የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ሥነ ቃል ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ እንደሚችል ያስረዳሉ። ነገሩም ግልጽ ነው፤ አንድ አካባቢ የሰማነው የቃል ግጥም ሌላ አካባቢ የተወሰነ ለውጥ ሊኖረው ይችላል። ምሳሌያዊ አነጋገር እንኳን ከቦታ ቦታ የተወሰነ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። ምክንያቱም ነባራዊ ሁኔታዎችም ከአካባቢ አካባቢ ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው።
የዛሬ ትኩረታችን የቃል ግጥሞች ላይ ነው። የቃል ግጥሞች ከምሳሌያዊ አነጋገሮች በበለጠ ከአካባቢ አካባቢ የመለያት ዕድላቸው ሰፊ ነው። በዚህ ጽሑፍ የምናየው የአርሲ አካባቢ ማህበረሰብ የሚጠቀማቸውን የቃል ግጥሞች ነው።
የዚህን አካባቢ የቃል ግጥሞች የምናስተዋውቃችሁ መደርደሪያ ከሚያሞቁ ጥናቶች መሀል ወስደን ነው። እንዲህ ያልኩበት ምክንያት አለኝ። በአገራችን የሚሰሩ ጥናቶች መደርደሪያ ከማሞቅ ውጪ ሲሰራባቸው አይታይምና። እንዲያውም ጥናት እስከ መሰራቱም አይታወቅም። ዩኒቨርሲቲዎች ለሪፖርት ነው የሚያሰሩት።
ተቋማትም ለመርሃ ግብር ማሟያ ነው የሚያሰሩት። ራሱ ሰሪውም ቢሆን ሰራሁ ለማለት ብቻ ይመስላል። ወደ ጥናቱ!
መምህር የሻው ተሰማ (የኮተቤው) በአርሲ ማህበረሰብ የቃል ግጥም ይዘት ላይ ጥናት ሰርተዋል። ጥናቱንም በ2006 ዓ.ም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አቅርበውት ነበር። እነዚህ የቃል ግጥሞች ትልቅ ፍልስፍና ያላቸው ናቸው። የውጭ አገር ፈላስፋ ስናደንቅ እኛው አገር እንዲህ ዓይነት ገበሬዎች መኖራቸውን ግን ዘንግተናል። ምሁራን በእነዚህ ላይ ጥናት አልሰሩልንማ!
መምህር የሻው በጣም ቢመሰገኑም በአንድ ነገር ግን ቅር አሰኝተውኛል። ጥናቱን የሰሩት በአገራችን ቋንቋ ወይም ደግሞ በአካባቢው ቋንቋ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ነው። ደግሞ እኮ በጥናታቸው ውስጥ የአካባቢው ማህበረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ በብዛት አማርኛ እና ኦሮምኛ እንደሆነ ነው ያስቀመጡት። እሺ ኦሮምኛ አይችሉም እንበል፤ ታዲያ ምነው በአማርኛ ቋንቋ አድርገውት ቢሆን? ይህን ለማለት የሚያስችለን ምክንያት ደግሞ የተነተኗቸው የቃል ግጥሞች በአማርኛ ቋንቋ ናቸው። የአካባቢው ማህበረሰብ በአማርኛ የተጠቀማቸው ። ግጥሙን በአማርኛ ያስቀምጡትና ትንታኔው ደግሞ በእንግሊዝኛ ይሆናል።
የተተነተኑት የቃል ግጥሞች ወሰን አላቸው። ደስታ ወይም ምቾት በማጣት ጊዜ የሚባሉ የቃል ግጥሞች ናቸው። ከችግርም ደግሞ በድህነት ምክንያት የሚባሉት ናቸው። የእርሳቸው ጥናት በዚያ አካባቢ ቢያተኩርም በሌሎች አካባቢዎችም የመመሳሰል ዕድሉ ግን ሰፊ ነው። ለምሳሌ አብዛኛው የአገራችን ገበሬ በሥራ የሚወጠረው በክረምትና በመኸር ወራት ነው። በድህነት የሚቸገረውም በክረምት ወራት ነው።
የተተነተኑ የቃል ግጥሞችን እንይ!
አምናም ድህነቴ
ዘንድሮም ማጣቴ
ቁጭ ብዬ ዳርኳት ወዳጄን እንደ እህቴ።
የዚህ ሥነ ቃል አንጎራጓሪ በድህነቱ ምክንያት የሚወዳትን ልጅ አጥቷል። ከእርሱ የተሻለ ሰው አግብቷታል። ምንም ማድረግ ስላልቻለ ልክ እንደ እህቱ ሠርግ ዓይኑ እያየ ሚስቴ ትሆናለች ያላትን ልጅ ዳረ ማለት ነው።
ድህነት ሲመጣ አይነግርም አዋጅ
ሌሊት ሲሄድ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ
ገበሬው ብሶቱንም ደስታውንም እንዲህ በቅኔ ይገልጻል። የሥነ ጽሑፍ ምሁራኑም እንደሚሉት የሥነ ጽሑፍ ጅማሮ ከሥነ ቃል ነው። ይህን ቅኔ የሚያንጎራጉር ገበሬ የድህነትን አስፈሪነት እየተናገረ ነው። ድህነት እንደ ጦርነት ወይም እንደ ሌላ የተፈጥሮ አደጋ በዓይን እየታየ አይመጣም፤ አዋጅ ነግሮ አይመጣም። ቀስ በቀስ ከገባ በኋላ ግን ማጠፊያው ያጥራል።
ቅኔዋ ሌላም ትርጉም አላት። ‹‹ቀን ይጥላል እንጂ›› የምትለዋ ጊዜ ያነሳል ጊዜ ይጥላል የሚለውን የተለመደ አገላለጽ ትነግረናለች። ‹‹ጊዜ ፈራጅ!›› ይባል አይደል?
ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ
ወፍጮው እንዳገሳ መስከረም ዘለቀ።
ሥነ ቃል ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል ለሚለው አንድ ማሳያ አገኘን። ይሄው ሥነ ቃል በሰሜን ሸዋ አካባቢ ‹‹ወፍጮው እንዳገሳ›› የሚለው ‹‹ወፍጮውም ሲያጋምር›› ነው የሚባል። ከዚህ በላይ እንየው ቢባል ራሴ በሰሜን ሸዋና በአርሲም ሌላ የሚባልበት ይኖር ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ግን መልዕክቱ አንድ ነው።
ሲያጋምርም ሆነ ሲያጋሳ ያው ድምጽ ሲያወጣ፣ ሲጮህ ለማለት ነው።
መምህር የሻው ወደሚነግሩን ትርጉሙ እንሂድ
የመስከረም ወር የክረምት ወራት አልቆ ፀሐይ የሚወጣበትና እንደ ብሩህ ተስፋ የሚታይ ነው። በአንጻሩ ክረምት ደግሞ እንደጨለማ ይመሰላል። በክረምት ወራት ደግሞ ድሃ ገበሬ በምግብ እህል የሚቸገርበት ነው። ቤተሰቡ ውስጥ ርሃብ ይኖራል። በቂ እህል የለም ማለት ነው። እህል ከሌለ ደግሞ ወፍጮው ሥራ ይፈታል (ድሮ በድንጋይ ወፍጮ ነበር የሚፈጭ)
ሀብታም ገበሬ ግን አይቸገርም፤ ወፍጮው ሥራ አይፈታም። ሀብታም ለመሆን ደግሞ ግልጹ ነገር ጠንክሮ ማረስ ነው። ሰነፉን ገበሬ ለማንቃት የሀብታሙን ገበሬ እስከ መስከረም ድረስ ወፍጮው ማጋመሩን ማሳያ ተጠቀሙ ማለት ነው።
ከዚሁ ጋር የምትያያዝ ሰነፉን ገበሬ ሸንቆጥ ማድረጊያ አንድ የቃል ግጥም እንጠቀም።
በፀሐይ ፀሐይ ፈሪ
በዝናብ ዝናብ ፈሪ
ልጁን በጅብ አስፈራሪ
ይሄው ሥነ ቃል እንዲህ ተብሎም ይታወቃል
በበጋ እንዳያርስ ፀሐይ እየፈራ
በክረምት እንዳያርስ ዝናብ እየፈራ
ልጁ ‹‹እንጀራ›› ሲለው በጅብ አስፈራራ
የመምህር የሻው ጥናት እንደሚያሳየን የመጀመሪያው የአርሲ አካባቢ መሆኑ ነው፤ ቢሆንም ግን ሁለተኛው ላይ ያለው በዚያ አካባቢ አይባልም ማለት እንችልም፤ መምህር የሻው ያስቀመጡትም በሌላ አካባቢ ሊባል ይችላል። የግጥሞቹ ቅርጽ ተለያየ እንጂ መልዕክቱ ግን አንድ ነው። በቃ የሰነፍ ገበሬ ልጆች ይራባሉ ነው። ሰነፉ ገበሬ ግራ ሲገባው ልጁ ‹‹እንጀራ›› እንዳይለው ያስፈራራል ነው።
የዘንድሮን ክረምት ወጣናት በመላ
በትንሽ ቂጣ ላይ ጎመን ተቆልላ
በብዙ የገጠር አካባቢዎች ጎመን እንደ ርካሽ ነው የሚታየው። ምናልባት ራሳቸው ስለሚያመርቱትም ይሆናል። የሚመገበውም ድሃ ብቻ ነው የሚመስላቸው። ይህን ለማሳየት አንድ የሕዝብ ሥነ ቃል እንጨምር
እስኪ ጎመን ዝሩ ጎመን የድሃ ነው
ሽምብራ ከዘሩ ጠርጣሪው ብዙ ነው
ይችኛዋ ቅኔም አላት። የዚች ቅኔ ሰም ያው ሽምብራ ተወዳጅ ነውና ማንም ይሰርቀዋል፣ ብዙ ሰው ስለሚበላው ባለቤቱ ምንም አያተርፍም ነው። ‹‹እሸትና ቆንጆ አይታለፍም›› ብሎም ራሱ ገበሬው ተርቷል። እንደተባለውም መንገድ ዳር ሽምብራ ያየ ሁሉ ጎራ እያለ ይነቅላል፤ ጎመን ቢሆን ግን ማንም አይነካውም።
የዚች ቅኔ ወርቅ ግን ሌላ ነው። ቆንጆ ሚስት ያገባ ሰው ብዙ ሰው ይመኛታል ለማለት ነው።
የጎመን ነገር ብዙ አስባለን አይደል? እንግዲያውስ ይሄን አባባልም እንጨምረው። ‹‹ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይደክማል›› ይላል ገበሬው። አሁንም የጎመንን አይረቤነት እየነገረን ነው።
የጎመንን ነገር ስንጠቀልለው በክረምት የሚቸገረው ድሃ ገበሬ ትንሽ ቂጣ ካገኘ ብዙ ጎመን ያደርግበትና ቀን ይወጣል ማለት ነው።
እስኪ ከቃል ግጥሞች በተጨማሪ ደግሞ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንመልከት። ከእነዚህም በእንስሳት ወኪልነት የተባሉትን እንጠቀም።
‹‹በሞኝ ክምር ዝንጀሮ ልጇን ትድር›› ይባላል። ዝንጀሮ የሚመገበው የገበሬዎችን ሰብል ነው። ጎበዝ ገበሬ ሰብሉን ስለሚጠብቅ ዝንጀሮን አያስነካውም። ሰነፍ ገበሬ ግን ስለማይጠብቀው ዝንጀሮ ይጫወትበታል። ሞኝ የተባለው ምናልባትም ሰነፉን ይሆናል።
እንዳልኳችሁ ምሳሌያዊ አነጋገር ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። መምህር የሻው ተሰማ ‹‹ወፍ የሚፈራ ዘንጋዳ አይዘራም›› የሚል አባባል ተጠቅመዋል። ይሄን አባባል የማውቀው በተቃራኒው ‹‹ወፍ የሚፈራ ዘንጋዳ ይዘራል›› በሚል ነው። ምክንያቱም ዘንጋዳ የሚባለው የማሽላ ዓይነት ወፍ አይበላውም። እንግዲህ በአርሲ አካባቢ ዘንጋዳ የሚባለው የማሸላ ዓይነት ወፍ ይበላዋል ማለት ነው።
እንግዲህ የሥነ ቃል ሀብቶቻችን እንዲህ ናቸው። በውስጣቸው ብዙ ፍልስፍና የያዙ። የዘርፉ ሰዎች በእንዲህ
ዓይነት አገርኛ ፍልስፍናዎች ላይ ጥናት ስሩልን!
በእንስሳት ወኪልነት ስለሚነገሩ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና የቃል ግጥሞች ደግሞ የተወሰኑትን እንይ። ሰዎች የልባቸውን መናገር ሲፈልጉ በእንስሳት መስለው ይናገራሉ። ልክ ሰውኛ ዘይቤ እንደምንለው ማለት ነው። ለምሳሌ
‹‹ምን ቢታለብ ያው በገሌ›› አለች ድመት፣ ‹‹ለሰው ሞት አነሰው›› አለች ቀበሮ፣ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አለች አህያ፣ ‹‹የቆዳን አበላል እናውቅበት ነበር›› አለ አያ ጅቦ፣ ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን›› አለች ዝንጀሮ… የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሰዎችን ባህሪ መናገር ሲፈልጉ በእንስሳት ባህሪ ይወክሉታል። ለምሳሌ ከጦጣ ጋር የዋለ ጉሬዛ እህል ፈጅቶ ይገባል። ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲስል ያድራል… ይባላል። እነዚህ ሁሉ የተባሉት ለሰው ነው። ለምሳሌ ከጦጣ ጋር የዋለ ጉሬዛ እህል ፈጅቶ ይገባል የተባለው ከሰው ጋር ሆነው ባህሪያቸው ለሚበላሽ ሰዎች ነው። ጉሬዛ እህል አይበላም፤ ጦጣ ደግሞ የእህል ፀር ነው። ባይበላው እንኳን ያበለሻሸዋል። እናም ይሄ ጉሬዛ ጦጣውን ሲያይ እሱም ማበለሻሸት ያምረዋል። ተምሳሌትነቱን ወደ ሰዎች ስናመጣው አንድ ጫት የማይቅም ወጣት ውሎው ጫት ከሚቅሙ ጋር ከሆነ እሱም ይለምዳል ማለት ነው። በአጠቃላይ እሱ የሌለበትን መጥፎ ባህሪ ከሌሎች ይለምዳል ማለት ነው።
‹‹ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲስል ያድራል›› የተባለውም ለሰዎች ነው። ጥንቃቄ የማያደርግ ሰው እንከን ያጋጥመዋል። ምግብን እንኳን በሚገባ አይቶና አላምጦ ካልሆነ ሌላ ያመጣበታል ማለት ነው።
እንስሳት ከሰው ጋር እንደተነጋገሩ ተደርጎም ተገጥሟል። ይህም የሚሆነው ሰዎችን በነገር ነካ ለማድረግ ነው። ለምሳሌ ዘንጀሮ ጠባቂን እንዲህ ይሉታል።
የኔማ አቶ እገሌ የጠይም ስብቅል
ከስንዴው ጠግበናል ውሃ አምጣልን በቅል
እንዲህ ምትል እንግዲህ ዝንጀሮዋ ናት። ሰውየው ዝንጀሮ ሰብሉን እንዳይበላው መጠበቅ ነበረበት። ሰነፍ ሆኖ ካስበላው ራሳቸው ዝንጀሮዎችም ይሳለቁበታል ማለት ነው። መምህር የሻው ተሰማ በአርሲ አካባቢ እንዲህ እንደሚባል ነግረውናል። የዚሁ ተመሳሳይ ደግሞ ሌላም ስነ ቃል አለ። አሁንም የዝንጀሮዎች ነው።
እገልዬ እገሌ የጦፈው ገበሬ
ሰው ገሎ ለአሞራ እህል ዘርቶ ለአውሬ
ይሄን የሚባለው ሰውየው ሰብሉን የማይጠብቀው ከሆነ ነው። አንዳንዱ ገበሬ በስንፍና ወይም በሌላ ሥራ በመወጠር የዘራውን ሰብል ለአውሬ ይተወውና ሙሉውን ይበላል።
በሌላ በኩል ደግሞ ዝንጀሮዎች በሰውየው እንዲህ ይሳለቁበታል።
በግርጌ ገብቸ በራስጌ ስወጣ
እገልየ እገሉ ‹‹ጉድ!›› እያለ መጣ
‹‹ጉድ!›› ማለቱን ትተህ ለጣቴ ውሃ አምጣ
ዝንጀሮዋ እንዲህ አለችህ ተብሎ ነው እንግዲህ ለሰነፉ ገበሬ ሚነገረው። የዝንጀሮ ጥበቃ በጠዋት ተነስቶ ነው። ሰነፍ ከሆነ ግን ያረፍድና ሰብሉን ዝንጀሮ በግርጌ ገብቶ በራስጌ ይወጣበታል ማለት ነው።
ሌላ ደግሞ አስቂኝ የዝንጀሮዎች ምጸትም አለች። የገበሬውን ሰብል ውድም አድርጎ ከበላ በኋላ እንዲህ ይላል።
ይሄ ጥራጥሬ ሆዴን አመመኝ
እባክህ እገሌ አረቄ አምጣልኝ
በገጠር አካባቢ አረቄ የሆድ መድሃኒት ተደርጎ ይታሰባል። የጥራጥሬ ምግብ ደግሞ ሲበዛ ሆድ ያማል። ያንን አረቄ ይበትነዋል ተብሎ ይታሰባል።
አንድ የዝንጀሮ ስነ ቃል እንጨምርና ይብቃን።
እገልየ እገሌ ዋሻዬን አረሰው
ይታዘብ እገሌ አንድ ራስ ባቀምሰው
ዝንጀሮ የሚኖረው በገደላማ ቦታና በጫካ ውስጥ ነው። ገበሬው ደግሞ ለእርሻ ማሳ ብሎ ጫካውን ጨፍጭፎ ያርሰዋል። እንግዲህ ዝንጀሮዋ ይህን ስትል ግዛቱ የኔ ነውና ይገባኛል ማለቷ ነው። እሱ ነው የኔን መኖሪያ መጥቶ ያረሰ እንጂ እኔ አልደረስኩበትም እንደማለት ነው። እምቢ ብሎ ከመጣም ልብ አድርጎ አንዲት ራስ እህል አያገኝም እንደማለት ነው።
ከዚህ ሁሉ ምንረዳው የገበሬዎችን እና የእረኞችን ከያኒነት ነው። በደመ ነፍስ የሚኖሩትን የማይናገሩ እንስሳት እንኳን እንዲህ እንዲናገሩ ያደርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011
በ ዋለልኝ አየለ