ኢትዮጵያ የምድር ውስጥ ገፀበረከቶቿ በሆኑት የማዕድን ሀብቶቿ ተጠቃሚ ለመሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች:: የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ፣ ለአምራች ኢንደስትሪ፣ ለግንባታና ለጌጣጌጥ የሚውሉ ማዕድኖችን ለይቶና የመገኛ ሥፍራዎችን ጭምር የያዘ ሰነድ ማዘጋጀት፣ የማዕድን ጋለሪ ከፍቶ ለኢንቨስትመንት ምቾት በመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች እየተከናወነ ለሚገኘው ርብርብ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ::
በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዩኒቨርሰቲዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር፣ከባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር በመፍጠር በዘርፉ ላይ የሚያጋጥሙ የህገወጥ ግብይትና መሰል ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት፣ ዘርፉን ለማዘመን፣ በዘርፉ በተለይም የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅን በውጭ ኩባንያዎች በማስጠናት፣ በማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ሀብቱን ለዓለም በማስተዋወቅ የተከናወኑ ተግባሮችም ሌሎች ጥረቶች ናቸው::
የማዕድን ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የስራና የገቢ አማራጭ በመሆን ያገለግላል፤ ስራው በተቀናጀ መልኩ እንዲመራ በማድረግ ለዜጎችም ለሀገርም ይበልጥ እንዲጠቅም ለማደረግ ዘርፉን የሚመራው ማዕድን ሚኒስቴር ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በሰው ሀይል ልማት፣ቴክኖሎጂ፣ ስራ ፈጠራና የስራ አካባቢ ደህንነት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል:: እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የሚደረጉት የማዕድን ዘርፉ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማስቻል ነው::
ይሁን እንጂ የማዕድን ዘርፉ ማነቆ የሆነውን ህገወጥ ንግድ ለመከላከል የተደረገው እንቅስቃሴ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ይገኛል::ለዚህም ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባት ያለበት የወርቅ መጠን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መምጣት አንድ ማሳያ ተደረጎ ሊወሰድ ይችላል::
በአንድ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በባህላዊ የወርቅ ማዕድን ምርት ላይ የተሰማሩትን የአካባቢውን ወጣቶችም ሆኑ ከውጭ ዜጎች ጋር በመመሳጠር የሚደርጉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ሥርዓት የማስያዝ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል::
በቅርቡም ሚኒስቴሩ ካወጣው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፤ ሚኒስቴሩ ወደ ቁጥጥር ስራው ገብቷል፤ በጉዳዩ ላይም ማዕድን ሚኒስቴር ማንኛውም ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች በእጁ ያለውን ወርቅ ወደ ቢሄራዊ ባንክ እንዲያስገባ ያሳሰበ ሲሆን፣ በቀጣይ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ወርቅ ወደ ቢሄራዊ ባንክ በማያስገቡት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስገንዘቡን በድረገጹ አስነብቧል::
ሚኒስቴሩ በፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር የሚመራ የተቀናጀ የማዕድን ቁጥጥር ኦፕሬሽን ቡድንና በጋምቤላ ክልል በዲማ ወረዳ ከሚገኙ ከልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ጋርም ውይይት መደረጉን ታህሳስ 5ቀን2015ዓ.ም በድረገጹ አስነብቧል::
የውይይቱ ዓላማ ህገወጥ የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር በዲማ ወረዳ የሚመረተው ወርቅ በህጋዊ መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማስቻል ነው :: የማዕድን ሚኒስቴር በወርቅ ኮንትሮባንድ ዙሪያ እንደ ሃገር አራት ቡድኖችን አደራጅቶ ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች አሰማርቷል፤ ከነዚህ አካባቢዎች አንዱ ዲማ ወረዳ ነው:: ከጥቅምት 23 ጀምሮ በስፍራው ተገኝቶ ስራውን የጀመረው ቡድኑ ያሉትን ችግሮች መለየቱንም ሚኒስቴሩ በድረገጹ አመልክቷል::
ከአካባቢው መስከረም ወር ላይ ብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ስድስት ኪሎግራም ብቻ እንደነበርና ቁጥጥሩ ከተጠናከረ በኃላ መጠኑ መጨመሩን መረጃው አስታውቋል:: ቡድኑ ባደረገው ቁጥጥር ከአካባቢው በጥቅምት ወር 2015ዓ.ም 10 ኪሎግራም፣ በህዳር ወር 2015ዓ.ም 18 ኪሎግራም ወርቅ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል:: ቡድኑ ባደረገው ኦፕሬሽን በኮንትሮባንድ የወርቅ ዝውውር የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል::
በሌላ በኩል በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች፣ህገወጥ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ፣ በመንግሥት በኩል በቂ ቁጥጥር አለማድረግ የሚሉ አስተያየቶችንም የልዩ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራቾች ማንሳታቸው በዘገባው ተጠቅሷል:: በዚህ በኩል መንግሥት የሚጠበቅበትን እንደሚሰራን በሚኒስቴሩ ተገልጿል::
ከወራት በፊት ጀምሮ የወርቅ ልማቱ በሚከናወንበት ዲማ ወረዳ ውስጥ ሆነው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ካሉት መካከል የጋምቤላ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ዋና የሥራ ሂደት ሃላፊ አቶ ሙድ ሎንግ አንዱ ናቸው:: አቶ ሙድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል እስከ አንድ መቶ ኪሎ ግራም ለብሄራዊ ባንክ ይገባ የነበረው ወርቅ እጅግ ማሽቆልቆሉን አቶ ሙድ ጠቅሰው፣ ይህ የሆነው ወርቅ አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ ለጥቁር ገበያ በማቅረብ ከሀገራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን በማስቀደማቸው ነው::
ክፍተቱ የተፈጠረው ከቁጥጥርና ክትትል መላላት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ህገወጥነቱ እየከፋ በመምጣቱ በቢሮአቸው ተወክለው ከግብረ ኃይሉ ጋር የመከላከሉን ሥራ ለመሥራት ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ የወርቅ ልማቱ በሚከናወንበት ዲማ ወረዳ እንደሚገኙ ተናግረዋለ::
ከተለያዩ አካላት ከተውጣጣ ግብረኃይል ጋር በመሆን በፀጥታ ኃይል በመታገዝ ከሶስት ወራት በፊት የተጀመረው የተቀናጀ እና የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ ለውጥ አስገኝቷል ሲሉም ገልጸዋል::
የቁጥጥር ሥራው ከተጀመረ አንስቶ በተከናወነው ተግባር ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ከ10 ኪሎ ግራም ወደ 18 ኪሎግራም ከፍ ብሏል ሲሉም አቶ ሙድ ተናግረዋል:: የቁጥጥር ሥራውን ለመሥራት የተዋቀረው የግብረኃል ቡድን የተጠናከረ ሥራ እንዲሰራ ለተጨማሪ ጊዜ በስፍራው እንዲቆይ መደረጉን ጠቅሰው፣ በዚህም የክትትልና ቁጥጥሩ ስራ መጠናከሩን ይገልጻሉ::
በግብረ ኃይሉ ውስጥ የክልሉ ማዕድንና ሀብት ልማት ቢሮን ጨምሮ ፖሊስ፣ ፍትህ፣ሰላምና ፀጥታ በአጠቃላይ የፀጥታ ኃይል፣ የጉሙሩክ ባለሥልጣን፣ ቱሪዝም ኮሚሽን፣ የወረዳ ተወካዮች ተካትተውበታል ሲሉም ነው ያብራሩት::
በአካባቢው እየለማ ያለው የማዕድን ሀብት ህጋዊ በሆነ አሰራር እንዲመራ ለማስቻል የግብረ ኃይል ቡድን ተዋቅሮ እየተከናወነ ያለው ተግባር በጊዜያዊነት የተወሰደ መፍትሄ መሆኑ ይታወቃል:: ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተቀመጠ አቅጣጫ ይኖር እንደሆን አቶ ሙድ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳመለከቱት፤ በግብረ ኃይሉ ህገወጥነትን ለመከላከል የተዘረጋው አሰራር በዘላቂነት ለሚወሰደው እርምጃም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ ወረዳውና ዘርፉን የሚመራው አካል ተቀናጅተው አሰራሩን ለማስቀጠል ቁጥጥርና ክትትሉ እንዲጠናከር ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል:: ቢሮውም በየወሩ በሥፍራው በመገኘት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል::
በአካባቢው ያለው የወርቅ ሀብት እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ሙድ፤ በተለይ እንደ ክልል ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ነው ያሉት:: ሀብቱን በአግባቡ በማልማት በሀገር ደረጃ የተቀመጠውን አሰራር ተከትሎ ግብይቱን መፈጸም እንደሚገባ ክልሉ ያምናል ሲሉም ገልጸዋል:: ህጋዊ መስመርን የተከተለ ግብይት የክልሉንም ገቢ በማሳደግ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰው፣ ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ከተቻለ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እንደሚውልም አስረድተዋል::
የጉሙሩክ ኮሚሽንን በመወከል በቡድን በተዋቀረው ግብረኃይል ውስጥ የሚሰሩና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ አባል በሰጡት አስተያየት የግብረ ኃይሉ ዋና ተልእኮ የተመረተው የወርቅ ማዕድን ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል:: ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል:: በቡድኑ እየተከናወነ ባለው ተግባር ህገወጦችንም ለህግ በማቅረብ ስራውንም ህጋዊ መስመር የማስያዝ ሥራ ጎን ለጎን እየተሰራ ነው ይላሉ::
እርሳቸው እንዳሉት፤ ህገወጥ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ አመላካች ነገር መኖሩን ቡድኑ ደርሶበታል:: በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መፍታት ተችሏል ማለት ባይቻልም፣ ለውጥ ማምጣት ግን ተችሏል:: በህገወጥ ድርጊቱ ተሰማርተው ተገኝተዋል የተባሉ ስድስት ሰዎችንም በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል:: እነዚህ ግለሰቦች ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ ከሁለት አመት እስከ አምስት ወር እንዲሁም ከሶስት አመት እስከ አምስት ወር በእስራት የሚቀጡ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከ50ሺ እስከ አንድ መቶ ሺ ብር የቅጣት ውሳኔ ይጠብቃቸዋል::
ከጥቅምት ወር ጀምሮ በግብረኃሉ በተከናወነው ሥራ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ 80 በመቶ መጨመሩንም ነው የግብረ ህይሉ ቡድን አባል የጠቆሙት:: ህገወጥነትን ለመከላከል በአንድ ወረዳ ላይ በተጀመረው ሥራ የተገኘው ውጤት ህገወጥነትን ለመከላከል እንደሚቻል አመላካች ሆኖ ተገኝቷል ሲሉም አመላክተዋል:: ህገወጥነቱን መከላከል ቢቻል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ማዕድን ልማት በአካባቢው መኖሩን ለመታዘብ መቻሉንም ነው የገለጹት::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ህገወጥ ድርጊቱ እዚያው አካባቢ በሚኖሩ አንዳንድ ህገወጦች እንደሚፈጸም በክትትልና ቁጥጥሩ ማረጋገጥ ተችሏል:: የአካባቢውን ማህበረሰብ የማስተማርና የማንቃት ሥራ ቢሰራ ችግሩን ለመቀነስ ይጠቅማል:: ጉሙሩክ በወጪና ገቢ ንግዶች ላይ የሚያደርገውን የቁጥጥር ሥራ በወርቅ ማዕድን ላይም ማድረግ ይኖርበታል::
በአካባቢው በማህበር ተደራጅተው ወርቅ ለማምረት መሬት ከወሰዱ ወጣቶች ላይ በኪራይ ወስዶ እየሰራ የሚገኘው የአዲቢሩ ድርጅት የሥራ ኃላፊ ወጣት ፖል በግሉ ህጋዊ ሆኖ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል::
ወጣቱ ህገወጥ ድርጊቱን ይቃወማል፤ ድርጊቱ እንዲጠፋም ነው የሚፈልገው:: ወርቅ ሀገራዊ ጥቅም እንዲያስገኝ የክትትልና ቁጥጥሩ ሥራ የመንግሥት ብቻ መሆን እንደሌለበት ጠቅሶ፣ አምራቹም፣ የአካባቢው ማህበረሰብም በቁጥጥር ላይ አብረው መሥራት እንዳለባቸው አመልክቷል::
ወጣት ፖል ለህገወጥ ድርጊቱ መስፋፋት ምክንያት ናቸው ያላቸውንም ጠቁሟል:: እርሱ እንዳለው፤ ለልማቱ ሥራ የሚያስፈልገው ነዳጅ በአካባቢው ከተመን በላይ እየተሸጠ ነው:: በዚህ ዋጋ ነዳጅ እየገዙ መስራት ያስቸግራል:: ብሄራዊ ባንክ ከአምራቾች የሚቀበልበት የወርቅ ዋጋም መሻሻል እንዳለበት ጠይቆ፣ አለበለዚያ ምርቱን ጥቁር ገበያው ይቆጣጠረዋል ሲል ስጋቱን ጠቁሟል::
አቶ ሙድ በጋምቤላ ክልል ወርቅ የሚገኝባቸው አካባቢዎች በአኝዋክ ብሄረሰብ ዞን ዲማ፣ አቦቦና ጋምቤላ ወረዳዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ:: አቦቦ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የወርቅ ክምችት አካባቢው በደን የተሸፈነና ደኑም በዓለም የባህል የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ በመሆኑ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቸለም ሲሉ ያመለክታሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ሌላው ችግር በአካባቢው ውሃ አለመኖሩ ነው:: ከመሬት ውስጥ በቁፋሮ የሚወጣውን ወርቅ ከጭቃ ለመለየት ውሃ ያስፈልጋል:: መንገድን ጨምሮ የመሠረተ ልማት አለመሟላትም ሌሎች ችግሮች ናቸው:: በነዚህ ምክንያቶች ሳቢያ የዚህ አካባቢ ወርቅ ለጊዜው ጥቅም ላይ አልዋለም::
ሌሎች ወረዳዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው:: ጋምቤላ ወረዳ ላይ ያለው ችግር ደግሞ በአካባቢው የሚገኘው የባሮ ወንዝ ለከተማዋ የመጠጥ ውሃ ስለሚውል ብክለት በማስከተልና የከተማ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው ሆኖ በመገኘነቱ ምክንያት ለማልማት አልተመረጠም::
የወርቅ ማእድን ልማቱ እየተከናወነ ያለው በዲማ ወረዳ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ክልሉ በመሳሪያና በተለያየ መንገድ የተደራጀ አቅም ባለመፍጠሩ በዚያ አካባቢ ያለው የወርቅ ሀብት መጠን ለመለየት አልተቻለም ይላሉ:: በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በተደረገ ጥናት ግን በዲማ ወረዳ የተሻለ የደለል ወርቅ ክምችት መገኘቱ ተጠቁሟል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህንንም ክልሉ ጥቅም ላይ እያዋለው ይገኛል ብለዋል::
የወርቅ ልማቱም በስፋት እየተከናወነ ያለው በአካባቢው ማህበረሰብና በማህበር በተደራጁ ወጣቶች በባህላዊና አነስተኛ ወርቅ አምራች በሚባሉት ነው:: ስቴላ እና ኢትዮ ኖርዌይ የሚል መጠሪያ ያላቸው ኩባንያዎችም በልማቱ ተሰማርተዋል፤ ስቴላ ወደ ማምረት ገብቷል፤ ይሁንና ግን እሱም በሚጠበቅበት በኩባንያ ደረጃ እያመረተ አይደለም::
ኢትዮኖርዌይም ገና በጥናት ሥራ ላይ ቢሆንም፣ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው:: በልማቱ ላይ በሚገኙት እየተከናወነ ባለው ሥራ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወርቅ ማጠቢያና መቆፈሪያ (ስካቫተር) ዘመናዊ መሳሪያ ወይም ማሽን በመጠቀም የተሻለ እንቅስቃሴ እየታየ ነው::በአካባቢው እየተከናወነ ያለው የወርቅ ማዕድን ልማት የቆየ ቢሆንም፣ ከ2012ዓም ጀምሮ ግን የተሻለ እንቅስቃሴ እየታየ ይገኛል::
ለብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የወርቅ ህገወጥ ግብይትን ለመቆጣጠር በፌዴራል መንግስትና በክልሎች በተቀናጀ መልኩ የተጀመረው ርብርብ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ያመላከት ውጤት እየታየበት ስለመሆኑ የዲማ ወረዳ ተሞክሮ ያመለክታል:: ተመሳሳይ ስራዎችን በሌሎች ወርቅ አምራች አካባቢዎች በማከናወን የወርቅ ምርቱን ከህገወጦች መታደግ ያስፈልጋል:: ዘላቂ መፍትሄ ማመላከትም ይገባል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015