የጋራ የሆነች እና ለሁሉም የምትመች አገር ለመፍጠር ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በአገር አቀፍ የምሁራን የምክክር መድረክ ላይ ማሳሰባቸው ይታወቃል።
መንግሥት ከምሁራን ጋር የሚሠራውም ሆነ ምሁራን ከመንግሥት ጋር የሚሠሩት ለጋራ የአገር ጥቅም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ይህ በመሆኑ የጋራ የሆነች፣ ሁሉም ሰው ሀብት የሚያፈራባትን እና ለሁሉም የምትመች አገር መፍጠር ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
ለሁሉም የምትመችና የጋራ የሆነች አገር ሲባል እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃ ባህል፣ ብሔርና ሐይማኖት ያላቸው አገሮች ህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተመራጭ የመንግሥት አወቃቀር መሆኑ ይታወቃል። ይህም አወቃቀር ሁሉም አካባቢዎች ራሳቸውን እንዲያደራጁና እንዲያለሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይገለጻል። ሁሉም ማንነቶች ሊከበሩና ሊጠበቁ የሚችሉት አገርና ሕዝብ እስካለ ድረስ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ አብሮ ለመኖር የሚያስችል እሴቶቻቸውን የበለጠ መጠበቅና መገንባት እንደሚጠበቅባቸውም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ለሁሉም የምትመች አገር በመፍጠር አገር ግንባታ ውስጥ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት ስንል ያነጋገርናቸው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደሚሉት፤ እስካሁን ባለው ደረጃ አገሪቱ ለሁሉም የምትመች ናት ወይ ብሎ ለመናገር ይከብዳል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እስካሁን የተመጣበት መንገድ ሲፈተሽ የተወሱኑ የብሔሮች የበላይነት ስለነበር ነው።
‹‹በእኔ ግምገማ እስካሁን የመጣንበት መንገድ ብዝሃ እንደመሆናችን ብዙ ቋንቋ፣ ኃይማይኖትና ብሔርም እንደመሆናችን ለሁሉም የሚመች አገር ፈጠርን ወይ ተብሎ የሚጠየቅ ከሆነ ምላሹ አልፈጠርንም ነው።›› ይላሉ። ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጡት የአንዱ የበላይነት የበዛበት እንደነበር ነው። ይህን አሰራር ደግሞ በየተቋሞች ጭምር ሁሉ ሲሰራበት የቆየ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። ስለዚህ ወይ የአንድ ኃይማኖት አሊያም የአንድ ብሔር የበላይነት ሲታይባት የቆየች አገር ናት ሲሉ ነው ያስረዱት።
አቶ ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ የአንድ ብሔር ወይም ኃይማኖት የበላይ የሚሆንበት ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፤ አንዳንዶቹ መዋቅራዊ ናቸው። በስርዓት ውስጥ የነበረ ወይም በፖሊሲ የታጀበ ስለነበረ በግልጽ የአንድ ቋንቋ እና የአንድ ኃይማኖት የበላይነት ነበር። በተለይ ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ቀደም ብሎ ያሉትንና ራሳቸውን ኃይለስላሴንም ጨምሮ መመልከት ከተቻለ በሕገ መንግስት ሳይቀር አገሪቱ የአንድ ብሔር ብሎም የአንድ ኃይማኖት እድትመስል በደንብ ተሰርቶበት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።
ከዚያ በኋላ በነበሩት መንግስታት መጠነኛ ማሻሻያዎች ለማድረግ ተሞክሯል የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፣ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የመጀመሪያ ኢትዮጵያ የብዝሃ አገር ናት የሚለውን እውቅና ያገኘነው ከ1986 እኤአ አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና በዛም ጊዜ ቢሆን ሁሉንም የሚወክል እና ሁሉን የሚመስል ነገር ላይ አልተሰራም ይላሉ። የሐሳብ የበላይነት፤ የቋንቋ እና የኃይማኖት ልዩነት ላይ መከባበር አልነበረም በማለት ያስረዳሉ።
የኢህአዴግ መንግስት ከመጣ በኋላ በሕዝቡም ጭምር እውቅና የተሰጠው ሁኔታ ስለነበር በተግባርም ተሰርቶ ነበር ማለት ይቻላል፤ እንዲህም ሲባል የተወሰነ ደረጃ መሄድ ተችሏል። ያለጥርጥር 50 በመቶ ያህል ለሁሉም የምትመች አገር ለመስራት የሁሉንም ቋንቋም ሆነ ኃይማኖት በማክበር ረገድ የተወሰነ ደረጃ ለመሄድ መሞከሩን አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል። ይሁንና ይላሉ፤ በዚህ ውስጥም ልዩነቶች ነበሩ። አንዱ የበላይ ሌላው ደግሞ የበታች የሚመስሉ ነገሮች ታይተዋል ሲሉም ያመለክታሉ። ስለዚህ እስካሁን የመጣንበት መንገድ ሲፈተሽ ለሁሉም የምትመች አገር አለመፈጠሩን ያስረዳሉ።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የፖሊሲ መምህር ዶክተር ደረጀ ተረፈ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም የምትመች አገር ለመፍጠር ሁሉም ምሁራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ቢቀበሉትም የምሁሩ ሚና እንደ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል እንጂ ከሌላው የተለየ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ባይ ናቸው። ምሁሩ፣ ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ አይነት ሚና ነው ያለው እንጂ የተለየ አይደለም ባይ ናቸው። ምሁራኑ ራሱ አንዱ የኅብረተሰብ አካል እንደመሆኑ ከሌላው ለይቶ ማየት አይቻልም። ምክንያቱም ምሁሩ አንዱ የኅብረተሰቡ አካል እንጂ የተለየ ሚና እንዳለው መግለጽ አግባብ አይደለም ብለዋል።
ይሁንና እንደማንኛውም የኅብረተሰብ አካል ደግሞ ማበርከት ያለበትን ማበርከት ይኖርበታል የሚሉት ዶክተር ደረጀ፣ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር በትምህርት ዓለም በተለይ በጥናትና ምርምር አካባቢ ስለሚገኝ ይህንን ተጨማሪ ነገር እንደግብዓት በማናቸውም መንግስት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የፖሊሲ ስትራቴጂዎች ላይ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ቢወሰድ መልካም ነው ብለዋል። አለበለዚያ ምሁሩን በጣም የተለየ በማድረግና ለአገር የሚያበረክተው እርሱ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ አገርን ያገለግላል ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የመከላከያ አባላት፣ የጸጥታ አካላት ሌሎችም አገርን ያገለግላሉ፤ ሕይወታቸውን ጭምር ይሰጣሉ። አርሶ እና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ነጋዴውና ሌላውም በተመሳሳይ አገርን ያገለግላሉ። ስለዚህ ለአገር እድገት ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ስለዚህ የምሁሩን ብቻ ነጥለን የምናወጣ ከሆነ የሌሎችን አስተዋጽኦ አሳንሰን እንዳየን ሊቆጠር ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።
በለጋ እድሜ ላይ ያሉትን ዜጎች የሚቀርጹት ምሁራን ናቸው የሚለው አባባል በራሱ መስተካከል እንዳለበት ይናገራሉ። ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጡት አንድን ዜጋ የሚቀርጸው በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ነው፤ ህጻናቱንና ወጣቱን ሁሉ አጠቃልሎ ለትምህርት ቤትና ለትምህርት ቤት ሰዎች ሰጥቶ መምህራን ናቸው ወጣቱን መቅረጽ ያለባቸው መባሉን አይቀበሉትም። ለዚህም ምክንያት ያሉትን ሲናገሩ፤ ትምህርት ቤት አንዱ ነው እንጂ ብቸኛው ባለመሆን ነው። ዜጎችን በመቅረጽ ረገድ፤ ህጻናት ይወለዳሉ፤ ወላጆቻቸው ዘንድ ያድጋሉ፤ ከዛ ወደትምህርት ቤት ይመጣሉ። ትምህርት ቤት ውለው የሚመለሱት ደግሞ ወደወላጆቻቸውና ኅብረተሰቡ ነው። ስለዚህ በዚህ አግባብ ድርሻው የሁሉም ነው ይላሉ።
አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ተቋሞቻችን ኢትዮጵያን እንዲመስሉ ጥረዋል። እንዲህም ሲባል ሁሉንም እንዲወክሉ፤ የሁሉም ኃይማኖት፣ ብሔር እንዲሁም ቋንቋ ተወካዮች እንዲኖሩ ለማድረግ ተሞክሯል። እሱም የራሱ የሆነ ደካማ ጎን ግን ነበረው ማለት ይቻላል። ለአብነትም ደካማ ጎኑ የሁሉንም ብሔር ተወካዮች ማምጣት በሚደረገው ሒደት ውስጥ ለቦታው የሚመጥኑ ሰዎች መጥተዋል ወይ? ለዛ ቦታ እውቀቱ ነበራቸው ወይ? ከተባለ ግን በዛ በኩል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልክ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ ። አሁን ገና ጅምር ላይ ነን። የሚጎድለን ደግሞ በርካታ ነገር አለ።
ስለዚህ ምሁሩ በዚህ ሒደት ውስጥ ምን አይነት ድርሻ ነበረው ሲባል የተምታታ ነው ቢባል ይቀላል። ወደ አንድ ከሚያመጡን ነገሮች ይልቅ የሚለዩን ነገር ላይ ያተኮረ ነበር ባንልንም በመጠኑም ቢሆን በተለይ የፖለቲካ ምሁሩ ብቻ ሳይሆን ሌላው የተማረውም የሰው ኃይል አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር፤ አንዱን ቋንቋ ከሌላው ቋንቋ የሚያለያይ የሚመስሉ ነገሮችን በመጠኑም ቢሆን ሚዲያዎችን በመጠቀም አገሪቷ እዚህና እዚያ እንድትሆን ያደረጉ አካላት አሉ። በተመሳሳይ በመጠኑም ቢሆን ቁጥራቸው አናሳ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ አገሪቷ ወደ አንድ እንድትመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር ለማንኛውም በኢኮኖሚ የበላይ ለሆነውም፣ ደሃ ለሆነም፣ ለተማረውም ላልተማረውም የምትመች አገር ለመስራት በጽሁፎቻቸውም በመልዕክቶቻቸውም ብሎም በሕትመቶቻቸውም ሕዝቡ ዘንድ እንዲደርሱ በማንኛውም ነገር ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችም አልጠፉም ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ትልቁ ሚና መሆን አለበት ብለው የሚያስቡት ምሁሩ ለሁሉም የምትመች አገር በመፍጠር ሒደት ውስጥ በብዕሩም ማለትም በሚጽፈው ነገር ሕዝቡን የሚያቀራርብ ብሎም ሕዝቡን አንድ ሊያደርጉ በሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። ስለዚህ ምሁሩ አገሪቱ ለሁሉም የምትመች አገር በማድረጉ ረገድ የራሱን እያስተዋወቀ የሌላውን እያከበረ እና ቦታ እየሰጠ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው። ስለዚህ እዚህ ላይ ካተኮርን በእርግጠኝነት አገሪቷን ለሁሉም ብሔር፣ ቋንቋና ኃይማኖት ብሎም ለድሃውም ሆነ ለሀብታሙ የምትመች አገር ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
በእርግጥ ምሁሩ በዚህ ልክ ከተጫወተ መልካም ነው፤ ይሁንና እንደ ዶክተር ደረጃ ሁሉ እርሳቸውም የምሁሩ ሚና ብቻ ለውጥ ያመጣ የሚል እምነት የላቸውም። ሌሎቹም አካላት በተለይ ፖለቲከኛውም የየራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
ለምሳሌ የሆነ ተቋም የሚመራ አንድ የመንግስት ባለስልጣንም ለራሱ ብሔር፣ ቋንቋ እና ኃይማኖት ቅድሚያ የሚሰጥ ከሆነ አሁንም የማትመች አገር መፍጠራችን ይቀጥላል። ስለዚህ በስልጣን ላይ ማንኛውም አካል ተደማጭነትም ጭምር ያላቸው አካላት ሕዝቡን ሊያቀራርብ በሚችል መልኩ በተግባር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። አገርንም የሚመሩ አካላት የየበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ሲሉ አመልክተዋል።
ምሁሩ በሚጽፈውና በሚያሳትማቸው ጽሑፎች በጥቅሉ ሕዝቡ ዘንድ በሚደርሱ ማንኛውም ነገር ላይ እንዲሁም ባለሙያ ስለሆነ ስራውን ይዞ በየሚዲያውም ሲቀርብ ሕዝቡን ሊያቀራርብ በሚችሉ ነገሮች ላይ ቢያተኩር በእርግጠኝነት ለሁሉም የምትመች አገር በመፍጠር ሒደት ውስጥ የራሱም የጎላ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
ዶክተር ደረጀ በበኩላቸው፤ በእርግጥ መምህር ሙያዊና አገራዊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ያንን መወጣት ይኖርበታል ይላሉ። ነገር ግን አንዱ የኅብረተሰቡ አካል በመሆኑ እርሱም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ሚና እንደ ሌሎቹ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። እርሳቸው፣ ለዜጎች መልካም መሆን የአንድ ወገን ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ያላሰለሰ ጥረት መሆን ይገባዋል ባይ ናቸው። ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚያሳልፉት በቀን አምስትና ስድስት ሰዓት ሊሆን ይችላል። የቀረውን ሰዓት የሚያሳልፉት ግን ወላጆቻቸውና ኅብረተሰቡ መካከል ነው። ስለዚህም ሁሉንም ነገር ለመምህራን መሰጠት የለበትም፤ እንዲያ ከሆነ ሌሎች የበኩላቸውን ከመወጣት ይልቅ ለመምህራን ብቻ ወደመተው ይመጣሉ ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ በእርግጥ በትምህርት ቤት ሲሆን መምህራን መሪ ናቸው፤ በቤት እና በአካባቢ ደግሞ ወላጆች እና ማኅበረሰቡ መሪ ናቸው፤ ስለዚህ መምህራን ሚና የሚኖራቸው በቦታቸው ብቻ ነው፤ ያንን ሚና መጫወት አለባቸው፤ የተቀረውን ድርሻ ደግሞ ሁሉም የየበኩሉን መወጣት አለበት። ስለዚህ ምሁሩ አገር ወደተቀመጠው ግብ እንድትደርስ ከሌሎቹ ጋር በመሆን ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ስለዚህ አገር የምትደርስበትን ግብ ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ምሁሩ መስራት አለበት። እያንዳንዱ አገር እንድትገነባ የሚጠበቅበትን የእውቀት፣ የክህሎት እንዲሁም ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣቱ ረገድ የየድርሻውን ሲወጣ አገር የጋራ ብሎም ምቹ መሆን ትችላለች። የሚያስፈልገውን ነገር ከሌሎች ጋር ሆኖ መፈጸምም ይቻላል። ክህሎትና እውቀት በልዩነት የሚፈልግበት አካባቢ ደግሞ እሱን ማበርከት ነው። ሁሉም ለአገርና ለሕዝብ የሚሆነውን ነገር ማበርከት ብሎም አገርም እንዲሻሻል፤ ሕዝቡም ከጉስቁልና እና ከድህነት እንዲወጣ ማድረግ ነው፤ ይህ መሆን ያለበት የሁሉም ዓላማ ነው። ስለዚህም አገርን የምንገነባው ሁላችንም ተባብረን ነው እንጂ ለአንድ ለተወሰነ ክፍል በመተው የሚመጣ ውጤት አይኖርም። በዚህ አይነት አግባብ መጓዝ ከተቻለ በጋራ ስራ አገር ትገነባለች፤ ሕዝብም ሕይወቱ ይሻሻላል የሚል እምነት አላቸው።
አቶ ሙሉዓለም፣ በግሌ ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ ይላሉ፤ አንዳንዶችን ነገሮች ስመለከት ለምሳሌ ባለፉትም ሁለት ዓመታት መሳሪያ ተሸክሞ ወደጦርነት የገባበት አንዱ ምክንያት ብዬ የማስበው አገሪቱ ለሁሉም የምትመች አገር ካለመሆኗ የተነሳ ነው የሚል ግምገማ አለኝ። ስለዚህ ልክ አንድ ቤት ውስጥ እንደሚኖር ሰው ለሁሉም የምትመች አገር እንድትኖረን ከተፈለገ ልዩነቶቻችንን ወደ አንድ ለማምጣት የሚያስችል ጉዳይ ላይ መስራት ይጠበቅብናል ባይ ናቸው።
ነገር ግን ይላሉ፣ ይህንን ማድረግ የማንችል ከሆነና ለሁላችን የምትመች አገር መፍጠር የማንችል ከሆነ ጫካ የገባውም ‹ራሴን ችዬ ለራሴ የምትመች አገር እመስርታለሁ፤ እስከመጨረሻውም እዋጋለሁ። እስከመጨረሻው የራሴን አገር እስከመመስረት እተጋለሁ› የሚል አካል መፈጠሩ አይቀርም በማለት ያስረዳሉ። አንተ አትጠቅምም ብለን ወደጎን የተውነው አካል ነገ እየተነሳ የራሱን ብሔር፣ የራሱን ደጋፊዎች ብሎም የራሱን ኃይማኖት ተከታዮች ተማምኖ ወደጫካ መግባቱም መዋጋቱም ሊቀጥል ይችላል። ይህ ደግሞ ወደፊት እበለጽጋለሁ፤ ሀብታም እሆናለሁ ለምትል አገር እንቅፋት ነው የሚሆነው። እንደዚህ አይነት ነገር አገሪቱ ወደኋላ ከማስቀረት ባለፈ ደሃ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርግ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ስለዚህ ለሁሉም የምትመች አገር ካልተፈጠረ አደጋው የከፋ ነው። ከአንድነት ይልቅ የሚለያዩን ነገሮች ላይ ማተኮሩ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ነገሮችንም በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጫካ ገብቶ ለመዋጋት ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ በርካታ አካላት ይፈጠሩና በየሰፈሩ ለማዕከላዊ መንግስትም ሆነ ለየክልል መንግስታት የማይገዙ የጎበዝ አለቃዎችን እያሰፋን መሄዳችን አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ነገ ግብር አንከፍልም፤ ምክንያቱም የእኔን ምቾት አልጠበቃችሁልኝ፤ አገሪቷ ለእኔ አልተመቸችኝም፤ የወሰድኩትን እዳ አልከፍልም እያለ የሚቀጥል አካል በየሰፈሩ የሚፈጠር ይሆናል። በአገሪቷ ውስጥ መረጋጋትና ሰላም ከመሰፍን ይልቅ ወዳለመረጋጋትና ግጭት ብሎም ወደጦርነት የሚኬድበት እድል የሰፋ ይሆናል። ስለዚህ አንዱ የተለያየውን ማንነታችንን አስተካክለን መቀጠል ከፈለግን በእኔ እምነትና ግምገማ መደረግ ያለበት ለሁሉም የምትመች አገር መፍጠር ነው ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015