መዲናችን አዲስ አበባ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ሁሉን አቻችላ በእቅፏ የያዘች ከተማ ናት:: ነዋሪዎቿም እንደየኑሮ ደረጃቸው ሰርተው ለማደር ከጠዋት እስከ ማታ ደፋ ቀና ይላሉ::
ያለው ባለው ላይ ለመጨመር የሌለው ደግሞ ካለበት የኑሮ ደረጃ ወደተሻለው ከፍ ለማለት፤ ከዛ ባስ ያለው ደግሞ የለት ጉርሱን ለማግኘት ይታትራል:: በዚህ ሁሉ መሃል ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ፣ ከቤት ወደ ስራ ከስራ ወደ ቤት የሚንቀሳቀሰው ሕዝብ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን እንደየ አቅሙ ይጠቀማል።
አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ የህዝብ ትራንስፖርት በተለይም የከተማ አውቶብስ ተጠቃሚ ነው:: ለዚህ የተለያዩ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የከተማ አውቶብሶች በሮቻቸውን ለመዝጋት እስከሚቸገሩ ድረስ በሰው ታጭቀው ከማየት የበለጠ ማረጋገጫ የለም።
የከተማ አውቶብሶች የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚው ሕዝብ እጅግ ብዙ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለማንም ምቾት የሚሰጥ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በተለይ ለሴቶች ደግሞ ምቾት ከማሳጣት ባሻገር ሌላም ጣጣ እንዳለው አዲስ አይደለም። በከተማ አውቶብሶች የሚጠቀሙ ሴቶች በወንዶች ፆታዊ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸው የሴቶች መብት ተሟጋቾች በተለያየ ጊዜ እየጠቆሙ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸው ግን አሁንም ድረስ በህግ ተደግፎ ሴቶች በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚገጥማቸውን የሞራልና የመብት ጥሰት ማስቀረት አልቻለም። ጉዳዩ በመብት ተሟጋቾችም በሌሎችም በአንድ ወቅት አጀንዳ ሆኖ ይነሳና ብዙም ሳይቆይ ይረሳል። እኔም በዚሁ ጉዳይ ላይ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ ብእሬን ያነሳሁት ድንገት ነው።
ከእለታት ባንዱ ቀን ነው፣ እግር ጥሎኝ የከተማ አውቶብሶች ብዙ ተሳፋሪ በማያጨናንቃቸው ሰዐት ተሳፍሬ ወደ ጉዳዬ እየሄድኩ በነበርኩበት ጊዜ አውቶብሱ ውስጥ ተለጥፎ ያየሁት ጽሁፍ ቀልቤን ሳበው። ጽሁፉ ‹‹የህዝብ ትራንስፖርት ውስጥ ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳን በጋራ እንከላከል ›› ይላል:: ይህንን ፅሁፍ ካነበብኩ በኋላ ከራሴ ጋር በብዙ አወራሁ:: እንዴት? የሚል ጥያቄ ውስጤ ተመላለሰ::
እንዴት ይሄ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ በገሃድ ያውም በጽሁፍ እስኪነገር ድረስ ከሰውነት ወረድን? ባህል፣ወግና እሴቶቻችን ምን ያህል ቢናዱ ነው ይህን ያህል የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የገባነው? ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። በእርግጥ ይህ ጉዳይ እንደ ከተማ አውቶብስ ባሉና በርካታ ሰው በሚጠቀምባቸው የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ እንደሚፈጠር ሰምቼ ባውቅም በተለያዩ ምክንያቶች የህዝብ ትራንስፖርት ከተጠቀምኩ ቆይቼ ነበርና በዚህ ልክ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብዬ አልገመትኩም ነበር:: በተሳፈርኩበት አውቶብስ ውስጥ ያነበብኩት ጽሁፍ ግን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ እንዳስበው አደረገኝና በዙሪያዬ የማገኛቸውን ሴት ጓደኞቼን እና በተለያየ አጋጣሚ የማገኛቸውን ሴቶች ስለነገሩ እንድጠይቅ አድርጎኛል።
ጉዳዩ በዚህ ልክ አሳሳቢ መሆኑን ለመረዳት ዘወትር የአውቶብሶቹን አገልግሎት የሚጠቀሙ ሴቶች የነገሩኝን ጉድ ስሰማ ነው የገባኝ። ታዲያ የሰው ልጅ ያውም ጥብቅ ባህልና ወግ ባለበት አገር በዚህ ልክ ሰው ከሰውነቱ ወርዶ ከተገኘ ከእንስሳት የሚለይበትን የማሰብ ፀጋ ተነፍጓል ማለት አይደል?
ከጊዜ በኋላ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ አውቶብሶችን መጠቀም ሳዘወትር በዚህ ጉዳይ መናደድ ጀመርኩ ብል ይቀላል:: ያቺን ጽሁፍ ካነበብኩበት ቀን አንስቶ የአውቶብስ ትራንስፖርት ስጠቀም ነገሩን በትኩረት መከታተል ጀምሬያለሁ። የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ የከተማ አውቶቢሶች ወንበሮቻቸው በሰዎች ከሞሉ በኋላ ቆመው የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ካፍ እስከ ገደፋቸው ጢም አድርገው መጫናቸው የተለመደ ነው።
ተሳፋሪው ከትራንስፖርት ችግሩ አኳያ ምቾቱን ወደ ጎን ትቶ ታምቆ ጉዞውን ሲጀምር አንዳንድ ስነምግባርም ሞራልም የጎደላቸው ወንዶች የአውቶብሱን በሰው መጨናነቅ እንደሰበብ ተጠቅመው ቆመው ወደሚጓዙ ሴት ተሳፋሪዎች በመጠጋት የወሲብ ትንኮሳ ለመፈጸም ይሞክራሉ። ይህን ለማድረግ ስራዬ ብለው አውቶብሶችን የሚሳፈሩ አሉ። ምቹ ሁኔታዎችን አይተው ሙከራ ለማድረግ የሚጥሩም ጥቂት አይደሉም።
እንዲህ አይነቱን ፀያፍ ድርጊት የሚፈጽሙ ወንዶች መጀመሪያ በቦታ ጥበት አሳበው ሴቶችን ይጠጋሉ። በሰዎች ታጭቆ መፈናፈኛ የሌለው አውቶብስ ውስጥ ብዙ ሴቶች ይህ ትንኮሳ እየተደረገባቸው መሆኑን እያወቁ እንኳን ራሳቸውን ለመከላከል አማራጭ የሚያጡበት ጊዜ አለ። በዚህም ምቾት በማጣት ፊታቸው ላይ የመጨነቅ ስሜት ይነበባል:: በዚህ የተነሳ ብዙ ሴቶች መሄድ የሚፈልጉበት ቦታ ሳይደርሱ እስከመውረድ ይገደዳሉ።
ብዙ ሴቶች እንዲህ አይነቱ ነውር ሲፈፀምባቸው ዝምታን መርጠው የራሳቸውን ርምጃ ይወስዳሉ እንጂ የወንዱን ፀያፍ ድርጊት እዚያው ሰው በተሰበሰበበት አውጥተው አይናገሩም:: ያው ጉዳዩ አሳፋሪና ከባህላችንም አንፃር ይህ ነው የሚሉት ባለመሆኑ ነው:: በራሳቸውም ይሁን በሌሎች ላይ ይህን ነውር የሚፈፅሙ ወንዶችን እየተመለከቱ ዝምታን የማይመርጡ አንዳንድ አንጀት አርስ ሴቶች አሉ:: ይህን ድርጊት ለመፈፀም የሚሞክረውን ሰው አደባባይ ላይ አውጥተው በማጋለጥ ከፍና ዝቅ አድርገው ተናግረው በጋራ ሲያዋርዱትና ያለቦታው ከመድረሻው ፌርማታ ሳይደርስ እንዲወርድ የሚያደርጉ::
የሰውየው ግዝፈት የሰው ብዛት ሳያስፈራት ምቾቷን የነሳትን ሰው ትግስቷ አልቆ ዞራ በጥፊ ፊቱን የምታቀላውም አለች:: አቤት ከዚያ በኋላ የሰውየውን ፊት ማየት ነው:: መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠው እየተመኘ እንደሆነ በሚያሳብቅ ሁኔታ አንገቱን ደፍቶ አውቶብሱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ጨዋ ወንዶችና ሴቶች የሚወርድበትን ቁጣ አምልጦ የሚገባበት ጠፍቶት ተገትሮ ይቀራል:: እንዲህ አይነቱ ከመድረሻው ቢደርስም ባይደርስም አንገቱን እንደደፋ ይወርዳል:: እዚህ ጋር ለሴት ልጅ ትንኮሳ ተቃዋሚ ሆነው እንዴት ብለው የሚቆጡ ወንዶችን ማመስገን አስፈላጊ ነው::
ሴቶች ጊዜ ተለውጦ እንደማንኛውም ሰው ኑሯቸውን ለማሸነፍ ከቤት ወጥተው ሰርተው መግባት በጀመሩበት በዚህ ጊዜ ሌላ እንቅፋት እንዳይገጥማቸው የማድረግ ሃላፊነት የሁሉም ነው:: ይህን ጉዳይ ቀለል አድርገን ልንመለከተውም አይገባም:: ሴቶች እንደማንኛውም ሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ይህ ጉዳይ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ የአንድ ሰሞን ብቻ አጀንዳ መሆን የለበትም::
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215