በመላው ዓለም ትናንት ለንባብ የበቁ ጋዜጣዎችና መጽሔቶች የፊት ገጽ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ አሸናፊነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በእርግጥ የማኅበራዊ ድረገጾች ትኩረትም አርጀንቲናውያን እና አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ላይ ያተኮረ ነው። ከ36 ዓመታት በኋላ ያለፈው ዓለም ዋንጫ ሻምፒዮና ፈረንሳይን በመርታት አሸናፊ የሆነው ቡድን ሶስተኛውን ዋንጫ በመደርደሪያው ላይ በክብር ለማስቀመጥ በቅቷል።
የቦነስ አይረስ ጎዳናዎችን በደስታ ጮቤ ያስረገጠው፤ በርካቶችንም በደስታ ያስነባው የአርጀንቲና ቡድን ለዘመናት በጉጉት የጠበቀውን ታላቁን ዋንጫ ከ42 ሚሊዮን ዶላሩ ጋር ይዞ ወደ ደቡብ አሜሪካዊቷ ሃገር ገስግሷል። ይህንን ተከትሎም የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ‹‹የቡድኑን አባላት አመሰግናለሁ። ሁሌም አንድ እንሁን፣ አሁን እኛ የዓለም ሻምፒዮን ነን። ከዚህ በላይ ቃል የለኝም›› በማለት ለሕዝባቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም የምንጊዜም ቁጥር አንዱ ተጫዋች ብራዚላዊው ፔሌ፤ አርጀንቲናን እና ሜሲን ስለ ዋንጫው ስኬት እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። በስፖርቱ ዓለም የገነነበትን ዓለም ዋንጫን በከባድ የጤና እክል ውስጥ ሆኖ ያሳለፈው ፔሌ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሕይወቱ ያለፈውና የምንጊዜም ተቀናቃኙ ማራዶና ‹‹አሁን ይስቃል›› በማለትም ገልጿል። አክሎም ‹‹እንደ ሁልጊዜው ሁሉ አሁንም እግር ኳስ መሳጭ ታሪኳን ቀጥላለች። ሜሲ የሚገባውን የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ወስዷል›› ሲልም ስሜቱን አንጸባርቋል። ታላቁ ተጫዋች የፈረንሳዩን ወጣት አጥቂ ኬሊያን ምባፔ በዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ሦስት ግቦችን ማስቆጠሩ አስደናቂ ተሰጥዖ እንዲሁም የወደፊቱን የስፖርት ተስፋ ያሳየበት መሆኑንም አንስቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የደረሰችውና ውድድሩን በአራተኝነት የፈጸመችው ሞሮኮንም አድንቋል።
በበርካታ ዓረቦች ዘንድ ቢሽት ተብሎ የሚጠራውን የክብር ካባ ተጎናጽፎ የዓለም ዋንጫን ያነሳው ሜሲ ከመወለዱ አስቀድሞ ነበር አርጀንቲና ሁለተኛውን ዋንጫ ያገኘችው። ከሦስት አስርተ ዓመታት በኋላም የዓለም ምርጡ ተጫዋች በእግር ኳስ ሕይወቱ ያላሳካውን ብቸኛ ዋንጫ ሲያነሳ እጅግ ይፈልገው የነበረ ነገር መሆኑን ጠቁሟል። በንግግሩም ‹‹ብዙ ታግሰን በመጨረሻም አግኝተነዋል፤ ፈጣሪ ይህን ሰጥቶኛል ከአሁን በኋላ የምጠይቀው ነገር አይኖርም። እግር ኳስን እጅግ እወደዋለሁ፤ ስኬት የተገኘው በመጨረሻው አካባቢ ቢሆንም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር መቀጠል እፈልጋለሁ። ከዚህ በኋላ ጥቂት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ከቡድኑ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ››ማለቱን ስካይ ስፖርት አስነብቧል።
የአርጀንቲናን ብሔራዊ ቡድን አስቀድሞ በተጫዋችነት አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት እያገለገለ የሚገኘው የ44 ዓመቱ ሊዮኔል ስካሎኒ፤ ዓለም ዋንጫውን ለሃገሩ ያስገኘ ሦስተኛው አሰልጣኝ ሆኗል። ከድሉ በኋላም በተጫዋቾቹ እጅግ መደሰቱን እንዲሁም መኩራቱን ጠቁሟል። የቡድኑን ሞተር ሊዮኔል ሜሲን በሚመለከትም እአአ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ እድሜው 39 የሚደርስ ቢሆንም የቡድኑ አባል ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎቱን ገልጻል። ሜሲ በተጫዋችነት የሚቀጥል ከሆነ ሃገሩ የምትፈልገው መሆኑን ‹‹እሱ ከቃላት በላይ ነው፤ ከእሱ ጋር በአንድ ቡድን በአሰልጣኝነት መሥራት አስደሳች ነው። ለሌሎች የቡድኑ አባላት የሚያስተላልፈው ነገር ከዚህ ቀደም አይቼው የማላውቀው ነው። ለቡድኑ ታላቅ ነገርን የሰጠ ሰው ነው›› በማለት አድናቆት ችሮታል።
በእግር ኳስ ሕይወቱ የጎደለውን የዓለም ዋንጫ ያሳካው ሜሲ የበርካቶች ግምት ከዚህ ዓለም ዋንጫ በኋላ ምናልባትም በብሔራዊ ቡድኑ እንደማይሰለፍ ነበር። በርካቶች ዋንጫውን እንዲያነሳ የመመኘታቸው ምክንያትም የዓለም ዋንጫ ሽኝቱ ያማረ እንዲሆን ነበር፤ ነገር ግን ሜሲ ሻምፒዮን ከሆነው ቡድን ጋር እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጠው።
ለአርጀንቲና ሁለት መለያ ምቶችን በማዳን የዋንጫ ባለቤት እንድትሆን ያስቻላት የወርቅ ጓንት ተሸላሚው ኤሜሊያኖ ማርቲኔዝ ዋንጫውን በማንሳቱ ሕልሙ መሳካቱን ገልጻል። ደስታውን መግለጫ ቃል ያጣው ግብ ጠባቂው ‹‹በመለያ ምቱ ወቅት በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ፤ ሁሉም ነገር የተከናወነውም እንደፈለግነው ነው›› በማለት ሃሳቡን ለቢቢሲ አጋርቷል።
የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ የሜዳ ቴኒስ ከዋክብቱ ሴሪና ዊሊያምስ፣ አንዲ ሙሪ እና ሮጀር ፌደረር፣ የጎልፍ ስፖርት ፈርጡ ታይገር ዉድስ፣ የዓለም ፈጣኑ ሯጭ ዩሴን ቦልት፣… ለአርጀንቲና እና ለሜሲ የደስታ መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም