አዲስ አበባ፦ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት አካል የሆነው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በያዝነው ዓመት እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እንዳሻው ከተማ (ኢንጂነር)፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት አካል ከሆኑት መካከል የሳይንስ ሙዚየም፣ የልጆች መጫወቻ እና የሰሠርግ ሥነሥርዓት ማከናወኛ ስፍራ ይገኙበታል፡፡
እነኝህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ያሉት ኢንጂነር እንዳሻው፤ የእነኝህ ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በ2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ቢያዝም በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ በያዝነው ዓመት ግንባታው እንደሚጀመር ታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከሦስት ዓመት በላይ ሲጓተት መቆየቱን አውስተው፤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የጨረታ ሂደቱ መራዘሙ፣ ሀገራችን ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተወዳዳሪ ተጫራቾች አለመገኘታቸውና ጨረታዎች በመሠረዛቸው ምክንያቶች ግንባታው ሊዘገይ መቻሉን አብራርተዋል።
በአሁኑ ጊዜም የጨረታና ዲዛይን ሥራው በመጠናቀቁና ሥራ ተቋራጭ በመለየቱ ከሦስት ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ግንባታው የሚጀመር መሆኑን ኢንጂነር እንዳሻው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ በኮሪያ መንግሥት ድጋፍ የሚገነባው የኮይካ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት በጥናት ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ጥናቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ለመግባት በጥረት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የሚገነባው ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናቱ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በጥናቱ መሠረት ከኮይካ ፕሮጀክት ጋር በማጣጣም የዲዛይን ሂደቱን ለመጨረስና ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቱ አምስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚረዝም መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸው፤ ይህም ከእንጦጦ ተነስቶ የጉለሌና አራዳ ክፍለ ከተሞችን አልፎ ወዳጅነት አደባባይ ድረስ የሚሸፍን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከተማይቱን ውብና ጽዱ ከማድረግ ባሻገርም የመዝናኛ እና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚሠሩትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ መሆኑን ገልፀዋል።
የፕሮጀክቶቹ ዋና ዓላማ ወንዞቹን ውብና ፅዱ በማድረግ የማኅበረሰቡ መዝናኛ ማድረግ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ሥራው ሲጠናቀቅ ከማኅበረሰቡ የሚወጣ ፍሳሽና የሽንት ቤት ቆሻሻ ወደ ወንዙ እንዳይገባና እንዳይጣል እንደሚደረግም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም መሸጋገሪያ ድልድዮች፣ የስፖርት ማዕከላትና የብስክሌት መንገዶች እንደሚኖሯቸው ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቶች ለከተማ ነዋሪዎቹ የተዋቡ የመዝናኛ ቦታ ከመሆናቸውም ባለፈ ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር እንዳሻው አገላለጽ፤ለቀበናው ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል አምስት ሚሊዮን ዩሮ የጣሊያን መንግሥት ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ የቴክኒክ እገዛ ይሰጣል። ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚታሰብም የቢሮው ምክትል ኃላፊ ጠቁመዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12 ቀን 2015 ዓም