በአንድ ሀገር የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ካላቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የፋይናንስ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።እነዚህ ተቋማት በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ካላቸው ሚና መካከል አንዱ ለኢንቨስትመንት ተግባራት የፋይናንስ ምንጭ መሆናቸው ነው።
የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ጨምሮ ባንኮችና የመድን (Insurance) ድርጅቶች በአነስተኛም ሆነ በትልልቅ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ኩባንያዎች የስራ ማከናወኛ የገንዘብ ምንጮች እና የንብረት ዋስትናዎች ሆነው ይሰራሉ።ውጤታማ የኢንቨስትመንት ተግባራት አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት የሚፈልግ በመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ከእነዚህ የገንዘብ ተቋማት ተሳትፎ ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም።
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በበጎ የለወጡት የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለአነስተኛና መካከለኛ የኢንቨስትመንት ስራዎች ውጤታማነት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አይዘነጋም።በኢትዮጵያ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ደንበኞች ቁጥር ከባንክ ደንበኞች ቁጥር በብዙ እጥፍ የላቀ ነው።ይህም ለአብዛኛው ህዝብ የብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት እነዚህ ተቋማት እንደሆኑ አመላካች ነው።አንጋፋ የሚባሉት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሻለ ነው።ዛሬ በትልቅ ስምና አቅም የሚታወቁ ብዙ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች መነሻቸው እነዚህ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድርና ቁጠባ (የማይክሮፋይናንስ) ተቋማት አስተማማኝና ፍትሐዊ በሆነ አሰራር እንዲሰሩና ሕዝባዊ ተዓማኒነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ባንክ ሆነው ለመንቀሳቀስ የሚስችላቸው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያስችል መመሪያ ከሁለት ዓመታት በፊት ማውጣቱ ይታወሳል።የብድርና ቁጠባ ተቋማቱ ያላቸውን ግዙፍ የደንበኛና የፋይናንስ አቅም ትልልቅ በሆኑና የተሻለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲያውሉት የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ ብዙ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩና ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ እያስቻለ ነው።
በዚሁ መመሪያ መሰረት ቀደም ሲል ‹‹ሲዳማ ማይክሮፋይናንስ ተቋም›› (Sidama Micro Finance Institution) በመባል የሚታወቀው የብድርና ቁጠባ ተቋም ‹‹ሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማኅበር›› (Sidama Bank S.C.) ሆኖ በባንክነት ለመደራጀት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል።ባንኩ 1 ሺ 988 ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፤ የተፈረመ ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን 447 ሚሊዮን ብር ነው።ከዚህ ውስጥ ከ583 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ገንዘብ የተከፈለ ካፒታል ነው።
የሲዳማ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃም ማርሻሎ ባንኩ ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በባንክ ዘርፍ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉትን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዳከናወነ ይናገራሉ።አቶ አብርሃም በዚህ ረገድ ስለተከናወኑ ተግባራት ሲገልፁ ‹‹የባንኩ የውስጥ አሰራር የሚመራባቸውን መመሪያዎችን የማዘጋጀት፤ በብሔራዊ ባንክ መስፈርት መሰረት ውስጣዊ አደረጃጀቶችን የማሟላት፤ ከባንክ ዘርፉ ወቅታዊ እድገት ጋር የሚጣጣምና ባንኩን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ግዢ ለመፈፀምና ባንኩ የሚመራበትን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ እቅድ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ተግባራትን የማጠናቀቅ፤ የሰራተኞችን አቅም በስልጠና የመገንባትና ተቋሙን በብቁ ሰው ኃይል የማጠናከር፤ በመጀመሪያ ዙር የተሟላ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 10 ቅርንጫፎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማዘጋጀት እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ሂሳብን ጨምሮ የመጠባበቂያና የክፍያ ሂሳቦችን የመክፈት ተግባራት ተከናውነዋል›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት 142 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 177 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ የበላይ የሆነ አፈፃፀም አስመዝግቧል።ይህም ካለፈው ዓመት የባንኩ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ58 በመቶ ብልጫ እንዲኖረው አድርጓል።48 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ 83 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በባንኩ ታሪክ የተሻለ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።165 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብም ከቀዳሚው ዓመት አፈፃፀም የ29 በመቶ እድገት አሳይቷል።
በብድር አቅርቦት ረገድ ደግሞ ባንኩ የሰጠውን ብድር በ86 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር (በ29 በመቶ) በማሳደግ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠውን ብድር 462 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል።‹‹የባንኩ የተበላሽ ብድር ምጣኔ ሦስት ነጥብ ስድስት በመቶ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ምጣኔ አንፃር ሲታይ የሲዳማ ባንክ የተበላሸ የብድር ምጣኔ ጤናማ እንደሆነ አመላካች ነው›› ይላሉ።
የሲዳማ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያ ባንኩ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በነበረበት ጊዜ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲያገለግል እንደነበር አስታውሰው፤ አገልግሎቱ አዋጭና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ማዕቀፍ መሰረት ባንኩ ይህን አገልግሎቱን እንደሚቀጥልም ይናገራሉ።ባንኩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የባንክ አገልግሎትን በገጠርና በከተማ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መሆኑም ይህን አገልግሎቱን የማስቀጠል አካል ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ተቋሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በእርሻ፣ በሆቴልና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ።የተቋሙ በባንክ አሰራር መደራጀት ደግሞ ይህን አገልግሎት ለማስፋትና ለማዘመን ተጨማሪ እድልና አቅም ይፈጥራል።
ተቋሙ ወደ ባንክ ሲሸጋገር ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን አነስተኛ መነሻ ካፒታል ለማሟላት የአክስዮን ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ የተፈረሙ አክሲዮኖች ተከፍለው እንዲጠናቀቁ በማድረግ ከመደበኛ የባንክ ስራዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የባንክ ስራዎችን ለማከናወን እየሰራ ይገኛል።‹‹ወደ ባንክ ስራ ስንገባ የጠንካራ የፋይናንስ አቅም ባለቤት መሆን ያስፈልጋል።አለበለዚያ አቅም ካላቸው ከሌሎች ባንኮች ጋር ለመወዳዳር አስቸጋሪ ይሆናል።ለትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች ብድር ማቅረብም ሆነ በፋይናንስ ገበያው ላይ ተፎካካሪ መሆን አይቻልም›› ይላሉ።ይህን ለማሳካትም የተፈረሙ አክሲዮኖች እንዲከፈሉና የኮርባንኪንግ (Core Banking) ስራን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አቶ ታደሰ ያስረዳሉ።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ መፈቀዱ መልካም እድሎችና ፈተናዎች እንደሚኖሩት የሚገልጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ መልካም እድሎችን መጠቀም ከተቻለ ፈተናዎቹን መቀነስና ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ነው የተናገሩት።የባንኮቹ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮች ውድድሩን ለመቋቋም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ፣ በዚህም ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል አቅምም ሆነ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ በሚጠበቅባቸውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ እየተንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ተናግረው፣ እነዚህን ክፍተቶች በማስተካከል ለውድድር መዘጋጀትና ለተገልጋዩ እርካታ መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ።ከዚህ አንፃር ሲዳማ ባንክ ትልቅ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶችን እንዲሁም ዳያስፖራውን ማሳተፍን ጨምሮ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅሞ በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ማቀዱን አቶ ታደሰ ገልፀዋል።
ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚኖረውን አወንታዊ አስተዋፅኦ በተመለከተም አቶ ታደሰ ሲናገሩ ‹‹ገበያው አዋጭ በመሆኑ ባንኩ ለኢንቨስትመንት ስራዎች የፋይናንስ ምንጭ የመሆን አቅም አለው።ቀደም ሲልም የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ።ወደፊትም ባንኩ ይህን ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል።
ሲዳማ ባንክ በማይክሮ ፋይናንስ ደረጃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲያገለግልና ለግለሰቦች እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ማኅበራት የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ግለሰቦችና ማኅበራትም በተቋሙ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ስራቸውን አሳድገው ዛሬ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።
የሲዳማ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ መስፍን ቂጤሳ እንደሚናገሩት፣ ተቋሙ በግል ንግድ ላይ ለተሰማሩ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ባለውለታ ነው። እርሳቸውም ከባንኩ ጋር ያላቸው ደንበኝነት የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ ‹‹ከባንኩ የወሰድነው ብድር በጣም ጠቅሞናል፤ትርፋማ ሆነን እንድንሰራ አግዞናል›› በማለት የባንኩ የብድር አገልግሎት ለውጤታማነታቸው አጋዥ እንደሆናቸው አስረድተዋል።
‹‹አካባቢው በቡና ምርት የታወቀ ስለሆነ ባንኩም ለቡናው ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ነው›› የሚሉት አቶ መስፍን፤ ለቡና አብቃዮችና ነጋዴዎች እንዲሁም ለተደራጁ ማኅበራትም የፋይናንስ እድል እንደሚያመቻች ይገልፃሉ።በቀጣይም ከባንኩ ጋር ያላቸውን ደንበኝነት አጠናክረው፣ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተፈጠረውን መልካም እድል በመጠቀም ቡናን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው የባንኮች ተደራሽነት ውስን ስለነበር ብድር ለማግኘት ችግሮች ነበሩ።ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ስራዎች ብድር በማቅረብ ጥሩ እድል ይፈጥራል፤ለልማት በተለይ ለኢንቨስትመንት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ባንክ ነው።ጥሩ ተስፋ ያለው ባንክም ነው›› በማለት አቶ መስፍን ባንኩ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ስለሚኖረው አስተዋፅዖ ይናገራሉ።
በግል የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አየለች ዱካሞም የባንኩ ደንበኛ ናቸው።‹‹ቀደም ሲል የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ነበርኩ›› የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ ተቋሙ ባንክ ከሆነ በኃላ ከባንኩ ብድር መውሰዴ ስራዬን ሰፋ አድርጌ እንድሰራ አግዞኛል።ብዙ ሰው ከሲዳማ ባንክ ብድር እየወሰደ እየሰራ ነው፤እየተለወጠም ነው።ከባንክ ጋር መስራት ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡›› ሲሉ ይገልጻሉ።ባንኩ በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትልቅ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰው፤ ከባንኩ ብድር ወስደው ከአነስተኛ የንግድ ስራ ተነስተው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ሰዎችን እንደሚያውቁም ነው የጠቀሱት።ወደፊትም ከባንኩ ጋር ብዙ ስራዎችን የመስራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም