ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ! ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ሳምንቱ ያለፈው በትምህርት ነበር እንዳላችሁ እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርት ነው። እናንተ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ እንደሆናችሁ አምናለሁ፡፡ ጎበዝ ተማሪ ትምህርቱን በአግባቡ ያጠናል፣ የቤት ስራውን ይሰራል እና የቤተሰብ ምክር ይሰማል። እናንተም እነዚህን ትግባራት ስለምታከናውኑ ጎበዝ ናችሁ።
ልጆች በልጅነታችሁ መሆን የምትፈልጉት ነገር ወደፊት ካደጋቹ በኋላ ለምትሆኑት ነገር ትልቅ መሰረት እንደሆነ ታውቃላችው? ብዙ ልጆች እኔ ሳድግ ፓይለት፣ ሣይንቲስት ፣ ፖሊስ፣ አስተማሪ፣ ወታደር እና የሌሎች ሙያዎች ባለቤት እሆናለሁ ሲሉ ትሰማላችሁ። እናንተም ስታደጉ መሆን የምትፈልጉት እና መስራት የምትፈልጉት ሙያ እንዳላችሁ እርግጠኛ ነኝ። መሆን የምትፈልጉትን ማወቃችሁ ለምን እንደሚጠቅማችሁ ልንገራችሁ፤ መሆን የሚፈልገውን የሚያውቅ ልጅ ወደፊት ሲያድግ መሆን የፈለገውን እንዲሆን ዛሬ ጠንክሮ ይማራል፤ ከሚፈልገው ነገር ጋር የሚያያዙ መፃህፍትን ያነባል እናንተም መሆን የምትፈልጉትን ስታውቁ የምትፈልጉት ነገር ጋር የሚያያዙ መፃህፍት ታነባላቹ በትምህርታቹም ጎበዝ ትሆናላችሁ።
ልጆች የምትመኙትና መሆን የምትፈልጉት ነገር ከሙያ ወይም ከስራ አንፃር ብቻ መሆን የለበትም። ጥሩ ስራ የሚሰሩና ለብዙ ሰው አርአያ የሚሆኑ ሰዎችን ስታዩ እናንተም ስታድጉ እንደዛ ሰው ለመሆን መመኘትና ጥሩ ስራ መስራት ካሁኑ መለማመድ አለባችሁ። ልጆችዬ ዛሬ በልጆች አምድ ይዤላችሁ የቀረብኩት ስታድግ ምን መሆን እንደምትፈልግ የምታውቀዋንና ካሁኑ እየተለማመደችያለችውን ህፃን በፀሎት ተከተልን ነው። በፀሎት የስድስት አመት ህፃን እና ‹‹የአርአያ ለትውልድ›› አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤት የመዋለ ህፃናት ተመራቂ ተማሪ ናት።
ልጆች በፀሎት ምን መሆን እንደምትፈልግ ታውቃላችው? አድጋ ትልቅ ስትሆን ሰው ስለሚረዳና በጎ ስራ ስለሚሰራ እንደ ዶክተር ቢንያም በለጠ መሆን ነው የምትፈልገው። ቢኒያም በለጠ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ያወቃችሁ ጎበዞች ናችሁ። ላላወቃችሁት ደግሞ በፀሎት ትነግራቹሃለች። በፀሎት ቢኒያም ማን ነው ብላችሁ ብትጠይቋት መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከል ያቋቋመውና ‹‹ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚለው ነው ብላ ትነግራቹሃለች።
በፀሎት የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት ያስደስታታል። ትምህርት ቤትም ጓደኞቿ ሲወድቁ ደግፋ ታነሳቸዋለች፣ ሲያለቅሱ ታባብላቸዋለች። ወደፊት አድጋ ቢኒያም ያስጀመራቸውን ሰው የመርዳት ስራዎች ለማስቀጠል ትፈልጋለች። ለዛ እንዲረዳት ደግሞ ከአሁኑ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን አንዱን ከአንዱ ሳትለይ በእኩል ዓይን በማየት ልትረዳቸው ትሞክራለች። ሁሉም ልጆችም ልክ እንደሷ ሁሉንም ሰው እኩል እንዲረዱ ልዩነት ሳያደርጉና ሳያዳሉ ለሁሉም እንዲደርሱ ትመክራለች።
በፀሎት ወደፊት ልክ እንደ ቢኒያም በለጠ የተቸገሩ አረጋዊያንን እና የአዕምሮ ህሙማንን እንዲሁም የተቸገሩ ህፃናትን መንከባከብ ፣መርዳትና የጎድላቸውን ማንኛውም ነገር በማሟላት ከጎናቸው መሆን ትልቁ ፍላጎቷ ነው። ቅርብ ጊዜም መቄዶኒያ ድረስ በመሄድ ከዶክተር ቢኒያም በለጠ ጋር በመሆን መቄዶኒያን ጎብኝታለች፤ መቄዶኒያ ዉሰጥ ያየቻቸው አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን “ያምራሉ ግን ያሳዝናሉ” ትላለች። የተሰማት የሀዘን ስሜት ፊቷ ይታያል። “ቢኒያምን በጣም ነው የምወደው። እሱ ብዙ በጎ ነገሮችን ይሰራል። እኔም እሱ የጀመርዉን አስቀጥላለሁ” ትላለች በህፃን ጣፋጭ አንደበቷ።
መቄዶንያን በጎበኘችበት ወቅት አረጋዊያንን እግራቸውን አጥባ ከአልጋ መነሳት የማይችሉትን ደግሞ እየዞረች አይዞዋችሁ ብላቸው መርቀዋታል። አያችሁ ልጆች ጥሩ ስራ መስራትና ሰውን መርዳት በትልልቅ ሰዎች እንድንመረቅ ያደርገናል። ምርቃት ደግሞ ያሳድጋል። ልጆች በፀሎት ገና የስድስት አመት ህፃን ናት ።ግን ህፃን መሆኗ ሰው ከመርዳት አላገዳትም፤ የምትሰጣቸው ብርም ሆነ የምታካፍላቸው ንብረት ባይኖራትም የተቸገሩ ሰዎችን ብቻችሁን አይደላችሁም አለሁላችሁ በማለት ነግራ ተስፋ በመስጠት ትረዳቸዋለች። እናንተም ሰው ለመርዳት ብር ወይም የምሰጣቸው ነገር ሊኖረኝ ይገባኛል ብላችሁ እንዳታስቡ፤ ሰው ብር ወይም ቁሳቁስ ብቻ አይደለም የሚቸግረው እናንተ ሲከፋችሁ እናትና አባታችሁ አብሮዋችሁ እንዲሆኑ ትፈልጉ የለ? እነሱም ሲከፋቸው አጠገባቸው የሚሆን ሰው ይፈልጋሉ። ስለዚህ አጠገባቸው በመሆን ብቻ ልትረዷቸው ትችላላችሁ እሺ።
በፀሎት ጥሩ ስነምግባርና ሰውን የመርዳት ፍላጎት እንዲኖራት ያገዛት የቤተሰቧን ምክር መስማቷ ነው። እናትዋ ሁል ጊዜ ‹‹ሰው የሚልሽን ስሚ ሰው የሚልሽን ከሰማሽ የምትፈልጊውን ታገኛለሽ›› እያለች ትመክራታለች።በፀሎት የእናቷን ምክር ሰምታ ስለምትተገብር ሁሉም ሰው ይወዳታል። እናንተም በሰዎች ዘንድ እንድትወደዱና ጥሩ ስነምግባር እንዲኖራችሁ የቤተሰብ ምክር መስማትና መተግባር አለባችሁ እሺ።
ልጆች በጸሎት ትምህርቷን ጎበዝ ሆና ተምራ ዶክተር መሆንና መቄዶኒያ ውስጥ የሚኖሩ የታመሙ ሰዎችን ማከም ትፈልጋለች። ስለሆነም ሁሌ ትመህርቷን በአግባቡ ትማራለች ።የቤት ስራዋን ትሰራለች እናም ጎበዝ ተማሪ ናት። በሉ ልጆች ለዛሬ እዚህ ላይ ላብቃ ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015