ጥር ወር በብዛት የሠርግ ወቅት ነው። ዘመነ መርዓዊ ይባላል። መርዓዊ በግእዝና በትግርኛ ሙሽራ ማለት ነው። ገበሬው የዘራውን ሰብል አጭዶና ወቅቶ ወደ ጎተራው ከከተተ በኋላ የሚያርፍበት እንዲሁም የሚዝናናበት ወቅት መሆኑም ዘመነ መርዓዊ ያሰኘዋል። በሌላ አገላለፅ የደስታና የፍስሃ ጊዜ እንደማለት ነው።
የእረፍትና የደስታ ጊዜን ተከትሎ ደግሞ መዋብና ማጌጥ እንዲሁም አምሮ ለመታየት የሚደረግ ጥረት በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ነው። ስለውበት ሲነሳ በኢትዮጵያ ከዘመናዊ መዋቢያዎች በበለጠ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ባህላዊ መዋቢያዎች በብዛት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል። ለሴቶች መዋቢያነት በማገልገል በዓለም የቆየ ታሪክ ያለው ሂናም በrገራችን በሠርግና በበዓላት ጊዜ በብዛት እንደ ፋሽን ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። እኛም በዛሬው የፋሽን ገጻችን ስለሂና እናነሳለን።
የሂና መዋቢያ የሚዘጋጀው ከዛፍ ቅጠል ነው። የሂና ዛፍ ከ10 እስከ 15 ጫማ ቁመት ወይም ከ2-5 ሜትር ርዝመት አለው። ዛፉ በግብፅ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በህንድ፣ በሞሮኮ፣ በኒጀርና በናጄሪያ ይገኛል። ጥንታዊቷ ግብፅ ሂናን ለመዋቢያ በስፋት ትጠቀምበት እንደነበር ይነገራል። በውበቷ ብዙ ጠቢባን የተቀኙላት ክሊዮፓትራ የተባለችው የጥንታዊት ግብፅ ንግሥትም ሂናን በመቀባት ትዋብ እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ። የሮማውያን ነገሥታትም ሂናን ለመዋቢያነት ይገለገሉበት ነበር። በሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ፣ በአረቢያ ሰርጥ፣ ሩቅ ምሥራቅና ደቡብ እስያም ሂና ተመሳሳይ ግልጋሎት አሁንም ድረስ እየሰጠ ይገኛል። የሂና ንቅሳት ዘመናትን አልፈው አሁንም በዓለም ዙሪያ ታዋቂ ፋሽን ናቸው፡፡
የሂና ዛፍ(ተክሉ) በኢትዮጵያ በአፋር አካባቢ ይገኛል። ሂና ወይም በሳይንሳዊ ስሙ (Lawsonia inermis) በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክም የሚገኝ ሲሆን በሥፍራው ያሉ የአፋርና የኦሮሞ ብሔሮች ለጤና፣ ለቅባትና ለመዋቢያ (Health, cosmetics and beauty) አገልግሎት እንደሚጠቀሙበት Plant Biology & soil health ጆርናል ላይ ዲንኪሳ በቼ እና ሌሎች ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያወጡት ጥናት ያሳያል። ከመዋቢያና መኳኳያ በተጨማሪ በሞቃታማ ቦታዎች ሂና የሚቀቡ ሰዎች ሙቀትን ለመቋቋም እንደሚያግዛቸው ሰነዶች ያሳያሉ፡፡
ሂና ለመዋቢያ አገልግሎት የሚውለው በብዛት ቅጠሉ ደርቆ ተወቅጦ፤ ዱቄት ከሆነ በኋላ ሻይን በመቀላቀል ወደ ቅባትነት ሲቀየር ነው። የሠርግና የበዓላት ጊዜ ሲሆን ሂናን ሴቶች ፀጉራቸውን ለማስዋብ ቅንድባቸውን ለማሰማመር እንዲሁም እጃቸውንና ክንዳቸውን፣ ባታቸውንና እግራቸው እንደ ንቅሳት ይጠቀሙበታል። በሶማሌ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ እና በአፋር አካባቢ ሴቶች እንደንቅሳት በብዛት ይገለገሉበታል። የሠርግና የሃይማኖት በዓላት ሲሆን ደግሞ ሂና እንደፋሽን ሆኖ ይዋቡበታል፡፡
ሂና በብዛት ፀጉርንና ቆዳን ለማስዋብ ያገለግላል። ሴቶች ፀጉርን ለማቅለምም በስፋት ይጠቀሙበታል። ለዚህ በተለይም ቀይ ሂና ተመራጭ ነው። በሠርግ ግዜም ሴቶች ለመዋቢያ በብዛት ይጠቀሙበታል፡፡በተለይ ሙሽሮችና ሚዜዎች። ከሠርግ ወቅት አገልግሎቱ በተጨማሪ እንደ ፋሽን ብዙ ሴቶች ሲዋቡበት ሲኳኳሉበት በብዛት ይታያል፡፡ከሠርግ ውጪም ሂና ርካሽና ተደራሽ በመሆኑ ተመራጭ ነው። ብዙ ሴቶች እጃቸውን፣ ክንዳቸውን፣ እግራቸውን፣ ባታቸውን እየተነቀሱበት ፋሽን አድርገው ይዋቡበታል። የሚነቀሱበትም ነገር እንደ ብዕር የሚመስል ሲሆን የሥዕል ክህሎት ያላቸው የውበት ሳሎኖች ሴቶችን በማሰማመር ይሠሩበታል። ሲነቀሱም መጀመሪያ ሰውነት ላይ በእስኪሪብቶ ነገር በመሳል ስለሆነ የህመም ስሜት የለውም።
በዋናነት ሰውነትን ማለትም እጅና እግርን እንዲሁም ክንድን መነቀስ የተለመደ ሲሆን ለዚህም የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን አበባዎችን በመሳል ለማሰማመር ሂና ትልቅ አገልግሎት ይሰጣል። ቆዳን ለማለስለስ የሚቀቡበት፣ ቅንድብን ለማሳመር የሚቀነደቡበት፤ ፀጉርን ለማስዋብና ለማቅለም የሚሰጠው ጥቅምም በበርካቶች ተመራጭ አድርጎታል።
ጥንታዊ ተፈጥሯዊ መዋቢያ የነበረው ሂና በዘመናችን ደግሞ ይበልጥ ስንና ኪን እየታከለበት የአጠቃቀም መሣሪያዎቹም እየዘመኑ ፋሽን ሆኖ በከተሞች አካባቢም ይታያል። በተለይ ቆዳን እንደንቅሳት ለማሰማመርና ለማስዋብ በዓለም በሴቶች ተመራጭና ተወዳጅ ፋሽን እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ሂናን ከሚያጎናጽፈው ውበት ባሻገር ፀጉር እንዲለሰልስና እንዳይሰባበር የሚያዘወትሩም አሉ። ስስ ቅንድብ ያላቸው ሴቶች እርሳስ በሚመስል ማቅለሚያ ቅንድባቸውን ያስተካክላሉ። ሂና በተለይ ለቅንድብ ከኩል በላይ ተመራጭ መሆኑን መሳለሚያ አካባቢ በሴቶች የውበት ሳሎን የምትሠራው ከድጃ ረዲ ትናገራለች። የሂና ንቅሳት በአገራችን ከሚደረጉት ንቅሳቶች የሚለየው ርካሽና ለብዙ ሰዎች ተደራሽ መሆኑንም ታስረዳለች።
በአዲስ ከተማ ጠቅላይ ቢሮ በሂና የምትሠራው ዘምዘም ከማል፤ በሂና ማስዋብ ከአካባቢው ሰዎች እንደለመደችና በሙያው መስራት ከጀመረች ሰባት ዓመት እንደሆናት ትናገራለች። ዘምዘም “የስዕልም ፍላጎቱ ስለነበረኝ፤ በሂና ንቅሳት ለመሥራት አስችሎኛል” ትላለች። ሴቶችን በሂና ለማስዋብ የሂናውን ቅጠል ከሐረርና ከአፋር አካባቢ እያስመጣች እንደምትጠቀም የምትናገረው ባለሙያዋ፣ ሠርግና በዓል ሲሆን ሴቶች የሂና ንቅሳትን በብዛት እንደሚጠቀሙበት ታብራራለች። ዘምዘም ከንቅሳቱ በተጨማሪ ቅንድብ እና ቆዳን ለማሰማመር ፀጉርን ለማስዋብና ለማቅለም የሚፈልጉ ሴቶችንም በብዛት አገልግሎቷን ፈልገው እንደሚመጡ ተናግራለች ።
በሂና እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት ሳምራዊት አበራ እና ሱመያ ኢብራሂም የሂና ንቅሳት እጅ እና ክንድ ላይ እስከ አንድ ወር እንደሚቆይ ገልጸዋል። የሂና የንቅሳት ስዕሎች በተለይ እጅና እግርን ከመታጠብ በስተቀር ፤ ልብስ ቁሳቁስ በብዛት የሚያጥቡበት ከሆነ ወዲያው ይጠፋል ይላሉ ተጠቃሚዎቹ ሲናገሩ ። ሂና ተክሉ በአገራችን ቢኖርም በከተሞች ከውጭ አስመጥቶ የመጠቀም ነገርም አለ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም