ሁለት ባዕዳን የሆኑ ተቃራኒ ጾታዎች በፍቅር የሚመሰርቱት ቤተሰብ መተሳሰቡ፣ ፍቅሩ ፣አንተ ትብስ አንቺ መባባሉ በዛን መካከል ደግሞ የሚፈጠረው ውህድ ህጻን የቤተሰቡ ድምቀት ይሆናል። የፍቅር ማጣፈጫ ሆኖ ይቆጠራል። አይኔን በአይኔ አየሁ ደስታን ይፈጥራል። ይሄ ደግሞ ሌላ ዓለም ቤተሰቡን አጽንቶ የሚያቆይ አዲስ ምዕራፍ ይሆናል።
አርዓያ የሚሆን ቤተሰብ ከራሱ አልፎ ተርፎ ለተጋቢው ወገንም ልጅ ፣ ወንድም፣ እህት በአጠቃላይ ዘመድ አዝማድ በመሆን የሚተሳሰር እና የሚተሳሰብ ነው። እኔ ብቻ ልደመጥ፣ ልብለጥ የማይል ፣የሀሳብ ልዩነት ሲያጋጥም እንኳን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለመሸነፍ ዝግጁ የሆነ የቤተሰብ አካል ይሆናል። የሰላም መድረክም ነው ቤተሰብ። ሁሉንም ነገር የሚያይበት መነጽር ፍቅር ፣ርህራሄ በተሞላው ሁኔታ ነው። ልክ የሆነውን ለማስቀጠል ስህተት የሆነውን በማረምና በማስተካከል ነው ቤተሰብን የሚሰራው። ወላጆች እንደ አያቶቼ አላደጉም፣ እኛም እንደ ወላጆቻችን አላደግንም።
ልጆቻችንም እንደኛ አያድጉም። በአጠቃላይ በዘመን ቅብብሎሽ ማህበረሰብ የሚገነባው ነው። ይሄ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የት ይደርሳል የተባለና ለብዙዎች አርአያ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ቤተሰብ ባልተጠበቀ መልኩ ለችግር ሲዳረግ ይታያል። ካለ አንተ ካለአንቺ የተባባሉ የትዳር አጋሮች ጭራሽ የማይተዋወቁ ያክል ለከፋ ጉዳትና አደጋ የሚገባበዙበት ሁኔታ ይፈጠራል ። በአለት የተገነባ የሚመስለው ትዳርም ነፋስ እንደገባው የሳር ጎጆ በቀላሉ ይፈርሳል። የነበረው ፍቅር፣ የነበረው መተሳሰብና መከባበር ፣ የነበረው ሁሉ ነገር በዜሮ ተባዝቶ ህይወት እስከመጠፋፋት የደረሰ እርምጃ ውስጥ ይገባል።አስከፊ ወንጀል ተፈጸመ ሲባል ይሰማል።ይሄ እየተለመደ መጥቷል።
ዛሬ ስለ ቤተሰብ ላነሳ የወደድኩት በጤናዬ እንዳልሆነ ትረዱኛላችሁ።ከፍትህ ሚኒስትር ፌስ ቡክ ገፅ ያገኘሁትን እና በቤተሰብ መካከል ተፈጥሮ ወደ አልተገባ መንገድ ካመራው ግጭት ብንማርበት ብዬ ነው። የወንጀል ድርጊት በስሜት ይፈጸማል። ነገር ግን ሲቆይ ይጸጽታል። ያቺን ሰዓት ከስሜት ወጣ ብሎ ማሰብ ቢቻል፤ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የተሻለ መፍትሄ መሳብ ቢቻል… አስከፊ የሚባለው ወንጀል ድርጊት ሁሉ አይኖርም ነበር።
ቤተሰባዊ ትስስር
አቶ አሰፋ ለአቅመ አዳም ደርሰው በወግ ማእረግ ተድረው የልጅነት ሚስታቸውን ይዘው አዲስ አበባ ከከተሙ አንድ ክፍለ ዘመንን ሊደፈኑ ጥቂት ይቀራቸዋል። በልጅነት ወዛቸው ለፍተው ጥረው ግረው ባጠራቀሟት ጥሪት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ልዩ ቦታው የካ ተራራ ትምህርት ቤት አካባቢ ሰፋ ያለ የመኖሪያ ቤትና ቅጥር ግቢ ሰርተው ከአምስት ልጆቻቸው ጋር በደስታ ይኖሩ ነበር።
ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ልጆች አድገው ለወግ ማእረግ ሲበቁ አቶ አሰፋና የልጅነት ባለቤታቸው ደክመው በእድሜያቸው ማየት የሚገባቸውን ደስታ በሙሉ አይተው ይህችን አለም ይለያሉ። ወላጅ ሲሸኝ ልጅ በውርስ መተካት የነበረ ነውና የእናት የአባታቸው ቅርስ ላይ ልጆች ተተክተው በስርአት የድርሻቸውን ተካፍለው ወልደው ከብደው መኖር ይጀም ራሉ።
ከአቶ አሰፋ አምስት ልጆች መካከል ሶሰቱ በእናት በአባታቸው ቤት ሲኖሩ ሁለቱ ደግሞ የድርሻቸውን በኪራይ እየወሰዱ ከግቢው ውጪ ይኖሩ ነበር። ፍቅራቸው ወገን ዘመድ ጎረቤት የሚያስቀና በመከባበር የሚኖሩ ወንድሞችና እህትማማቾች ነበሩ።
በፍቅር መካከል ሳንካ አይጠፋምና በመካከል ወንድምና እህትማማቾች መካከል አልፎ አልፎ ግጭት ይታይ ጀመር። በማንኛውም ግጭት መካከል የአንደኛዋ ባል መካሪ ተቆጪ አስታራቂ ሆነ መካከላቸው በመግባት ነገሮቹ እንዲረግቡ የማድረግ ስራ ይሰራ ነበር።
ስር እየሰደደ የመጣው ቁርሾ
ፀቡ ሲደጋገም፤ የዛሬው በይቅርታ ሲታለፍ ደግሞ ነገ ሌላ ጉዳይ ሲነሳ፤ እንዲሁ በቀላሉ ሲለባብስ የቀየው የቤተሰብ ፀብ ጭራሽ የትዳር አጋሮች መካከል አስገብቶ ያናጭ ጀመር። የእህትማማችና የወንድማማች ጉርብትና ከፍቅር አልፎ ለመገዳደል ወደ መፈላለግ ደረጃ ደረሰ።
መዋደዳቸው መደጋገፋቸው ቀርቶ አይንህን ላፈር፤ አይንሽ ላፈር መባባል ጀመሩ። የአንድ አያት ልጆች የሆኑት ልጆቻቸውም ባልተገባው የቤተሰብ ፀብ የተነሳ አብረው መጫወት አቁመው ተኩራረፉ። የልጅነት ልባቸው ባይገባውም ቤተሰቦቻቸው መካከል ግን የከረረ ፀብ ስለመኖሩ ደመነፍሳቸው ነግሯቸዋል።
በፊት ሰላምን ቅድሚያ አማራጭ ያደረጉት በሙሉ እልህ ተጋቡ። ቆም ብሎ በማሰብ ያለባቸውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ነፍስ ለመጠፋፋት ማሰብ ማሰላሰል ባገኙት አጋጣሚ ደግሞ መዛዛትና ጥርስ መነካከስ ጀመሩ። በተለይም አቶ ሙሉነህ አሰፋ የተባለው ወንድማቸው የእህቱን የወይዘሮ አልማዝ አሰፋን ባለቤት አቶ አበበ ለብሶን መካከላችን የገባ ጋሬጣ በማለት በክፉ አይኑ ይመለከተው ጀመር።
በክፉ አይን ከመተያየትም አልፎ መዛትና ማስፈራራትም እየተከተለ መጣ። ፀቡ ከእለት ወደ እለት እየከረረ መጥቶ አቶ ሙሉነህ አቶ አበበን እገልሃለው ብሎ ሲዝትበት ይውላል። ይህ ተደጋጋሚ ዛቻ ስጋት ውስጥ የከተተው አቶ አበበ ለክፉም ለደጉም በማለት ፖሊስ ጣቢያ አመልክቶ ሲመለስ ያልታሰበ ዱብዳ ይወርድበታል።
ያልታሰበው ቅጥፈት
አቶ አበበ ለብሶ ለክፉም ለደጉም ህግ ያወቀው ነገር ይሻላል በማለት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ስለጉዳዩ አብራርተው ስጋታቸውን አስመዝግበው ወደ ቤት ይመለሳሉ። ገና ከቤት ሲወጡ የት እንደሚሄድ ተከተለህ እየው የተባለው የአቶ ሙሉነህ ልጅ የአክስቱ ባል ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን ተከታትሎ በማየት ለአባቱ መጥቶ ይነግራል። ይሄኔ እንዴት ተደፈርኩ ያለው አቶ ሙሉነህ በመደንፋት ቤት የደበቀውን ሽጉጥ ይዞ ሲወጣ ሁለቱ እህቶቹ ይከተሉታል። ደጅ ቆሞ የእህቱን ባል የሚጠባበቀው አቶ ሙሉነህ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እየደነፋ አካባቢውን ያውካል።
ሀገር ሰላም ብለው ከፖሊስ ጣቢያ ወደ ቤታቸው የሚመለሱት አቶ አበበ ደጅ ሰብሰብ ብለው የቆሙትን ባለቤታቸውንና ወንድም እህቶቻቸውን በአይናቸው ገረፍ በማድረግ ወደ ቤታቸው ሊገቡ ሲሉ። “ አንተ ማን አባክ ስለሆንክ ነው ፖሊስ ጣቢያ ሄደህ የምትከሰኝ፤ ከእንግዲህ በኋላ እዚህ ቤት መኖር አይደለም በህይወት አትቆይም….” በማለት የያዘውን ሽጉጥ ወደ አቶ አበበ
ያነጣጥራል።
በድንጋጤ መካከል የገቡት እህትማማቾችን “ዞር በሉ ሰበብ እንዳትሆኑብኝ..” በማለት ቢጠይቃቸውም እህቶቹ ግን በእንባ መማፀንን ምርጫቸው አድርገው ወንድማቸውን ይለምኑት ጀመር። ምንም ጉዳት አያደርስበንም ብለው እግሩ ስር የተደፉትን እህቶች በትእግስት ማጣትና ንዴት አቅሉን የሳተው አቶ ሙሉነህ በየተራ አቁስሎ ጠላቴ ወዳለው የእህቱ ባል ፊቱን አዞረ።
ከፉከራ ባለፈ ጨክኖ ይሰነዝራል ብለው ያልጠበቁት አቶ አበበ እህቶቹ ላይ ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ለማምለጥ ሙከራ አደረጉ። ፊታቸውን አዙረው ከድንጋጤ የተረፈ ጉልበታቸውን አጠረቃቅመው እግሬ አውጪኝ ብለው ሊሮጡ ቢሞክሩም አንዴ በደም የሰከረው አቶ አበበ እጁን ሳያጥፍ ደጋግሞ በተኮሰው ጥይት የተነሳ እስከ ወዲያኛው አሸለቡ።
“ የገደለው ወንድምሽ የሞተውም ባልሽ፤ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” ይሉት ነገር የደረሰባት ሴት በዚህ ከወንድሟ በተሰነዘረው ጥይት ደሟን እያዘራች በዛ የልጇ አባትን ሞት ሊያውም በወንድሟ ስለመገደሉ ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆና ራሷን ሳተች።
በአካባቢው ነዋሪዎች የድረሱልኝ ጥሪ በቦታው የተገኘው ፖሊስ የቆሰሉትንና አስክሬኑን ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በመላክ ተጠርጣሪውን ይዞ ወደ ህግ ቦታ አመራ።
የፖሊስ ምርመራ
ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ይዞ በህግ ጥላ ስር ካቆየ በኋላ ሆስፒታል ወደ ተኙት እህትማማቾች በመሄድ ቃላቸውን ይቀበላል። ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢውን ነዋሪዎች የአይን ምስክሮችን አንድ በአንድ በመጠየቅ መረጃውን ያጠናቅራል። ወንጀሉም ሆን ብሎ በቂም በቀል ተነሳስቶ የተፈፀመ መሆኑን ከደረሰበት በኋላ ዐቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰርት ያደርጋል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሙሉነህ አሰፋ በ4 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን ታህሳስ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 10፡40 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ልዩ ቦታው የካ ተራራ ትምህርት ቤት አካባቢ የቤት ቦታን አስመልክቶ ከሟች አበበ ለብሶን ጋር በነበረ ፀብ ተከሳሹ እገልሃለው ብሎ
ሲዝትበት ሟች ፖሊስ ጣቢያ አመልክቶ ሲመለስ አስቀድሞ በመዘጋጀት በሽጉጥ ተኩሶ ትከሻውን በመምታት ሲገድለው በስፍራው የነበሩ አልማዝ አሰፋ እና አዲስ አሰፋን ተኩሶ ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ እና የመግደል ሙከራ ወንጀል 3 ተደራራቢ ክሶች ቀርበውታል።
እንዲሁም ተከሳሽ ወንጀሉን የፈጸመበት ሽጉጥ የፀና ፈቃድ ያልነበረው በመሆኑ የጸና ፈቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያ መያዝ እና መገልገል ወንጀል ሌላ ተጨማሪ ክስ የቀረበበት በመሆኑ በአጠቃላይ በ4 የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ቀርቦ ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።
ግራ ቀኙን ያደመጠው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ወሳኔ ለማሳለፍ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ይሰጣል።
ውሳኔ
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው መግደል ወንጀል ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ ድርጊቱን አልፈፀምኩም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ፤ ዐቃቤ ህግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ተከራክሯል።
ምንም እንኳን ተከሳሽ ወንጀሉን አልፈፀምኩም እያለ ሲከራከር ቢቆይም ዐቃቤ ህግ ክሱን በማስረጃ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ ዐቃቤ ህግ ባቀረባቸው 4 ክሶች ጥፋተኛ እንደሆነ ተረጋግጦ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 2/2006 እርከን 38 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኑ 1 ማቅለያ ተይዞለት በእርከን 37 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተከሳሽ በሁሉም መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻር ሲል ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215