በኪነህንፃ ውበታቸውና ሰማይ ጠቀስ ሆነው በመገንባታቸው አድናቆት የሚቸራቸው፣የአንዳንድ አገራት ህንፃዎች የጥበበኛው እጅ ውጤቶች መሆናቸው ቢታወቅም፤ ለግንባታ የዋለው ግብአትም ለውበታቸው ወሳኝ እንደሆነ በምክንያትነት ይጠቀሳል። የህንፃው ምሶሶ፣ጣሪያና ግድግዳው፣ ማጠናቀቂያው በአጠቃላይ ጥቅም ላይ የሚውለው አብዛኛው የግንባታ ግብአት ከምድር ውስጥ የተገኘ የማዕድን ሀብት ውጤት ነው።
እንደ ሴራሚክ፣ ለደረጃ፣ ለወለልና ለመሳሰሉት የሚውለው እብነ በረድና ሌሎችም የህንፃው ማጠናቀቂያ ግብአቶች የተለያየ ህብረቀለም ያላቸው በመሆኑ የህንፃውን ውበት ከፍ ያደርጉታል። ለተፈጥሮ ሀብት ያለው አድናቆት እንዲጨምርም ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ በተለይም በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ከተሞች በጭቃ እና በእንጨት የሚከናወኑ ግንባታዎች በዘመናዊ የግንባታ ግብአቶች መተካት ከጀመሩ ወዲህ የምድር ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት የሆነው ማዕድን ጥቅምና አስፈላጊነቱ እየጎላ መጥቷል።
ለማጓጓዣ ዘርፉ ጥቅም እየሰጠ ያለውና ለአንድ አገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተደርጎ የሚወሰደው ነዳጅም እንዲሁ የምድር ውስጥ ፀጋ ነው። የተፈጥሮ የነዳጅ ሀብታቸውን በመጠቀም የበለፀጉ አገራት በርካታ ናቸው። በዋጋ መናር የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም በእጅጉ እየተፈታተነ ያለውን ከውጭ የሚመጣውን ነዳጅ ማስቀረት የሚቻለው አገር ውስጥ አለ የሚባለውን የምድር ውስጥ ሀብት/ ነዳጅ/ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ብቻ ነው።
የማዕድን ዘርፉ ለጌጣጌጥና መዋቢያዎች ጭምር የሚውል ሀብት በመሆኑ አገልግሎቱና የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፍ ብዙ ነው። በብዙ ድካም በቁፋሮ ከምድር ውስጥ ወጥቶ እሴት ተጨምሮበት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የምድር ውስጥ ሀብት የሆነው ማዕድን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ እያለ በመምጣቱ የመንግሥታትም የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል።
ነዳጅ፣ ወርቅና ለጌጣጌጥ እንዲሁም ለኢንዱስትሪና ለግንባታው ዘርፎች ግብአት የሚሆኑ እምቅ የማዕድን ሀብቶች በስፋት እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያም በዘርፉ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ በተለይም አገራዊ ለውጥ ከተደረገ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ተጠናክሯል። በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው (ሪፎርም) በአገር ኢኮኖሚ ላይ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ናቸው ተብለው ከተመረጡ አምስት የትኩረት አቅጣጫ ዘርፎች አንዱ ማዕድን ተደርጓል።
በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ውጤት ለማስመዝገብም ኢንቨስትመንትን መሳብ ይጠበቃል። ለእዚህ ደግሞ በመጠንና በአይነት በየትኛው የአገሪቱ አካባቢ ሀብቱ እንደሚገኝ በጥናት ታግዞ በተደራጀ ሁኔታ ሀብትን በመለየት ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ በዩኒቨርሲቲዎችና ዘርፉን በሚመራው ተቋም የጥናትና ምርምር ሥራዎች መሰራታቸው ይታወሳል። ሆኖም ግን አጥጋቢ እንዳልሆነና ሥራዎች እንደሚቀሩ ይነገራል።
በጥናት የተለየውንም ሀብት በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተደረገው ጥረት አነስተኛ እንደሆነም ይተቻል። በሌላ በኩልም ሀብቱ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ያለው የተቋም አደረጃጀትና በባለሙያዎች የታገዘ ሥራ በመሥራት ረገድም ክፍተት መኖሩ ይነሳል።የተጠናከረ አደረጃጀት ሲኖር በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል። ለማእድን የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የአደረጃጀት ለውጦች ቢደረጉም፣ አሁንም ዘርፉን የሚመራው የቢሮ አደረጃጀት ትኩረት እየሰጠ ያለው ሀብቱ በሚገኝበት አካባቢ ላይ አለመሆኑ እየተጠቆመ ይገኛል። ዘርፉ ከሌላ የሥራ ክፍል ጋር እንዲመራ መደረጉና በአንዳንድ የማዕድን መገኛ አካባቢዎች በጽህፈት ቤት ደረጃ የተደራጀ መሆኑ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ በማሳያነት ይጠቀሳል። እንዲህ ያለውን አሰራርም መፈተሽ ይገባል የሚል ሀሳብ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጣል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለይቶ ለለውጥ መነሳሳት እየተፈጠረ ባለበት በዚህ ወቅት በአካባቢያቸው ያለውን የማዕድን ሀብት በአይነትና በመጠን ለይቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙት ክልሎች መካከል የአማራ ክልል ይጠቀሳል። ክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ከሚገኝባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከልም አንዱ መሆኑ ይነገራል። በዋጋ ውድ የሆነና በዓለም ገበያ ተፈላጊ ከሆኑት የጌጣጌጥ ማዕድናት መካከል ኦፓል ማዕድን በክልሉ ወሎ አካባቢ በስፋት እንደሚገኝ፣ በአጠቃላይ የዓባይ ሸለቆን እና በሰሜን ሸዋ ዞን የጀማ ተፋሰስን ተከትሎ ባሉ አካባቢዎች ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ዘርፎች ግብአት የሚውሉ ከፍተኛ ክምችት ያላቸው የማዕድን ሀብቶች መኖራቸውን የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ መረጃውን ካሰራጨው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ቢኖርም ከዕውቀት እና ክህሎት እጥረት እንዲሁም ከትኩረት ማነስ ጋር በተያያዘ ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አለማግኘቱም በመረጃው ተጠቅሷል። በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያሠራ የሚችል ግልጽና አስተማማኝ ፖሊሲ እና ስትራቴጅ ተቀርፆ አለመተግበሩም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ተመልክቷል።
ክልሉ ቀድሞ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላትና ያለውንም ሀብት በጥናት ለይቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ በዚህ ወቅት እንደ አገር ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረትና በዘርፉ የተደረገውን የፖሊሲ ማሻሻያ መሠረት በማድረግ በለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። በተለይም በክልሉ የሚገኘውን ሀብት በአይነትና በመጠን ለይቶ በተደራጀ ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የክልሉ ማዕድንና ሀብት ልማት ኤጀንሲ በራሱ አቅም ካካሄዳቸው የጥናት ሥራዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ሰርቬይንግ ጨምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት ባካሄዱት ጥናት በአምስት ዘርፎች የተከፈሉ 40 ያህል የማዕድን አይነቶችን ለይቶ ዝግጁ ማድረጉንና በጥናት ለይቶ ያደራጃቸውን የማዕድን አይነቶች በቅርቡ በክልሉ ባካሄደው የማስተዋወቂያ መርሃግብር ላይ ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያደረገው ጥረት ይታወሳል።
ኤጀንሲው በዘርፉ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያግዙት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ሰሞኑን ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። ዩኒቨርሲቲዎቹም በስምምነቱ መሰረት ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
በመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ እንዳስረዱት፤ በማዕድን ዙሪያ በተዘጋጀ መድረክ ከትምህርት ተቋማቱ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው የጥናትና ምርምር የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው።የማዕድን ሀብት ልየታና ግመታ መሠረት ባደረገ ነው የጥናት ሥራው የሚከናወነው።
በክልሉ በማእድን ሀብቱ ላይ የጥናት ሥራዎችን ማከናወን አዲስ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ከዚህ ቀደም በሥነምድር ወይም ካርታ (ማፕ) ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል። የዚህ ጥናት ወሰኑ (ካሬ ሜትር) አነስተኛ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የዚህኛውን የጥናት ሥራ ለየት የሚያደርገው፤ ጥናቱ በቅርብ ርቀት በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ያደረገና ጥናቱ የሚሸፍነውም የካሬ ሜትሩ ስፋት ከፍ ይላል። በዚሁ መሠረትም 6ሺ742ካሬ ኪሎ ሜትር አካበቢ ነው የሚሸፍነው። ጥናቱ በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን መጠንና ክምችትን ያካተተ መሆኑም የተለየ ያደርገዋል።
ኃላፊው እንዳሉት፤ ጥናቱን የሚያካሂዱት ዩኒቨርሲቲዎች ጂኦ ኬሚስትሪና ጂኦ ፊዚክስ የሚባለውን በመለየት በቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ) የተረጋገጠ ሥራ እንዲያቀርቡ ይጠበቃል። ስምምነቱ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባት ግንቦት ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የጥናት ሥራው መጠናቀቅ ይኖርበታል።
በክልሉ በሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሰሜሸዋ አንኮበር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ አምባሰል ወረዳ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መተማ ቋራ፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች እንዲሁም ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በዙሪያው ትኩረት በማድረግ ጥናቱን ያካሂዳሉ።
የጥናት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰው፣ ሰሞኑን ጎንደር ላይ ለተመሳሳይ ሥራ ከአስር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ለማድረግ እቅድ መያዙን አቶ ኃይሌ ገልጸዋል።
የጥናት ሥራው ዋና ተልእኮ በቤተሙከራ የተረጋገጠ የጥናት ሥራ በማከናወን በክልሉ ያለውን የማእድን ሀብት በመጠን እንዲሁም ሀብቱ የሚገኝባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል። ከሀብት ልየታው በኋላ ወደ ልማቱ ሥራ ለመግባት ስላለው ቁርጠኝነት አቶ ኃይሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከዚህ ቀደም በጥናት የተለዩትን ወደ ሥራ በማስገባት የተሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አሁንም ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በገባው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሠረት ጥናቱን በወቅቱ አጠናቅቆ ለማስረከብ ሥራ መጀመሩን በጥናቱ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰርና የጥናት ቡድኑ ኃላፊ ዶክተር ዳዊት ለበኔ ገልጸውልናል። እንደ ዶክተር ዳዊት ገለጻ፤ የጥናቱን ሥራ የሚያከናውኑትን አምስቱን ዩኒቨርሲቲዎች ጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው የሚመሩት።
ዩኒቨርሲቲዎቹም ለጥናት ሥራው ግማሽ የሚሆን በጀት በማዋጣት ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው የተደረገው። የጥናት ሥራውንም የሚያከናውኑት በቅርብ አካባቢ ነው። ስምምነቱ የማዕድን አይነቱን ለመለየትና መጠኑንም ለማወቅ በመሆኑ ለዚህም ዝግጅት ተደርጓል። በጥናት ሥራው ማዕድኖቹ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በቀላሉ ለማወቅ እንዲቻል የሥነምድር ካርታ (ማፕ) ሥራ ይቀድማል። ማዕድኑ መኖሩ ከተረጋገጠ የማዕድኑ የአለት ናሙና በቤተሙከራ ይመረመራል። የጥናት ሥራው የሚጠናቀቀው ይህን ሁሉ ሂደት አልፎ ነው።
የጥናት ሥራውን በዘመናዊ ቤተሙከራ የታገዘ ለማድረግ አቅም ስለመኖሩ ዶክተር ዳዊት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የአቅም ጉዳይ አንዱ ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል። የስምምነት ሰነዱ ከመፈረሙ በፊትም በውይይት ላይ የተነሳ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ባለው ሁኔታ የተሻለ ተሞክሮ ያለው አገር ተመርጦ የአለት ናሙናውን በመላክ የመመርመሩን ሥራ ለማከናወን መታሰቡን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የማዕድን አይነቱንና ክምችቱን ማረጋገጥ የሚቻለው በቤተሙከራ በመሆኑ ማስመርመሩ ወሳኝ ነው። እንዲህ ባለ መንገድ ነው ከትንሽ ወደ ትልቅ ሥነምህዳር ካርታ ማሳደግና ሥራውንም አገራዊ ማድረግ የሚቻለው። አሁን ዘመኑ የሚጠይቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ከጊዜው ጋር መሄድ ግድ ይላል።
ቤተሙከራውን በአገሪቱ ለማቋቋም አቅም ይጠይቃል። በሂደት ግን ማቋቋሙ የግድ ይሆናል፤ ሀሳቡም አለ ሲሉ ጠቁመዋል።
የጥናት ሥራው ውጭ አገር ድረስ በመላክ የሚከናወን በመሆኑ ከፍተኛ በጀት ይጠይቃል። ከዚህ አኳያ ስለተደረገው ዝግጅትም ዶክተር ዳዊት እንዳብራሩት፤ ሥራው ከፌዴራል ወደ ክልል የወረደ መሆኑንና ጠንክሮ መሥራትን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ከዚሁ አኳያ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ነው የማውቀው ሲሉ ገልጸዋል።
በጥናት የተገኘውን ውጤት ወደተግባር መቀየር ሲቻል ነው የማዕድን ዘርፉ በኢኮኖሚ ላይ ያለውን አበርክቶ ማረጋገጥ የሚቻለው። ተደጋግሞ እንደሚባለው የጥናት ሥራዎች ወደተግባር አይለወጡም። እንዲህ ያለው ክፍተት አሁን በተጀመረው የጥናት ሥራ ላይም በተመሳሳይ እንዳያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበትም ዶክተር ዳዊት ምክረሀሳብ ጠይቀናቸው ‹‹ትክክል ነው፤ ለአብነት ከዚህ ቀደም ቋራ ላይ በሥነምድር ካርታ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆን ብረት ማግኝቱን ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለግንባታና ለኢንዱስትሪው ግብአት የሚሆኑ ማዕድናትን በምርምር ለይቶ ለሚመለከተው አካል የጥናት ውጤቱን ሰጥቷል። ይህ ሁሉ ግን ወደተግባር መቀየሩን አላወቅንም።ተመራማሪው ከማሳየት በላይ መሄድ አይችልም ሲሉ አብራርተዋል።
ዘርፉን የሚመራው አካል ግን ተከታትሎ ለሥራ እንዲውል ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስታውቀው፣ የውጭ ኢንቨስተርን ከመሳብ ጎን ለጎን ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። ዘርፉን የሚመሩት በየጊዜው መቀያየር የጥናት ሥራዎች ወደተግባር እንዳይቀየሩ አንዱ እንቅፋት እንደሆነም ነው ያመለከቱት።
የክልሉ ማእድን ልማት ኤጄንሲ በማእድን ሀብት ላይ ጥናት በማድረግ ለባለሀብቶችና ለሌሎች አልሚዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያከናወነ ያለው ጥረት አርአያነት ያለው ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ሌሎች ክልሎችም ከዚህ መማር ይጠበቅባቸዋል። ክልሉ በጥናቱ ይህን ያህል ርቀት እንደ ሆነ ሁሉ ጥናቱ መሬት ላይ ወርዶ ክልሉንም አገሪቱንም ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መስራት ይኖርበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም