ይህ ወቅት በአትሌቲክስ ስፖርት በብዛት የአገር አቋራጭ ውድድሮች የሚካሄዱበት ነው። በመሆኑም የተለያየ ደረጃ የተሰጣቸው የአገር አቋራጭ የዙር ውድድሮች በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሁለተኛ ወር አጋማሽ ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት የሚከናወነው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ይካሄዳል። ይህንን ውድድር ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ የምታስተናግደው አውስትራሊያ ናት።
ይህ ውድድር እአአ ከ1973 ጀምሮም ሳይቆራረጥ እአአ እስከ 2019 ድረስ ቢካሄድም በኮቪድ 19 ወረርሽን እና ሌሎች ምክንያቶች እየተራዘመ በ2023 ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በውጤት ረገድ የበላይነቱን የያዙ ሲሆን፤ በተለይ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት አላቸው። ይሁንና በወንዶች በኩል እአአ ከ2013 ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ውጤታማነት ይዛ መቀጠል አልቻለችም። በ2019 ደግሞ በግል የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት አልቻለችም፤ በቡድንም ሶስተኛ ነበረች።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በረጅም ርቀት ውድድሮች ስኬታማ መሆናቸው ይታወቃል። ልምምድ የሚያደርጉባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎችና የመልከዓ ምድር አቀማመጥም በርካታ መሰናክሎች ባሉት አገር አቋራጭ ውድድር ስኬታማ ለመሆን ምክንያት ሆኗቸዋል። በኢትዮጵያም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የሚዘጋጀውና በዓለም አትሌቲክስም ዕውቅና የተሰጠው ብቸኛው ዓለም አቀፍ ውድድር የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር ነው። በመሆኑም አገር አቋራጭ ውድድሮች ለኢትዮጵያ እንደሌሎች ረጅም ርቀት ሩጫዎች ሁሉ ውጤት ሊመዘገብበት የሚችል የሩጫ ዘርፍ ነው ለማለት ይቻላል።
በእርግጥም እንደ መሃመድ ከድር እና ቀነኒሳ በቀለ ያሉ አትሌቶች በዚህ ርቀት ያገኟቸው አስደናቂ ድሎች ለዚህ ማስረጃ ይሆናሉ። የዓለም አቀፉ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ተሳትፎ መነሻውን የሚያደርገው እአአ በ1981 ነው። በስፔን ማድሪድ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይም መሃመድ ከድር የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ ታሪካዊ አትሌት ሊሆን ችሏል። አትሌቱ በቀጣዩ ዓመት ውድድሩን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፤ እአአ በ1983 ደግሞ በቀለ ደበሌ ድሉን ማስቀጠል ችሏል። ወዳጆ ቡልቲ እና አበበ መኮንን እአአ በ1985 እና 1986 የነሃስና የብር ሜዳሊያ ቢያስመዘግቡም፤ እአአ እስከ 1991 ባለው ጊዜ ደግሞ ውጤታማነቱ ተቋርጦ ነበር። እአአ በ1992 ፊጣ ባይሳ ኢትዮጵያን ወደ ሜዳሊያ ባለቤትነት ሲመልሳት፤ ኃይሌ ገብረስላሴ እና አሰፋ መዝገቡም በዚህ ሻምፒዮና በተለያዩ ጊዜያት ለአገራቸው ሜዳሊያ ማስገኘት ችለዋል።
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ወደ አስደማሚ የስኬት ዘመን የተሸጋገረችው እአአ 2002 ላይ ነው። የአየርላንዷ ደብሊን አዘጋጅ በነበረችበት በዚህ ውድድር ላይ የአገር አቋራጭ ውድድሮች ንጉሱ ቀነኒሳ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረኩን በድል ሊቀላቀል ቻለ። ከዚያ በኋላ ባሉት አምስት ተከታታይ ዓመታትም አትሌቱ የውድድሩን የበላይነት ጠቅሎ መያዝ ችሏል። ከአንድ አመት መቋረጥ በኋላም እአአ 2008 ላይ በድጋሚ ወደ ድሉ ሲመለስ በአጠቃላይ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በመድረኩ ቁጥር አንድ አትሌት ነው። አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ስለሺ ስህን፣ ኢማና መርጋ፣ ሙክታር እድሪስ እና አባዲ ሃዲስም በመድረኩ ውጤታማ መሆን የቻሉ አትሌቶች ናቸው።
በአጠቃላይም ኢትዮጵያ በወንዶች የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና 10 የወርቅ፣ 6 የብር እና 8 የነሃስ በድምሩ 24ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። በቡድን ደግሞ 10 የወርቅ፣ 13 የብር እና 8 የነሃስ ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። ይህ ውጤትም ከኬንያ ቀጥሎ የሚቀመጥ ውጤት ነው፤ ይሁንና ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ መካሄድ የጀመረበት እአአ ከ2011 አንስቶ ይህ ውጤታማነት እየሳሳ መምጣቱን ባለፉት አመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ ናቸው። ለዚህም እንደምክንያት ከሚነሱት ነጥቦች መካከል በሻምፒዮናው ተሳታፊ የሚሆኑት አትሌቶች በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች የሚመረጡ መሆኑ የውጤት መቀዛቀዝ ፈጥሯል።
በተለይ ክለቦች እና ክልሎች ታዋቂ አትሌቶችን በአገር ውስጥ ውድድሮች እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ሚናቸውን በትክክል እየተወጡ አለመሆኑንም ለውጤቱ መቀዛቀዝ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎችም የሚስማሙበት ነው። አትሌቶች በማራቶን ውድድሮች ላይ ትኩረት ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞም የአገር አቋራጭ ውድድሮች የቡድን ውጤት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ ይታመናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም