
ስገምት ማን ማንን ነው የሚበልጠው? እንደው ልጄን አባትህን እኮ ትበልጠዋለህ ብላ ልታሳምፅብኝ ይሆን እያልክም እያሰብክ ይሆናል። ደግሞ የእኔ ልጅ በምኑ ነው እኔን የሚበልጠው? የቀረበለትን ምግብ እንኳን አስተካክሎ አይጎርስም እኔው ነኝ ሸምቶ ከማምጣት እስከ ጠቅልሎ ማጉረስ ሚናውን የምጫወተው ትልም ይሆናል።
ከእኔ ውጭ መሰረታዊ ፍላጐት እንኳን የለውም። ያለማንም ከልካይ እኮ የቃል ስልጣኔን አስፈፅምበታለሁ። ውጣ ብዬ አስወጣዋለሁ ግባ ብዬ አስገባዋለሁ ፈጣሪን ካልፈራሁ ደግሞ እንደ እንዝርት ላሾረው እችላለሁ። አእምሮህም እንደው በምን ይሆን የሚበልጠኝ ብሎ በእድሜ ይሆን ኧረ አይሆንም እሱ እኮ ልጄ ነው።
በገንዘብ? ምን እያልኩ ነው የገንዘብ ስር አልባነት እና እንዴት ተሁኖ እንደሚመጣ እንኳን መረዳት ተስኖት ስወጣና ስገባ አባቴ ያንን ግዛ ይሄንን አምጣ ያንን አውጣ እያለ እያሰቃየኝ ነው።
በትምህርት ይሆን እንዴ? አይ አይ እሱም አይሆንም የኔ ልጅ እኮ ገና መዋዕለ ህፃናት ተማሪ ነው እኔ ደግሞ በ 1983 ነው 12ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቅኩት።
መቼም የፈለገ ጊዜ ቢራቀቅ ዘመኑም ቢዘምንም ምንም እንኳን እኔም ትምህርቱን ካቆምኩ ሶስት አስርት አመታት ቢያልፍም እንደው ምንም ቢሆን የዛሬው የመዋዕለ ህፃናት ተማሪው ልጄ አይበልጠኝም…” አልኸኝ አይደል ? እኔ ግን እልሀለሁ ካንተ ማነፃፀሪያዎች በተለየ ማወዳደሪያ ልጅህ ይበልጥሀል። አይበልጠኝም ካልክ እናሲዝ ብዬ ትንሿን ጣቴን አውጥቻለሁ። እነሆ ወዳጄ ልጅህ በምን እና እንዴት ካንተ እንደሚበልጥ እንዲህ እያልኩ አስረዳሀለሁ።
በመጀመሪያ ልጅህ ካንተ በተሻለ ትሁት ነው። በትላንትናው ድሉ አይኩራራም የዛሬንም ውድቀቱን እያብሰለሰለ ነገውን በጭጋግ ውስጥ አያይም። የትኛውንም ነገር ይሞክራል ካቃተው አንተ አባቱ ከሱ እንደምትሻል በማሰብ ርዳታህን እንድትቸረው ቀኝ እጁን ይዘረጋልሀል። “ምን ይለኝ ይሆን ? ባለመቻሌ ይታዘበኝ ይሆን?” አይልም እንደማይችል ከገባው ያንተን እርዳታ ይጠይቃል።
ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያለ ልጅ ለመቆም ሲንገዳገድ ታየዋለህ ካቃተው ተንፏቆ በመሄድ ያገኘውን ነገር ተደግፎ ይቆማል። መቆሙን ካረጋገጠ በኋላ ያንኑ የተደገፈውን ነገር ሳይለቅ ለመሄድ ይሞክራል። ይሄ ከተሳካለት ሁሌ ተደግፌ ካልሄድኩ አይልም ያለ ማንም እርዳታና ድጋፍ ራሱን ችሎ መቆምን ይፈልጋል። ምናልባት ግን ወገቡና አጥንቶቹ ስላልጠነከሩ ይወድቅ ይሆናል።
በሚገርም ሁኔታ ግን ዛሬ ወድቄአለሁ ብሎ ነገ አልነሳም፣ አልቆምም፣ አልሄድም አይልም። ነገም ይሞክራል። ነገ ሲሞክር ግን ከዛሬ በተሻለ መቆምን ይማራል። ይኸው ያንተው ልጅ በራሱ መቆምን ከተማረ በኋላ ያንን ብቻ እንደ ስኬት አይቆጥረውም፤ ካልሄድኩ ካልሮጥኩ ይልሃል።
እጁን ይዘኸው ራሱ መሄድ አይፈልግም አምልጦክ ሊሮጥ ይከጅለዋል። መቆሙ ብቻ አያረካውም ያንተ ወፌ ቆመች እያሉ ማጨብጨብም አኩራርቶት በቃ መቆሜ በቂ ነው ይኸው ተጨብጭቦልኛል አይልም። ያንተን ማሞካሸት ብቻ በማየት ከነገው ርምጃው እና ሩጫው መቅረት አይፈልግም አድናቆትህ አያስኮፍሰውም መሄድ እና መሮጥ ለሚባሉ ነገሮች መነሻ እንጂ መድረሻ እንዳልሆነ ደመነፍሱ ይነግረዋል።
ያንተን ልገምት አለቃህ እንድትሰራ የሚሰጥህን ስራ ላንተ ደሞዝ መከፈል ምክንያት የሆነን ስራህን እንኳን ልትሰራ ፈቃደኛ አይደለህም። አንድ ቦታ ላይ ቆመሃል። ተደግፎም ለመሄድ አትፈልግም በራስክ መቆም ካቃተህ ተደግፎ መሄድ እንደሚሻል አታስብም። ክብርህን የምታስነካ ይመስልሃል፤ ራስህንም ችለህ አትሄድም መቆምህ ብቻ አኩርቶሃል።
የስራ ወንበር መያዝህ በራሱ ስኬት መሆኑ ይታይሃል። አንተ ቆመሃል ዘመኑ ዘምኗል ጊዜውም ነጉዷል። ሁሉም ይሮጣል አንተ ግን ቆመሀል። መሄድና መሮጥ እንዳለብህ እንደ ልጅህ ደመነፍስህ ብቻ ሳይሆን ዓይነ ህሊናህም እንዳይነግርህ ስኬት ማለት ስራ መያዝ እና እንዳይባረሩ በስራ ስዓት መግባት መውጣት መሆኑን ለአመታት አስጠንተህው እሱም አብሮህ ቆሟል።
ልጅህ የሚማር አዕምሮና የሚምር ይቅርታ የሚያደርግ ልብ አለው። በሚማረው አዕምሮው አንተን ይጠይቃል። ጥሩ ወላጅ ከሆንክ አሁንም ትመልሳለህ። የሚያስገርመው ነገር ግን አንተ መልስ ያልቅብሃል እንጂ የእርሱን ጥያቄ ስትመልስ ብትውል አያልቅም።
አንድ የማውቀውን ነገር ሳጫውትህ አንተም እንደሱ ነበርክ። ቤተሰቦችህ ላይ የጥያቄን ጎርፍ ያለምንም ርህራሄ የምታፈስ። ግን ምን ያደርጋል በወላጆችህ የመልስ አልበኝነት ወይም ስልቹነት ይህንን ዋነኛ የአዕምሮ ማጎልበቻ የሆነውን የመጠየቅ ባህልህን ወስደው ጠይቆ መረዳትን እንደ የበታችነት ስሜት እንድትቆጥረው ያደረጉክ።
አንድ ወዳጄ እንደውም ምን ይላል “አላውቀውም አስረዱኝ ስትሉ አንዴ ብቻ ነው እንደ አላዋቂ የምትቆጠሩት ከዛ ቀን በኋላ ግን ካለማወቅ አረንቋ ትላቀቃላችሁ። ሰው ምን ይለኛል ብላችሁ ባትጠይቁ ግን ለዘላለም ላለማወቅ ጨክናችኋል” ይላል።
ቤተሰቦችህ ስትጠይቃቸው አንተ ልጅ ነህ። አሁን ከትልቅ ሰው ጋር እያወራሁ ነው። አትጨቅጭቀኝ ስራ ይዣለሁ። ውጣና ተጫወት። እሱን ስታድግ ትደርስበታለህ በሚሉ አዕምሮን በሚያቀጭጩ መልሶች ነው ለዚህ ያበቁክ።
ታዲያስ አንተስ ምንህ ሞኝነው ከቤተሰቦችህ በወረስካት ልምድ ልጆችህ በጥያቄ ልብህን ሲያወልቁህ ‹‹ስታድግ ትደርስበታለህ›› በምትል አጭር አረፍተ ነገር አስፈላጊ ሆኖ ስታገኘው መዥረጥ አድርገህ ለልጅህ ትጠቀማታለህ።
አሁንም ግን እልሃለሁ ልጅህ ከአንተ ይሻላል ስለማያውቅ አለማወቁን አውቆ አዋቂ ነኝ የምትለውን አንተን ከመጠየቅ ባስ ሲልም ከመሞገት አይመለስም። ስንቶቻችን አዋቂ ሰዎች ነን ግን የማናቀውን ነገር አላውቅም ብለን ለማወቅ የምንጥረው?
እኔ ግን በብዙ የሕይወት ተሞክሮዬ ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ብዙ አዋቂ (በዕድሜ) የሚባሉ ሰዎች ስለማያውቁት ነገር ሲጠየቁ አላውቅም ከማለት ይልቅ ከነገሩ ጋር የማይያያዝ ምላሽ ይሰጡሃል። እኔ እኮ ማለት የፈለኩት አሁን አንተ ከመለስከው ምላሽ ጋር ተያያዥነት የለውም ወይም ጥያቄዬ ካልገባህ…… ምናምን ብለህ ሳትጨርስ ፊታቸው መቀየር ይጀምራል ከዚያም አቂመውብህ ያርፉታል።
አንተም እኔም እንደዚህ አይነት ነገር ሲገጥመን ስቀን አዎ ይሆን ይሆናል ብለን የሰዎችን ስሜት ጠብቀን እናልፋለን። ልጅህ ግን ስለ አንተ ስሜት አይጠነቀቅም። መልስህ ልክ መስሎ ካልታየው አንተ በንዴት ጨርቅህን ትጥላለህ እንጂ እሱ ከመጠየቅና ስህተት መሆኑን ከመግለጽ ወደ ኋላ አይልም።
አንተም አዋቂ የሚለውን የወል ስምህን ላለመጣል ብለህ አላውቅም የኔ ልጅ ነገ ከሰው ጠይቄ፣ ከመጽሐፍ አንብቤ ዘመኑ ጥሩ ነው ከድረ ገጽ አይቼ እመልስልሃለሁ አትለውም። ከፊትህ ዞር እንዲል ብቻ ምክንያት ፈጥረህ ታባርረዋለህ ባስ ሲልም በቁጣ ታሸሸዋለህ። ምክንያቱም አንተም እንደዚህ ተደርገህ ነዋ ያደግከው።
ልጅህ ከአንተ በተሻለ የሚምር ልብም አለው። መቼም እንደሚታወቀው አብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን በተለይም ከተሜዎቹ ከጎረቤት ጋር ነው የምንኖረው እናማ ያው ሰው ከሰው ጋር ሲኖር ይጋጫል አይደል። ይህ አይነቱ ግጭት በልጆች ላይም ይከሰታል።
ረጅሙን ሰዓታቸውን አብረው እንደመዋላቸው ማለትም በትምህርት ቤት ከዚያም ሲመለሱ ደግሞ በሰፈር ጨዋታ ስለሚገናኙ የሚያጋጫቸው ነገር አይጠፋም። ይኸው ግጭት ሲከፋ አንዱ አንዱን እስከ መማታት ሊደርስ ይችላል። የሚደንቀው ነገር ግን አዋቂ የሚባሉት የልጆቹ ወላጆች በዚህ ግጭት ላይ ያላቸው ሚና ነው።
ለልጆቻቸው ተደርበው ከሌላኛው ወላጅ ጋር ይጣላሉ። የኔ ልጅ ጨዋ ነው ያንቺን ነገረኛ ልጅ አሳርፊ የማታሳርፊ ከሆነ ግን…የሚልን ዛቻ ሳይቀር ይለዋወጣሉ። ግጭቱ ውሎ አድሮ ተደጋግፎ በሚኖሩ ቤቶች የሚኖሩ ሁለት ጎረቤታሞችን የፈጣሪን ሰላምታ እንኳን እንዳይለዋወጡ አድርጎ ዓመታትን ሊያስቆጥሩ ይችላል።
የሚገርምህን ነገር ልንገርህ ልጅህ ከጓደኛው ጋር በተጣላ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ታርቆ እንደውም አንተ ተጎድቷል አልቅሷል ብለህ ማባበያ የገዛህለትን ከረሜላ ሳይቀር ካንተ ተደብቆ አካፍሎታል። አንተ ግን ቂምህን አልረሳ ብለህ አንድ አደጋ ቢደርስብህ አለኝ ከምትላቸው ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ ቀድሞ የሚደርስልህን ጎረቤትህን መቻል ይቅርታ ማድረግ ተስኖህ ተኳርፈዋለህ። ልጅህን ከተጣላው ምናልባትም ካቆሰለው ጓደኛው ጋር ስታየው ጸጉርህ ሊቆም ወይ ደግሞ ቆሽትህ ሊያር ይችላል።
ነገር ግን እሱ ያንተ ልጅ አዋቂ ነኝ ባይ አላዋቂ አይደለም። እሱ ልጅ ብቻ ነው። ልጅ ደግሞ አያቄምም። የምሩን ይምርና ወደ ቀጣዩ ምእራፉ አንድም የቀድሞ ዶሴ ሳይዝ ከነገው ጋር ይገናኛል። ለዛም ይመስለኛል አብዛኛውን ጊዜ ጨጓራና ደም ግፊት የያዘው ህፃን ልጅ አይተን የማናውቀው። አንተም ከበሽታህ ለማገገም ለመዳን የምትችለው ውስጥህ ያለውን የቂምና የጥላቻ ቋጠሮን ስትፈታ ብቻ ነው። ስለዚህ ወዳጄ እንደሚበልጥህ ልጅህ ሁን ስል እመክርሃለሁ።
ብዙ ጊዜ መታዘብ ከቻልክ ልጅህ ለሳቅ እና ለደስታ ቅርብ ነው። የአንድ ብር ጣፋጭ ገዝተህ ብትሰጠው ልቡን በሀሴት ትሞላዋለህ። የምር ደስታውን ከፊቱ ላይ ሲያበራ ታስተውላለህ ባለው ነገር መደሰትን ያውቃል። አንተ ግን እጅህ ላይ ያለው ነገር ብዙሃን ሰዎች ጋር እንደሌለ አታስተውልም።
ባለህ ነገር ሳታመሰግን ሌላ ነገር ትፈልጋለህ። እሱን ስታገኘው መልሶ ይቀልብህና ያስጠላሃል። ነፍስህን ጥቂት ጊዜ ሀሴት እንድታደርግ እንኳን አትፈቅድላትም። ሁሌ የጎደለብህና የሌለህ ነገር ብቻ ይታይሀል። ያለህ ነገር ዋጋው አይታይህም ለዚም ነው ደስታ ካንተ የራቀው።
ልጅህ በእግሩ ከትምህርት ቤት እስከ ቤት ከጓደኞቹ ጋር እየተጫወተ እየተላፋ ይመጣል። ምን ያህል ኪ.ሜ እንኳን እንደሄደ አያስተውልም። ደስ እያለው ስለሚጓዝ ጸሐዩ አቧራው መንገዱ ርቀቱ አይታወቀውም። አንተስ? የመስሪያ ቤት ሰርቪስ ሰፈርህ አድርሶ ለምን ቤቴ ደጃፌ ድረስ አያደርሰኝም? አንድ ፌርማታ እንዴት በእግሬ እሄዳለሁ ደስ ሲለው ብቻ ስራ ለሚገባው የኛ አለቃ እኮ መኪና ተሰጥቶታል።
ድሮም እዚህ መስሪያ ቤት…ትላለህ። አንተ አንድ ፌርማታ ብቻ እንድትሄድ ነው የተደረገው፤ ነገር ግን አንተ በዛው ሰርቪስ ውስጥ ሆነህ በትራንስፖርት ማጣት ምክንያት በበጋ ጸሐዩ በክረምት ዝናብ የሚፈራረቅበትን ረጃጅም ሰልፍ ላይ ያለውን ሕዝብ አትመለከትም ብታይም አንተ ስለእነርሱ ግድ የለህም። ያ የረጅም የታክሲ ወረፋ የድርጅትህን ሰርቪስ እንድታመሰግን ምክንያት አይሆንህም።
ለራስህ ደስታን እና ሳቅን ለመፍጠር ፍቃደኛ አይደለህም ያለህን የሚያሳይ ዓይን ሳይሆን በጎዶሎህ የሚወቅስህ ሕሊና ብቻ ነው ያለህ። ህጻናት ግን እንዲህ አይደሉም ባላቸው ነገር ይደሰታሉ ። ለዚህም ነው ብዙ አዋቂ ሰዎች ላይ የሚታየው የጭንቀት በሽታ እምብዛም ህጻናት ላይ የማይስተዋለው።
ልጅህን ንጹህ ልብስ አልብሰኸው አየር ለመቀበል ትንሽ ከሰፈር ወጥታችሁ ብትሄዱ እመነኝ ይህ ቀን ከልጅህ የልብ ጽላት ላይ ተጽፎ ለዘላለም ይቀራል። በቀጣዩም ቀንም ለጓደኞቹ እኔና አባቴ እኮ በዚህ መንገድ ስንሄድ ይህንን አይተን ያንን አልፈን እያለ የሚያወራው ታሪክ ትሰጠዋለህ።
በዚያ ሰዓት ግን ምናልባትም አንተ ከልጅህ ጋር እየሄድክ የሚታይህ ውሃ ልማት ንጹሕ ውሃ ለማቅረብ የቆፈረው ጉድጓድ አይተህ ምን እንደው እዚህ አገር በተቆፈረው ጉድጓድ ወድቀን ወጌሻ ጋር እንድንሄድ አስበው ነው እንዴ የሚሰሩት እያልክ እየተማረርክ ይሆናል።
ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሲቆፈር አማርረህ መሠረተ ልማቱ ሳይኖር አማርረህ እንዴት ሕይወትን ትገፋዋለህ? በእነዚህ ሁሉ ነጥቦች ልዩነታችሁን ዘርዝሬ ታዲያ አሁንስ ልጅህ ካንተ አይሻልም? አይበልጥህም ? መልሱን ላንተው ተውኩት።
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም