≪ክፉ ንግግር እንጨት ላይ እንደተመታ ምስማር ነው፤ በይቅርታ ብንጠግነውም ጠባሳው አይተውም≫ የሚል አባባል ጊዜውን በውል ባላስታውሰውም አንድ ወቅት ላይ ማንበቤ ትውሰ ይለኛል። እውነት ነው፤ በአንደበታችን የምንናገረው ነገር መልካም ሲሆን፣ ጽድቅ ሆኖ እንደሚቆጠርልን ሁሉ መጥፎ ከሆነ ደግሞ እርኩሰት ይሆንና በፈጣሪ ፊት ጭምር ተጠያቂ ያደርገናል። ኃጢአት በአብዛኛው ካልተገባ ንግግር የሚመነጭ ነው። ስለዚህም እንደስድብ እና የሐሰት ንግግር እንዲሁም አሳሳች ከሆኑና መሰል አባባሎች ከአንደበታችን እንዳይወጡ ልጠንቀቅ ይገባል።
አስከፊ በሆነ ንግግር ሰዎችን መናገር እንዲሁም ቁጣና ጭካኔ የተሞላባቸው ቃላት እና ግብታዊ ንግግሮች፣ የማስፈራሪያ ቃላት፣ የሐሰት ምስክርነት እና በሐሰት መማል ሁሉም በአንደበት የምንሠራቸው እርኩሰት ናቸውና ከአንደበታችን ሊወጡ አይገባም የሚል እምነት አለኝ።እንዳውም በተቃራኒው ≪መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች≫ የሚለውን መከተል ያስፈልጋል። መጥፎ ንግግር ምላሹም መጥፎ ነውና ሰዎችንም ወደ ስሜታዊነት ይከታል።
ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፤ ‹‹መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤ ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራልና።›› የምንናገረው ቃል በሌሎች ላይ ተጽእኖ አለው፤ ስለዚህም ከአንደበታችን የምናወጣው ቃል በማስተዋል መሆን አለበት።
ይህን ሀሳብ እንዳነሳ ያስገደደኝ ከፍትህ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ያገኘሁት ታሪክ ነው። ዘወትር ‹‹አንቺ የማትረቢ በሽተኛ›› እየተባልኩ ስሰደብና ስዘለፍ ኖሪያለሁ ያለች የ39 አመት ወይዘሮ፣ ውስጧ የተፈጠረው መርዘኛ ቁሰል አልሽር ቢላት የልጆቿ አባት በሆነው በትዳር አጋሯ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እጇን አንስታበታለች። ይህንን አስመልክቶ የሚከተለውን አሰናድተናል።
ታታሪዋ ወይዘሮ
ወይዘሮ ከበቡሽ አለሙ አበበ፣ ኑሮዋን ለማቃናት ዘወትር የምትለፋ ወይዘሮ ናት። አነሰ አደገ ሳትል ኑሮዋን ለመደገፍ ትታትራለች። ምንም እንኳን ፊደል ያልቆጠረች ቢሆንም ተፈጥሮ በለገሰቻት እውቀት ነግዳም በጉልበቷ አድራም ልጆቿ ምንም ሳይጎድልባቸው እንዲያድጉ ጥረት ታደርጋለች። በተቃራኒው ደግሞ የተማረውና የተሻለ ገቢ የሚያገኘው የትዳር አጋሯ በምትሰራው ነገር ምንም ደስታ ያልነበረው እንዲሁም በትዳሩ የሚናደድ ዘወትር ጭቅጭቅን አማራጭ ያደረገ ሰው ነበር።
በወጣ በገባ ቁጥር በውሃ ቀጠነ ሚስቱን መነዝነዙን ሳያንስ ያለመማሯን ነገር እያነሳ ያንቋሽሻትና ያዋርዳት ጀመር። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ የሆነበት ሴት እንደ ምንም ለልጆቼ ስል ልታገስ ብላ አንገቷን ደፍታ የሆዷን በሆዷ ይዛ ለመኖር ብትጥርም ‹‹አንቺ የማትረቢ! በሽተኛ!›› የሚለው ስደብ ግን ከውስጧ አልወጣ እያለ የልጆቿን አባት በጥላቻ እንድትመለከት አልፎ ተርፎም እሱን ለማጥፋት እቅድ ለማውጣት የምታስብ ሴት እንድትሆን አደረጋት።
እለት እለት ውስጥን አቁሳይ በሆነ ቃላት ወትሮም መርቅዞ አልድን ያላትን የውስጥ ቁስሏን እየነካካ ወደማትወጣው ጥላቻ ውስጥ ይከታታል። ከጥላቻም በላይ ፍፁም ጭካኔን እለት ከእለት እንድትለማመድ ትሆናለች። በከባድ የበታችነትና ራስን የመጥላት ስሜት ውስጥ ሆና ልጆቿን በማሰብ ነገሮችን ልታልፋቸው ብትሞክረም የውስጧን ጩኸት ግን ማስቆም አልቻለችም ነበር።
‹‹ግደይው!…ግደይው!…›› የሚለውን ስሜቷን ሊያሽር የሚችል ምንም ሀይል ጠፋ። ስለ ልጆቿ ብታስብ ስለነገዋ ብታልም ምንም ከልክ በላይ የሞላውን የጥላቻ ስሜት ከውስጧ ፍቆ ሰላምን እንድታስብ ብሎም ነገን በተስፋ እንድታይ ሊያደርጋት የሚችል አማራጭ አጣች። ከዛ ያንን የጥላቻና የበቀል ስሜቷን የምታበረድበት እቅድ ማውጣት ቀጠለች ።
የበቀል ዛቢያ
አቶ ፀጋዬ ሞላ ይባላል። ብዙም ደስተኛ የሚባል አይነት ሰው አይደለም። ማማረርና አቃቂር ማውጣት የዘወትር ተግባሩ የሆነ ሰው ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ ‹‹አይጠዳሽ›› የሚባል አይነት ሰው ነበር። አድጎ ተምሮ ስራም ይዞ እንኳን ያንን ባህሪውን አልተወም። በዚህ ባህሪው ብዙም ከሰው ጋር የማይግባባ ጓደኛ ያልነበረው ሰውም ነበር።
ልክ ስራ ይዞ የመጀመሪያ ደመወዙን እንደተቀበለ ነበር የወላጆቹን ቤት ትቶ በመውጣት ብቻውን መኖር የጀመረው። ወትሮም በሰላም ከቤተሰቡ ጋር ኖሮ የማያውቀው ይህ ሰው፣ ዞር ብሎ አንድም ቀን ወላጆቹን ለመጠየቅ ተመልሶ አያውቅም ነበር። አንዳንዴ በተከራያት አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ምግቡን እያበሰለ ይመገባል። ቤቱ ካላበሰለ ግን ለመኖር የተከራየባት አንድ ክፍል ቤት አካባቢ ከበቡሽ አለሙ የተባለች ወጣት በከፈተችው አነስተኛ ምግብ ቤት ሄዶ ይመገብ ነበር።
ቤት ከሚያበስለው ይልቅ የከበቡሽን ምግብ ምርጫው ያደረገው ፀጋዬ ወደ ምግብ ቤቷ መመላለስ አበዛ። ብዙም ፊቱ የማይፈታው ሰው በመመላለሱ ከከበቡሽ ጋር ተላመደ፤ መላመዳቸው ወደ ፍቅር አድጎ አብረው መኖር ጀመሩ። የተጋቡ ሰሞን በደስታና በመከባበር የተወሰኑ ወራትን ቢገፉም ውሎ ሲያድር ግን የፀጋዬ አመል ከተሸሸገበት ብቅ ማለት ጀመረ።
በዚህ መካከል የመጀመሪያ ልጃቸውን ሰላገኙ ከበቡሽ ስራዋን እርግፍ አድርጋ ትታ ቤት መዋል ጀመረች። የገቢው መቀነስ ከአባወራው አመል ጋር ተደማምሮ ንትርክ የማያጣው ኑሮ ለመግፋት ተገደዱ። በዚህ መካከል ሁለተኛ ልጃቸውን ደገሙ። አሁን ሁሉም ነገር አይን አውጥቶ ዘለፋና ማንጓጠጡ በርክቶ ዱላም ተከተለ።
ያን ጊዜ ከበቡሽ እንደምንም ራሷን አጠናክራ ወደ ቀድሞ ስራዋ ተመለሰች፤ ያ ደግሞ አባወራውን ጭራሽ አስቆጣው፤ ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ንዝንዝ ሆነ። ዝልፊያውና ማንጓጠጡን ግን እማወሪት መቋቋም ተስኗት ነበር።
የቂም ጅራፍ
ዘወትር ዝልፊያና ማንጓጠጡ የሰለቻት ወይዘሮ፣ ቂም ቋጥራ መጥረቢያዋን ስላ ሰው ሁሉ እንቅልፍ እስኪወስደው መጠበቅ ጀመረች። በተቀመጠችበት እንቅልፍ የጣላት ወይዘሮ፣ መጥረቢያዋን እንደታቀፈች ከእንቅልፏ ስትባንን
የቀን እቅዷን አስታወሰች። ያለምንም ማወላወል ባሏ ወደተኛበት ተመለከተች። ለጥ ብሏል። ልጆቿም ጭልጥ ያለ የእንቅልፍ ዓለም ውስጥ መሆናቸውን አረጋገጠች።
ዕለቱ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ነው። ከሌሊቱ በግምት 9፡00 ሰዓት አካባቢ። በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው 58 ቆጣሪ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው። በወቅቱ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ አገር ሰላም ብሎ የተኛውን የሁለት ልጆቿ አባት የሆነውን ሟች ፀጋዬ ሞላ፣ ‹‹አንቺ የማትረቢ! በሽተኛ!›› እያለ ይሰድበኛል ከሚል ቂም በመነሳት በጭካኔ መጥረቢያውን ሰነዘረች። በአንድ ምት ጭንቅላቱን በመጥረቢያ የተመታው አቶ ፀጋዬ፣ እስከወዲያኛው ላይነሳ አሸለበ። ይሁንና ውስጧ ይንተከተክ የነበረው የበቀልና የጥላቻ ስሜት ጠፍቶ ውስጧ በሽብር ተሞላ። የሟችን ፊት ሸፍና ወደደጅ በመውጣት በውደቅት እጇን ለህግ አካላት ሰጠች።
የፖሊስ ምርመራ
‹‹ባለቤቴን ገድያለሁ›› ስትል እጇን ለፖሊስ ያስረከበችውን ሴት በመያዝ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኘው ፖሊስ፣ ያየውን ማመን አቅቶታል። የተሸፈነው ሰው እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ጭንቅላቱን ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል። በዛ ያለ ሰው ድምፅ ሰምተው ከእንቅልፋቸው የነቁት ህፃናት ግራ ተጋብተው የእናታቸውን አይን አይን ይመለከታሉ።
ፖሊስ ይጠቅመኛል ያለውን መረጃና ማስረጃ በመውሰድ ተከሳሿን ይዞ ወደ ማረፊያ ይወስዳል። በእጁ የገባውን መጥረቢያ፣ የተከሳሽን የእምነት ቃል፣ የፎረንስኪ ምርመራን በማድረግ ያጠናቀረውን ሕግ የሰው፣ የሰነድ እና የኢግዚቢት ማስረጃዎችን በመያዝ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት ያደርጋል።
ተከሳሽም ለፖሊስ በፍርድ ቤት እና በፖሊስ ጣቢያ ድርጊቱን ስለመፈጸሟ አምና የሰጠችውን ቃል ዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባት በኋላ በችሎት ቀርባ ክዳ የተከራከረች በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የሰው፣ የሰነድ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን በማቅረብ ክሱን በበቂ ሁኔታ አስረድቷል።
የፍርድ ቤት ክርክር
ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ግድያ ችሎት ነው፤ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጎአ እንደገለጹት የ39 ዓመቷ ወይዘሮ ከበቡሽ አለሙ አበበ፣ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 9፡00 ሰዓት በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው 58 ቆጣሪ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካለ የመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የሁለት ልጆቿ አባት የሆነውን ሟች ፀጋዬ ሞላ ‹‹አንቺ የማትረቢ! በሽተኛ!›› እያለ ይሰድበኛል ከሚል ቂም በመነሳት በጭካኔ ጭንቅላቱን በመጥረቢያ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገች በመሆኑ የወንጀል ምርመራ ሲደረግ ቆይቶ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ዐቃቤ ህግ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ መስርቶባት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።
ተከሳሽም ለፖሊስ በፍርድ ቤት እና በፖሊስ ጣቢያ ድርጊቱን ስለመፈጸሟ አምና የሰጠችውን ቃል ዐቃቤ ህግ ክስ ከመሰረተባት በኋላ በችሎት ቀርባ ክዳ የተከራከረች በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የሰው፣ የሰነድ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን በማቅረብ ክሱን በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንድትከላከል ብይን ቢሰጣትም የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለት ያላቀረበች በመሆኑ የመከላከል መብቷን አሳልፋ ሰጥታለች።
ውሳኔ
ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ዐቃቤ ህግ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል የመሰረተውን ክስ ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ሶስት የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ በእርከን 36 ስር በ21 ዓመት ጽኑ እስራት እና ለ5 ዓመት ከማህበራዊ መብቷ እንድትታገድ ወስኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015