ዶክተር አበራ ደሬሳ ሙሉ የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ነው። ትምህርታቸውም ከዘርፉ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ለሙያው ክብር አላቸው። በግብርናው ዘርፍ ሥራ የጀመሩት ከታች አንስቶ ሲሆን፣ በምርምር ዘርፍ ከረዳት እስከ ከፍተኛ ተመራማሪነት፣ በኋላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ዘርፉን በመምራት አገልግለዋል።
አሁን በጡረታ ላይ ቢገኙም ከግብርናው አልተለዩም። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የኦሮሚያ ግብርና ምርምር አማካሪ የቦርድ አባል በመሆን እየሰሩ ናቸው። ከልማት ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በመሥራት በዘርፉ በአማካሪነት መንግሥትን በበጎ ፈቃድ እያገዙ ይገኛሉ። ከዘርፉ ሳይለዩ መቆየታቸው ለሙያው ያላቸውን ክብርና በሙያው ጥልቅ እውቀት ያላቸው መሆኑን ያመለክታል። በግብርናው ዘርፍ የካበተ ልምድ ካላቸው ከዶክተር አበራ ዴሬሳ ጋር ባለፉትም፣ አሁንም ካለው የግብርና እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ግብርና በአንድ በኩል ከኋላቀር የአመራረት ዘዴ ባለመላቀቁ ዘርፉ አላደገም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብርናው አድጓል ይባላል። እነዚህ ሁለት ሀሳቦች መነሻቸው ምንድነው? አድጓል ከተባለስ እድገቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አበራ፡- የኢትዮጵያ ግብርና የት ላይ ነው? ለምንስ ነው ስለኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ለውጥ የምናወራው? ለምንድነው በምግብ እህል ራሳችንን ያልቻልነው? የሚሉት በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። ጥያቄዎቹ ተገቢ ናቸው። ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደ አመራርም እንደ ተመራማሪም ስለ ግብርና ወይንም የግብርናን ተፈጥሮ ማወቅ ያስፈልጋል፤ በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ግብርና በሬ ጠምዶ ማረስና መኮትኮት፣ በአጠቃላይ ከጉልበት ሥራ ያለፈ እንዳልሆነ አርገው የሚመለከቱ ጥቂት አይደሉም። ይህ ባህላዊ የአመራረት ዘዴ ለመኖር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ግብርና ግን ሳይንስ ነው። ሳይንሱን ተከትለን ሰርተናል ብለን መናገር አንደፍርም። ግብርና እውቀትና ሀብት ይጠይቃል። ረጋ ባለ መንፈስም ማሰብን ይጠይቃል። ሰብሉ ስለሚፈልገው ንጥረ ነገር፣ ምን አይነት በሽታ እንደሚያጠቃውና ሌሎችም ነገሮች በምርምር ተለይተውና ድጋፍ ተደርጎ መሰራት ያለበት። በዚህ መልኩ ግንዛቤ መያዝ ስላለበት ነው ሀሳቡን ያስቀደምኩት፡፡
ግብርና አድጓል፣ አላደገም ስለሚባለው ጉዳይ እንመልክት። ግብርና አላደገም የሚሉ ወገኖች ያነሱት ሀሳብ ስህተት ነው፤ ግብርና አድጓል። በአገሪቱ እኤአ በ2002 ስድስት ሚሊየን ቶን ሰብል ነበር የሚመረተው። አሁን ደግሞ እስከ 42ሚሊየን ቶን ለማምረት ታቅዷል። ከስድስት ሚሊየን ቶን ወደ 42 ሚሊየን ቶን መድረስ የግብርናውን እድገት ያሳያል።
የምርምር ሥራም አድጓል። ነገር ግን ያደገው የግብርና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥርና የፍላጎት መጨመር ጋር ባለመጣጠኑ አላደገም ሊባል ይችላል። ምርትማነትንና የምርት ተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የጥናት ሥራ ያስፈልጋል። የዛሬ 20 አመትና ከዚያ በፊት የነበረው ፍላጎትና አሁን ያለው ፍላጎት ይለያያል። አርሶ አደሩ ልጁን ለማስተማርና የኢንደስትሪ ግብዓቶችን ለመግዛት፣ ዘመናዊ ኑሮ ለመኖር በውድድር ላይ ነው ያለው። ይሄ ሁሉ ፍላጎት ከምርት መጨመር ፍላጎት ጋር መታየት አለበት። እንደ አገርም ኢንዱስትሪዎችና የትምህርት ተቋማት ተስፋፍተዋል። እነዚህ ሁሉ ምርት ይፈልጋሉ፡፡
እኔ በሥራ ላይ በቆየሁባቸው ጊዜያቶች የሚመረተው የበቆሎ ምርት በአገር አቀፍ በአማካይ በሄክታር 24 ኩንታል ደርሶ ነበር። ዛሬ ወደ 38 ከፍ ብሏል። ፍላጎት እየጨመረ ስለሆነ ከዚህም በላይ መሄድ አለበት።
እድገቱ በሂደት አቅምን መሠረት አድርጎ የተገኘ ነው። ግብርናን ለማሳደግ የተሻሻለ፣ የማዳበሪያ፣ ኬሚካልና ሌሎችንም ግብአቶች አቅርቦት ያስፈልጋል። የምርት ብክነትን ለመቀነስ ሜካናይዜሽን መጠቀም ይጠበቃል። ለምርትና ምርታማነት እድገት የሚያስፈልጉ ግብአቶችና ቴክኖሎጂን ለማሟላት የአገር አቅም ውስን ነው። በዚህ ምክንያት መላ የኢትዮጵያ አርሶ አደርን ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም።
አገሪቱ ያላት ሀብት መሬትና የሰው ጉልበት ነው። በዚህ እድገታችንን እንጀምር ተብሎ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ ሲሰራበት ቆይቷል። በዚህም ላለፉት 20 አመታት ጥሩ ነው የሚባል የግብርና እድገት ታይቷል፤ እድገቱ 19 በመቶ ደርሷል። ከዚህ አንፃር ግብርናው አድጓል ነገር ግን እድገቱን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም ላይ ይቀረዋል የሚለውን መቀበል ነው። ፖሊሲው ተገምግሞ ክፍተቶችን በመለየት፣ ምርታማነት የሚጨምርበትን አቅጣጫ መቀየስ የወደፊት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ሥርዓትና አሁን በለውጡ መንግሥት የታዩ የአሰራር ለውጦች አሉ?
ዶክተር አበራ፡- አዎ አለ። እኔ በሥራ ላይ በነበርኩበት ጊዜ /ባለፈው ሥርዓት / መንግሥት ይከተል የሚከተለው ነፃ ገበያ ነው። ለገበሬው የማዳበሪያ፣ የብድርና የተለያዩ የግብዓት ድጎማ አያስፈልግም የሚል አቋም ነበረው፤ ይህ አቋሙ ግን ብዙ አላራመደውም፡፡ምክንያቱም ገበሬው በተበጣጠሰ ማሳ ላይ የሚያመርትና የሀብት አቅምም የሌላው በመሆኑ በራሱ አቅም መንቀሳቀስ አልቻለም።
አሁን ላይ ያለው የለውጥ መንግሥት አቋም ደግሞ አርሶ አደሩ ድጋፍ ማግኘት አለበት የሚል ነው። ትራክተር ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ፣ ከባንክ ብድር እንዲመቻች፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴና ሌሎችም የሚጠቀሱ ለውጦች ታይተዋል። እድገት ስለማይቆም ባለው ላይ እየጨመሩ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ወቅት መንግሥት ለስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክረምት ከበጋ እንዲመረት እያበረታታ ይገኛል። እንደ ግብርና ባለሙያነትዎ ይህን ሁኔታ እንዴት ገመገሙት?
ዶክተር አበራ፡- የስንዴ ልማቱን የፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው የሚያደርጉ አካላት አሉ። ይህ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ቀድሞም ቢሆን የስንዴ ልማት አለ። በዚህ ወቅት እየተከናወነ ያለውን የስንዴ ልማት ከቀድሞው ለየት የሚያደርገው የቀድሞው ዝናብን መሠረት ያደረገ ብቻ መሆኑ ላይ ነው። ይህ ሲባል ግን ቀድሞ ስንዴ በመስኖ አይለማም ማለት አይደለም። ስንዴ በመስኖ ሊለማ እንደሚችል በ1970 እና 1980 ዓ.ም በተደረገ የምርምር ሥራ ተረጋግጧል። ዓለም አቀፍ ውጤትም አለ።
አሁን ላይ የተለወጠው ነገር የአመራር እይታ ነው። አመራሩ ከችግር ነው የተነሳው፡፡ዝናብን መሠረት ያደረገ የስንዴ ልማት የምግብ ፍጆታንም መሸፈን አልቻለም። ድርቅ ሲያጋጥም ችግር ውስጥ እንገባለን፤ ከውጭ ለመግዛት እንገደዳለን። ለምን በመስኖ አናለማም ከሚል መነሻ ጥናት ተደረገ። በጥናቱም አማካሪ ሆኜ ተሳታፌያለሁ። ለልማቱ የሚውል ውሃ፣ መሬትና ዘር መኖሩ ተረጋገጠ። መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑ። በዚህ ሂደት ነው ወደ ልማቱ የተገባው። ከቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች የተጀመረው የስንዴ ልማት ወደ መላ አገሪቱ ተዳርሶ ውጤቱ እየታየ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ለማከናወን የሚያስችል መሬት፣ ውሃ የግብዓት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ አቅምስ እንዴት ይታያል?
ዶክተር አበራ፡- እጽዋት ውሃና ሙቀት ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የለም። ተጨማሪ የሚያስፈልጉት ማዳበሪያ፣ የአረም መከላከያ ኬሚካልና ሌሎች ግብዓቶች ናቸው። ለመስኖ የሚውል ወደ ሰባት ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬት፣ በሚሊየን የሚቆጠር ሜትሪክ ኩዩቢክ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ አለ።
በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ያለው የስንዴ ልማት አንድ ሚሊየን ሄክታር እንኳን የሸፈነ አይደለም። አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመሸፈን ነው እቅዱ። በመኸር የግብርና ሥራ ወደ ሜካናይዜሽን የተገባው ከጥቂት አመታት ወዲህ ነው። ምክንያቱም ትራክተርና ኮምባይነር በመኸር ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ያለጥቅም ነበር የሚቀመጠው። ይህ አላበረታታም።
አሁን የመስኖ ልማት መጀመሩ ክፍተቱን አስቀርቶታል። መንግሥት በዚህ የልማት እንቅስቃሴ አራት ግቦችን አስቀምጧል። እነዚህም በምግብ እህል ራስን መቻል፣ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት፣ የወጪ ንግድ መጨመር፣ የሥራ እድል መፍጠር የሚሉት ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ለአገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑም መዘንጋት የለበትም። የግብርና ዘርፉ ከ33 በመቶ በላይ ነው ለአገሪቱ አጠቃላይ ምርት አስተዋጽኦ የሚያደርገው፡፡ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም 77 በመቶ ድርሻ አለው። 72 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የግብርና ውጤት ነው። የኢንዱስትሪ ግብዓትም እንዲሁ ከግብርና ነው የሚገኘው፡፡በመሆኑም የግብርና ሥራውን ከማሳደግ ውጭ አመራጭ የለንም። ግብርናው ይህን ሁሉ ቱሩፋት እያስገኘ ነገር ግን በበቂ ድጋፍና ክትትል ተደርጎለታል ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናው ለማዘመን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በተለይም ሜካናይዜሽን በመጠቀም ረገድ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ዶክተር አበራ፡- ካለፉት ሥርዓቶች ጀምሮ በመስኖ የማልማት ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡በፖሊሲ ደረጃም ይገለጻል። አሁንም መስኖ ትኩረት ተሰጥቶታል። መንግሥት ያመቻቸው የሚቆጠር የመስኖ መሰረተ ልማት የለም። በመስኖ ለማልማት ከፍተኛ ሀብት ወይንም ካፒታል ይጠይቃል። ለመስኖ ልማት የሚውሉ የተለያዩ ማሽነሪዎች ወይንም መሳሪያዎች በአገር ውስጥ አይመረቱም። በውጭ ምንዛሪ ነው ከውጭ የሚገቡት። ይህን ማሟላት በአገር አቅም አይቻልም። በአበዳሪና በለጋሽ አገሮች ካልታገዘ የመስኖ ልማት ፍላጎት ብቻ ሆኖ ይቀራል። መንግሥት በዚህ ላይ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናን ትራንስፎርም ማድረግ ያስፈልጋል በሚል እየተሰራ ነው። የኢትዮጵያ ግብርና እንዴት ትራንስፎርም ሊደረግ የሚችለው በምን መልኩ ነው?
ዶክተር አበራ፡- ሁልጊዜ ለተሻለ ነገር መሥራትና ማሰብ ያስፈልጋል። በግብርናው ላይ በየአመቱ ሶስትና አምስት ኩንታል ብቻ እየጨመሩ መሄድ አያዋጣም። በሄክታር 15፣20፣ ከዚያም በላይ በመጨመር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ወደ ትራንስፎርሜሽን መግባት ይጠበቃል። በምርምርም፣ በዘርም፣ በኤክስቴንሽንም፣ በተፈጥሮ ሀብትም ትራንስፎርም በማድረግ ወደ ተሻለ እድገት መሄድ ይገባል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ፖሊሲው መፈተሽ አለበት ተፈትሿል። በዚህ ረገድ ያለው እንቅስቃሴም አበረታች ነው፡፡ከተናጠል እንቅስቃሴ በጋራ የመሥራት ፍላጎት እየታየ ነው። ይህ ሲሆን ግብርናው ትራንስፎርም ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት አገሪቱ ስንዴና ዘይት በስፋት ከውጭ ታስገባ ነበር። በወቅቱ ኢምፓርት መር ስትራቴጂም አልነበራትም፤ በተለይ ከውጭ ዘይት እየገባ የነበረበት ሁኔታ አነስተኛ ዘይት አምራቾችን ከገበያ አስወጥቷል፤ ምንም አይነት እሴት ያልተጨመረበት የግብርና ምርት ለውጭ ገበያ እየቀረበ ከውጭ የሚገባው ዘይት በውድ ዋጋ ይሸጣል የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ይሰጡ ነበር። ባለፈው ሥርዓት እርስዎም በዘርፉ በአመራርነት ላይ ስለነበሩ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር አበራ፡- የሚሰጠውን አስተያየት እኔም እሰማለሁ። ከንጉስ አፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ጀምሮ በግብርናው ዘርፍ እድገት እየተመዘገበ መሆኑ ሀቅ ነው። 19 በመቶ እድገት የተመዘገበው በኢህአዴግ የአመራር ሥርዓት ነው። በደርግ ሥርዓትም ቢሆን የበቆሎ ምርት ተትረፍርፎ ኩንታሉን በስምንት ብር የሚገዛ ጠፍቶ እንደነበር አስታውሳለሁ። በወቅቱ ኬንያ እንድትገዛ ተጠይቃ ፍቃደኛ አልሆነችም። በዛን ጊዜ እኔ ተመራማሪ ስለነበርኩ መረጃው አለኝ።
ምርትን ማሳደግ ጥሬውን ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች ካሉ ተሳስተዋል። በምርት እድገት ውስጥ በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር ለሰው ልጅ እድገትና ጤና አስፈላጊነቱ ጭምር ይታያል። ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ ማስገባት የጀመረችው በቅርብ ጊዜ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የፍላጎት መጨመር ለውጥ ነው። ኢንዱስትሪዎች ተስፋፉ። ፍላጎትን ለማሟላት ከውጭ ማስገባት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው መግባት የጀመረው። አንዳንዴ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ከማምረት ይልቅ በተመጣጣኝ ዋጋ ከውጭ ማስገባት ተመራጭ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን በማየት የውጭ ምርትን መጠቀም የሚመርጡ አገራት አሉ።
ዘይትን በተመለከተ ለተነሳው። የተጠቃሚው ምርጫ ነው ለውጡን ያመጣው፡፡የታሸገና በዋጋም የተሻለ ማግኘት ሲጀምር በባህላዊ መንገድ የሚቀርበውን እየተወ ሲመጣ አምራቾቹ ከገበያ ወጡ። ከውጭ የሚገባው ዘይት በብዛትና በዋጋ የተጠቃሚውን ፍላጎት ማሟላት የቻለ ነበር። እውነታው ይሄ ነው እንጂ ኢምፖርት መር አልነበረም።
አሁን ደግሞ ዘይት በስፋትና በዋጋ ተመጣጣኝ የሚያቀርቡ አገሮች በጦርነት ውስጥ መሆናቸው የዘይት ዋጋ ንሯል። አሁን ላይ ደግሞ መፍትሄ መፈለግ ይገባል። ዘይት በአገር ውስጥ ተመርቶ እንዲቀርብ በመንግሥት ጥረት እየተደረገ ነው። ለዘይት ምርት ግብዓት የሚሆን ምርት እንዲመረትም እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኃላፊነት በቆዩባቸው አመታት ግብርናውን አሳክቻሉ ውጤታማ ነበርኩ ይላሉ?እግረመንገድዎንም ለሀገርዎ ያለዎትን ምኞት ይግለጹልን፡፡
ዶክተር አበራ፡- ምንም እንኳን ሰው እራሱን ጥሩ ሰርቻለሁ ባይልም የምችለውን አድርጊያለሁ። በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ ብሆንም ብዙ ሥራ ነበር የምሰራው። መዘንጋት የሌለበት ነገር የግብርና ሥራ የአንድ ሰው ብቻ ውጤት አይደለም። እኔ አንድ ሚኒስትር ዴኤታ ነው የነበርኩት። ከፌዴራል እስከ ገበሬ ማህበር በግብርናው ዘርፍ የተሳተፉ ሰዎች አሉ። የነዚህ ሁሉ አካላት ውጤት ነው ብዬ የምወስደው፡፡
ምኞቴን በተመለከተ፤ የግብርናው ሥራ፣ ምርምሩም፣ የትምህርት ሥርዓቱም፣የአመጋገብ ስልቱም፣ ሁሉም ተቀይሮና ተሻሽሎ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ የሚፈልገውን አግኝቶና በልቶ በሰላም ሲኖር ማየት ምኞቴና ፍላጎቴ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለትብብርዎ አመሰግናለሁ
ዶክተር አበራ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም