ዘመን እውቅና ፈቃድ እድሳት ምዘና ተደርጎለት 46 ነጥብ 28 ውጤት በማምጣቱ በማስጠንቀቂያ የቀጠለና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ባለስልጣን በቁጥር የት/ስ/ት/ሙ/ብ/ም/ግ/ባ/አ.ም 1.2/8523/ በ10/9/2013 ለተቋሙ ደብዳቤ ጽፏል።
በተፃፈው ደብዳቤ ተቋሙ በ2012 ዓ.ም የእውቅና ፈቃድ እድሳት ለማካሄድ ምዘና በማካሄድ በኮቪድ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱ ለአንድ ዓመት በማስጠንቀቂያ እንዲቆይ መደረጉንና ተቋሙም ይህንን ምክንያት በማድረግ ትምህርት ቤቱ የሚዘጋ መሆኑን ለወላጅ ያሳወቀ ቢሆንም ወላጆች ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የወላጆቹን ጥያቄ በመረዳት እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ቢሆንም ከመንግስት ጎን በመቆም ያሉትን ተማሪዎች በመማር ማስተማር ስራው በማስቀጠል በትምህርት ዘርፉ ድርሻችሁን እንድትወጡ በማሳሰብ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱም የመማር ማስተማር ስራውን የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉ ይላል።
በደብዳቤ መሰረትም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱም ተቋማችሁን ተቀብሎ ለ2014 የትምህርት ዘመን ያስቀጠለ ሲሆን ለ2015 የትምህርት ዘመንም ባቀረባችሁት የእውቅና ፈቃድ እድሳት ጥያቄ መሰረት ተቋማችሁ በ23/07/2014 ዓ.ም በባለሙያዎች የመጀመሪያ ዙር ምዘና ተደርጎለት 51.86% ውጤት አምጥቷል። ለ2ኛ ዙር ምዘና በወጣው ፕሮግራም መሰረት በ02/10/2014 ዓ.ም በድጋሚ በተደረገለት ምዘና ምንም ዓይነት መሻሻል ሳያሳይ 51.86% ውጤት በማምጣት ዝቅተኛ የማለፊያ ነጥቡን 75% ማሟላት አልቻለም።
በመሆኑም ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ እውቅና ፈቃዱ የተሰረዘ መሆኑን እያሳወቅን ለ2015 ትምህርት ዘመን ምንም ዓይነት የተማሪ ምዝገባ እንዳይካሄድና ለተማሪ ወላጆች፣ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ለትምህር ቤቱ ወላጅ፣ተማሪና መምህራን ህብረት አባላት ከወዲሁ እንድታሳውቁ እና የ2014 ትምህርት ዘመን ሲጠናቀቅ ማንኛውም የትምህርት ተቋም ሲዘጋ ፈቃድ ለሰጠው አካል ማስረከብ ያለበትን መረጃዎች በመመሪያው መሰረት ተቋሙ ፈቃድ ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥበት የነበሩ ማህተሞች፣ የተማሪ መረጃዎችና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን እንድታስረክቡን እናሳስባለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚደርሰው የወላጅና የተማሪ እንግልት ተጠያቂ መሆናችሁን በጥብቅ እናሳውቃለን።
በግልባጩም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ለትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ አራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ለወረዳ 06 ትምህርት ፅህፈት ቤት፣ ለንግድ ጽህፈት ቤት፣ ለወረዳ 06 ንግድ ጽህፈት ቤትና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል።
አሁን ትምህር ቤቱን ማን እያስተዳደረው ነው?
ለትምህርት ቤቱ ወላጅ፣ ተማሪና መምህራን ህብረት አሁንም ግልጽ ያልሆነው አሁናዊ የትምህር ቤቱ ገጽታና ባለቤት አልባ መሆኑ ነው። ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቅሬታቸውን የገለፁት ወላጆች እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የኮቭሮኮፍ አርመኒያ ትምህርት ቤት ባለቤት አልባ ሆኗል። ትምህርት ቤቱ ከአጠገቡ የባህላዊና ዘመናዊ አልኮል መጠጦች እየተሸጡበት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተቋማት ቁመና ከማጣቱም በላይ ምንም ጥቅም እየሰጠ አይደለም። ይልቁንም ትምህር ቤቱን ከማፍረስ ሌላ የቢዝነስ ማዕከል ወይንም ህንፃ ለመገንባት ፍላጎት መኖሩን የሚናገሩ አሉ። ጉዳዩንም በመከታተል ላይ ነን ይላሉ። በሂደትም ወደ ንግድ ተቋም ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራት በህቡዕ እየተከናወኑ ነው ብለው ያምናሉ።
ቀድሞ ሥም እና ዝናው ገንኖ የነበረው ትምህርት ቤት ዛሬ ባለቤት አልባ መሆኑም እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ። ከወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ለክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ደብዳቤዎችን በማስገባት አቤት ያሉ ቢሆንም ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› መባሉ ክፉኛ አሳዝኖናል ይላሉ። በመሆኑም አሁንም ቢሆን ትኩረት ተሰጥቶ ወደ መማር ማስተማሩ እንዲመለስ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት
አርመኒያ ትምህርት ቤት በተመለከተ ቀጣዩ እጣ ፋንታ ምንድነው፤ ተረክቦ ማስተዳደር ያለበት አካልስ ምን እርምጃዎችን ወሰደ የሚሉትንና ሌሎችን ጉዳዮች ይዘን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት እንናግራለን። ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ፣ መረጃ ያለው ማንኛውም የሚመለከተው አካል ለሚያቀርባቸው መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ለማስተናገድ ዝግጁ ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015