ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽና አስተማማኝ እንዲሁም ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማት ከቴክኖሎጂ /ሶፍትዌር/ አልሚዎች ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ናቸው። ከዚህም በርካታ ተቋማት የአሠራር ሥርዓታቸውን በመፈተሽ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። ለአብነትም የግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ግዥዎች በሙሉ በቴክኖሎጂ እንዲፈጸሙ እያረገ ይገኛል። የተለያዩ ተቋማት ክፍያዎችም እንዲሁ በጥሬ ገንዘብ ከመሆን እየወጡ ናቸው።
ተቋማቱ በአሁኑ ወቅት ይህን እያደረጉ ያሉት በሀገር ውስጥ በሚለሙ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት ነው። ከነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ጋር የሚስማሙ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ አቅም እንዲለሙ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጣቸውን እያዘመኑ ናቸው። ቴክኖሎጂዎቹ በሀገር ውስጥ መልማታቸው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በማስቀረት በሀገር ውስጥ አቅም የመሥራት ባህል እንዲዳብር ማድረግ ያስችላሉ። ቴክኖሎጂን ለመግዛት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ መቀነስ ያስችላሉ በሚል ታምኖባቸዋል ።
ባለፈው ወር የገቢዎች ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን (TIN NUMBER) ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙም ከዚሁ አኳያ ይታያል። ስምምነቱ እስካሁን ባለው ሂደት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግብር ከፋዮች መለያ መታወቂያ (ቲን ነምበር) ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከውጭ ሀገራት ለመግዛት ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ውጪ የሚያስቀር እንደሆነም ተመላክቷል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ለግብር ከፋይ መለያ ቁጥር አገልግሎት ለመስጠት ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚቀንስ ከመሆኑም ባሻገር ቴክኖሎጂውን በሀገር ውስጥ አቅም በራስ ባለሙያዎች ማልማት መቻሉ አጠቃላይ ሀገራዊ አቅም እየጎለበተ ለመምጣቱ አንድ ማሳያ ነው። ሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ግዥ ሲፈጽም የቆየው ከውጭ ሀገራት ሲሆን፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት የሚችል ነው።
የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የሚሰራው አዲሱ አሠራር የግብር ከፋዩ መለያ ቁጥር ለመስጠት የሚወሰደውን የጣት አሻራ የሚተካ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አዲሱ አሠራር ለብሔራዊ መታወቂያ የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ተወስደው በሚሰጠው ቁጥር መሠረት መሥራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለግብር ከፋዩ የሚሰጠው አዲሱ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በሀሰተኛ ሰነድ ማስረጃ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች መከላከል የሚያስችል ነው ። ግብር ከፋዩ አንድ ብሔራዊ መታወቂያ የሚይዝ ከሆነ፣ በግብር ሥርዓት ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ይጠቅማል።
‹‹ይህንን ቴክኖሎጂ ከኛ ሀገር ውጪ ሌሎች ሀገራት የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ እስካሁን ሲሰራበት የነበረው ባዮ ሜትሪክ ዳታ የሚወሰድበትን መንገድ የቀየረ ነው።›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ‹‹ በቀጣይ እኛ ለመገንባት ለምናስበው የቴክኖሎጂ ሥርዓት ከወዲሁ የጠራ መረጃ ለመያዝ ያስችላል›› ብለዋል። የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የወሰዱ ግብር ከፋዩችን ቁጥር በማጥራት ወደ አዲሱ ብሔራዊ የመታወቂያ ሥርዓት እንዲገቡ በማድረጉ ሂደት መረጃ የማጥራት ሥራ በሚገባ እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል። ወደ አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ውስጥ ለመግባት የሚደረገውን ሂደት የሚያቀልና መልካም አጋጣሚን የሚከፍት እንደሆነም አስረድተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር የሚተገበረው የአሠራር ሥርዓት ግብር ከፋዩን በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ስለ ግብር ከፋዩ ግልጽና ተአማኒነት ያለው መረጃ እንዲኖር እድል ይፈጥራል። ግብር ከፋዩ ዜጋም በአንድ ብሔራዊ መታወቂያ በመጠቀም ማንኛውንም አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት ያግዘዋል። መረጃን ከሚሰጡ ሌሎች ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር የተናበበ ሂደት እንዲኖር እድል ይፈጥራል።
ለዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ከጣት አሻራ የተሻለ ጠቀሜታ ያስገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አሻራ መስጠት ለማይችሉ ዜጎች እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸውን ዜጎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት። ቴክኖሎጂውን ‹‹ሁሉን አካታች ሥርዓትን የሚከተል›› ሲሉም ገልጸውታል።
አዲሱን የቴክኖሎጂ አሠራር ለመተግበር ቀደም ሲል የግብር መለያ ቁጥር ያላቸው ግብር ከፋዮች በሂደት ወደ አዲሱ አሠራር እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አዲስ የግብር መለያ ቁጥር ለሚፈልጉት ሁሉ ብሔራዊ መታወቂያ መያዝን አስገዳጅ ይደረጋልም ብለዋል። ብሔራዊ መታወቂያ መያዝና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን (ቲን ነምበር) መያዝ ማለት አንድና ተመሳሳይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት እስከ አሁን የጣት አሻራ ለመውስድ የሚገለገሉባቸው ከአምስት መቶ በላይ የታክስ ማዕከላት በመሄድ ምንም ሳይንገላታ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችልም ጠቁመዋል። ‹‹ አንድ ግብር ከፋይ ብሔራዊ መታወቂያ ካገኘ በኋላ እኛ ብሔራዊ መታወቂያውን እንደቅድመ ሁኔታ ወስደን በማጥራት በሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አገልግሎቱን እንሰጣለን፤ ግብር ከፋዮቻችን አቅራቢያቸው ወደሚገኙ የታክስ ማዕከላት እየሄዱ የብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚ ሲሆኑ እኛ የግብር መለያ መታወቂያቸውን እናድስላቸዋለን›› ሲሉም አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አዲሱ አሠራር የግብር መለያ ቁጥር ወስደው የግብር ከፋይ ያልሆኑ እንዲሁም የተሰረዙ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አሰራሩ አሁን ላይ ያለውን ወቅታዊ መረጃ ለማወቅ ይጠቅማል። ይህ መሆኑ ለፋይናንስ ተቋማት ፣ለባንኮች፣ ለኢንሹራንሶች እና ለተለያዩ ግብር ከፋዩን መዝግበው ለሚይዙ አካላትም ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት። ተቋማቱ በማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርና ብሔራዊ መታወቂያቸው አንድና ያው ሆኖ የሚያገለግሉ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ አሠራር ግብር ከፋዮች በቀላሉ ከየትኛውም ቦታ ሆነው አገልግሎቶችንም ሆነ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችላቸው እንደሆነም ጠቁመው፣ ‹‹ለእኛም በቀላሉ ከሌሎች ተቋማት የምንፈልገውን መረጃ ለመወሰድም ሆነ ትስስር ለመፍጠር እድል ይፈጥራል›› ይላሉ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ እዮብ አለሙ በበኩላቸው ዲጅታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የሚሰራው ሥራ የእያንዳንዱን ግብር ከፋይ ማንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መለየት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው የግብር ከፋዮች ማንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ ከማድረግም በላይ ከግብር አሰባሰብ ሂደቱ ጋር በተያያዘ ጊዜ እና ተጨማሪ ውጪዎችን የሚጠይቁ ሥራዎችን መቀነስ እንደሚያስችልም ይገልጻሉ። እስካሁን ይህ አሠራር ባለመዘርጋቱ አሠራሩ ቀልጣፋ እንዳይሆን አድርጎ ቆይቷል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህ ደግሞ ግብር ለመሰብሰብ አድካሚ የሚያደርግ መሆኑን ነው የተናገሩት። የገቢ ግብር በትክክል እንዳይሰበሰብ ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለታክስ ማጭበርበር ሲያጋልጥና ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር እንደነበር አመላክተው፣ አዲሱ አሠራር ይህንን የሚቀርፍና አስተማማኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር አንድን ሰው ከገቢ ግብር ጋር በተያያዘ ማንነትን ለማረጋገጥ ተብሎ የሚሰጥ ሲሆን፣ ግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሚጠየቀው ቢያንስ በባዮ ሜትሪክ አሠራር መሠረት መለያ ቁጥር ስላለበት ለመለየት ይችላል። ተደራሽነቱ ግን ውስን ስለሆነ ሁሉም ተቋማት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በመጠቀም አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። በብሔራዊ መታወቂያ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።
ብሔራዊ መታወቂያ የተለያዩ ተቋማት የሚገናኙበትን ሥርዓት በመፈጠር አሠራርን ያዘመናል፤ ያቀላጥፋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም ተቋማት አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ ተጠቅመው ማከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ እያንዳንዱን ተገልጋይ ብሔራዊ መታወቂያ ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ይህም የመረጃ ልውውጥን ፈጣን ከማድረጉም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው ዳይሬክተሩ የሚገልጹት ።
እንደ አቶ እዮብ ገለጻ፤ የብሔራዊ መታወቂያ አሠራርን በማቀላጠፍና ዘመናዊ በማድረግ ዲጅታል አሠራር ለመከተል ከተሞከረ ከአሥር ዓመት በላይ ሆኖታል። ይህ አብዛኛውን ጊዜ ከአካሄድ ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ሲጎተት ቆይቷል፤ የተሞከሩትም አንዳንድ አማራጮች ረጅም ርቀት የሚያስኬዱ ሆነው አልተገኙም ነበር።
አሁን ላይ እንደገና በአዲስ መልክ ለመሥራት ሲታሰብ ቴክኖሎጂው በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲለማ ማድረግ ተችሏል። ይህም አገልግሎቱ አንዴ ከተጀመረ በቴክኖሎጂ ምክንያት መቋራረጥ የሌለበት በመሆኑ አስተማማኝ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል አካሄድ እንዲከተል ለማድረግ ያስችላል።
አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኛውን የቴክኖሎጂ ሂደት ሀገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና አቅምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቆመው፤ አዲሱ አሠራርም በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠር ችግርን ቅርብ በሚገኙ ባለሙያዎች እየፈቱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ።
ቴክኖሎጂ ውስብስብ ነው ያሉት አቶ እዮብ፤ የቴክኖሎጂን ውስብስብነት መገንዘብ የሚችል የሀገር ውስጥ አቅምን መጠቀም ከቻልን ችግሮች በኛው ሀገር ባለሙያዎች እየፈቱ እንደሄዱ ማድረግ እንችላለን ይላሉ።
እስካሁን ተቋማት እንደዚህ አይነቶቹን ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ሀገር ሲገዙ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ ሆኖም ግን ቴክኖሎጂው የተወሰኑ ዓመታት ከተሰራበት በኋላ የመቀጠል አቅሙ አናሳ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት አብዛኛው ጊዜ ከቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር ከክፍያ ጋር ከቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር የተገናኘ አለመግባባት ፤ ሲስተሞች የመቋራረጥ ሲያጋጥም የቆየ መሆኑን አመላክተዋል። ይህ የሚሆነው በሀገር ውስጥ ያለውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ቀሪውን ጊዜ ለማስኬድ የሚያስችል አቅም ከመጀመሪያ ጀምሮ ታሰቦበት ስለማይሰራ እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹ይህንን ቴክኖሎጂ ለየት የሚያደርገው ቴክኖሎጂውን ሲንጀመር በራሳችን ፍላጎትና አቅም ላይ የተመሠረተ ሆኖ የውጭ ሀገራትንም ቴክኖሎጂ አጣምሮ የያዘ እንዲሆን አድርገን ነው›› ይላሉ ። ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ የሀገር ውስጥ ነው ሲባል ሀገር ውስጥ ብቻ የተሰራ ነው ማለት እንዳልሆነም ተናግረዋል፤ ከውጭ ሀገር የሚመጣ መኖሩን አመላክተዋል፤ ሙሉ ለሙሉ የውጭ አቅራቢዎች ላይ ጥገኛ እንደማይሆን ነው ያመለከቱት። ከውጭ አቅራቢዎች ጋር የሆነ ችግር ቢፈጠር እንዲሁም ውል ቢቋራጥ በሀገር ውስጥ አቅም ቴክኖሎጂውን ማስቀጠል የሚቻልበት አቅም መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም