ክትባት ማለት ሰው ራስን ከበሽታ ለመጠበቅ የሚያስችል መከላከያ ነው:: የክትባት ንጥረ ነገሮች የተገደሉ ወይም የተዳከሙ የቫይረስ ባክቴሪያና ሌሎችም ትልልቅ ጥገኛ ተዋህስያን የተሠሩ ናቸው:: በጥሩ የክትባት ግኝቶችም ብዙ በሽታዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ጠፍተዋል:: በተለይም በወረርሽኝና በተለመደ ሁኔታ የሚነሱ በሽታዎችን ከምንከላከልበት መንገድ አንዱና ዋነኛው ነው:: በዚህም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል በርካታ ክትባቶችን በእርዳታና በተለያዩ መንገዶች እያስገባች ትገኛለች::
ማንኛውም ሕጻን ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ በተቀመጡ የጊዜ ሰሌዳዎች መሠረት ሁሉንም ክትባቶች የማግኘት የመከተብ መብት አለው:: ይህ በትክክል በሆነ ቁጥር ደግሞ አገር ከበሽታ የጸዳ ተተኪ ትውልድን ማፍራት ትችላለች:: አንድ ልጅ የክትባት መርሐግብሩን በአግባቡና በጊዜው ካጠናቀቀ የሚከተሉት በሽታዎችን መከላከል ይችላል:: ለምሳሌ፦ ሜኒንጎካል ሜነጃይተስ፣ ሮታቫይረስ፣ ኩፍኝ፣ መምፕስ፣ ሩቤላ፣ ከወቅት ጋር የሚመጣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ዳይፔቲሪያ ፣ ቴታነስ፣ ውፒንግ ካፍ ፣ፓሊዮ፣ አይነ፣ት ቢ ሂሞፊለስ ኢንፍልዌንዛና የኒሞኒያ በሽታን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው::
ሁሉም ሰው ልጆቹን ከባድ ከሆነ በሽታ ለመከላከል ክትባት ቀላሉ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዘዴ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ሁሉም ክትባቶች ለልጆች እንደሚሰጡ የክትባት መርሐ ግብር አካል በነፃ የሚሰጡ ሲሆን፤ ልጆች ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ ክትባት ወሳኝ የሆነ ዘዴ ነው:: እናም በሕይወት ውስጥ ለመልካም ጅማሮ ክትባት አይነተኛ ዘዴ መሆኑን በመረዳት ልጆችን ማስከተብ ሀገርንም ማገዝ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
ክትባታቸውን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁ ሕጻናት ከተለያዩ የበሽታ አይነቶች የተጠበቁ የመከላከል ብቃታቸውም የዳበረ ሲሆን፤ ያልተከተቡት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለከባድ ሕመም ተጋላጭ፤ በትንሽ በትልቁ ችግር ውስጥ የሚወድቁ ይሆናሉ:: እናም አገራችንም በተለይም እንደ ፖሊዮና ኩፍኝ እንዲሁም ሌሎቹን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከመደበኛው የክትባት ፕሮግራም በተጨማሪ የተለያዩ ዘመቻዎችን በማድረግ ብዙ ርቀቶችን ተጉዛለች:: ያም ሆኖ ግን በተለያዩ ምክንያቶች በክትባት ልንከላከላቸው በምንችላቸውን በሽታዎች ዛሬም ድረስ እየተፈተንን ነው:: በዚህም አሁንም ከመደበኛው የክትባት ሰሌዳ ውጪ በዘመቻ መልክ ክትባቶችን በመላው አገሪቱ ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው::
በያዝነው ዓመት ከታኅሳስ 13 ቀን እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በመላው አገሪቱ በተቀናጀ ሁኔታ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባትን የመደበኛ ክትባት ያልተከተቡና ላቋረጡ እንዲሁም ለሕጻናት ለመስጠት ጤና ሚኒስቴር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል:: ከክትባቱ ጎን ለጎንም አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕጻናት ልየታ ፣የቫይታሚን ኤ ጠብታ እደላ፣የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እደላና ከወሊድ ጋር የተያያዘ ፌስቱላ ያጋጠማቸውን እናቶች ልየታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል::
በተለይም ኩፍኝ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያልጠፋ ከመሆኑም በላይ እስከ አሁንም በዓለም ላይ 140 ሺህ የኩፍኝ ኬዞች ተፈጥረዋል:: በሀገራችንም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሕጻናት ኩፍኝን ጨምሮ ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ክትባት ያላገኙ ስለመሆናቸው በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የክትባት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን ለማ ይናገራሉ:: ስለሆነም ኩፍኝ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትን የሚያጠቃ በጣም ሕመም በማስከተል እስከ ሞት የሚያደርስ ነውና በክትባት መከላከል እየተቻለ ትኩረት ሊነፈገው እንደማይገባ ያስረዳሉ::
ኩፍኝ በሀገራችንም ስርጭቱ ከ ከ1 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከ20 እስከ 50 የኩፍኝ በሽታ ታማሚዎች ይገኛሉ:: ይህ ደግሞ ስርጭቱ ቀላል አለመሆኑን ያሳያል:: በመሆኑም ክትባት መስጠት በሽታው የሚያስከትለውን ሕመምና ሞት ያስቀራል:: ክትባቱንም ሕጻናቱ ሲያገኙ የሰውነታቸውን በሽታን የመከላከል አቅም እንዲጨምር ያደርገዋል:: እናም አቶ ተመስገን እንደሚሉት፤ ክትባቱን ከ95 በመቶ በላይ መከተብ ሲቻል በተከተቡት ሕጻናት ምክንያት ሌሎች ሕጻናትን ከበሽታው መጠበቅ ይችላልና መከተብን ቅድሚያ እንስጠው::
ክትባት ውጤታማ የሚሆነው አንድና ሁለት ሕጻናትን በመከተብ ሳይሆን ከግማሽ በላዩን ማግኘት ሲቻል ነው:: የክትባት ዋና ጥቅምም ይህ ነው:: አንድ ልጅ የኩፍኝ ክትባትን ተከትቧል ለመባል ሁለት ጊዜ መከተብ አለበት:: በዚህም በተወለደ በዘጠነኛ ወሩ ከዚያ በኋላ ደግሞ አምስት ዓመቱ ላይ መከተብ ይገባዋል:: ስለዚህ ኅብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ ልጆቹን ማስከተብ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ::
እስከ አሁን በሀገራችን ይሰጥ የነበረው ልጆች ዘጠነኛ ወር ላይ ሲሆኑ ብቻ ነበር የሚሉት አቶ ተመስገን፤ ከኅብረተሰቡ የግንዛቤ ችግር አንጻር እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች በስፋት በመኖራቸው የኩፍኝ ክትባትን በሁለት ዙር መስጠትን እንደ ሀገር በፖሊሲ ደረጃ ጸድቆ ለመጀመር አስገድዷል:: ይህም ቢሆን ግን የተሠራው ሥራ ውስን በመሆኑ ኅብረተሰቡ እየተረዳውና እየለመደው እንዳልመጣ ያነሳሉ::
የኩፍኝ ክትባት አሰጣጥ ላይ እንደ ሀገርም ችግር ያለብን መሆኑን የሚያሳየው የበሽታው ስርጭትና የመግደል መጠን ከዓመት ዓመት ያለመጥፋቱ ነው:: በዚህም እኤአ በ2015 ላይ 197 የነበረው እኤአ በ2016 ወደ 50 ዝቅ ብሎ ነበር፤ እኤአ በ2021 ላይ ደግሞ 18 ሕጻናት ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ብዙ ጊዜም ዘመቻዎች የሚደረጉትም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት፣ የከፋ ሞትና ሕመም እንዳይመጣ ለማስቻል ነው:: አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የኩፍኝ ወረርሽኝ በመኖሩ ምክንያት የዘንድሮው ዘመቻው ማስፈለጉን ይገልጻሉ::
በአሁኑ ወቅትም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል እንዲሁም አፋር ላይ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ እንዳለ መረጃዎቻችን ያሳያሉ ያሉት አቶ ተመስገን፤ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከፍ ያለ አለመረጋጋት የሚታይባቸው በመሆናቸው አሁንም ተደራሽነቱ ላይ ችግር ያጠላ ሊሆን ይችላል:: እናም ዘመቻውን በተቻለ መጠን ለማድረግና ወረርሽኙን አማራጭ እንዳይጠቀምብን ለማድረግ ይሠራል:: በአሁኑ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ላይም ከተወለዱ ሕጻናት ጀምሮ ምንም ዓይነት ክትባት ያልወሰዱ ፣ ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናት ልየታና ክትባት የሚሰጥ ይሆናል::
ጎን ለጎንም መጠኑ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ይሰጣል:: በተለይም ክትባቱ እስከ አሁን ላልተከተቡ እንዲሁም በጦርነት ቀጠና ውስጥ ለነበሩና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይቸራቸዋል:: በመሆኑም በመላው አገሪቱ ያሉ እናቶች ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ልጆቻቸውን የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲሁም ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸውን ወጣቶች ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባትን በአቅራቢያቸው ባሉ ጤና ኬላዎች ወይም ጊዜያዊ ጣቢያዎች እየሄዱ እንዲያስከትቡ ሲሉ ይመክራሉም::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215