ፊፋ የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ደረጃ መሻሻል አላሳየችም። በዚህም ከነበራት ደረጃ ከፍም ዝቅም ሳትል ከዓለም 138ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 41ኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች። ይህም ባለፉት ጥቂት ወራት ዋልያዎቹ የአቋም መለኪያም ይሁን ሌሎች ጨዋታዎችን ባለማድረጋቸው ምክንያት የደረጃ ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ታውቋል።
ሁልጊዜም አወዛጋቢ በሆነው የፊፋ የሀገራት ደረጃ አሰጣጥ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ በመሆን የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር የሆነችው ሞሮኮ የአፍሪካን ቀዳሚ ደረጃ ከሴኔጋል ተረክባለች። የዓለም ዋንጫው ክስተት የሆኑት የአትላስ አንበሶች ሀገር የሆነችው ሞሮኮ 11 ደረጃዎችን አሻሽላ ከዓለም 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። ይህም በትልቁ የዓለም ዋንጫ መድረክ ከምርጥ አራት ቡድኖች አንዷ ሆና ሳለ ቢያንስ ከአስሩ የዓለም ደረጃ ውስጥ አለመካተቷ በርካቶችን ያስገረመ ሆኗል። ሞሮኮ በዓለም ትልቁ ደረጃዋ 10ኛ ሲሆን ይህም እኤአ 1998 ላይ ያስመዘገበችው ነው። የአትላስ አናብስት ዝቅተኛ ደረጃቸው 92ኛ ሲሆን እኤአ 2015 ላይ ያስመዘገቡት ነው።
ከአትላስ አንበሶች በተጨማሪ የዓለም ዋንጫውን ያነሳችው አርጀንቲና በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ በሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ የተሰናበተችው ብራዚል በአንጻሩ ከዓለም አንደኛ ሆና መቀመጧ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።
ፊፋ ወርሐዊ የሀገራትን ደረጃ ማውጣት የጀመረው እኤአ ከ1992 አንስቶ ሲሆን ደረጃውን የሚሰጠውም ሀገራት በተቀመጠው ወር ውስጥ በሚያስመዘግቡት ነጥብ መሠረት ነው። ፊፋ ለሀገራት ደረጃ የሚሰጥበትን ስልት እኤአ ከ2018 ወዲህ የለወጠ ሲሆን በአዲሱ ስሌት መሠረት ሀገራት የሚሰጣቸው ደረጃ በወር ውስጥ ከሚያስቆጥሩት አማካኝ ነጥብ ይልቅ ሀገራት ቀደም ሲል የነበራቸው አጠቃላይ ነጥብ ላይ የሚያስመዘግቡትን አዲስ ነጥብ በመደመር ወይም በመቀነስ ነው። በዚህም መሠረት ሀገራት የሚያስመዘግቡትን ነጥብ ለመደመር ወይም ለመቀነስ የሚገጥሙት ሀገር እንደሚገኝበት ደረጃ ሊለያይ ይችላል።
ለምሳሌ ያህል ከአንድ እስከ አስር ደረጃ ውስጥ የሚገኝ አገርን ማሸነፍ ከአስር በላይ ደረጃ ውስጥ የሚገኝ አገርን ከማሸነፍ የተሻለ ነጥብ ያስገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የውድድር መድረኮች ደረጃም የነጥብ አሰጣጡ ላይ ልዩነት ይፈጥራል። ለምሳሌ አንድ ሀገር የዓለም ዋንጫ ላይ አሸንፎ የሚያገኘው ነጥብ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ አሸንፎ ከሚሰጠው ነጥብ ይበልጣል። እንደ ዓለም ዋንጫ፣አፍሪካ ዋንጫ፣አውሮፓ ዋንጫ ወዘተ ባሉ ውድድሮች ላይ ሀገራት በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ቢሸነፉ የሚቀነስባቸው ነጥብ አይኖርም። አንድ አገር በመለያ ምት ቢሸነፍ ነጥብ አይቀነስበትም፣ እንዲያውም አንድ ነጥብ ከጨዋታው ያገኛል። ፊፋ ለሀገራት ደረጃ የሚሰጠው እነዚህንና ሌሎች በርካታ ነጥቦችን ከግምት በማስገባት ነው።
በዚህ መሠረት ለምሳሌ ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው ብዙ ግብ ካለማስተናገዷ በተጨማሪ በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ላይ የነበረችው ቤልጂየምን፣ፖርቹጋልና ስፔንን አሸንፋለች። ሦስቱም ሀገራት በፊፋ ደረጃ አስር ውስጥ የነበሩ ሲሆን ስፔንን ብቻ ነው በመለያ ምት ያሸነፈችው። ይህም በዓለም ዋንጫ አራተኛ ሆና ከማጠናቀቋ ጋር ተደምሮ ቢያንስ ከዓለም አስሩ የመጀመሪያ ደረጃዎች ውስጥ መግባት ነበረባት የሚሉ ክርክሮችን ያስነሳል።
በተመሳሳይ የዓለም ዋንጫው ሻምፒዮን አርጀንቲና ከዓለም ዋንጫው አስቀድሞ 37 ጨዋታዎችን ያለመሸነፍ ጉዞ አድርጋ በሳውዲ ዓረቢያ ብቻ ነው የተሸነፈችው። ሻምፒዮን እስከሆነችበት ጉዞ ድረስም ጥሩ ደረጃ ያላቸው የአውሮፓ ሀገራትን ማሸነፍ ችላለች። ብራዚል በአንጻሩ በዓለም ዋንጫው ከሩብ ፍጻሜ የዘለለ ስኬት ማስመዝገብ ካለመቻሏ በተጨማሪ በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ካሜሩን በምድብ ጨዋታ መሸነፏ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ ብራዚል አርጀንቲናን በልጣ የዓለም ቁንጮ ሆና መቀመጧ ለብዙዎች የሚዋጥ አልሆነም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215