ሁለተኛው የአዲስ አበባ አትሌትክስ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል። ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በቆየው የክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር መቻል አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በአጭርና በመካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ሃያ ሁለት የአትሌቲክስ ክለቦች የተፎካከሩበት የአቋም መለኪያ ውድድር በሁለት ካታጎሪ ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን፤ በአንደኛ ዲቪዚዮን ስምንት ክለቦች፣ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ አስራ ሶስት ክለቦች ተካፋይ ሆነዋል።
በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድር መቻል አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን በወንዶች ደግሞ ሶስተኛ ሆኖ ጨርሷል። ይህም አጠቃላይ ውድድሩን በነጥብ ቀዳሚ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል። በሁለቱም ጾታ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በአጠቃላይ በሰበሰበው ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ በወንዶች አንደኛ በሴቶች ደግሞ ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን እንደ አጠቃላይም ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ጨርሷል።
ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው ይህ የአቋም መለኪያ ውድድር በተለያዩ ርቀቶች ጠንካራ ፉክክሮችን ያስተናገደ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የሴቶች ስምንት መቶ ሜትር ተጠቃሽ ነው። በዚህ ርቀት በተደረገው ፉክክር ንግስት ጌታቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 2:03:57 በማጠናቀቅ ቀዳሚ ስትሆን፣ ፅጌ ድጉማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2:05:31በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላኛዋ የንግድ ባንክ አትሌት ሳሮን በርሄ ደግሞ 2:06:20 በሆነ ሰአት በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።
በወንዶች መካከል ከተካሄዱ ውድድሮች ጠንካራ ፉክክር ያስተናገደው የመቶ ሜትር ተጠቃሽ ሲሆን፤ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ናታን አበበ 10:32 በሆነ ሰአት አሸናፊ መሆን ችሏል። ከተመሳሳይ ክለብ አዲሱ ሂሬ 10:59 በመግባት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሸሪፍ ረዲ ከኢትዮ ንግድ ባንክ 11:03 በማጠናቀቅ ሶስተኛ ሆኗል።
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራው ገብሬ፣ ውድድሩ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው አመታዊ መርሃግብሮች አንዱ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ የተለያዩ የውድድር ፕሮግራሞችን እንደሚያወጣና ከነዚያም አንዱ ይህ የአቋም መለኪያ ውድድር መሆኑን የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ተናግረዋል። የአቋም መለኪያ ውድድሩን በ2014 ዓ.ም መጀመራቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እታፈራው፣ የአቋም መለኪያ ውድድሩ ትልቁ አላማ ክለቦች ለቀጣይ ውድድሮች የአትሌቶቻቸውን ብቃት መለካት መሆኑን አስረድተዋል። ይህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሚያዘጋጃቸው የአጭር ርቀት፣ የመካከለኛ ርቀትና የሜዳ ተግባራት እንዲሁም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የክለቦች ቻምፒዮና ለመሳተፍ ክለቦችና አትሌቶቻቸው በስልጠና ላይ ቆይተው አቋማቸውን የሚመዝኑት በዚህ ውድድር መሆኑን ተናግረዋል። በዘንድሮው ውድድር የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉንም የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ አክለዋል።
በዘንድሮው ውድድር ከተሳታፊ ስፖርተኞች አንጻር ሲታይ በሴት 234 አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በወንድ ደግሞ 342 አትሌቶች በአጠቃላይ 576 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነው የመቻል ስፖርት ክለብ አባል የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል አማረ አራጌ ስለውድድሩ ሲናገሩ “ውድድሩ ደስ የሚልና ተተኪ አትሌቶች የታዩበት ነው፣ ተወዳዳሪ አትሌቶች ራሳቸውን የሚፈትሹበት እንዲሁም አሰልጣኞች ልጆቻቸውን በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚመለከቱበት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ኮሎኔል አማረ አክለውም “በአጭርና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በሃገራችን ብዙም ታዋቂነት ስለሌላቸውና ከሃገር ውስጥ የዘለለ ተሳትፎ ስለማያደርጉ እንዲህ አይነት ውድድሮች ሲፈጠሩ ተተኪ አትሌቶች የማይገኙበት ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል። በዚህም እንደሌሎች የውድድር አይነቶች በአለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን በአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች አትሌቶች መወከል እንዲችሉ ከስልጠና ባሻገር እንደዚህ አይነት የአቋም መፈተሻ ውድድሮች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም