አዲስ ዘመን ድሮ

የኢትዮጵያን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የመረጃ ቋት አዝሎ ከጫፍ ጫፍ ሲጓዝና ሲያጓጉዝ የነበረው የዘመን መርከብና መረብ ዛሬም በጉዞው አልተገታም። ብቻውን ተነስቶ፣ በብቸኝነት ዛሬን የዘለቀው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የትናንትናውን ያለፈበትን መንገድ ዛሬም “አዲስ ዘመን ድሮ” ሲል ያስቃኘናል። የዛሬዎቹን የትውስታ መረቦቻችንን የጣልነውም በ1957ዓ.ም እና 1963ዓ.ም፤ በሁለቱ ዓመታት ውስጥ የተከሰቱ አስገራሚ ወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

አንድ የ75 ዓመት ዕድሜ ያለው አዛውንት ያውም ሊጡን ከቡሃቃው ሰረቀ ሲባል ብንሰማ ‹ምነው በመቁረቢያ ዕድሜው…› ከማለትም ያለፈ አግራሞትን የሚያጭር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አጥፍቶ ጠፊዋ አህያ የባለቤቷን የእጅ ቦምብ አፈንድታ ተያይዘው ወደ ሞት መውረዳቸውን ይነግረናል። ባለቤቷ ከእዚህ ቀደም ሰው ገድሎ የተሰወረ፣ ተፈላጊ ወንጀለኛ መሆኑ ደግሞ የባሰ አጃኢብ ነው። ለነጭ ልጃገረድ የፍቅር ደብዳቤ ጽፈሃል ተብሎ በፍርድ ቤት የተቀጣው ናታሊ ማሎይ፤ ከአህጉራችን ከደቡብ አፍሪካ ሌላኛውን የነጭ ትንኮሳ ደግሞ ከናይጄሪያ ሌጎስ እናስታውሳቸዋለን።

የ75 ዓመት ሰው ሊጥ ሰርቆ ታሰረ

አሥር ጊዜ የሌብነት ወንጀል ፈጽሞ የዘጠኝ ዓመት ተኩል ቅጣት ከተቀበለ በኋላ የተቦካ ሊጥ ከነባሊው ሰርቋል በመባል የተከሰሰው ሰውዬ የፈጸመው ወንጀል በሕግ ማስረጃ ስለተረጋገጠበት በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው ዓርብ ፈረደ።

የሚኖረው በአዲስ አበባ ከተማ የካ ሚካኤል አካባቢ ሲሆን ሌብነት የዘወትር ሙያው በማድረግ የሰውን ቤት በሌሊት እየሰበረ ልዩ ልዩ የቤት ዕቃዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ ሰርቆ እንደነበር ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ መሠረት ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል፡፡

የ75 ዓመቱ ሽማግሌ የተቦካውን ሊጥ ከነባሌው በሰረቀበት ዕለት ሁለት የቡና ስኒ እና አንድ የስፌት አገልግልም ጨምሮ መውሰዱን ራሱ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል አረጋግጧል፡፡

ተከሳሹ በየጊዜው በፍርድ ቤት የተወሰነበትን ቅጣት ተራምዶ የተደጋገመ ወንጀል መፈጸሙን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ ከገለጸ በኋላ የተከሳሹ ዕድሜ የገፋ ስለሆነ ቅጣቱን አሻሽሎለት በአንድ ዓመት ተኩል ቅጣት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

እንዲሁም ከተከሳሹ ጋር የወንጀል ግብረ አበር ሆኗል በመባል የተከሰሰው ደበበ ጫላ ከእዚህ ቀደም የሌባ ተቀባይ መሆኑ ቢረጋገጥም፤ በአሁኑ ጊዜ የፈጸመው ወንጀል ከእዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል፡፡

(አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 1963ዓ.ም)

አህያ ወንጀለኛ በቦምብ ገደለች

ሰው በመግደል ወንጀል ለሁለት ዓመታት ያህል ተደብቆ ይኖር ነበር የተባለው ዑመር ሱሪ የጫናት አህያ ረግጣው በኪሱ ደብቆት የነበረው የእጅ ቦምብ በመፈንዳቱ ምክንያት እርሱም አህያውም ወዲያውኑ ሞተው መገኘታቸውን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል ትናንት ገለጠ፡፡

ማስታወቂያ ክፍሉ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስረዳው፤ ዑመር ሱሪ ለይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ደቄ ራህመዶ ወረዳ ግዛት ውስጥ ሐምሌ 18 ቀን 1961ዓ.ም ሐዊ እንድሪስ የተባሉትን ሴት በጥይት ገድሎ ተደብቆ ይኖር ነበር። ነገር ግን የካቲት 27 ቀን 1963ዓ.ም በአንዲት አህያ እህል ጭኖ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ ጭነቱን ሊያስተካክል ሲል በአህያዋ እርግጫ ከኪሱ ያለው ቦምብ ተመቶ በመፈንዳቱ ከአህያዋ ጋር ሞተው ተገኝተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 1963ዓ.ም)

በፍቅር ደብዳቤ 350 ብር ተቀጣ

ለአንዲት ነጭ ልጃገረድ የፍቅር ደብዳቤ የጻፈ አንድ አፍሪካዊ የሙዚቃ መሪ የልጃገረዲቱን መብት ተዳፍረሃል ተብሎ በቀረበበት ክስ መሠረት ሦስት መቶ ሃምሳ ብር ተቀጥቷል፡፡

ናታሊ ማሎይ የተባለው ይህ የ28 ዓመት ዕድሜ ያለው የሙዚቃ መሪ ገንዘብ ባስቀመጠበት በአንድ የደቡብ አፍሪካ ባንክ ውስጥ ለምትሠራ የ23 ዓመት ዕድሜ ላላት ነጭ ልጃገረድ የጻፈው ደብዳቤ ተገኝቶበታል።

ስሟ ያልተገለጠው ይህቺ ልጃገረድ ፍርድ ቤቱ ከእዚህ በፊት ባደረገው ችሎት ላይ አፍሪካዊው ናታሊ ናሎይ ብዙ ደብዳቤዎች እያከታተለ የጻፈላት መሆኑን ገልጻለች፡፡

ናታሊ ማሎይ ለልጃገረዲቱ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ “በሰውነቴ ውስጥ የፍቅር እሳት አቀጣጥለሽብኛል፤ በሙሉ ልብ አፈቅርሻለሁ። በነፍሴም በሥጋዬም ያንችው በመሆኔ እንደፈለግሽው ልታደርጊኝ ትችያለሽ” የሚሉ ቃላት ተገኝተውበታል።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 16 ቀን 1957ዓ.ም)

ልጃገረዷ በጥፊ ስለተመታች የኩባንያው ሠራተኞች አንሠራም አሉ

ከሌጎስ፤ በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘውን የኪንግስዌይ ግምጃ ቤት ሥራ ይመራ የነበረው እንግሊዛዊው፤ የግምጃ ቤቱ የሽያጭ ክፍል ሠራተኛ የነበረችውን አንዲት ልጃገረድ በጥፊ ስለመታት፤ ይህ ሰው ከሥራው ካልተወገደ በማለት በግምጃ ቤቱ ውስጥ ይሰሩ የነበሩት አንድ ሺህ ናይጄሪያውያን ሠራተኞች ሥራቸውን አቁመዋል፡፡

የግምጃ ቤቱ ባለንብረት የሆነው የተባበረው የአፍሪካ ኩባንያ የሠራተኞች አንድነት ኤክስኪዩቲቭ፤ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ፤ የናይጄሪያዋን ልጃገረድ አደገኛ ጥፊ የመታት የብሪታኒያው ተወላጅ ሚስተር ፒተር ቻድዊክ ከሥራው እንዲወጣ የተጠየቀ መሆኑንና በሚመጣው ቅዳሜ ናይጄሪያን ለቅቆ ይወጣል ሲል አስታውቋል፡፡

የግምጃ ቤቱ የወሬ ምንጭ፤ ሚስተር ፒተር ቻድዊክ የልጃገረዷን ትከሻ መታ በማድረግ በደንብ እንደተሠራ አሳስቧታል ሲል ገልጧል፡፡

በመቶ የሚቆጠር ፖሊስ ግምጃ ቤቱን ከብቦ እንደነበር ወሬው ሲያመለክት፤ እስካሁን አደጋ ያልደረሰ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ (አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 1957ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You