ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ውስንነት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የገንዘብ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ካሉ ከ31 በላይ የስፖርት ማህበራት መካከል የራሳቸው እውነንነቶች እንዳሉ ሆኖ በፋይናንስ ረገግ ራሳቸውን ችለዋል ተብለው የሚታሰቡት ሁለቱ(የአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች) ናቸው። ስፖርት በባህሪው ከፍተኛ መዋዕለነዋይ የሚፈልግ ዘርፍ እንደመሆኑ እምቅ አቅሙ ያላቸው ስፖርቶች ሳይቀሩ ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴያቸው ሲገደብ ማየት የተለመደ ነው። በገንዘብ እጥረት ምክንያት የፈረሱ ክለቦችና ቡድኖች ጥቂት አይደሉም። ከዚህም አልፎ የዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀት እድሎች ሲመክኑም ታይተዋል። አስፈላጊውን በጀት አጥተው ህልማቸው የከሸፈባቸው ስፖርተኞች ለዚህ አንድ ማሳያ ናቸው።
የኢትዮጵያ ስፖርት ሁሌም በበጀት እጦት እንደተፈተነ ነው። ዛሬም ይህ ፈተና ቀጥሏል። ለአብነት ያህልም የካራቴ ብሄራዊ ቡድን በገንዘብ እጦት ምክንያት የዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎውን አቋርጦ መመለሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በቦክስ ስፖርትም ኢትዮጵያ በሁለት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ያልቻለችው ፌዴሬሽኑ የገንዘብ አቅም ስለሌለውና አስፈላጊው ድጋፍ ስላልተደረገለት ነው። በዚህም ስፖርተኞች የሚያገኙትን ልምድ እና ውጤት፣ ሃገርም ስሟ በውድድር መድረኮች የመጠራት አጋጣሚውን አጥተዋል። የችግሩ ተጽዕኖ ቀላል የማይባል በመሆኑም ስፖርቱ የተቋቋመበትን ዓላማም እስከማዛባት ሊደርስም ይችላል።
በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ለዘመናት ለኖረው ለዚህ ችግር ዘላቂ የሚሆነው መፍትሄ የስፖርት ልማት ፈንድ ነው። ይህ በበርካታ ሃገራት የሚተገበርና ውጤታማ የሆነ አሰራር በኢትዮጵያም ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው በተደጋጋሚ ፡ ሃገራዊ የስፖርት ሪፎርም ጥናቱም ይህንኑ የሚጠቁም ሲሆን፤ ለስፖርት ልማት የሚውሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ገቢ በማሰባሰብ ስፖርቱን መደጎም እንደሚቻልም አስቀምጣል። ከጥናቱ ባለፈም በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ መድረኮች እንዲሁም በብሄራዊ የስፖርት ምክር ቤት አባላትም ለሃገሪቷ ስፖርት እድገት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ተመላክቷል።
ስፖርትን የሚያስተዳድሩ አካላት ትልቅ ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅሱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለውድድር፣ ለስልጠና፣ ለስፖርት ቁሳቁስ ግዢ፣ ለማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ለባለሙያዎች ደመወዝ ወዘተ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ። ለዚህ የሚውለው የገንዘብ ምንጭም የተለያዩ ተቋማት፣ የመንግስት በጀት፣ ሎተሪ፣ ግብር፣ ብሄራዊ የስፖርት ተቋማት፣ ስፖንሰሮች፣ ስፖርተኞች፣ ክለቦችና በድጋፍ መልክ ይሰበሰባል። ይህም ኦሊምፒክን የመሳሰሉ ታላላቅ አለም አቀፍ ውድድሮች ሲመጡ ብቻ ተግባራዊ ሲደረግ ማየት የተለመደ ነው። ከዚያ ውጪ ባሉ ታላላቅ አለም አቀፍና ሌሎችም ውድድሮች በተለይም ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ስፖርቶች በተጨማሪ ሌሎች ስፖርቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታይም።
ይህን ፈር ለማስያዝ አንዱ መፍትሄ ተደርጎ የሚቆጠረው ብሔራዊ የስፖርት ልማት ፈንድ ነው። በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ፣ የስፖርት ልማት ፈንድ ማለት ከተለያዩ ምንጮች ሃብት በማሰባሰብና በአንድ ቋት እንዲገባ በማድረግ መጠቀም የሚቻልበትና በርካታ ሃገራትም የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን ይጠቁማሉ። ይህ አሰራርም በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ የሚስተዋሉ ገንዘብ ነክ ችግሮችን መፍታት እንደሚችልም የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ በስፖርት ማህበራት ለሚነሱ የገንዘብ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት፣ በጀቱን ለማብቃቃት እንዲሁም ማህበራቱ ራሳቸውን እንዲያበቁ ለመደገፍም ሊውል እንደሚችልም ያብራራሉ።
ጉዳዩ በሀሳብ ደረጃ ከተነሳ የቆየ ቢሆንም በተለይ በዚህ ዓመት ወደ ስራ ለማስገባት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አቶ ተስፋዬ ይጠቁማሉ። አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት የስፖርት ልማት ፈንድን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ብሄራዊ ሎተሪ ካሉ ተቋማት ጋር ግንኙነት የተፈጠረ ሲሆን፤ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ በሚል ከተቀመጡ አካላት በተወሰነ መልክ በዚህ ዓመት ለመስራት ታቅዷል። ይህንን ስራ ሊሰራ የሚችል ኮሚቴ ተዋቅሮም ወደ ስራ ገብቷል። ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባም በስፖርት ማህበራቱ በኩል ለሚነሱ ቅሬታዎች በተወሰነ መልኩ መፍትሄ ይሆናል በሚል እንደሚጠበቅም ስራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ።
ይህ የስፖርት ልማት ፈንድ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ለስፖርት ማህበራት ድጋፍ በሚል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ከሚመደበው በጀት እንደየስፖርት ዓይነቱ፣ የስፖርተኛ ብዛት እንዲሁም ከሚያስገኙት ውጤት አንጻር በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የሚደርሳቸው ይሆናል። ሌላው ደግሞ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚካሄዱበት ወቅትም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፍ ያደርጋል። በእርግጥ የስፖርት ህዝባዊው አደረጃጀት የተፈጠረው በራሱ ገቢ በማመንጨት ራሳቸውን እንዲችሉ ነው። ነገር ግን ከሃገር ገጽታ ግንባታ አንጻር ለተሳትፎ እንዲሁም ማበረታቻ ሽልማትን በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ይደረጋል። ከስራው አስፈላጊነት አንጻር ሲታይ ግን ይህ ሁኔታ በቂ እና አርኪ ሊባል አይችልም። ሆኖም ከአዋጭነት አንጻር እየታየ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ከግንባታ ጋር በተያያዘም የስፖርት ማህበራቱ በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል መሰረት በጀቱን በማብቃቃት ድጋፍ ሊደረግ ይችላል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም