“ባለ ትዳርና የመንግስት ሠራተኛ ነኝ። ልጅ የወለድኩት የመውለጃ ጊዜዬ ሊያልፍ በተቃረበበት ወቅት ነው። ሰው ባይረዳኝም ዘግይቼ የወለድኩበት የራሴ ምክንያት ነበረኝ” ሲሉ የእናትነት ተሞክሯቸውን ያካፈሉን ወይዘሮ ሣራ ገብረማርያም ናቸው። ወይዘሮዋ እንደሚናገሩት ዘግይተው የወለዱበት ምክንያት ብዙ ነው። በወቅቱ የወሊድ ፈቃድ በቂ የነበረ አለመሆኑ የመጀመሪያው ሲሆን ከ40 ባልበለጠ ቀናት ውስጥ ዘጠኝ ወር ሙሉ ተሸክመውት የቆዩትንና በጭንቅ ምጥ የተገላገሉትን ጨቅላ ህፃን ልጃቸውን ጥለው ወደ ሥራ ለመመለስ ይገደዱ ነበር።
በዚህ የወሊድ ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሥራ ገበታቸው የተመለሱ ብዙ እናቶች እንዳጋጠሙዋቸው ወይዘሮ ሣራ ይናገራሉ። የጡታቸው ወተት እየፈሰሰ ሲቸገሩ የነበሩ እናቶችም በተደጋጋሚ አጋጥመዋቸዋል። እናቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ስለሚገደዱም ህጻናቱን ለሰራተኞች ለመተው ይገደዳሉ። ህፃኑን የተውላቸው ሠራተኞችም ይሁኑ ቤተሰቦች እንደራሳቸው የእናትነት ፍቅር እየሰጡ ሊንከባከቡና ሊጠብቋቸው ባለመቻላቸው ቅሬታ ሲሰማቸው ታዝበዋል።
በተለይ ህፃን ልጆቻቸውን ለሰራተኛ ትተው ወደ ሥራ ገበታቸው የተመለሱ እናቶች ልጆቻቸው በመውደቅና በተለያየ ምክንያት ለጉዳት መዳረጋቸውን በፀፀት ሲናገሩ አድምጠዋል። ጓደኛቸው “ልጄን የአእምሮ ዝግመት የያዘው ሰራተኛዬ በሁለት ወሩ ጥላብኝ ነው” ስትል የነገረቻቸውን ለአብነት ያነሳሉ። እሳቸው ሳይወልዱ የዘገዩበት ምክንያት ይሄን ዓይነቱን ችግር ከመፍራት የዘለለ አልነበረም። ከወለዱ ጀምሮ ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ድረስ ለልጃቸው ጡታቸውን ከማጥባት ጋር የእናትነት ፍቅር በመስጠት መንከባከብ መፈለጋቸው ሌላው ምክንያታቸው ነበር። 40 ቀን የወሊድ ፈቃዳቸው ሲያልቅ ያልጠነከረ ልጃቸውን ጨክነው ጥለው ወደ ሥራ ለመመለስ የሚደፍር አንጀት ያላቸው ባለመሆኑ ለመውለድ ዘግይተዋል።
ሌላዋ የወሊድ ፈቃድ ተሞክሮዋን ያካፈለችን የ24 ዓመቷ ወጣት እናት ስንዱ አየነው ትባላለች። ስንዱ እንደነገረችን የመጀመሪያ ልጇን የወለደቻት የዛሬ ሰባት ዓመት ነው። ያኔ ትሰራ የነበረው በአንድ የግል ድርጅት ነበር። የድርጅቱ ባለቤት ወደ ሥራዋ እንድትመለስ ይፈልግና በስልክም ይጨቀጭቃት ስለነበረ 40ውን ቀንም በመከራ ነው የቆየችው። በዚህ ላይ እሷ ወደ ሥራ ስትመለስ ልጇን የሚይዝላት ሰው አልነበራትም ። ወላጅ አልባ በመሆኗና እጓለ ማውታ በማደጓ ዘመድ አልነበራትም። ልጇን የሚጠብቅላት ሰራተኛ እንዳትቀጥር ደሞዟ ለቀለቧና ለልጇ ሳሙናም አይበቃም።
አጋጣሚ ሆኖ ልክ ወደ ሥራ መመለሻዋ ዕለት ልጇ ክፉኛ ታመመ። ሆስፒታል ይዛው ሄደች። ስላልተሻለው በማግስቱ ቀረች። በሦስተኛው ቀን ልጄ ስለታመመብኝ ፈቃድ ይሰጠኝ ብላ ወደ ሥራ ቦታዋ ስትሄድ በእሷ ቦታ ሌላ ሰው ተተክቶ አገኘች። ምነው ወደ ሥራዬ መልሱኝ ብትል አሰሪዋ የተሰጠሽን ፈቃድ እንደጨረሽ ሥራ ገበታሽ ላይ ባለመገኘትሽ ሌላ ሰው ስለቀጠርን ልንመልስሽ አንችልም አላት።
ጋዜጠኛና ደራሲ ሮዝ መስቲካ የነዚህን ተሞክሯቸውን ያካፈሉንንና የሌሎቹን ወላድ ሠራተኛ እናቶች ጽዋ በመጠኑም ቢሆን ቀምሳ አይታዋለች። ሮዝ ሦስተኛ ልጇን ወልዳ እያጠባች ባለችበት ወቅት የቀመሰችው ጽዋ ከብዙ ወላድ እናቶች ገጠመኝ ጋር በአእምሮዋ ሲብሰለሰል በመቆየቱ እረፍት አሳጣት። ሠራተኛ እናቶች በሚወልዱበት ወቅት የሚሰጣቸው የወሊድ ፈቃድ ጨቅላ ልጆቻቸውን በተገቢ ሁኔታ እንዲንከባከቡና እንዲያጠቡ የሚያስችል አለመሆኑን እንደ ሌሎቹ የጾታ አጋሮቿ በዝምታ ልታልፈው አልወደደችም። ሮዝ ዕድለኛ ሆና አማራጭ ስላላት ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው ሥራ ልትዛወር ብትችልም ይሄን ማድረግ ያስገደዳት ሁኔታ የተሰጣት የወሊድ ፈቃድ በማነሱ መሆኑ የሌሎች ሴቶች ችግር የበለጠ እንዲሰማት አደረጋት። ሁኔታቸው ከራሷ ጋር ተዳምሮ መላ እንድትላቸው ቆሰቆሳት።
እናም ሮዝ መስቲካ ፈጥና ይሄን ድምፅ ለማሰማት ሦስተኛ ልጇን እያጠባች የወሊድ ፈቃድ ዘመቻን መሰረተች። የወሊድ ፈቃድ ስድስት ወር እንዲሆን የሚጠይቀውን ዘመቻ የጀመረችው በኦንላይ ሲሆን የወሊድ ፈቃዱ አሁን ላይ በቂ ባለመሆኑ ይጨመር የሚሉ ተከታዮቿ ቁጥር ከ10ሺህ በላይ ደርሷል።
‹‹ህፃናት የጨቅላነት ጊዚያቸውን ጨምሮ እስከ ስድስት ወራቸው በእናታቸው ጉያ ውስጥ ሆነው ነው ማሳለፍ ያለባቸው›› የምትለው ሮዝ ብዙ ሰራተኛ እናቶች ይሄን ዕድል ባለማግኘታቸው የተሰጠቻቸውን አጭር የወሊድ ፈቃድ ጨርሰው ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ሲቸገሩ የነበረበት ሁኔታ መኖሩን ታስታውሳለች። የወሊድ ፈቃዱ አጭር በመሆኑ ልጆቻቸውን የእናትነት ፍቅር እያጋሩ መቆየት ቀርቶ ጡት ማጥባት እንኳን አለመቻል፣ ወደ ሥራ በሚመለሱበት ወቅት ልጆቻቸውን የሚይዝላቸው ሰው ማጣት፤ ሰራተኛ የመቅጠር አቅም ማነስ፤ ሰራተኛ የመቅጠር አቅም ያላቸው ቢኖሩም አንዳንድ ሠራተኞች ለልጅ አያያዝ የሚመቹ አለመሆናቸውና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።
ከዚህ አኳያም ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ለሰው አሲዘው ወደ ሥራ ለመመለስ ደስተኛ ያለመሆናቸው ከችግሮቹ እንደሚጠቀሱ ታሰምርበታለች። እናቶች ወደ ሥራ ሲመለሱ ለሰራተኞች የሰጧቸው ህፃናት ልጆቻቸው የአካል ጉዳተኛ ይሆናሉ። የከፋ የስነ ልቦና ችግርም ይገጥማቸዋል። ጉዳቱ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ይተርፋል። ያኔ የወሊድ ፈቃድ እንደ ዛሬው አራት ወር ቢሆንና እሷም በወለደችበት ወቅት ይሄን ያህል በተለይም ልጇን ምግብ ማስጀመር እስከምትችልበት ስድስት ወር ቤቷ ውስጥ ከልጇ ጋር ቆይታ ቢሆን፤ እንዲሁም የህፃናት ማቆያ በየመሥሪያ ቤቱ ቢኖር ወደ ሥራዋ ገብታ ተመልሳ ለመሥሪያ ቤቷ አስተዋጽኦ ታደርግ እንደነበር ታነሳለች። ለራሷም የገንዘብ አቅሟን ታሳድጋለች። የወሊድ ፈቃድ በቂ ባለመሆኑና የህፃናት ማቆያ በየመሥሪያ ቤቱ ባለመኖሩ ኑሮ የከበዳቸው ወላድ እናቶች አማራጭ ስለሌላቸው ልጆቻቸው ላይ ጨክነው ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ። የባሰባቸው እናቶች ደግሞ ስራቸውን በመልቀቅ እቤታቸው ቁጭ ብለው ልጆቻቸውን ማሳደግ ይመርጣሉ።
ሮዝ እንደምትናገረው የስድስት ወር የወሊድ ፈቃድ ዘመቻውን የጀመረችው ይሄን ሁሉ ታሳቢ አድርጋ ነበር። በእርግጥ ጥረቷ ውጤት አፍርቶ 40 ቀናት የነበረው የወሊድ ፍቃድ ወደ አራት ወራት እንዲያድግ በመንግስት ተወስኗል። ያኔ ታዲያ ብዙ ደጋፊዎች የማግኘቷን ያህል ሴቶችን ስራ ፈት፤ ሀገሪቱን ደግሞ ደሃ ለማድረግ ነው በማለት ዘመቻዋን የተቃወሟት አሉ። ‹‹አንቺ ይሄን እንዴት ልታስቢ ቻልሽ›› ያሏትም ነበሩ። የዘመቻው መስራች ጋዜጠኛ እንደመሆኗ የወሊድ ፈቃዱ በቂ ባለመሆኑ እሷንና ሌሎች ሰራተኞችን በተጨባጭ የገጠማቸውን ከማስረዳት በዘለለ የሴቶች ጉዳይ የሀገር ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ስትሞግት ቆይታለች።
ምክንያቱም እናት በምትወልደው ልጅ ሀገር እየገነባች ትውልድ እየቀረጸች ነው። እንዲያውም ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያየ መልኩ በሀገሪቱ ላይ የተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭትና መናቆር፤ በዚሁ ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወትና የወደመው ንብረት መንስኤው የቢሮ ሠራተኛ እናቶች በቂ የወሊድ ፈቃድ አግኝተው ልጆቻቸውን በመልካም ስብዕና ማሳደግ ባለመቻላቸው የተነሳ መሆኑን ጋዜጠኛ ሮዝ ትሞግታለች። በዋነኛነት እናቶች በቂ ፈቃድ ሳያገኙ ወደ ስራቸው በመመለሳቸው ለህፃናት ጤናማ ዕድገት ወሳኝና መሰረታዊ የሆነውን ተፈጥሯዊውን የጡት ማጥባት ሂደት ማሳካት አለመቻላቸውን በማንሳት የዘመቻውን መነሻ ትጠቅሳለች።
ሮዝ የወሊድ ፈቃድ እንዲራዘምና እናቶች በበቂ ሁኔታ ልጆቻቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የጀመረችው ዘመቻ ተቀባይነት አግኝቶ መንግስት የወሊድ ፈቃድን ለመንግስት፤ ለግል ሰራተኞች እያለ ደረጃ በደረጃ በማሻሻል ወደ አራት ወር ሊያደርሰው በቃ። በሚገርም ሁኔታም እነ ሮዝን ፈትኗቸው የነበረውን ችግር በየፈርጁ ለመፍታት በየተቋማቱ የህፃናት ማቆያዎች በስፋት ማቋቋም ጀመረ። በየጤና ተቋማቱም የእናት ጡት ለነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናት ጤናማ ዕድገት ያለውን ጠቀሜታ ከመስበክና እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ከማበረታታት ጀምሮ ብዙ ዘመቻውን የሚያጎሉ እርምጃዎችን ወሰደ።
እቤቷ ሆና ሦስተኛ ልጇን እያጠባች በዚህ መልኩ ስኬት ያገኘውን የወሊድ ፈቃድ የጀመረችው ሮዝ በኑሯቸው ምክንያት ከሥራቸው መቅረት ለማይችሉ ሴቶች፤ እንዲሁም የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆኑ ህፃናት መልካም ዕድገት የምታደርገውን ጥረት በዘመቻው ብቻ አልገታችውም። ጨቅላ ልጄን ጨክኜ ጥዬ ወደ ሥራ ገበታዬ አልመለስም በማለት ጨቅላ ልጇን በጡቷ ተንከባክባ እያሳደገች ሁለት መጽሐፍት ከመፃፍ ባሻገር የዛሬ አምስት ዓመት ምቾት የተሰኘውንና አሁን ላይ ወደ ምቾት መልቲ ሚዲያ ወደ መሰኘት የሰፋውን የሬዲዮ ፕሮግራም አቋቋመች። መሰረቱን እናት በምትጥለው ቤተሰብ ዙሪያ በማድረግ ሰርክ ቅዳሜ ግንዛቤ ማስጨበጡን ተያያዘችው። በፕሮግራሙ ስለ እናት ጡት ጠቀሜታ በሰፊው ይወራበታል። እናቶች ከወሊድ ፈቃድ ጋር በተያያዙ ህጎች፤ ፖሊሲዎችና ሌሎች ከመብቶቻቸው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሲያነሱ ምላሽ ይሰጥባቸዋል። አቅጣጫ ይመለከትባቸዋል። መፍትሄም ይጠቆምባቸዋል።
ከገንዘብ በላይ ስለሆነው እናትነት ‹‹እኛ እናቶች ጡረታችንን እያሰብን ነው። ለጡረታችን እየሰራን ነው ብዬ ነው የማስበው›› የምትለው ሮዝ የዛሬ ሦስት ዓመት አራተኛ ልጇ ወደ ህፃናት ማቆያ ስትገባ እሷ ወደ ሥራዋ መመለሷንም አውግታናለች። ሮዝ ለቤተሰብ ብሎም ለሀገር ግንባታ መሰረት በሆኑት እናቶች ጉዳይ ዛሬም ያገባኛል ብላ ከመሥራት አልተቆጠበችም። አሁን ላይም መንግስት የወሊድን ፈቃድ ከአራት ወደ ስድስት ወር እንዲያሳድግና የመንግስት ሰራተኛ እናቶች ልጆቻቸውን ከስድስት ወር በኋላ ምግብ አስጀምረው ወደ ሥራቸው በሚመለሱበት ሁኔታ በዘመቻው ሙግቷን ቀጥላለች። ጎን ለጎንም አባቶች በልጆች ጉዳይ እናቶችን እንዲያግዙ በቂ የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚያስችለውን ዘመቻ ለመጀመር እንቅስቃሴም እያደረገች ትገኛለች።
እናት መደገፍ አለባት። በተለይ የኢኮኖሚው ሁኔታ ፈታኝ በሆነበት ጊዜ የአራት ወሩን ፈቃድ ማግኘቷ ተረጋግታ ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ጡቷን በማጥባት ከእህል አገናኝታ ወደ ሥራ ለመመለስ ያስችላታል የምትለው ሮዝ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ልጅ ወልዶ ለማሳደግ አጋዥ ቤተሰቦችንም ማጣት ፈተና እንደመሆኑ ለአባቶች በቂ የወሊድ ፈቃድ መሰጠቱ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብላ እንደምታምንም ትናገራለች። ፍቃዱ አባቶች እናት ከምግብ አገናኝታ ወደ ሥራዋ ስትመለስ ለሚያግዙበት ሂደት ይጠቅማል። ወገቧን አጎንብሳ ዳይፐር የምትቀይርበትን ድርሻ ከመውሰድ ጀምሮ ጉልበት ነክ ነገሮችን ፤ማጣጠቡንና ጡጦውን እንዲያግዙ ያስችላልም ትላለች።
እናት ጡት ለማጥባት በቂ ጊዜ ማግኘቷ ለሀገር የሚጠቅም ጥሩ ዜጋ ማፍራት ያስችላታል። ብዙ ሴቶችንም ሮዝ በዘመቻዋ እንዳሳካችው በጊዜ እንዲወልዱና በሥራና በእናትነት መካከል ያለውን ስጋት በመቅረፍ ይታደጋል። አባቶችም የሴቷን ጫና ለመቀነስ ፈቃዱን አግኝተው የድርሻቸውን ቢወጡ የተሻለ ቤተሰብ መመስረት ይቻላል። በመሆኑም ሮዝ የእናቶችን የወሊድ ፈቃድ ወደ ስድስት ወር ለማሳደግ እንዲሁም ለአባቶች ፈቃድ እንዲሰጥ የጀመረችው ትግል ለስኬት እንዲበቃ በመመኘት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015