በ1938 እና በ1939 ዓም የታተሙ የአዲስ ዘመን ጋዜጦችን ለዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ቃኝተናል።በወቅቱ ጋዜጣው ሳምንታዊ እና ታብሎይድ ነበር።ዜናዎቹም የሳምንት የሀገርና ከተማ ውስጥ ወሬ በሚል ርዕስ በውስጥ ገጽ ይወጡ ነበር።የአንዳንዶቹ ርዕሰ ወሬዎች አዝናኝና ግርምትን የሚፈጥሩ ሆነው አግኘተናቸዋል።ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናካፍላችሁ።
የሳምንት የሀገርና የከተማ ውስጥ ወሬ
የእሳት አደጋ
ግንቦት ፳፬ ከ፰ ሰዓት ሲሆን በንግሥት ኤልሳቤጥ መንገድ ቁጥር ፮፻፴፫ የሆነ መኪና ተገልብጧል ብለው በቁጥር 1690 ስልክ ተጠርተው ሄደው መኪናው ሳይጎዳ አውጥተው ተመለሱ።
፪. ከቀኑ ፲ ሰዓት ሲሆን በወይዘሮ ወለተ ዮሐንስ መንገድ አጠገብ አረርሶ የምትባል ልጅ ዕድሜ ፲፪ ዓመት የሆናት ከውሀ ጉድጓድ ገብታለች ብለው በእግር መጥተው ስለጠሩዋቸው ሬሳዋን አውጥተው ተመለሱ፡፡
፫. ግንቦት ፳፭ ቀን ከቀኑ ፬ ሰዓት ሲሆን በአርበኞች መንገድ ቁጥር ፪፻፵፪ የሆነ መኪና ከድልድይ ውስጥ ተገልብጧል ተብለው በቁጥር 1256 ስልክ ተጠርተው ሔደው መኪናው ሳይጐዳ አውጥተው ተመለሱ።የቆሰለም የሞተም የለም፡፡
፪ኛ. ከምሽቱ ፫ ሰዓት ሲሆን ከሥላሴ ቤተክርስቲያን በታች ቤት ተቃጥሏል፡ ተብለው በቁጥር 1807 ስልክ ተጠርተው ሔደው መንገዱ ለመኪና የማይመች ስለሆነ ተመለሱ።(ሰኔ 8 ቀን 1938 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ከ፫ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጠፍቶ የተገኘ እሥረኛ
ተገኝ የሚባል ሰው በሠራው ወንጀል እፍርድ ቤት ቀርቦ አንድ ዓመት እሥራት ተፈርዶበት አቃቂ ወህኒ ቤት ታስሮ ስለነበረ፤ ፰ ወር ከታሰረ በኋላ ለሥራ ወጥቶ ሲሠራ ከፖሊሶች እጅ አታሎ ጠፍቶ ሲፈለግ ግንቦት ፳፮ ከቀኑ ፯ ሰዓት ሲሆን በዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ ሲንሸራሸር መኰንን እሸቴ በተባለ ፖሊስ ተይዞ ታስሯል፡፡
ከእሥር ቤት ለማምለጥ መሞከር በወንጀል ላይ ወንጀል መጨመር ነውና አይገባም።ከሕግ ለማምለጥ መሞከር ወንጀል ነው፡፡እንኳን በወንጀል ታስሮና አላግባብም ቢሆን ሰው ያገሩን ሕግ አይሸሽም ።(ሰኔ 8 ቀን 1938 ከወጣው አዲስ ዘመን)
መልካም ሥራ
አቶ አፈወርቅ አዳፍሬ ‹‹ንጹህ ደም›› የሚባል ቲያትር አዘጋጅተው፤ በቲያትሩ የተገኘው ገቢ ገንዘብ በሙሉ ፤በበጐ አድራጊዎች እርዳት ለቆመው ለተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት ዕርዳ ስለሰጡ በዚሁ ገንዘብ ፪ሺህ፭፻ ሜትር ካሬ ቦታ ለትምህርት ቤቱ ተገዛበት፡፡
ከፍ ባለ ትጋት ትያትሩን አዘጋጅተው ለሕዝብ ከማሳየታቸው በላይ፤ በበጐ አሳብ ተመርተው ገንዘቡን ለትምህርት ቤት በመስጠታቸው መታሰቢያነት ያለው ሥራ እንደሰሩ የሚገልጽ ስለሆነ ፤ስለሠሩት መልካም ሥራና ስለአሳዩት በጐ አርአያ እያመሰገንናቸው ይህን የመሰለውንም የበጐ አድራጐት ምሳሌ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚከተለው እንዲሆን ምኞታችን ነው።(ሐምሌ 6 ቀን 1938 ከወጣው አዲስ ዘመን)
የሚያስደንቅ ፍጥረት
አቶ አረዲ ወልደ ሐና ሐረር አቦከር ጊዮርጊስ ቀበሌ የሞኖሩ አንዲት ፍየላቸው ቅዳሜ ሰኔ ፳፪ ቀን ከደረቱ በታች መንታ ስምንት እግር አንድ ራስ ሁለት ዐይን ሦስት ጆሮ ያለው አንድ ፍየል ብትወልድ፤ ይህንኑ አስደናቂ ፍጥረት ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ለሕዝቡ ለማሳየት ሲሉ በዚያኑለት በስምንት ሰዓት ይዘውት ወደ ማዘጋጃ ቤት አምጥተውት ነበረ።ሕዝቡ ይህንን ሰምቶ ማዘጋጃ ቤት እየመጣና እያየ የእግዚአብሔርን ታክ ሲያደንቅ አመሸ።ይኽንኑ ፍጥረት ማዘጋጃ ቤት ሲያመጡት ለመሞት ያጣጥር ስለነበረ አንድ ሰዓት ያህል እንደቆየ ሞተ።
ሱካር ነጋዴዎች ባልተፈቀደ ዋጋ እየሸጡና ሕዝቡን እንዳይጐዱት በማለት የንግድና የእንዱስትሪ ሚኒስቴር በአምስተኛው ዓመት በቁጥር ፴፮ ሰንደቅ ዓላማችን ባወጣው ማስታወቂያ ፤ነጭ ሱካር በአንድ ኪሎ ፸፮ ሳንቲም እንዲሆን ወስኖ ነበረ፡፡አሁን ግን ማስታወቂያው ሳለወጥ የሱካር ዋጋ ባንድ ኪሎ ፺ ሳንቲም ሆነ፡፡
ዋጋው አነሰ በዛ ለማለት ሳይሆን በማስታወቂያ እንደተወሰነው ዋጋ ባለመሸጡ አትራፊው ማን እንደሆነ አልታወቀምና የዋጋውን ልክ ሕዝቡ እንዲያውቀው ቢደረግ የተሸለ ስለመሰለን ይታሰብበት ዘንድ ለክፍሉ ባለሥልጣኖች እናስታውሳለን፡፡
በሚስ ሲልቢያ ፓንክረስት መንገድ በሚወስደው ትንሽ መንገድ በየጊዜው መኪናዎች ሲገለበጡ፤ ጋሪዎች በጉድባ ሲገቡ እናያለን ።ምክንያቱም መንገዱ በመጥበቡና ግራናቀኝ ያልተደለደለ በመሆኑ ነው።ስለዚህ በሕዝብ ላይ ታላቅ ጉዳት ሳያደርግ ቢታሰብበት መልካም መሆኑን ለክፍሉ ባለሥልጣን እናስታውሳለን።(ጥር 16 ቀን 19 39 ዓ.ም አዲስ ዘመን)
ከረጅሙ ባጭሩ
በዓየር ኃይል ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ከስዊድን ሀገር ስለመግባታቸው፡፡
አዲስ አበባ በሚገኘው የአየር ኃይል ትምህርት ቤት አኤሮፕላን ለማብረር ከሚማሩት ተማሪዎች ውስጥ አበራ ወልደ ማርያም ፤የእግረኛ ጦር ሠራዊት የሌየተናንት ማዕረግ የተሰጠው ሌየተናንት ታምራት ተስፋዬ፤ዓለማየሁ አበበ፤ ግርማ በዳኔ አሰፋ አየለ የተባሉት ትምህርታቸውን ለማጥናትና የውጭውን ሀገር ዓየር ለመጐብኘት በአለፈው ወር ውስጥ ከአስተማሪዎቻቸው ጋ ወደ ስዊድን ሀገር ሔደው ስለነበረ ፤ በስዊድን ሀገር በቆዩበት ጊዜ ሰዓብ ተባለውን የአኤሮፕላን ፋብሪካና የሠፈሩንም ሁኔታ ተመልክተው በዚሁ ፋብሪካ የተሠሩትን ፭ አኤሮፕላኖች እየነዱ ታኅሳስ ፲፭ ቀን ማክሰኞ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
ልኡል መኰንን መስፍነ ሐረር ብርጋዲየር ጄኔራል ዓቢይ አበበ እጣቢያው ድረስ ሒደው ተቀበሉዋቸው።እነዚህ ወጣቶች በጥቂት ጊዜ ባገኙት ትምህርት አኤሮፕላን ለመንዳት ችሎታ አግኝተው ለታቹበት ሥራ በመብቃታቸው ለወገናቸው ትምክህት፤ ለሀገራቸው ኩራ የሚሰጡ ናቸው፡፡
እንዲሁም ወደፊት ትምህርታቸውን ቀጥለው በበለጠ ሁኔታ ሀገራውን ለመርዳ እንዲችሉ ተስፋን ሙሉ ነው። ከነዚሁ ወጣቶች ጋ በዚሁ አኤሮፕላን ትምህርት ቤት ፹ የሚሆኑ ተማሪዎች ይማራሉ።እነዚህ ወጣቶች ትምህርታቸውን እቅርብ ቀን ድረስ እንደሚፈጽሙ ተረጋግጧል።ኢትዮጵያ ወደፊት የምትፈልገውን የሥልጣኔ እርምጃ በወጣቶቿ ትጋ ታገኘዋለች።
(ታኅሳስ 19 ቀን 1939 ከወጣው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም