በርካታ የስፖርት አይነቶች በኢትዮጵያ ጥሩ እንቅስቃሴና እድገት እንደነበራቸው በሚነገርበት 1970ዎቹ የእጅ ኳስ ስፖርት ትልቅ ስም ነበረው። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ስፖርት ፌዴሬሽንም የተቋቋመው በ1970 ሲሆን ወርቃማ ዘመኑም በነዚህ ዓመታት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ሌሎች አገራት ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች ከተሳትፎ በዘለለ ወርቅ የሚመዘገብበት ስፖርት አሁን ላይ በኢትዮጵያ እንቅስቃሴና እድገቱ እዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን በአፍሪካና በአለም ታላላቅ መድረኮች ስሟን ማስጠራት የቻለ ነው።
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተመሰረተበት ጊዜ ስፖርቱ በአዲስ አበባ ብቻ ይካሄድ እንደነበር ይነገራል:: ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በ1971 የአለም ዓቀፉ እጅ ኳስ ፈዴሬሽን አባል መሆኗን ተከትሎ በ1972 በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በተዘጋጃው ኦሊምፒክ ሳይቀር ኢትዮጵያ መሳተፏን የሚጠቁሙ መረጃዎችም አሉ። የደርግ መንግስት ወደስልጣን ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም በሚሊተሪ ተቋማት ውስጥ በርካታ ስፖርቶች ለሁለት አስርት ዓመታት የተሻለ እንቅስቃሴ ሲደረግባቸው እጅ ኳስ አንዱ ነበር። ለዚህም ስፖርቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ክለቦችን በማወዳደር ጥሩ የእድገት ጎዳና ላይ እንደነበር ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ስፖርት እንደ አብዛኞቹ ስፖርቶች ሁሉ ባለፉት ሰላሳ አመታት ሽቅብ እንደ ማሽላ ከማደግ ይልቅ ቁልቁል እንደ ካሮት ማደጉ የአደባባይ ሃቅ ነው። ፌዴሬሽኑን በተለያዩ ጊዜያት የመሩ ሰዎች ስፖርቱን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ ቢናገሩም መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር የለም። በየትኛውም ጊዜ ፌዴሬሽኑን የመሩ ሰዎች የሚጋሩት አንድ ነገር ግን ተደጋግሞ ይነሳል። ይህም እጅ ኳስን ለማሳደግ እጅ አጥሮናል የሚል ነው።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት በርካታ አመታት ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ ማደግ ባለበት ደረጃ ባይጓዝም አንድ አበረታች ጅምር ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ ማሳየቱ አይካድም። ይህም በዘወትር ችግሩ የበጀት እጥረት እየተፈተነም ቢሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ክለቦችን በፕሪሚየርሊግ ማወዳደሩ ሲሆን ዘንድሮም ይህንኑ ውድድር ለሰባተኛ ጊዜ እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ሞላ ተፈራ፣ የእጅ ኳስ ስፖርትን ለማሳደግ እና ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በመላ አፍሪካና በአለም አቀፍ መድረኮች ተፎካካሪ ለማድረግና ብቁ ስፖርተኞችን ለማፈራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል:: ለዚህም የፌዴሬሽኑ የዘወትር እንቅፋት ከሆነው የበጀት እጥረት ለመላቀቅ የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል። “ከመንግስት የሚመደበው በጀት በቂ ባለመሆኑ ከሌሎች ስፖንሰር አድራጊዎች ጋር በመስራት ስፖርቱን ለማገዝ ጥረት እየተደረገ ነው” ያሉት የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ በቂ ባይሆንም ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ድገፍ እንደሚያደረግለቸው ገልጸዋል። ሌሎችም የነዚህን ተቋማት አርአያ በመከተል ድገፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘው የጽህፈት ቤት ሃላፊው እንደተናገሩት “ስፖንሰር ለማግኘት ብዙ አስቸጋሪ ጉዳዮች አሉ፣ ተቋማትና ድርጅቶች ስፖርቱን በገንዘብ ለመደገፍ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ከማቅረብ ይልቅ ከጥቅም ጋር የማገናኘት ነገር ይታያል” ::
ለስፖርቱን ለማንቀሳቀስና ውድድሮችን በስፋት ለማካሄድ ትልቅ የበጀት እጥረት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ሞላ፣ አሁን ክለቦች የሚወዳደሩበትን ፕሪሚየርሊግ እንኳን ከመንግስት ውስን በጀትና ከተወሰኑ ስፖንሰሮች ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች እያንዳንዳቸው 60ሺ ብር ከፍያ ፈጽመው እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል:: ይህም ከክለቦች የሚገኘው ክፍያ ለውድድሩ ማካሄጃ እንደሚውል አስረድተዋል። ይህን ችግር ተረድተውም የሚመለከታቸው አካላት ስፖርቱን እንዲደግፉ አቶ ሞላ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::
ከፕሪሚየርሊጉ ውድድር በተጨማሪ ስፖርቱን መሰረት ለማስያዝና እድገቱ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በመክፈት ለፕሪሚየርሊጉ ክለቦች ተጫዋቾችን መጋቢ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ሞላ ተናግረዋል:: ፌዴሬሽኑ የሴቶች ፕርሚየርሊግንም ለመጀመርና በሴቶች የእጅ ኳስ ኢትዮጵያን በተለያዩ መድረኮች የሚወክል ቡድን ለመፍጠር እየሰራ እንደሆነ አክለዋል።
የ2015 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕርሚየርሊግ ውድድር ከታህሳስ 9/2015 ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ስቴድየም እየተካሄደ ይገኛል:: ውድድሩ ከ1ኛ እሰከ 4ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚደረግና እስከ ታህሳስ 18 እንደሚቆይም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ፕሪሚየርሊጉ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን አስር ክለቦችን ያፎካክራል:: ውድድሩ እስከ አራተኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ተካሄዶ ወደ ሌሎች አዘጋጅ ከተሞች እንደሚያመራም ይጠበቃል። ከአራተኛ ሳምንት በኋላም ውድድሩን የሚያስተናግዱ ከተሞች ድሬዳዋና ባህርዳር ይሆናሉ:: በውድድሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ መቻል፣ ኦሜድላ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ባህርዳር ከነማ፣ ፌደራል ማረምያ፣ ከምባታ ዱራሜ፣ ፋሲል ከነማ፣ ሚዛን አማን ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ናቸው:: ውድድሩ በዓመት በአጠቃላይ ዘጠና ጨዋታዎችን በማስተናገድ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015