ሳይንስ እንደሚለው የተስተካከለ አመጋገብ ስርዓት ያለው ህብረተሰብ አምራች ይሆናል። ስርዓተ ምግብ ደግሞ የተመገብነውን ምግብ በስነህይወታዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ሂደቶች በማለፍ በአጠቃላይ ሰውነታችን፤ በአሰራርና በሰውነት ግንባታ ዙሪያ እድገት ማምጣት ነው። እነዚህ ንጥረ ምግቦች በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፤ ዋና እና ንዑስ ይባላሉ። ዋና ንጥረምግቦች የሚባሉት ማንኛውንም ፍጥረት በብዛት ኃይል የሚሰጡትና የሰውነታችንን ስርዓተ ኡደት በትክክል እንዲሰራ የሚረዱ ናቸው። ንዑስ ንጥረ ምግቦች ደግሞ ስርዓተ ዑደቱ እንዲካሄድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት ናቸው። ሁለቱም ዓይነት ንጥረ ምግቦች ከአካባቢያችን ይገኛሉ።
የሰውነታችን ሙቀት በመጠበቅ፤ በመገንባትና የተጎዱ አካላት በመጠገን ኃይል የሚሰጡ ናቸው። ለመሆኑ ስርዓተ ምግብ ማለት ምን ማለት ነው? በአገራችን ያለው ሁኔታስ ምን መልክ አለው? ከተባለ መልሱን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና የስነ ምግብ ከፍተኛ ተመራማሪ እንዲሁም ብሔራዊ የስነ ምግብ መረጃ ማዕከል የኢትዮጵያ አስተባባሪ ከሆኑት ዶክተር አረጋሽ ሳሙኤል ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናልና እንደሚከተለው እንመልከተው።
አዲስ ዘመን ፦ ስርዓተ ምግብ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር አረጋሽ ፦ ስርዓተ ምግብ ጥሩና መጥፎ በሚል በሁለት ይከፈላል። ጥሩ ስርዓተ ምግብ ማለት ተመጣጣኝና በቂ የሆነ ምግብ መመገብ ማለት ነው። በቂ ሲባል ግን ሁልጊዜ አንድ አይነት ምግብ እየተመገብን የሚበቃኝን አግኝቻለሁ ማለት አይደለም። ከሁሉም አይነት ተመጣጣኝ ምግቦችን ማግኘት የግድ ነው። የምግቡን ተመጣኝነት ለመጠበቅ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እንቅስቃሴ አንዱ የስርዓተ ምግብ አካል ነው። በጠቅላላው ጥሩ ስርዓተ ምግብ የሚባለው በመጠኑ በቂ፣ በይዘቱ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ጥሩ ያልሆነ ስርዓተ ምግብ ደግሞ ሶስት ዓይነት ነገሮች አሉት። እነዚህም ከላይ ጥሩ ስርዓተ ምግብ ብለን ያነሳነውን በቂና ለሰውነት ግንባታ ኃይል መስጠት ብሎም ሌሎች ተጨማሪ አቅሞችን የሚፈጥሩ ምግቦችን ያልያዘ ዝም ብሎ ለረሃብ ማስታገሻ ብቻ የሚበላ ማለት ነው። እዚህ ጥሩ ያልሆነ ስርዓተ ምግብ ውስጥ የበዛ ከሚፈለገው መጠን እልፍ ያለ አመጋገብ ማለት ነው።
ሌላው እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ነገር ደግሞ ሰዎች ምግብ ይመገባሉ በገጽታቸውም ላይ እጥረትም ሆነ ሌላ ነገር አይታይም። ነገር ግን ውስጣቸው ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ሲያጡ ማለት ነው። ይህ በራሱ ጤናማ ያልሆነ የስርዓተ ምግብ አካሄድ ነው። ለምሳሌ፡- ደም ማነስ ያለበት ሰው አልጋ ይዞ አይተኛም፤ ስራ ይሰራል፣ ይማራል ነገር ግን ውስጡ ያለው የደም ዝውውር በቂና በተገቢው ልክ አይደለም። እንደዚህ ዓይነቶቹ ችግሮችም ጤናማ ካልሆነ የአመጋገብ ስርዓት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ስርዓተ ምግብ ለእከሌ ያስፈልጋል የሚባል ነው ?
ዶክተር አረጋሽ ፦ ስርዓተ ምግብ ለሁሉም ሰው የሚያስፈልግ ነው። ነገር ግን ማነው የበለጠ ተጠቂ ሊሆን የሚችለው ብለን ከተነሳን ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ተጋላጭ የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ስለዚህም ለእነሱ በተለየ ሁኔታ ያስፈልጋል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፡- አንድ ህጻን ከጽንሱ ጀምሮ ተወልዶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ጊዜ ድረስ ያሉት 1ሺህ ቀናት በርከት ያለ ተመጣጣኝ ምግብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። እናም ለአንድ ሰው የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ተዘጋጅተው፣ አድገው የሚያስፈልጋቸውን ይዘት አሟልተው የሚገኙበት በመሆኑ በእነዚህ ጊዜያት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። ስለዚህም የተለየ ለእከሌ ያስፈልጋል ወይ ላልሽው መልሱ የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም የሚያስፈልግ ቢሆንም በተለይ ከጽንስ ጀምሮ ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ልጆች በጣም ያስፈልጋቸዋል።
በሌላ በኩልም ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ከማንም በላይ የተመጣጠነ ምግብ ተመጋቢ ሊሆኑ ይገባል። ምክንያቱ ደግሞ እነሱ የሚመገቡት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሆዳቸው ላለው እንዲሁም ወልደው እያጠቡት ላለው ልጅ ነው።
ሌላው ወጣት ሴቶች ናቸው። ከሌላው በተለየ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ያለባቸው። ዋናው ምክንያት ደግሞ እነዚህ ሴቶች በወር አበባ ጊዜ የሚያጡት ንጥረ ነገር አለ። ይህ ንጥረ ነገር ሊተካ የሚችለው ጥሩ የሆነ የስርዓተ ምግብ ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ከሆነ ብቻ ነው። ጥሩ የሆነ የስርዓተ ምግብ ሂደት ከሌላቸው በተለይም አርግዘው ለመውለድ ሲያስቡ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን የሚያረግዙትና የሚወልዱት ልጅም የተጎዳ ይሆናል። በመሆኑም በመውለድ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ተገቢነት ያለው ስርዓተ ምግብ ሊከተሉ ይገባል። ነገር ግን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተሟላ የስርዓተ ምግብ ሊኖረው ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ሁሉም ሰው የተስተካከለ ስርዓተ ምግብ አካሄድን ይከተል ዘንድ ምን አይነት ምግቦች ምንጮቹ ሊሆኑ ይገባል?
ዶክተር አረጋሽ፦ በባህላችን ሁልጊዜ ስጋ የሚመገብ ሰው ሰውነቱ ሞላ ያለ ሰው ነው። ከጤነኛ ብሎም የተመጣጠነ ምግብ ካገኘ በጠቅላላው ከተመቸ ኑሮ ጋር የምናያይዘው። ይህ ግን ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት ነው። በአጭሩ ለተሟላ የስነ ምግብ ሂደት የሚረዱ የምግብ አይነቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ገብስ እና ሌሎችም የእህል ዘሮች ሲሆኑ፤ በጥራጥሬው ምድብ ደግሞ ሽምብራ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ማሾ፣ ምስርና ሌሎችም ሊሆኑ ይችለሉ። ወተትና የወተት ተዋጽዖ የአሳ ስጋ፣ የበሬ ስጋ፣ የዶሮ ስጋና ሌሎችም እንዲሁ ወሳኝ ምግብ ናቸው። እንቁላልና በአትክልት ዘርፍ ቢጫና ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው የምግብ አይነቶችን መመገብ የተሟላ ስነምግብ እንደተከተልን ማሳያዎች ናቸው።
ቀለል ባለ መልኩ ስንገልጸው ግን አንድ ሰው እዚህ ከተዘረዘሩት መካከል በቀን የተወሰኑትን እንኳን ቢያገኝ መልካምና ተገቢ ነው። ቀላል ምሳሌ ብነግርሽ የተለመደው የምንበላው በየዓይነቱ እንኳን ከሞላ ጎደል እህሉንም ጥራጥሬውንም ይይዛል። ስለዚህም እዛ ላይ አንድ ሙዝ ወይም ሌላ የፍራፍሬ አይነት ብንጨምርበት የሚያስፈልገንን የተመጣጠነ ምግብ አገኘን ማለት ነው።
ሌላውና ትልቁ ነገር ውሃ ሲሆን፤ ብዙ ሰው የሚቸገርበትም ነው። ነገር ግን የተሟላ የስነምግብ ስርዓትን ተከተልን ማለት ውሃ የመጠጣት ልምዳችንን ማዳበር ስንችል ነው። በህክምናውም በሳይንሱም የሚመከረው በቀን ቢያንስ ከስምንት እስከ 10 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ያስፈልጋል። ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠር ድርቀትን ይከላከላል። የምግብ ዝውውርን ያፋጥናል፤ ሰውነት በስራም ሆነ በተለያዩ ነገሮች እንዳይደክም ይልቁንም እየታደሰ እንዲሄድ ያግዛል። ነገር ግን ሁልጊዜ ስጋ ቅባት የበዛበት እንዲሁም አቅም የሚጠይቁ ምግቦችን መመገብ ወሳኝ አይደለም። እንደውም እነዚህ ምግቦች ሲዘወተሩ የተለያዩ ችግሮችን ይዘው ይመጣሉ። ስለሆነም የተመጣጠነ የሚለውን መለየት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የስነ ምግብ ስርዓታችን መዛባቱ ወይም ደግሞ በሚመከረው መጠን አለመጠቀማችን የሚያስከትለው ጉዳትስ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አረጋሽ፦ ብዙ የስነ ምግብ ተመራማሪዎች እንደሚሉት አገራችን ላይ መቀንጨር በጣም የሚታይ ችግር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ መቶ ህጻናት መካከል 37ቱ ለእድሜያቸው የሚገባቸውን ቁመት የያዙ አይደሉም። ወይም ደግሞ የሚቀነጭሩ ናቸው። ልጆች ሁለት ዓመት እስከሚሆናቸው ድረስ የጭንቅላታቸው፣ የሰውነታቸው እንዲሁም የሴሎቻቸው እድገት የሚፈጠረው በወቅቱ በሚገባቸው መልኩ የስርዓተ ምግብ ስርዓትን ባለመከተላቸው ነው። ይህ ደግሞ ምርታማነታቸው ይቀንሳል፤ በትምህርት ደካማ ይሆናሉ፤ በማህበራዊ ግንኙነታቸውም የተጎዱ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ የስርዓተ ምግብ መጎዳት ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው። እናም ከጅምሩ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
ችግሩ ዘርፈ ብዙ መሆኑን የሚያሳየው አንድ ጽሁፍ አለ። እሱም “ለስነ ምግብ አንድ ዶላር ማዋል 16 ዶላር ያተርፋል” የሚል ነው። እኛም ለመንግስት አካላትና ለውሳኔ ሰጪዎች ማሳሰብ የምንፈልገው ስነ ምግብ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አገርን መገንባት ነው። በመሆኑም ስርዓተ ምግብ ላይ መንግስታት ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ አንደ አገር በስነ ምግብ ስርዓት ዙሪያ ያለንበት ደረጃ ምን ይመስላል? ችግሩንስ ለማስተካከል ምን መሰራት አለበት?
ዶክተር አረጋሽ ፦ አገራችን ጥሩ ያልሆነ አመጋገብ ስርዓት ተጠቂ ናት። ይህም ማለት በአላስፈላጊ ሁኔታ የሚበዛ የስርዓተ ምግብ ስርዓት ዝቅተኛ የምግብ ስርዓት እንዲሁም ድምጽ አልባ (ሂድን ) የስነ ምግብ ስርዓት አለባት ማለት ነው። ይህንንም ለመከላከል ሁላችንም የራሳችን አስተዋጽኦ ሊኖረን ይገባል።
እንደአገር ያለንበት ሁኔታ ከባድ ነው። ከመቶ ህጻናት 37ቱ ለሰውነታቸው የሚገባቸውን ቁመት የያዙ አይደሉም። በሌላ በኩል ደግሞ ከኪሎ በታች ያሉት 24 በመቶ ናቸው። መቀንጨር በስፋት የሚታየውም ለዚህ ነው። መቀጨጭ ደግሞ ለሰውነታቸው የሚገባቸውን ክብደት አለመያዝና ደማነስ ጎልተው በአገር ደረጃ የሚታዩ የስርዓተ ምግብ ውስንነታችን ያመጣብናል። እናም ይህንን አስቦ መንቀሳቀስ ይገባል። ሁኔታውን ለመቀየር ደግሞ ሁሉም ኃላፊነት አለበት።
በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ በስርዓተ ምግብ ችግር የተጠቁ ህጻናት ድምጽ አልባ ናቸው። በመሆኑም መገናኛ ብዙኃኑም ባለሙያውም የሚያውቀውን ሁሉ ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ ይገባዋል። ውሳኔ ሰጪዎች ደግሞ ኢንቨስትመንትን ሲታቀዱ፣ በጀት ሲመደብ ይህንን ያካተተ ማድረግ ይገባቸዋል። ከዚያም አለፍ ብለው ትኩረት የሰጠ እንዲሆን መገፋፋት አለባቸው። ምክንያቱም ትርፉ ቀላል ስላልሆነ። በጠቅላላው ጤናማ ዜጋ እንዲኖረን ከፈለግን ሁሉም የድርሻውን ይወጣ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር አረጋሽ ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015