ዶክተር ይቅናሸዋ ሰለሞን ይባላል:: በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስነ አዕምሮ ሰልጣኝ ሐኪም ሲሆን፤ በአገራችን ያለው የአዕምሮ ሕመምተኛ መጠን 27 በመቶ አካባቢ እንደሆነ ያስረዳል:: ይህ ደግሞ ከሆስፒታሎቻችን አቅም እንዲሁም ከባለሙያው ቁጥር አንጻር የማይመጣጠን ነው:: በመሆኑም ብዙ ቁጥር ያለውን ታካሚ ለማየት ማድረግ የሚቻለው ነገር ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሆነ ያነሳል::
እስከ አሁን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የሕክምና አገልግሎትን ማግኘት እድሉ ያልነበረ ከመሆኑ አንጻር በርካቶች አገልግሎት ማግኘት ሲገባቸው ሳያገኙ ቀርተዋል:: ይህ ደግሞ አገልግሎት ፈላጊውን በሆስፒታሎች እየተመላለሰ እንዲሰላች አድርጎታል:: ነገር ግን ቴሌ ሜዲስን ኔትዎርክ ማበልጸግ ቢቻል ይህ ነገር በሙሉ መፍትሔ ያገኝ ነበር:: የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የራሳቸው የሆነውን ቴሌ ሜዲስን ማበልጸጋቸው እጅግ የሚያስደስትና እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚፈታ ነው ባይ ነው::
አገልግሎቱ በቦታና በጊዜ የሚገደብ ስላልሆነ በአቅም ችግር በቦታ ርቀት ወደጤና ተቋም መምጣት የማይችሉትን ብሎም መጥተውም የሚፈልጉትን ስፔሻሊስት ማግኘት ላልቻሉ አካላት ባሉበት ቦታ ሆነው የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም የሚፈልጉትን ጠይቀው ተረድተው ምርመራቸውን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል:: የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት ታዞላቸው በቀላሉ እንዲጨርሱም ይሆናሉ:: ይህ ደግሞ በተለይም ከስነ አእምሮ ሕክምና ጋር ተያያዥነት ያለውና ለህክምናውም ከፍ ያለ ጥቅምን የሚሰጥ ሁኔታ አለውም ይላል::
“የሥነ አዕምሮ በሽታ በአብዛኛው በንግግርና በመድኃኒት የሚታከም ሕመም እንደመሆኑ መጠን ቴሌ ሜዲስን ደግሞ ጥሩ አማራጭ ነው:: ግለሰቡ ያለበትን ችግር በቀጥታ ከሐኪሙ ጋር እየተወያየ ሐኪሙም በንግግር የሚመክረውን ምክርም ሆነ የሚያዝለትን መድኃኒት በዛው መጨረስ ይችላል:: ይህ በጣም ፈጣን ቀልጣፋ 24 ሰዓት የሚሠራ በመሆኑ ጥቅሙ የጎላ ነው” ብሏል::
አገልግሎቱ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ የተዘረጋ ነው:: በቀጣይ ሊሠራ የሚገባው ነገር ቴክኖሎጂውን እንዴት መጠቀም ይቻላል የሚለው ላይ ነው፤ ይህንን ደግሞ በመላው አገሪቱ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ በሚያግባባቸው ቋንቋዎች ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው::
በክሊኒካል ፋርማሲስትነት የምትሠራው ሕይወት ግርማ በበኩሏ፤ ቴሌ ሜዲስን አሁን ሀገራችን ያስፈልጋታል ከሚባለው የጤናው ዘርፍ ምርኩዝ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ታነሳለች:: ይህንንም የተገነዘቡት በኮቪድ ወቅት የተስተዋለው የታማሚና የኅብረተሰቡ መራራቅ እንደነበር ታወሳለች:: ስለዚህም ይህንን መራራቅ ለማቀራረብ ደግሞ እንደ ቴሌ ሜዲስን ዓይነት መላዎች በጣም ያስፈልጉ ነበር:: አሁን ላይም ይህ እውን መሆኑ በጣም አስደሳች ነው ትላለች::
ሌሎች አገሮች በዚህ ዘርፍ ብዙ ርቀትን ለመጓዝ ችለዋል:: እኛ ደግሞ ወደኋላ ነበርን:: ነገር ግን ይህ ሥራ ይህንን ርቀታችንን የሚያጠብና እነሱ የደረሱበት ላይ ከማድረስም ባሻገር በጤናው ዘርፍ ላይ ያሉትን ባለሙያዎች በሙሉ ከበሽተኞች ጋር በቀላሉ ለማገናኘት ጥሩ አማራጭ ነውና እንድንጠቀምበት ትመክራለች::
አሁን ሀገራችን ላይ አንድ የጤና ባለሙያ ለ10 ሺህ ሕመምተኞች ነው:: ይህ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው:: አብዛኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በገጠሪቱ የሀገሪቱ አካባቢ ላይ የሚገኙ ናቸው፤ በመሆኑም እነሱም የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻል አንጻር ጥሩ መላ ነው ያለችው ሕይወት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከተማ ላይ ያሉ ሆስፒታሎችም ቢሆኑ የሚያስተናግዱት የታማሚ ቁጥር ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ነገሮችን ያቀልላቸዋልና ማየቱ ያስፈልጋል:: ጤና ሚኒስቴር እንደ ሀገር ዘርፉን ለማሳደግ ችግሮቹን ለመፍታት ሰፋ ያለ ጥረት እያደረገ ብዙ ሥራዎችንም እየሠራ ነው፤ ነገር ግን ውጤታማነቱ ብዙም አይደለም:: እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ጥረቱን ከማገዛቸውም በላይ የሚታዩ ለውጦች እንዲመጡ የራሳቸውም ሚና ይጫወታሉ:: እናም ቢመለከታቸው ስትልም ሀሳቧን ታስቀምጣለች::
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቴክኖሎጂው ይፋ በሆነበት ወቅት እንዳሉት፤ ይህ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ እኤአ በ2020 ሀገሪቱን ወደ ዲጂታሉ ዓለም በይበልጥ ለማስገባት ዓላማ አድርጋ ከምትሠራቸው ሥራዎች ጋር ተያያዥነት አለው:: ስለሆነም ቴሌሜዲስን አፍሪካ ውስጥ ላሉ አዳጊ ሀገራት ብዙ እንቅፋቶችን በማስወገድ አዎንታዊ ፋይዳ ይኖረዋል::
የአሜሪካ ሚዲካል ሴንተር ባለቤት ዶክተር አከዘ ጣዕመም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ:: አክለውም የሕክምና ባለሙያዎች በቁጥር እጅግ አናሳ ናቸው:: እናም አሁን ላይ ባለን የሕክምና ባለሙያዎች አቅርቦት ስሌት የዓለምን ሕዝብ የጤና ሽፋን ለማዳረስ አዳጋች ነው:: ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ሦስት መቶ ዓመታት ይፈጅባቸዋልም:: በዛው ልክ እጅግ እየፈጠነ ያለው የሕዝብ ብዛት ይህንን ስሌት ያባብሰዋል:: ስለሆነም ከማመጣጠን የዘለለ ችግር ያለበትን የሕክምና ባለሙያዎችና ሕክምና የሚያሻቸውን ሕዝቦች ተደራሽ ለማድረግ ቴሌ ሜዲስን ፕላትፎርም ፋና ወጊ ተስፋ ነው ብለዋል:: ታካሚውና የሕክምና ባለሙያው አካላዊ መገኘት ሳያሻቸው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና ሰዎች ሆስፒታል መምጣት ሳይኖርባቸው የሚታከሙበት አማራጭ ነውና ለሕክምናው ዘርፍ የገዘፈ ስኬት እንዳለውም ተናግረዋል::
በአህጉሪቱ ያሉትን የጤና ባለሙያዎች በአንድ ጥላ ስር በዲጂታል የጤና ኔትወርክ ማስተሳሰር ያስችላል የተባለለት ይኸው አገልግሎት አሜሪካን ውስጥ የተጀመረ ሲሆን፤ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ቴሌሜዲስን ኔትወርክ በተናጠል ፤ ብሎም በአህጉሪቱ ስር ያሉትን ደግሞ በአንድ ጥላ የሚተሳሰሩበትን የዲጂታል አሠራርን ይዞ መጥቷል። አገልግሎቱ ደግሞ ዜጎች ከየትኛውም የአህጉሪቱ ክፍል፤ ገጠራማውን አካባቢ ጨምሮ ማንኛውንም አይነት ሕክምና በሚያሻቸው ወቅት ካሉበት ሆነው፥ ስልካቸው ላይ በሚጭኑት ሃባሪዶክ (HabariDoc) የሞባይል መተግበሪያ የሚያሻቸውን የጤና ባለሙያዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ብቻ የማግኘት፣ የማማከር እንደ አስፈላጊነቱም ቀጠሮ የማስያዝ ብሎም ለአገልግሎት የሚያስወጣቸውን ክፍያ በ online የክፍያ ሥርዓት ዝርጋታ መፈፀም የሚያስችላቸው ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215