የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችን መሠረት አድርጎ የዛሬ አራት አመት በሶስት ሺ 500 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው ሀገራዊ የስንዴ ልማት አካል የሆነው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ ባለፈው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሸፈነው ማሳ ከ600 ሺ በላይ ሄክታር የደረሰ ሲሆን፣ በተያዘው 2015 በጀት አመት ይህ አሀዝ ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ እንደሚደርስ የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሀገራዊ ስንዴ ልማቱ አላማ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ማሟላትን፣ በግዥ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ መተካትን፣ ስንዴ ለወጪ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ በተከናወነው ተግባርም በመኸር ወቅት በስንዴ ዘር የሚሸፈነው ማሳ ብዛትም የሚገኘው ምርትም እየጨመረ ይገኛል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2013/14 የምርት ዘመን ከ600ሚሊየን ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ስንዴ በመዝራት 26 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማግኘት ተችሏል፤ በ2015 የበጋ ወቅት ደግሞ ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 52 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
የግብርና ስራውን ከተበጣጠሰ ማሳ ወደ ኩታ ገጠም ማሳ በመቀየር በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በመሳሰሉት ላይ ለውጥ ማምጣት እየታቸለ ሲሆን፣ በሜካናይዜሽን በኩልም በትራክተር፣ በኮምባይነር የመጠቀሙ ሁኔታ፣ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አቅርቦትና እየጨመረ ይገኛል።
በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ልማት፣ በሜካናይዜሽን፣ በኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋትና በመሳሰሉት እየታዩ ያሉት ለውጦች ከግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር/ ትራንስፎርሜሽን/ አንጻርስ እንዴት ይታያሉ? ለግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር እውን መሆን ምን ምን ነገሮች ያስፈልጋሉ? ሽግግሩስ በምን መልኩ ሊገለጽ ይችላል?
በቅርቡ ዋልታ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሀሚድ ጀማል፤ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን (ትራንስፎርሜሽን) ማሳየት የሚቻለው በዘርፉ በሚካሄደው ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ፣ ግብርናው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ሲችል ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በበሬ ጫንቃ የሚከናወነው ግብርና በሜካናይዜሽን ተተክቶ ልማቱ በስፋት መከናወንና በበጋ ጭምርም መሥራት ሲቻል መሆኑን ያመለክታሉ። በተበጣጠሰ መሬት ላይ ይከናወን የነበረን ልማት ኩታገጠም (ክላስተር) የስንዴ ልማት በማካሄድ ውጤታማነቱን ማሳየት መቻሉንም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት ገበያ ተኮር መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። አብዛኞዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ስንዴን ከውጭ እንደሚገዙም ተናግረው፣ ይህም ለኢትዮጵያ የገበያ መዳረሻ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል ይናገራሉ። ሀገሪቱ ገበያዋን ወደ ጎረቤት ሀገሮች በማስፋት ተጠቃሚነቷን ማሳደግ እንደምትችል፣ የስንዴ ልማቱ ለሌሎችም የሰብል ልማቶች ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይፍሩ ታፈሰ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፤ የግብርናው ድርሻ በአብዛኛው በሌሎች ዘርፎች እየተተካ መጥቷል ሲሉ ይገልጻሉ። በሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ውስጥ የግብርናው ድርሻ ሲታይ ወደ31 በመቶ ወርዷል ያሉት አቶ ይፍሩ፣ ከ20 አመት በፊት 50 በመቶ ገደማ የነበረው በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ግብርና የነበረው ድርሻ ቀንሷል። አሁን ወደ አገልግሎቱ፣ ኢንዱስትሪው እየሄደ መሆኑን የግብርናው ሚና እየታየ መጥቷል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የሚለካው በግብርና፣በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ነው። የሶስቱ ድርሻ እየተሸጋሸገና አንዱ ሌላውን እየተካው ሲሄድ በመቶኛ ነው ድርሻቸው የሚገለጸው። ለአብነት በአሜሪካ የግብርና ድርሻ ሶስት በመቶ ብቻ ነው። ሌላው የአገልግሎትና የኢንዱስትሪው ድርሻ ነው።
ሽግግር የሚመጣው የግብርናው ድርሻ እያነሰና በኢንዱስትሪው፣በአገልግሎቱ ሲተካ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግብርናው ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል እንጂ መዋቅራዊ ሽግግር ግን አላካሄደም ወይም ትራንስፎርም አልሆነም ሲሉ አቶ ይፍሩ ይናገራሉ።
የግብርና መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማምጣት ምርታማነትን የሚያቀላጥፉ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ያሉት አቶ ይፍሩ፤ በባህላዊው የአስተራረስ ዘዴ ቀናት የሚወስደው ሥራ በሜካናይዜሽን ከታገዘ በሰአት ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ይናገራሉ፤ ይህ ሲሆን በኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ የሚባክነውን የሰው ኃይል ወደ ኢንዱስትሪውና ሌላ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማራ ማድረግ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አርሶ አደሩ ልጁን ትምህርት ቤት በመላኩና በተለያየ ምክንያት እያጋጠመው የመጣውን የሰው ኃይል ችግር መፍታት የሚቻለው ግብርናው በሜካናይዜሽን ታግዞ ሲሰራ ነው። ግብርናው ሲዘምን የመሥራት ፍላጎትም ይነሳሳል።
በሀገሪቱ እንደ ማረሻ፣ምርት መሰብሰቢያ፣መውቂያ የመሳሰሉት የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራ በሬ ጠምዶ ከማረስ አልተላቀቀም። በምርጥ ዘር አቅርቦትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትልቅ ሥራ ተሰርቷል የሚባለው የበጋ መስኖ ልማት ከተጀመረ ወዲህ ባለው እንቅስቃሴ ነው።
በሌሎች ሰብሎች ልማትም በቆሎ ላይ የተሻለ ሲሆን፣በምርጥ ዘር አቅርቦትም ጭምር መልካም የሚባል ውጤት ተመዝግቧል። ጤፍን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረተባይና ሌሎችንም ግብአቶች እንዲሁም በሜካናይዝሽን አቅርቦት ላይ ጠንካራ ሥራ ይጠበቃል።
በተበጣጠሰ የአርሶ አደር መሬት ላይ የሚከናወን ልማት የትም አይደረሰም። አርሶ አደሩ መሬቱ የኔ ነው የሚል አስተሳሰብ ስለሚኖረው በውጤታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መኖሩ አይቀርም ያሉት አቶ ይፍሩ፣ በሰፊ መሬት ላይ ማልማት ወይንም ኮሜርሻላዝ ማድረግ እንዲሁም ጠፍ መሬትን ለልማት ምቹ በማድረግ የግሉን ዘርፍ በግብርናው ዘርፍ ማሳተፍ ይጠበቃል። ይህ ሲሆን፣ የግብርናው መዋቅራዊ ሽግግር ወይንም ትራንስፎርሜሽን እውን ይሆናል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
አቶ ይፍሩ ይህን ሁሉ ለመፈጸም ዘርፉን ከሚመራው አካል ብዙ ሥራ ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል። ለአብነት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች በምርምር ምርጥ ዘር በስፋት እንዲያወጡ የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ ያደርጋል። በምርምር የተገኘው ዘር ጥቅም ላይ እንዲውልም አርሶ አደሩ መንደር በመሄድ ስለአጠቃቀሙ የማሳየትና የማላመድ እንዲሁም የማነቃቃት ሥራ ይሰራል። ከአመት በፊት በምርምር የወጡ የተሻሻሉ ቦራና እና ቦሰት የተባሉ የጤፍ ዝርያዎች ምንጃር አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በግላቸው ለሙከራ ሰጥተው ለአካባቢው ሥነምህዳር ተስማሚ ሆኖ የተገኘውና በአርሶ አደሩም የተመረጠው የቦራ ዝርያ ያለው ጤፍ መሆኑን መረዳት ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለምግብ ፍጆታና ለፋብሪካ ግብአት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ላይ ትኩረት በማድረግ በምርጥ ዘር አቅርቦት በአስር የሰብል አይነቶች ላይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል ጤፍ፣ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እንደሚጠቀሱ ያመለክታሉ። በተመሳሳይ በአትክልትና ፍራፍሬ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ቲማቲም ዝርያዎች ላይ ድጋፍ አድርጓል ይላሉ። ኢንስቲትዩቱ የአምስት አመት እቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ከገባ ሁለት አመታት ተቆጥረዋል ያሉት አቶ ይፍሩ፣ ሥራውን ለማጠናከር ደግሞ ‹‹ቴን ኢን ቴን››የሚል የአስር አመት እቅድ ቀርጿል ብለዋል፡፡
አዳዲስ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ነባር ዝርያዎች እንዲዘነጉ አያደርግም ወይ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም አንዴ ከተለመደ ነገር የመውጣት ችግር ካልሆነ በስተቀር ምርታማ ለመሆንና የአርሶ አደሩም ኑሮ እንዲሻሻል ለተያዘው ሥራ አማራጮችን መፈለግ እንጂ በነበረ ነገር መቀጠል አዋጭ እንደማይሆን ገልጸዋል። በተሻሻሉ ዝርያዎች እንደ ስጋት የሚነሳው የበሽታ አለመቋቋምን በተመለከተ መፍትሄም አብሮ የሚዘጋጅ መሆኑና አሳሳቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
የምርምር ብቃትን እያሳደጉ ተለዋዋጭ የሆነውን በሽታ መቋቋም እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ነባር ዝርያዎችም እንዳይጠፉ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግና እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ግብርናን ትራንስፎርም ለማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመጠቆም፣መልካም የሆኑ የቴክኖሎጂ ተሞክሮዎች ከአንዱ ወደሌላው እንዲሸጋገሩ፣ተመራማሪዎች በዘርፉ የምርምር ሥራ እንዲሰሩና ለምርምር ሥራ እገዛ በማድረግ፣ቴክኖሎጂዎች እንዲመቻቹና በሌሎችም የሀገራቱን አቅም በመፍጠር እየደገፈ የሚገኘው አግራ የተባለ ዓለምአቀፍ ድርጅትም በኢትዮጵያ በግብርና ማምጣት ለሚፈለገው መዋቅራዊ ሽግግር ስራ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
ዶክተር ጥላሁን አመዴ በዚህ ተቋም ውስጥ ይሰራሉ። እርሳቸው ከሚሰሩባቸው 15 ሀገራት መካከል ፈጣን የግብርና ልማት የሚታየው በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነ ዶክተር ጥላሁን ይጠቅሳሉ። በሀገሪቱ አነስተኛ ምርት የሚታይበት ሰብል እንዳለም ተናግረው፣ በእጥፍ እድገት ያስመዘቡ የሰብል አይነቶች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት። አጠቃላይ ምርት መጨመሩንም ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥያቄ ግን ገና ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቀዋል።
ይሄ የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው ሲሉም ዶክተር ጥላሁን ይጠቁማሉ። አንዱ ምርት ያደገው በመኸር በሚከናወን የግብርና ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ። በአየር መዛባት ዝናብ በወቅቱ ባለመገኘቱ፣ የአየር ለውጡንም አርሶ አደሩ ባለመገንዘቡ በተፈጠሩ ምክንያቶች በበልግ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 30 በመቶ ይገኝ የነበረው ምርት ቀንሷል ሲሉም አብራርተው፣ በዚህ ምክንያት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ መድረስ አልተቻለም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
የአፈር ልማትና የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የውሃ ሀብቱን በአግባቡ መጠበቅ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበትም ዶክተር ጥላሁን ተናግረዋል። በዝናብ ከሚመረተው የበለጠ በመስኖ የሚለማው ውጤታማ እንደሆነ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳይም አመልክተው፣ ይህ የሚሆነው በመስኖ የሚከናወን ልማትን መቆጣጠርና አስፈላጊ የተባሉ ግብአቶችንም ማቅረብ ስለሚቻል እንደሆነ ጠቁመዋል።
ዝናብ ጠብቆ የሚከናወን የግብርና ሥራ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች የበዙበትና ስጋት የተሞላበት መሆኑን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጥሩ ማሳያ ቢሆንም ሥራው ገና በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው ይላሉ። ልማቱ በመኸር ልማት ላይ በሚሳተፍ የኤክስቴንሽን ባለሙያ እየተመራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በመስኖ በኩል የተለየ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። አመራረቱም ገበያው በሚፈልገውና አርሶ አደሩ ለማምረት ፍላጎት ባደረበት ላይ መመስረት እንደሚኖርበትም ያመለክታሉ፡፡
ዶክተር ጥላሁን የግብይት ፋይዳም ያነሳሉ። አርሶ አደሩ ምርቱን በፈለገ ጊዜ እንዲሸጥ የምርት ማከማቻ መጋዘን ሊመቻችለት እንደሚገባ፣ እሴት የተጨመረበት ምርትም እንዲያመርት መበረታታት እንዳለበት ጠቁመው፣ በአጠቃላይ የልማቱን አማራጭ ለአርሶ አደሩ መተውና ገበያው እንዲመራው ማድረግ ይገባል፣ ግብርናውን የሚያግዝ ፋይናንስ(የገንዘብ አቅም) መኖር አለበት ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
አርሶ አደሩ የገንዘብ አቅም ሲኖረው ቴክኖሎጂን ቶሎ ለመቀበልና፣ ለመጠቀም፣ ወደ ኢንቨስትመንት ለማደግ እድል ይፈጥርለታል ያሉት ዶክተር ጥላሁን፣ እነዚህ ሁሉ ሲከናወኑ ነው የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማምጣት የሚቻለው ሲሉ ገልጸዋል።
እሳቸው የሚሰሩበት ተቋም በዘርፉ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን መንግሥትን በፖሊሲና በተለያየ መንገድ እንዲረዱ በማድረግ፣አርሶ አደሩ እጅ የሚገኙ 30 እና 40 አመታት ያስቆጠሩ ዝርያዎች እንዴት ይተኩ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተለያየ መንገድ እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን በመንግሥት ብቻ ማሟላት እንደማይቻልም አመልክተው፤ በግብርናው ላይ የግሉ ዘርፍ መግባት አለበት ይላሉ። መንግሥት የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በተለያየ ማበረታቻ ሊያግዝ እንደሚገባ ገልጸው፣ የመንግሥት ሥራ መሆን ያለበት አገልግሎቱን መቆጣጠር ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ከ2003 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ በተደረጉት በሁለቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ጥረት ቢደረግም የተባለውን ሽግግር ግን እውን ማድረግ ሳይቻል መቅረቱ ይታወቃል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015