ሰላም ሰዎች እንዴት ነን? መግቢያ ሳላበዛ ቀጥታ የሆነውን ልንገራችሁ! እንዲህ ነው፤ ለምን እንደሚወዷት አላውቅም? ይሯሯጡላታል፣ ይ ጣ ሉ ላ ታ ል ፣ ይ ጨ ቃ ጨ ቁ ላ ታ ል ፣ ይቧቀሱላታል። «በውበቷ አማላይ፣ በመልኳ ሺህ ገዳይ» የሚሏት ዓይነት ስለሆነች ይሆናል ብዬ አተኩሬ አይቻት አውቃለሁ፤ ቅናት እንዳይመስልብኝ እንጂ ብዙ የምታምር አይደለችም። ቆይ! ልብወለድ መስሏችሁ እንዳይሆን? ታሪክ ነው የምነግራችሁ፤ በመሃል አገር ሸገር አዲስ አበባ የተፈጠረ ታሪክ።
እና ይህቺን ልጅ እኔም የማውቃት በርቀት ነው። አንዳንድ ጸባይዋን በድፍረት ለመናገር ያስቻለኝ ከሰው ሰምቼ ወይም ሰው አምቶልኝም አይደለም፤ ያው ሁሌም ስለማያት ነው። መግቢያ መውጪያዬ በእርሷው ቤት በኩል ስለሆነም ነው። ባልወድም በግዴ አያታለሁ።
እናላችሁ ከማውቀው ስጀምር፤ የኔን ወንድም ጨምሮ ሁለት ወንዶች ተጣልተውባታል። እንደ አቤልና ቃየን፤ «የእኔ ነው መሆን ያለባት!» ብለው መጋደል ነው የቀራቸው እንጂ ያልተባባሉባት የለም። እርሷ ግን ግድ ያላት አትመስልም፤ እንደው ጊዜ ማሳለፊያዋ እንጂ የማናቸውም መሆኗን ተናግራ አታውቅም። እንደውም በእርሷ ስም አንድ ግጥም ጽፌ ነበር፤ ድሮ ማለት ነው። ግጥሜን ሰብሰብ አድርጌ በአራት ተኩል ስንኝ ሳቀርበው እንዲህ ይላል፤
«…አይ ልጅት መልከኛ ሲጣሉ ታያለች
በምኗ እንደሆነ እርሷ የት ታውቃለች?
እነርሱም አልተዉ!
የእኔ ነች የእኔ ነች ብለው ተጣሉባት
ባይገባቸው እንጂ እርሷስ የራሷ ናት…»
ደስ ይላል! በብዙዎች መወደድ ጥሩ ነው። እርሷም ለአንዳቸውም «የአንተ ነኝ» ሳትል ለሁሉም እኩል ፈገግታን ትሰጣለች። ስትቀልድላቸው፣ ስትስቅላቸው እኩል ነው፤ ስትስቅባቸው እንኳ አዳልታ አታውቅም። ለእርሷ ቅድሚያ ራሷ ናት እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። የመጣውን ተቀብላ ታስተናግዳለች፤ የሄደውን ደህና ሁን ብላ ትሸኛለች።
እንደው ግን ወንድሜን ጨምሮ እነዚህ ወዳጆቿ ለአንድ ቀን ፉንጋነቴን ታግሰው ጆሮ ሊሰጡኝ ቢፈቅዱ የምነግራቸው ነበረኝ። በመጀመሪያ ደረጃ እንዴት ብር እንደማይበቃት እያወቁ «የእኔ ነች!» ይላሉ? አሃ! ሰው ለምን ሲል ለወጪ እንዲህ ይራኮታል? «እኔ ወጪ ስለማላስወጣ እኔን ይፈልጉኝ» ማለቴ አይደለም፤ ግን በቃ! ብር አይበቃትማ።
ይሄ ፊልሞቻቸን ላይ እንደሚታዩት አይነት የገንዘብ ፍቅር አናውዟቸው እንደተገለጹ ገጸባህርያት አይደለም። እነርሱ በሚመለከት ይህቺን ተወዳጅ ሴት ባካተተ መልኩ «አይወክሉን!» ብለን ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት እስኪቀረን ድረስ አይወክሉንም ብለናል። ግን በቃ ኑሮ ነገር ናት! እንዲሰጣት የምትፈልገው ነገር ሁሉ ለእርሷ መሰረታዊ ነው፤ ነገሩ ቅንጦት ባይሆንም ከባድ ነው።
ለምሳሌ የኔ ወንድም አብሯት አንድ አካባቢ ስለሚገኝ እንጂ ሌሎቹ ለትራንስፖርት ብለው ብዙ ያወጡላታል። መኪና ሁላ ሳያስፈልጋት አይቀርም። በቃ! ለእርሷ ይሄ መሠረታዊ ፍላጎት እንጂ ቅንጦት አይደለም። «ታክሲ ጥበቃ መሰለፍ ስጠላ!» ካለች አለች ነው፤ በፍጥነት የሆነ እርምጃ መወሰድ አለበት። አለበዚያ ከእርሷ ጋር መኖር አይታሰብማ! የጠየቀችውን ሳያደርጉ «ይኔ ነሽ!» ብሎ ነገር የለማ!
አንድ የሰፈር ሰው መቼ እለት ጸበል ጸዲቅ ቅመሱ ብሎ ቤቱ ጠርቶን እርሷም በዛው መጥታ አግኝቻት ነበር። «እንዴ! ፀሐዩ ፀሐይ ነው እንዴ? በዚህ ፀሐይ መሰለፍ ራሱ አስቸጋሪ ነው። ታክሲ ውስጥ ተቀምጦ መቀቀል ደግሞ ደስ አይልም። ባስ ውስጥማ ብገባ በማግስቱ የምታመም ሁላ ይመስለኛል! መኪና ሲኖር ግን በአቋራጭ መንገድም ቢሆን በጊዜ መግባት ይቻላል። መኪና’ኮ መሠረታዊ ነገር ሆኗል…» አለች።
ደመወዙን በተቀበለ በአስራ አምስት ቀኑ «እስቲ ለደሞዝ የምመልሰው ብር አበድሪኝ» የሚለኝ ወንድሜ አፉን ሞልቶ፤ «ልክ ነሽ! አልተሳሳትሽም» ብሎ ፈገግ ይልላታል። ይህን እያወቀ ነው እንግዲህ ከሌሎቹ ቀድሞ የራሱ ሊያደርጋት የሚታገለው። በእርግጥ «ውድ» ከመሆኗ ውጪ እንዲሁም ከማይዋጥልኝ ተወዳጅ ያደረጋት መልኳ ባለፈ፤ ከሁሉ ተግባቢና ተጫዋች እንዲሁም ግልጽና አራዳ መሆኗን እኔም አደንቅላታለሁ።
ምን ያለ ፍቅር ነው ግን? እንዴት ቢወዷት ነው «የእኔ ናት!» እያሉ የሚጣሉባት? በቃ! ሲነጋም ሲመሽም የማስበው ይህንን ነው። ነው ወይስ እየተፎካከሩ ነው? መቼም ብዙዎች ተንጋግተው የሚሄዱበት መንገድ ስለሚመቸን፤ «አንዱ የእኔ ናት ያለው አንዳች ነገር ቢያገኝባት ወይም ቢያይባት ነው» ብለው ካልሆነ ጸባይዋንና ችግራቸውን አስተያይተው እርግፍ አድርገው ትውት ሊያደርጓት አይገባም ነበር? ፍቅር ሲበዛ’ኮ አስቸጋሪ ነው።
ታድያ ይህን ታሪክ እንድነግራችሁ ያስገደደኝ በወንድሜና በሌላው እርሷን «የእኔ ናት» ባይ መካከል መስማማት አልመጣ በማለቱ ነው። ከዛም አልፎ ቤታችን ድረስ መጥቶ አባቴ ከአያቱ ያየው ፉከራና ሽለላ ትዝ ብሎት ሰሞኑን ቤቱን በቀረርቶና በፉከራ ግጥም ሞልቶታል። የሌላውም አባት በተመሳሳይ መልኩ ቀን ይጠብቃል፤ ቢችል መሃል ከተማ ላይ ጠልፎ ሊያስወስዳት ሁሉ ይከጅላል።
ቢቸግረኝ አስታራቂ ልሆን ተነሳሁ። የወንድሜን አባት ወይም አባቴንም ሆነ የሰፈራችንን ልጅ አባት፤ አልያም ሌሎች «የልጄ ናት!» የሚሉት አባቶች ጋር አልሄድኩም። በቃ! ራሷ ጋር ሄድኩኝ። «የማን ነሽ?» አልኳት፤ ፈገግ ብዬ። ነገሬ ግን በቁጣ ቢሆን ሊያደባድበን ሁላ ይችል ነበር።
«የማን ነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው…» አለች በዛወርቅ!፤ አሁን ትዝታን ራሱን ቀስቅሳ የምትጠራው የምትመስለዋን ድምጻዊት በዛወርቅን ሙዚቃ ብታነጎራጉርልኝ ምን ልል ነው? ደግነቱ እርሷም ነገሩ ገብቷት ፈገግ ብላ ተቀበለችኝ። «ውይ! ምንድን ነው መረጋጋት ያነሳችሁ? ሁሉም የማን ነሽ ይለኛል? ምን አይታችሁብኝ ነው?» አለች።
አሁን እንደው እኔን ለማናደድ እንጂ ሳታውቅ ቀርታ ነው? ወንድሞቻችን ሁሉ ጨርቃቸውን መጣል ቀርቷቸው፤ ከምትሰጠው ይልቅ የምትቀበለው ብዙ እንደሆነ እያወቁ እንኳ «የእኔ ናት» እያሉ በመጣላት አባቶቻቸውን በእርጅና ዘመን በከዘራ እያደባደቡ መሆኑ ጠፍቷት ነው? ልታስቀናኝና ልታናድደኝ እንጂ! ተበሳጨሁ። ግን አስታራቂ ልሆን መሄዴ ትዝ ሲለኝ ንዴቴን ዋጥኩት። ለመናደድ እልፍ ምክንያት አለ አይደለ እንዴ? ምን አስቸኮለኝ?
«አየሽ ለአንዳቸው ቁርጣቸውን ንገሪያቸው። ማለቴ ሁሉም ስለሚወዱሽ ይሁን ወይም እርስ በእርስ ካለመዋደዳቸው የተነሳ አንቺን ዋንጫ አድርገው እየተጣሉብሽ…እኔ የማውቀው ነገር የለም። ግን በየቤታችን ሰላም እየነሱን ስለሆነ…ቁርጡን ነግረሽ አረጋጊያቸውና እኛም እንረፍበት» አልኳት። ከፊቷ ላይ ፈገግታዋ ሳይጠፋ አየችኝ፤
«እኔ ምን ላድርጋቸው? ያውቁኛል! እንዲርቁኝ ብዬ የኑሮ ደረጃዬን ከፍ ባደርግም፤ ዝብርዝቅርቅ ብዬ ሳልኳኳል ብታይም፣ በሰፈሩ ያሉ እናቶች ባህልና ሥርዓት የማታከብር ምን ዓይነት ሴት ናት እያሉ ከፍ ዝቅ ሲያደርጉኝ ቢሰሙም… በእኔ ከመጣላት የሚያገዳቸው ነገር የለም። እኔ እንደሆነ ከእናቴ ቤት አልወጣ… ቢቻለኝ እርሷን እያገለገልኩና እያገዝኩ ብኖር ነው የምመርጠው። ሲደክማቸው ይተውኛል ተያቸው…ቀስ እያለ ይገባቸዋል።» አለችኝ።
የቀደመውን ግጥሜን መዝጊያ «… አልተረዱም እንጂ እርሷስ የእናቷ ናት…» ልበለው ማለት ነው? «እና የማናቸውም የመሆን ወይም ማናቸውንም የማግባት ሃሳብ የለሽም?» አልኳት፤ የባሰ አታምጣ! «ኧረ በጭራሽ! ለጊዜው ደስ ካሰኘኋቸውና እኔንም በሚገባ የሚጠቅሙኝ እስከሆነ ድረስ ከሁሉም ጋር ነኝ። የሁሉም ነኝ በይው! እንጂ የማንም አይደለሁም። የሚሰሙሽ ከሆነ እንደውም የእናቷ ናት በያቸው።» አለችኝ።
በዛው ቅጽበት ስልኳ አንዳች ሙዚቃ በማሰማቱ ዝም ልታሰኘውና ደዋዩን ልታናግር ተነስታ ሄደች። መቼም ለእኔ የነገረችኝን ነገር ለወንድሜና መሳዮቹም ነግራቸው ይሆናል’ኮ! ግን ምንድን ነው የጋረዳቸው? አጠገባቸው ከእርሷ የተሻለ የለምን? ነው ወይስ እውነትም ፍቅር ይሆን? ብቻ ግራ ገብቶኛል። ዛሬ ለወንድሜ ያለችኝን ሁሉ ደግሜ ልነግረውና ላስረዳው ቤት ተመለስኩ።
እርቅ ለመፍጠር መሄዴን ረስቼ «የዚህች ልጅ ጓደኛዋ ብሆን ያዋጣኛል ማለት ይሆን?» እያልኩ ሳስብ ነበር። የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን አገኛለሁ፤ ቢያንስ እርሷን ብለው ከሚመጡት መካከል አንዱን ወዳጅ አደርግ ይሆናል። ወይም ለትዝብት የሚሆን ብዙ መረጃ አግኝቼ ልብወለድ ነገር እጽፍ ወይም ፊልም እሠራ ይሆናል። «ልጅቷ የማን ናት?» በሚል ርዕስ። ወይ ጉድ! የት ሄድኩ…አሁን ቆይ ለወንድሜ ታድያ በምን ቋንቋ ነው የማስረዳው? ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በሊድያ ተስፋዬ