ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ ቅርስ፣ ታሪክና አያሌ ሃብቶች የታደለች ነች። በቀደምት ኢትዮጵያውያን ስልጣኔና ኃያልነት ከተሰሩና ትንግርት ከሚመስሉ የስነ ህንፃ፣ ስነ ፅሁፍ፣ የህክምናና አስትሮኖሚ ሃብቶች ባሻገር “የ13 ወር ፀጋ” የሚል ስያሜን ያጎናፀፋት ሁሉንም መልክአ ምድሮች የአየር ንብረቶች የታደለች ውብ ነች። ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ ጥብቅ ደኖች በአጠቃላይ የአያሌ የምድር በረከቶች ባለቤት ከመሆኗም ባሻገር፣ የሰው ዘር መገኛ “ምድረ ቀደምት” አገር ስለመሆኗ ዓለም ጭምር መስክሮላታል፡፡ ጊዜ ወስዶ እነዚህን የሚዳስሱና የማይዳሰሱ ሀብቶች በመመልከት ዘና ማረጋገጥና ዘና ማለት ይቻላል።
ቱሪዝም እነዚህን መስህቦች ሁሉ ያካትታል። እነዚህን ሃብቶች በመጠበቅ፣ በማልማት እንዲሁም በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አገራት የቱሪዝም መስህቦቻቸውን ለዜጎቻቸው ስራ በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ በማድረግ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር ገፅታቸውን ለመገንባትም ይጠቀሙባቸዋል።
ዘርፉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ በርካታ አዳዲስ ነገሮች ተካተዋል። የውሃ ላይ የጀልባ ቀዘፋ (ራፍቲንግ)፣ ተራራ መውጣት (ሃይኪንግ)፣ የብስክሌት ቱሪዝም (ባይክ ቱር)፣ ስፖርት ቱሪዝም፣ የከተማ ቱሪዝም፣ የህክምና ቱሪዝም፣ ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ ወዘተ…እያልን መቀጠል እንችላለን። በዚህ መልክ ነው የቱሪዝም ዘርፍ ራሱን እያሰፋና እያሳደገ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እየሆነ የመጣው።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምዱ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚጠቀሱ ሃብቶች ውስጥ አንዱ እየሆነ የመጣውን “የዋሻ ቱሪዝም››ን ሊያስተዋውቃችሁ ወዷል። በተለይ በዚህ ዘርፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዋሻ ተመራማሪ ብዙ ይለናል። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የዋሻ ሃብት አለን ይህ ሀብት ከቱሪዝም ሃብትነቱ አንፃርስ እንዴት ይታያል?
ናስር አህመድ፣ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ስፔሎሎጂስት (በዋናነት ዋሻዎች ላይ የሚያተኩር የትምህርት አይነት ባለሙያ) ነው። ይህ ስነ ትምህርት እርሱ ተወልዶ ባደገበት ምስራቅ ሐረርጌ ከምቦልቻ ከተማ ብቻም ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያም እምብዛም አይታወቅም። ብዙ ሀብት ካላቸው ወይም ስለዚህ የጥናት መስክ ግንዛቤው ካለው ቤተሰብ የተገኘም አይደለም። የስፔሎሎጂ የትምህርት አይነት በአገሪቱ ጭርሱንም አልነበረም ማለትም ያስደፍራልና ለአገርም ብርቅ ነው።
ቤተሰቦቹ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወላጅ ልጃቸው ሐኪም እንዲሆን ይመኙ ነበር። በተለይ አባቱ የህክምና ባለሙያ ስለሆኑ ናስርም የእሳቸውን ሙያ ይይዛል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። በሙያው አይስራበት እንጂ በእርግጥም ናስር በክሊኒካል ነርሲንግ በዲፕሎማ ተመርቋል። የኢትዮጵያ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ስፕሎሎጂስት ለመሆን ያደረገው ጥረት ለቤተሰቦቹ አስገራሚ ከመሆንም አልፎ ግርታንም ፈጥሯል።
ናስር በልጅነቱ ነበር ዋሻዎችን መመልከት እንዲሁም በውስጣቸው ስላለው ውበት፣ ሃብት መማረክ የጀመረው። “ከልጅነቴ ጀምሮ አያሌ የቱሪዝም ሃብቶችን የሚያስቃኘውን ናሽናል ጂኦግራፊን ማየት ያስደስተኝ ነበር። በአንድ ወቅት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በአቅራቢያዬ ወደሚገኝ ዋሻ በትምህርት ቤታችን አማካኝነት ሄድን። ሌሎች ወደ ውስጥ ለመግባት ሲፈሩ፣ እኔ ግን ገባሁ። ከዋሻው ማዶ ብርሃን ይታየኝ ነበር። በድፍረትም ተመለከትኩት። ከጉብኝቱ በኋላ ናሽናል ጂኦግራፊን መመልከቴን ቀጠልኩ እና ከጂኦግራፊ ጋር የተያያዙ ሁሉንም ነገሮች አነበብኩ” በማለት እንዴት በዋሻ ላይ ትኩረት ወደ ማድረግ እንደገባ ያብራራል።
ናስር መሆን የሚፈልገውን ጠንቅቆ ያውቃል። እናም ህልሙን እውን ለማድረግ የሚፈልገውን ትምህርት ለመከታተል ራሱን አሳልፎ ሰጠ። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች የትኛውም የስፔሎሎጂ ትምህርት ክፍል ስለሌለው እሱን ለመሆን ያደረገውን ጉዞ ፈታኝ አረገበት። በዚህ ምክንያት ወደ ውጭ አገር ማማተር ነበረበት።
በዋሻ ጥናት ላይ የሚያተኩረው የትምህርት አይነት “ስፔሎሎጂ” እንደሆነም ደረሰበት። ካሰበው ለመድረስ የቤተሰቡ ድርሻ ቀላል አልነበረም። እናቱ እና እሱ የባንክ ብድር ለማግኘት እና የኦላይን ትምህርት ለመከታተል ቤታቸውን እንደ መያዣ ማቅረብ ነበረባቸው። ሃሳቡም ተሳክቶ አልፒኖ ኢታሊአኖ በተባለ ኢንስቲትዩት ለሶስት ዓመት ያህል በመማር በዲፕሎማ ተመረቀ።
ትምህርቱን እየተከታተለ በነበረባቸው ከ2005 ጀምሮ ባሉት ሶስት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በቅርበት በዋሻ ውስጥ ስላሉ ሃብቶችና ለቱሪዝም ዘርፉ ስለሚሰጡት ጥቅም ይሰራ ነበር። ለናስር በዋሻ ምርምር ዲፕሎማ ማግኘቱ በቂ አልነበረም። የእውቀቱን አድማስ የበለጠ ለማስፋት ፈለገ። ለሁለት ዓመታት “በዓለም አቀፍ ስፕሎሎጂካል ሶሳይቲ ዩኒየን” በፈረንሣይ አገር መማር ቻለ። ከዚያም በጀርመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት በዓለም ስፔሎሎጂካል ሶሳይቲ የተማረ ሲሆን፣ ባስመዘገበው አመርቂ ውጤትም የ36 ሺ ዩሮ ሽልማት ማግኘት ቻለ።
ይህ ጥረቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የዋሻ ሃብቶች ለማጥናትና ለቱሪዝም መስህብነት እንዲውሉ ለማድረግ እንዲሰራ መነሳሳትን ፈጠረላት። ናስር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 እና 2015 መካከል 321 የኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ ዋሻዎችን ማጥናት ችሏል። በዚህ ብቻ ሳያበቃ በጎግል ካርታዎች ላይ 200 ካርታዎችን ስለዋሻዎቹ ዝርዝር መረጃ በማስቀመጥ ዓለም አቀፍ ይሁንታን እንዲያገኙ ሰርቷል።
ለጎብኚዎች፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራማሪዎችና መሰል ባለድርሻ አካላት “ስለዋሻ ቱሪዝም” ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የተደራጀ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ 346 ገፆች ያሉት “ዋሻዎች በኦሮሚያ” በሚል ርዕስ መፅሃፍ በማሳተም ዘንድሮ ክልሉ የዓለም ቱሪዝም ቀንን በምስራቅ ሐረርጌ ባከበረበት ወቅት በይፋ አስመርቋል።
የ‹‹ናሲኦል ዋሻ›› በምስራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ ቤሎ ወረዳ በጃጃ ከተማ ይገኛል። ዋሻው እጅግ በጣም ውብና እና ትልቁ ዋሻ ነው። ስያሜውንም ያገኘው በእርሱ ስም እና የእርሱን ታላቅ ስራ በሚዘክር የኦሮምኛ ቃል ጥምረት የተሰጠው ነው፤ “ታላቁ ናስር የሚል ትርጉም አለው።
ዋሻው አነስተኛና ትላልቅ ስፋት ያላቸው 59 መግቢያዎች አሉት። በጥናቱ መሰረት የናሲኦል ዋሻ ውስጠኛ ክፍል 500 ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ከ 30 ሴንቲ ሜትር /ሁዋላ ላይ እሱ 30 ሴንቲ ሜትሩን በመቦርቦር 60 ሴንቲ ሜትር አድርሶታል/ እስከ 20 ሜትር ስፋት (ከመሬት በላይ) ከፍታ ያለው ልዩ እና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ መሆን የሚችል ዋሻ ነው።
ዋሻው ከሌሎች ዋሻዎች ይለያል፤ የውስጠኛው ክፍል ተስማሚ የአየር ንብረት አለው፤ በውስጡ ያለው የኦክስጂን ይዘት 19 ነጥብ6 በመቶ ነው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም እድሜ ላይ ያሉ ጎብኚዎች ዋሻውን በሰላም ለመጎብኘት በቂ ኦክስጅን ማግኘት ይችላሉ።
የአገር ውስጥ እና የውጭ የዋሻ አሳሾች እንደሚሉት፤ የተሟላ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት፣ የቱሪስት ማረፊያ እና መስተንግዶ የሚያገኙ ከሆነ የተለያዩ የተፈጥሮ ዋሻዎችን፣ ደኖችን እና እንደ ድኩላ እና የኒያላ የመሳሰሉ የዱር እንስሳትን በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ናስር ይናገራል። የዱር እንስሳትን እና የአእዋፍ ዝርያዎችን ለመጎብኘት ልዩ እድል የሚሰጡ በርካታ የዋሻ ሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉም ይናገራል፤ ይህም አገሪቱን ልዩ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ተመራጭ ያደርጋታል ይላል።
ናስር የስፕሎሎጂ ጥናቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም እድገት እንደሚያፋጥኑና በዋሻዎች ውስጥ ያለን የተደበቀ ሀብት ለመለየትና ዋሻዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ መንገድ እንደሚከፍቱ ያስረዳል። በኢትዮጵያ በዋሻዎች ጥቅምና ዓይነት ላይ በቂ እውቀት አለመኖሩን ይናገራል። በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢዎች ያሉ ሰው ሰራሽ ዋሻዎች ግን በሃይማኖታዊና በሌሎች ምክንያቶች አንጻራዊ ትኩረት እንደሚያገኙ ነው የሚገልፀው።
“በርካታ የቱሪዝም አቅም ያላቸው የተፈጥሮ ዋሻዎች ተረስተዋል። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ዋሻ ዋጋ በቂ ግንዛቤ የለም። ጣሊያን ውስጥ ዋሻዎችን ለቱሪስቶች በማሳየት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው” የሚለው የዋሻ ተመራማሪው ናስር፤ እዚህ ግን ለዋሻዎች ያለን አመለካከት አሉታዊ ነው ይላል። ይህም ከአጉል እምነት ጋር እንደሚያያዝም ነው የሚናገረው። ከሶፍ ኦማር ዋሻ በስተቀር ብዙዎቹ የተፈጥሮ ዋሻዎቻችን በአግባቡ ተለይተው እና ተዋውቀው ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየሰጡ እንዳልሆነም ይገልጻል።
ኢትዮጵያ ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውሉ ዋሻዎች እንዳላት ናስር ይናገራል። ዋሻዎቹ ቱሪስቶችን የሚስብ ውበት ያላቸው ከመሆናቸው ጎን ለጎን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ማዕድናትም መያዛቸውን ይጠቁማል። እነዚህ ልዩ ልዩ ጥቅም የሚያስገኙ ዋሻዎች የቱሪዝም ዋሻዎች፣ ለፊዚዮቴራፒ ህክምና የሚውሉ ዋሻዎች፣ የመድኃኒት ዋሻዎች እና የማዕድን ቁፋሮዎች ዋሻዎች በመባል እንደሚታወቁ ያብራራል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዋሻዎች የተለያዩ ማዕድናትን በውስጣቸው እንደያዙም ያስረዳል፤ ለአብነትም በኢትዮጵያ ምስራቃዊ ክፍል ኦጋዴን እና ከሐረር እስከ ባሌ ባሉት አካባቢዎች በሚገኙ ዋሻዎች የተትረፈረፈ የኖራ ድንጋይ እንዳለ በማስረጃ አስደግፎ ያቀርባል።
በናስር የተፃፈው ጥናታዊ ይዘት ያለው “ዋሻዎች በኦሮሚያ” የሚለው መጽሐፍ በኢትዮጵያ ዋሻዎች ላይ ከተደረጉ ጥናቶች መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያዊ ተመራማሪ የተጻፈ የመጀመሪያው መጽሀፍም ነው። ናስር “በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ዋሻዎች” የአገር ሀብትን እና ቀጣይ ጥናቶችን ለማስተዋወቅ መሰረት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነው።
“መጽሐፉ ስለ ስፔሎሎጂና የኢትዮጵያ ዋሻዎች ብዙ ነገሮችን ይዟል። ለቱሪስቶች፣ ተመራማሪዎች እና በዘርፉ ፍላጎት ላለው ሁሉ እንደ መመሪያ መጽሐፍ ሊያገለግል ይችላል” የሚለው ናስር፤ ጎብኚዎች በዋሻ ጉብኝት ወቅት ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ እና ሌሎች እንደ ልብስ፣ ችቦ፣ ምግብ እና ተዛማጅነት ያላቸው ነገሮችም በመፅሃፉ ተካተዋል። ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዋሻዎች እውነታዎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ማግኘት ይቻላል።
ምንም እንኳን የሱ መጽሃፍ እና ጥናት በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ዋሻዎች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ዋሻዎች በደንብ ለማወቅ ሞክሯል። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት ፈጥሯል። በአገሪቱ ውስጥ ስፔሎሎጂን ሊያሳድጉ በሚችሉ መንገዶች ላይም ተወያይቷል። ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም የስፔሌሎጂ ትምህርት ክፍል ለመክፈት ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል።
“ወደፊት ማየት የምፈልገው ኢትዮጵያ እንደእኔ ብዙ ስፔሎሎጂስቶች እንዲኖራት ነው። ዋሻዎቻችንን በብዛት የሚያጠኑት የውጭ ዜጎች ናቸው” የሚለው የዋሻ ተመራማሪው፤ በዚህ በኩል የራሳችን ባለሙያዎች ካሉን በርካታ ጥቅም ማግኘት እንችላለን የሚል እምነት አለው። በዚህ የትምህርት ዘርፍ በማስተማር እና ግብዓቶችን በማቅረብ በአገሪቱ እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚፈልግም አስታውቋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም